>

"የአለቃ አባ ገብረሃና ጨዋታዎች...!!!" (ዳንኤል በቀለ)

የአለቃ አባ ገብረሃና ጨዋታዎች…!!!”

ዳንኤል በቀለ

አለቃ አንድ ቀን ከባለቤታቸው ማዘንጊያ ጋር ለቅሶ ዉለው በጣም ርቧቸው ይመለሳሉ።ቤት እንደደረሱም፣ “በይ እስቲ ቶሎ ብለሽ የምንበላዉን አምጭልን” ብለው የሚበላ ሲጠባበቁ ማዘንጊያ እጓዳ ገብተው ቀለጡ። አለቃ ነገሩ ገርሟቸው፣ “ማዘንጊያ! አረ ማዘንጊያ!” እያሉ ሲጣሩ ማዘንጊያ በትልቁ ጎርሰው ኖሮ፣ “አቤት” ማለት ተስኗቸው “እምም” አሉ። አለቃም ገብቷቸው “ወላዲተ አምላክ ! ከምኔው ድመት ሆንሽ?” አሏቸው።
አፄ ቴዎድሮስ አባን በምሁርነታቸው ቢወዷቸውና ቢያከብሩዋቸውም ቀልዳቸውና ፌዘኛነታቸውን ይጠሉ ነበር። ዳሩ ግን ከልጅነት ጀምሮ እስከ ጐልማሳነት አብሮ ያደገ ልምድ ከተፈጥሮ ባህርይ የበረታ ነውና አባ ገብረሐና ቀልዳቸውንና ምፀታቸውን ማቆም አልቻሉም ለምሳሌ፤ ብላታ አድጎ የተባለዉን የአፄ ቴዎድሮስ አሽከር፣ አለቃ ምንግዜም ሲጠሩት “ብላታ አህዮ” እያሉ ነበር። አፄ ቴዎድሮስ “ተው ገብረሃና፣ ሰው እንዲህ አትዘርጥጥ” ብለው ቢመክሯቸውና ቢገስፁዋቸዉም፣ “አባቱ ያወጣለትን ስም ሁዋላ ምን ላድርግ? አድግ ማለት በግዕዝ አህያ ማለት አይደለምን?” ብለው አሻፈረኝ አሉ።
የረሃቡ ዘመን እንደተገባደደ እንዲት የጐጃም ሴት የቃና ዘገሊላን በዓል ምክንያት በማድረግ ጠበል ጠዲቅ እንዲቀምሱ ትጠራቸዋለች :: አባ ገብረሐና ጥሪውን አክብረው እንደደረሱ ሴትዬይቱ ጠላውን እየቀዳችላቸው፣ «አባቴ የችኮላ ሥራ ሆኖ ጠላው ቀጠን ብሏል» ብትላቸው «አዬ አካላቴ የምናከብረውስ የውሃ በዓል አይደል?» አሉዋት ይባላል
 አለቃ ሚስታቸው እረጅም ነበሩ ይባላል። ያን ጊዜ ምሽት ሆነና ሴትዮይቱ ከወዳጅ ቤት ወደ ቤት ሲገቡ አለቃ በሩን ሊዘጉ ሲሉ በመካከሉ ሴቲቱ እራሳቸውን ገባ አድርገው ቆም እንደ ማለት አሉ። አለቃ ሚስታቸውን ማዘንጊያ ገብተሽ አልቀሽ እንደሆነ በሩን ልዝጋው አሉ።
በጎንደር አገር መጠጥ ለሰው ሲሰጥ አሳላፊው ቁሞ የሚጠጣው ሰው መጠጡን ጎደል በአደረገ ቁጥር እየተጠባበቀ በላይ በላዩ ላይ መቅዳት ነው። አንድ ቀን አለቃ ገብረ ሐና ከድግስ ቤት ጠጥተው ሲወጡ አንዱ አለቃ ስንት ብርሌ ጠጡ ቢሏቸው «ዘጠኝ አንገት ጠጣሁ» አሉ።
ቴዎድሮስ እንዲነሱ ካሴሩት ቀንደኛ ካህናት አንዱ አባ ገብረሐና መሆናቸው እንደተደረሰበትም አባ ገብረሐና እንዲታሰሩ አዘዙ። ይህን የሰሙት ገብረሐና ሸሽተው ዘጌ ገዳም ተደበቁ ፡፡ አባ ገብረሃና ዘጌ ገዳም ሁለት አመታት በስደት እንደተቀመጡ ይወሳል። በዚህ ቆይታቸው ወቅት ረሃብ ይገባና ይቸገራሉ። አንድ ቀን ለወስፋት ማስታገሻ የምትሆን ቁራሽ ዳቦ ከአገልጋያቸው ጋራ ተካፍለው ከበሉ በኋላም ዲያቆኑ ተነስቶ «ጌታዬ ስብሃት ልበል? (ምስጋና ላቅርብ)» ቢላቸው፣ «ተው ልጄ ቀለዳችሁብኝ ብሎ ይቆጣል» አሉት ይባላል፡፡
Filed in: Amharic