አዲስ አበባ፡ በረሃብ አድማ ላይ የሚገኙ እስረኞች ሁኔታ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ይህ መግለጫ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የረሃብ አድማ ላይ የሚገኙት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የተከሰሱ እስረኞች እና ሌሎች እስረኞችንም ሁኔታ ተመልክቷል። ኮሚሽኑ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እና በቂሊንጦ ጊዜያዊ ማቆያ በመገኘት እስረኞቹን የጎበኘ ሲሆን፣ ከእነ አቶ ጃዋር መሐመድ በተጨማሪም፣ የኮሎኔል ገመቹ አያና እና የአቶ ጥላሁን ያሚ አያያዝ ላይ ክትትል አድርጓል። በክትትሉም ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት እና ከቂሊንጦ ጊዜያዊ ማቆያ ቤት አስተዳደሮች እንዲሁም ከእስረኞቹ ጋር ተነጋግሯል።
ኢሰመኮ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በተገኘበት ወቅት፣ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሀምዛ አዳነ (ቦረና) እና አቶ ሸምሰዲን ጣሃ ከጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በረሃብ አድማ ላይ ነበሩ። የረሃብ አድማው ዓላማ “መንግስት በሕዝብ እና በፓርቲያቸው ላይ እያደረሰ ያለውን አፈና እና የመብት ጥሰት ለመቃወም፣ የኮሎኔል ገመቹ አያናን አላግባብ የሆነ አያያዝ እና እንግልት እንዲቆም ለመጠየቅ እና የችሎት ሂደታቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡ እና እነሱን ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤት በሚመጡ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ” መሆኑን እስረኞቹ ለኢሰመኮ ገልጸዋል።
የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በበኩሉ ለረሃብ አድማው በምክንያትነት የተጠቀሱ አብዛኛዎቹ ጉዳዮች ማረሚያ ቤቱን የማይመለከቱ መሆኑንና እስረኞችን ለመጠየቅ የሚመጡ ሰዎች ላይ ወከባ እንደማይፈጽም ገልጿል። አስተዳደሩ አክሎም የረሃብ አድማው በእስረኞቹ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል፣ በተለይም ከመካከላቸው ሁለቱ የጤና ችግር ስላለባቸው በቋሚነት መድኃኒት የሚወስዱ በመሆኑ ቅርብ የህክምና ክትትል እንደሚደረግላቸው አስረድቷል። ኢሰመኮ በቦታው በነበረበት ወቅት የተባለው ህክምና ክትትል እንደሚደረግ በምልከታ ለማረጋገጥ ችሏል።
በሌላ በኩል፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ ተቀርጾ በማኅበራዊ ሚዲያ ከተሰራጨ ቪዲዮ ፊልም ጋር በተያያዘ ደኅንነታቸው አደጋ ላይ ወድቋል የተባሉትን ኮሎኔል ገመቹ አያና እና የአቶ ጥላሁን ያሚ ደኅንነትና አያያዝ ሁኔታ ኮሚሽኑ አጣርቷል። ሁለቱም ታሳሪዎች በደኅንነት ላይ እንደሚገኙና አካላዊ ጥቃት እንዳልደረሰባቸው አረጋግጧል። ሆኖም ግን ኮሎኔል ገመቹ አያና ከዚህ በፊት ከነበረበት የእስር ክፍል (ዞን) እንዲወጣ ተደርጎ ‹‹ለደህንነቱ ምቹ ወዳልሆነ የእስር ክፍል (ዞን) እንዲዛወር መደረጉን›› እና ከዚህም በፊት በተደጋጋሚ ከቦታ ቦታ በመዘዋወሩ የደረሰበትን እንግልት በሚመለከት ቅሬታውን ለኮሚሽኑ አስረድቷል። የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በበኩሉ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የእስረኞች ክፍል (ዞን) ዝውውር ሊደረግ የሚችል መሆኑን ገልጾ፤ ኮሎኔል ገመቹ የተዛወሩበት የእስር ክፍል (ዞን) ሌሎች እስረኞችም የሚገኙበት መሆኑን ይገልጻል። ኮሚሽኑም በጉብኝቱ ወቅት የማረሚያ ቤቱን ደንብ በመተላለፍ ምክንያት ወደዚህ የእስር ክፍል (ዞን) መምጣቱን የገለጸ አንድ ታሳሪ መኖሩን ኢሰመኮ ተመልክቷል፡፡
ኢሰመኮ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ለማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የሰጠውን ምክረ ሃሳብ ተከትሎ፣ አስተዳደሩ እስረኛውን ወደ ሌላ ዞን ለማዛወር በዝግጅት ላይ የነበረ ቢሆንም፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት እስረኛው ከቂሊንጦ እስር ቤት ወደ ቃሊቲ እስር ቤት መዛወሩ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሶ ወደ ቂሊንጦ እንዲመለስ ትዕዛዝ ሰጥቷል። በዚህም መሰረት፣ ከጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እስረኛው በቂሊንጦ ጊዜያዊ ማረፊያ ቤት የሚገኝ መሆኑን ኢሰመኮ እስረኛውን በመጎብኘት አረጋግጧል።
በተመሳሳይ መልኩ፣ ኢሰመኮ በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጠርጥሮ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኘውን የአቶ ጥላሁን ያሚን ደኅንነትና አያያዝ አጣርቷል። እስረኛው በሙሉ ደኅንነት የሚገኝ ሲሆን በማሕበራዊ ሚዲያ የተሰራጨውን ቪዲዬ ተከትሎ ከማቆያ ቤቱ ቅጥር ግቢ እንዳይወጣ ከመደረጉ በስተቀር በቂሊንጦ ጊዜያዊ ማቆያ እያለ ድብደባም ሆነ ሌላ አይነት የመብት ጥሰት ያልተፈጸመበት መሆኑን አስረድቶ፣ ነገር ግን ከዚህ ቀደም በፖሊስ ጣቢያ በምርመራ ወቅት የነበረውን ተገቢ ያልሆነ አያያዝ በተመለከተ ለኢሰመኮ ቅሬታውን አስረድቷል ።
በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በረሃብ አድማ ላይ የሚገኙ እስረኞችን አስመልክቶ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የእስረኞቹ ጤንነትና ሕይወት የከፋ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የቅርብ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ለታሳሪዎች ምክንያታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ መስጠትና የእስረኞችን ጠያቂዎች በማረሚያ ቤቱም ሆነ በፍርድ ቤቶች በአግባቡ ማስተናገድ ይገባል›› በማለት ገልጸዋል።