>

አንድ መሆን ካልቻልን ዘጠኝ ትንንሽ ለመሆን እንኳን እድል አይኖረንም...!!! (መላኩ ብርሀኑ)

አንድ መሆን ካልቻልን ዘጠኝ ትንንሽ ለመሆን እንኳን እድል አይኖረንም…!!!

መላኩ ብርሀኑ

*.. .በጣም ሰግቻለሁ! ህልውናችን አደጋ ላይ እንዳለ እየተሰማኝ ነው!!  
 
*…ከውጭ የቆመው ጅብ ወደቤታችን መግቢያውን ቀዳዳ አግኝቷል!
 
*… መሰሪዋ ምስሪ (ግብጽ) ናት ይቺ ጅብ!! 
ሰሞኑን በኢትዮጵያ ላይ ከረር ያለ አስተያየት ከመሰንዘር አልፋ ቀይ መስመሩ ተረግጧል ብላለች። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ትታገድ የሚል ጥያቄ አቅርባለች።
 ከዚያም አልፋ “ህዳሴ ግድቡን አናፈርሰውም ነገር ግን ኢትዮጵያ እንዳታጣጥመው እናደርጋታለን” የሚል ግልጽ መልዕክት በሚዲያዎቿ ልካልናለች። ኢትዮጵያን ለመበተን እና ለማጥቃት ጊዜው አሁን ነው አይነት ውሳኔ ላይ የደረሰች ይመስላል።
ለዚህም ግብፆች ከፕሬዚዳንታቸው ጀምሮ እስከታች ምሁራኖቻቸው ድረስ የታቀደና የተጠና ስራ ላይ ናቸው። ለህዳሴው ግድብ በጣም በጎ ምልከታና ከፍ ያለ ድጋፍ የነበራቸውን የሱዳኑን የቀድሞ ፕሬዚዳንት በቂም በቀል አመጽ አቀጣጥለው ካስወገዱ በኋላ ለነርሱ ፍላጎትና ትዕዛዝ የሚገዛ ታማኝ መንግስት ፈጥረዋል።
አሁን ኢትዮጵያ ይደግፉኛል ብላ የምትተማመንባቸውን ሁሉ ወደራሳቸው በማዞር በከፍተኛ ሁኔታ ከአለምአቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ አሳጥተው ሁለተኛው የግድቡ ሙሌት ሲጀመር በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለማወጅ ተዘጋጅተዋል።
በርግጥም የውስጥ ጉዳያችንን ስናጤነው ለግብጽ ዓላማ መሳካት ከአሁን ጊዜ በላይ የተመቸ ጊዜ የፈጠርን አይመስለኝም። ጅቡ ከውጭ በራችንን ሰብሮ አንገቱን አስገብቷል። እኛ ደግሞ በቤታችን ውስጥ ባየናት ትንሽ አይጥ ላይ ዱላችንን ይዘን ስንራኮት ውለን እያደርን ነው።
በዚህ መካከል የጋራ መኖሪያችንን መልሰን እንዳናገኛት ሆና እንዳናጣት እሰጋለሁ።
ወዳጄ ግብጽ ኢትዮጵያን በውስጥም በውጭም ለመውቀጥ የመጨረሻ እድሏን በሙሉ ሃይል መተግበር የጀመረች እለት “ኦሮሞ ነኝ አማራ ነኝ ፣ ወላይታ ነኝ ብልጽግና ነኝ ፣ ኢዜማ ነኝ ኢዴፓ ነኝ ብትል ለርሷ ኢትዮጵያዊ ነህና አንድ ነህ። መጥፋት አለብህ። እንዳታንሰራራ ሆነህ መውደቅ አለብህ።
ዛሬ ግብጽ ግፊ እንቁላል ቀቅለን እንቆይሻለን የምትል ባንዳ ሁሉ ግብጽ ከኢትዮጵያ ገንጥላ የብቻህ ሃገር ታቋቁምልህ ከመሰለህ የዓለም የመጨረሻው ቂላቂል ነህ። “ባሌን ጎዳሁ ብላ ….” የተባለውን ተረት አትርሳ!
አንድ መሆን ካልቻልን ዘጠኝ ትንንሽ ለመሆን እንኳን እድል አይኖረንም።
Filed in: Amharic