>

ግሪካዊው ሐበሻ ሙሴ ጆርጅ (ባላምባራስ ጊዮርጊስ) በአድዋ ....!!! (ሳሚ ዮሴፍ)

ግሪካዊው ሐበሻ ሙሴ ጆርጅ (ባላምባራስ ጊዮርጊስ) በአድዋ ….!!!

ሳሚ ዮሴፍ

ግሪካዊው ባላምባራስ ጊዮርጊስ ጦር ጎራዴ ይዘው ከኢትዮጵያውያን ጋ አድዋ ዘምተው ተዋግተዋል፤ ከአዲስ አበባ ምኒልክን ተከትለው ለኢትዮጵያ ሊሞቱ የዘመቱና የኢጣልያ ነጮችን የወጉ ነጭ ናቸው።
እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአዲስ አበባ ውስጥ ሠርተው (ነግደው) የሚያድሩና ምኒልክ “በርታ” ብለው በሐበሻ ፍቅር ያጠመቋቸው ሰው ነበሩ። ምኒልክ #ጎራዴና #ጋሻ ታጥቆ “ዘራፍ” የሚል ፈረንጅ የፈጠሩ ሰው ነበሩ። የግሪኩ ጆርጅ ባላንባራስ ጊዮርጊስ ተብለው በአድዋ ጀግንነታቸው ተሾሙ።
እኝህን ሰው በ1900 ዓ.ም ከቤታቸው ሄዶ ያነጋገራቸው እንግሊዛዊው ፓወል ኮተን ሲጽፍ “ባላምባራስ ጊዮርጊስ ከረዥምና የተንዠረገገ ነጭ ጢማቸው ጋር ድምቀትና ሞገስ ያላቸው ግሪካዊ ሽማግሌ ናቸው። በምኒልክ ጦር ውስጥ በክብር አገልግለዋል፤ ከኢትዮጵያውያን ጎን ተሰልፈው ኢጣልያኖችን የወጉ ብቸኛው አውሮፓዊ ናቸው።” ብሏል።
ባላምባራስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ውስጥ የመታሰቢያና የስጦታ እቃዎች መሸጫ ሱቅ ነበራቸው፤ የእጅ ሥራና የእደጥበባት ውጤቶችን ከባለሙያዎች እየገዙ አንዳንዴም በትእዛዝ እያሠሩ በሱቃቸው በኩል ለጋበያ ያቀርቡ ነበር፤ ብራና ሠሪዎች አዲስ ብራና ፍቀው መጽሐፍ ቅዱስን በግዕዝ ቋንቋ እንዲገለብጡላቸው ያደርጋሉ። በዚህም ለብራና ባለሙያዎች ይብዛም ይነስ አነስተኛ ሥራ ፈጥረው እራሳቸውንም እየረዱ ይኖሩ ነበር።
– ክብር ለባላንባራስ ጊዮርጊስ
– ክብር ለእምዬ ምኒልክ
– ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!!!
ማስታወሻ:- 
ምኒልክ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይሉ በአንድ ግብር ጎን ለጎን ያበላሉ። ምኒልክ በኃይማኖቱ ወይ በዘሩ አሊያም በቆዳው ቀለም የሚያገልሉት ሰው አልነበረም። እንኳንስ ሐበሾችን ነጮችንም በመንግሥታቸው ውስጥ ወዳጅ አርገው በሐበሻ ፍቅር አጥምቀው ተገልግለውባቸዋል።
ተርሲስ ተረዚያን ትውልዱ አርመናዊ ነበር፤
 ኢንጂነር ኢልግ የስዊዝ ተወላጅ፣
ሚስተር ሸፍኔ ደግሞ ፈረንሳዊ ነበሩ፤ እነኚህ ሰዎች ላባቸውንና አእምሮአቸውን አንጠፍጥፈው በፍቅር ኢትዮጵያን አገልግለዋል። በክፉ ሰዓት አልከዱም፤ ኢልግ የቢትወደድነት ማዕረግ ሲያገኝ፣ ሸፍኔ ደግሞ በአንድ ወቅት የቆንሲልነት ማዕረግ ተሰጥቶታል፤ ፈረንሳዊው ቆንሲል ላጋሬድም ጥሩ ስለረዳቸው #የእንጦጦ #ዱክ ብለውታል።
ሳሚ #ዘብሔረ #ኢትዮጵያ።
Filed in: Amharic