>

የኤርትራ ጣልቃ ገብነትና የተንሸዋረረው  እይታ...!!!  ( ጎዳና ያዕቆብ ) 

የኤርትራ ጣልቃ ገብነትና የተንሸዋረረው  እይታ…!!!

 ጎዳና ያዕቆብ  

ህዋሀት አፈሩ አይቅለለውና ሰይ ጣናዊ ግለሰቦች የወረሩት ሰይጣናዊ ድርጅት ነው። እንደው ሰይጣን ስል ሰይጣን እኔን ከህዋሀት ጋር ማመሳሰል ፌር አይደለም ቢለኝ እውነት ነው አንተ እንኳን ለሚከተሉህ እና ለሚገብሩልህ የተሻል ነገር ታደርጋለህ የምለው ይመስለኛል። ህዋሓት ኢትዮጵያን የምታክል ገናና ሀገር ይዞ የንዕስ ብሄርተኛነት ዲሪቶውን ማውለቅ ያልቻለ፤ የሚያስተዳድራትን ሀገር ቢሄራዊ ጥቅም አሳልፎ የሰጠ፤ ከስሁት ትርክት መላቀቅ ያልቻለ ትልቅ ሆኖ ሳለ ትንሽነት ላይ ሙጭጭ ብሎ ያረጀ ድርጅት ነው። አሁን በቅርብ ሞተ ቢባል የሚለቀስለት ሳይሆን የማያምነው እግዜር አሳረፈው የሚባል ድርጅት ነው። ድርጅት የሚለው ግን እንዲሰመርልኝ እፈልጋለሁ። መሞቱም እንደዛው። የመነጋገሪያ አጀንዳው የኤርትራ ሰራዊት በኢትዮጵያ ለምን ገባ? ከገባስ እስካሁን መቆየት ስለምን ተፈቀደለት? መንግስት በክህደቱ መጽናቱና ነጻና ገለልተኛ ሚዲያን፣ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች በነጻነት የመንቀሳቀስ እና ካለምንም የመንግስት ጣልቃ ገብነት የትግራይን ህዝብ በቀጥታ እንዲደርስ አለመደረጉ በትግራዋይ ላይ እየተፈጸመነው ነው ሲለሚባሉት ወንጀሎች መፍትሄ እንዳያገኙ የሚያደርግና ችግሩን የሚያባብስ ነው።
«የኤርትራ መንግሥት ሠራዊት በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው ወንጀል ካለ ህዋሓትን አዲስ አበባ ድረስ ተሸክሞ ማድረሱ ነው» ይላል ሲሳይ አጌና። እንደሚመስለኝ የዛሬ ሠላሳ ዓመት ስለተፈጸመ ወንጀል እያለ ያለው ጸጉር ስንጠቃ አይሁንብኝና የዛሬ ሠላሳ አመት የኤርትራ መንግስት የሚባል ልዋላዊነት ያለውና በአለም መንግስታትም ይሁን በኢትዮጵያ መንግስት እውቅና የተሰጠው የኤርትራ መንግስት የለምና የሚያወራው ስለሻቢያ መሆን አለበት። በፓርቲ፣ በድርጅት፣ በሀገር፣ በሀገረ-መንግስት እና በሕዝብ መካከል ያልተገባ አንድነት መፍጠር እና ማምታታት ህዋሓትንና የትግራይ ህዝብን አጃምሎ የማየት አባዜው «ኤርትራ ብትገባስ» በሚል ርዕስ የዛሬ አራት ቀን በእለታዊ ፕሮግራማቸው ላይ ተደጋግሞ ስለሚንጸባረቅና በዚህ ጽሑፍ ተደጋግሞ ስለሚነሳ ከጅምሩ ጠቁሞ ማለፍ መልካም ነው።
ይህን ብዬ ሳበቃ ትላንት ኤርትራ የሚባል ሀገር ሠራዊት የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት በሆነው በትግራይ ክልል ስለምን ገባ የሚል ጥያቄ ሲጠየቅ በአንድ ጎን የዛሬ ሠላሳ ዓመት ሄዶ ሀተታ መስጠት ማስተባበያ ከማጣት የመነጨ እንደሚሆን የሚያሳስብ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ልዋላዊነት የሚለውን ፅንሰ-ሀሳብ ካለመረዳትና የትግራይ ህዝብንና ህዋሓትን ላይቶ ካለማየት የሚመነጭ ነው።
በዚህ ረገድ ቢያንስ ከመንግስት አክቲቪስቶች በተልየ መልኩ የኤርትራ ሰራዊትን ማስገባት ማለት ስህተት፣ ከፖለቲካ አንጻርም ችግር የሚፈጥር ነው ሲል ብርሀኑ ጁላ፣ አብይ አህመድ ደግሞ ዕብደት ነው ሲሉ ገልጸውታል። አንዳንዶች ብገባስ ብለው ግልብ ከሆነ እውቀት በድፍረት ከሚናገሩና ቀን ከሌት ውሀ የማይቋጥሩ ማስተባበያ ከሚሰጡ አክቲቪስት ጋዜጠኞች የአብይ አህመድ እና የብርሀኑ ጁላ ውሸት የሚሻል ነው። እዙሁ ፕሮግራም ላይ የሰሜን ዕዝን መጠቃት፣ የህዋሓት መፈርጠም፣ ማይካድራ ላይ የተደረገው ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ (በመተከልና የኦሮሚያ የተደረገውና የሚደረገውን ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ እውቅና ሳይሰጡ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰምተነው የማናውቀው ጭካኔ የሞላበት ጭፍጨፋ በማለት የገለጹበትም ግብዝነትና መርጦ አዛኝነት አስገርሞኛል) እና የመሳሰሉ የህዋሓት ድርጊቶች የኢትዮጵያን መንግስት አዳክሞ የኤርትራን መንግስት እርዳታ እንዲሻ አስገድዶታል የሚል መከላከያ አቅርበዋል።
ፕሮግራሙ ተጀምሮ እስኪያልቅ በኔ እይታ አንድ ፍሬ ያለው ነገር ያቀረቡት ይኽንን ነውና እሱን ተቀበልነው እንበልና ይህን የመሰለ ምክኒያት ካለው የኢትዮጵያ መንግስት ለምን መዋሸት አስፈለገው? ለምን ለኢትዮጵያ ህዝብ እውነቱን አልተናገረም? ለአለም አቀፍ ማህበረሰቡስ ለምን መዋሸትና ተአማኒነቱን ማጉደል አስፈለገው? ጦርነቱ እንደተባለው ሦስት ሳምንት ባልሞላ ኦፕሬሽን ተጠናቀቀ ብለው የድል ዜና ካበሰሩ በኃላ በህግ የማስከበር ሂደቱ ላይ መከላከያን ሳይሆን የፌደራል ፖሊስን ተጠርጣሪዎች (ጁንታ የተባሉትን) በማሰስ ላይ ይገኛል አብይ አህመድ ብሎን ሳለ በምን ምክኒያት የኤርትራ ሰራዊት በትግራይ ላይ እንዲሰፍር፣ እንደልቡ እንዲንቀሳቀስና መልሶ ግንባታውም ይሁን ህግ ማስከበሩ ላይ እንዲሳተፍ ተደረገ? ማን እና ለምን እንዲቆይ ተደረገ? ስለምን እስካሁን የትግራይን ክልልም ይሁን የኢትዮጵያን ድንበር ለቆ እንዲወጣ ትዕዛዝ አልተሰጠም፣ ወይም ስምምነት ላይ አልተደረሰም?
ከኤርትራ ሠራዊት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ወንጀሎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ወሲባዊ ጥቃቶች እና ሌሎችም ክስተቶች ጎልተው እየወጡ ባለበት ወቅት ለምን በአስቸኳይ እንዲወጡ አልተደረገም ?   ሲሳይ እንዳለው በትግራይ ያሉ ወገኖቻችን ላይ ደረሰ የሚባለው ጥቃት « ከህዋሓት ፍርፋሪ ሲሰበስቡ የነበሩና በህዋሓት መጥፋት የተደናገጡ» ሳይሆኑ በብልጽግና የተሾሙ አመራሮችን ጨምሮ እየተፈጸመ ያለውን ወንጀሎች እየተናገሩና የኤርትራን ሠራዊት እንዴት እናስወጣ የሚለውን ከህዝብ ጋር እየተወያዩ ይገኛሉ። በጀግንነት ሀገራቸውን ያገለገሉ እነሲሳይ የአዞ እንባ የሚያፈሱላቸው የመከላከያ አባላት እና መኮንኖች ጭምር የባዕድ ሀይል መግባት አልነበረበትም አሁንም መውጣት አለባቸው እያሉ ይገኛሉና የተለየ ሀሳብ ያለውን ሰው ሁሉ ፍርፋሪ ሰብሳቢ አድርጎ መሳል ጎስቋላ ሙግት ብቻ ሳይሆን ሀገር ወዳድ የመካላከያ ሰራዊት አባላትንን የአብይ አህመድ ሹሞችን የሚነካ ነው።
ሲቀጥልም ሲሳይ አጌና « ኤርትራ የሚባል ሀገር ሠራዊት ኢትዮጵያ የሚባል ሀገር የእርስ በርስ ጦርነት (Civil War) መግባቱ ችግሩ ምን እንደሆነ አልታየኝም» ላለው የመጀመሪያው ችግር “ህግ” የሚሉት ነገር ነው። መቼም ያለፉት ሀምሳ አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የገባው ወረርሽኝ ህግንና መርህን በርካሽ ተወዳጅነት፣ በአድር ባይነት፣ እና ለበቀል መለወጥ ነው። የውስጥ ግጭት  (internal conflict)/ የእርስ በርስ ጦርነት (Civil War) የአለም አቀፍ የህግ ትርጉም በተለያዩ ምክኒያቶች የሚነሱና ከውጭ ጣልቃ ገብነት ነፃ የሆነ ጦርነት የሚ ትርጉም ይሰጠዋልና ልዋላዊ ሀገር ነኝ ያለቸው ኤርትራ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረግ የእርስ በእርስ ግጭት ጣልቃ መግባት ከአለም አቀፍ ህግ አንፃር ችግር ቁጥር አንድ ይባላል።
 ሌሎች ሀገራት በቀጥታ በጦርነቱ የሚሳተፉ ከሆነ (አሁን ኤርትራ እያደረገች እንዳለችው) ጦርነቱ ከእርስ በእርስ ጦርነት ወደቀጠናዊ ጦርነት ይሸጋገራል ማለት ነው። ችግር ቁጥሩ ሁለት በልልኝ። የሌሎች ሀገራትን ጣልቃ ገብነት በሚመለከት የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በEssentials of Peace Resolution ሁሉም ሀገራት በዛቻም ይሁን በድርጊት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሀገራትን ነጻነት፣ ልዋላዊነት፣ ክብር ከሚነካም፣የእርስ ግጭት ከሚያባብስና የህዝብን ፈቃድ የሚያዛባ ማንኛውም ጣልቃ ገብነት እንዲታገድ ይደነግጋል። ሌሎች ሀገራት ከጀርባ ሆነው ወይም በቀጥታ ጦር ሳያሰማሩ በቁስ፣ በሎጀስቲክስና ሌሎች እርዳታዎችን በመስጠት ከተሳተፉ ጦርነቱ የውክልና ጦርነት (proxy war) ይሆናል ማለት ነው።
የኤርትራ ጦር ለምን ገባ የሚሉት ከብስለት ጉድለት ወይም ፖለቲካን ካለመረዳት ነው መሳይ (ስምን መላአክ ያወጣዋል) ሲል ምን ያህል የህግም ይሁን የፖለቲካ እውቀት ድህነት እንዳጠቃው ተረፍቶ ከማዘን ውጪ ምን ማድረግ ይቻላል?! ጣልቃ ያለመጋባት መርሆዎችን በዝርዝር ማየት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትንታኔዎችን እሰጣለሁ ለሚል ጋዜጠኛና ተንታኝ መሰረታዊ ስለሚሆን ትንታኔና ፍረጃ ከመስጠት ይልቅ በጥቂቱም ማንበብ ባይጠቅምም አይጎዳም። ከአስትር አመታት በላይ በጋዜጠኝነት እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆነው ስመ ጥሩ መሳይ በአራት ወር አንድ  የጋዜጠኝነትናን የፓለቲካ ተንታኝነት ስራውን የሚመለከት መጽሀፍ ቢያነብ በአመት ሦስት በአስር አመት ደግሞ 30 መጽሀፍት የእውቀት ድርቀቱን ባለዘበለት ነበር። የአለም አቀፍ ህግጋትን በሰነድ ያሰፈረውና በውል ያደራጀው ህግጋት ከሰባ አመት በላይ አስፍሮት እያለ የአለም አቀፍ ህግ በእንዲህ አይነት የውጭ ጣልቃገብነት ላይ ምን ይላል ሳይል ጭራሽ ይባስ ብሎ አለማወቅ ነው እንጂ ኤርትራ እርስ በእርስ ጦርነታችን ውስጥ እስከአንገቷ መዘፈቋ እኮ ትክክል ነው ሊለን ይቃጣልዋል። የተባበሩት መንግስታት ቻርተር አንቀጽ 2 (4) «ሁሉም አባል ሀርራት ዓለም አቀፋዊ ግንኙነታቸውን ከማንኛውም ልዋላዊ ግዛት አንድነት ወይም የፖለቲካ ነጻነት ጋር የሀይል እርምጃን፣ ወይም ከተባበሩት መንግስታት ዓላማዎች ጋር ከሚቃረን በማንኛውም መንገድ  ይታቀባሉ» ይላል።
 እዛው አንቀጽ ላይ ንዑስ አንቀጽ 7 ላይ ደግሞ የተባበሩት መንግስታትም ይሁን ሀገራት በሌላ ሀገር የውስጥ ጉዳይ በሀይልም ይሁን በሌላ ጣልቃ እንዳይገባ ያግዳል። የአለም አቀፉ ህግጋት ውስብስት ከሆነባቸው የኛኑ ሀገር ህገ-መንግስት እንኳን እንዱ ክልል ሊሌላው ክልል የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ ይደነግጋል።  ለምሳሌ፦ በቤንሻንጉል ላይ ስለሚደርሰው የዘር ጭፍጨፋ፣ የዜጎች መፈናቀልና ሰቆቃ ምላሽ ለመስጠትና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የአማራ ልዩ ሀይል ልግባ ሲል ይህ ልዋላዊነትን የሚነካና በክልሉ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው በሚል በቤንሻንጉል ክልላዊ መንግስት እንደተከለከለና ከፌደራል ከመንግስቱም  ፍቃድ እንዳልተሰጠው ማስተዋላችን የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ሆኖ ሳለ እንዚህ በአለቃቸ በአንዳርጋቸው ፅጌ አባባል « ነጻ ያልወጡ ነጻ አውጪዎች» ኤርትራ ብትገባ ምን ችግር አለው ይሉሀል። የባዕድ ሰራዊት በውስጥ ጉዳያችን ገብቷል፣ በትግራዋይ እህቶቻችን ላይ ወሲባዊ ጥቃት እያደረሰ ነው።
በወንድሞቻችን ላይ ጉዳት እያደረሰ፣ ቅርስ እያወደመ፣ ቁስ እየሰረቀ ነው ሲባል ምን ችግር አለው የሚል ጋዜጠኞች ስታይ አምላክ በኪነ-ጥበብ ያቺን ሀገር እንዳቆማት ትረዳለህ። በህዋሓት ጥላቻ ላይ አድር ባይነት ሲታከልበት እንዴት መርህ አልባ እንደሚያደርግ ታያለህ። እውነቱ ህዋሓት እስከጠፋላቸው ድረስ እንኳን የትግራይ ህዝብ ቀርቶ መላው ኢትዮጵያ ብትጠፋ ግድ የሚያሳጣ መሪር ጥላቻ ውስጥ ስትገባ መልስህ «ምን ችግር አለው» የሚል ከምክኒያታዊነት የተፋታ፣ ከእውቀት የጸዳና ተራ ነው የሚሆነው። እኔማ አንዳንዴ እነዚህ ሰዎች ህዋሓትን ለምን እንደሚጠሉ ሁሉ ረስተው አስተሳሰብን እርግፍ አድርገው ትተው ድርጅቱ ላይ የሙጥኝ ያሉ ነው የሚመስለኝ። የብሔር አደረጃጀትና ፌደራሊዝሙ እንዳለ፣ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክቱ ተጠናክሮ፣ አማራና ኦርቶዶክስ ጠልነቱ ሰዎችን እንደከብት በማረድና አስሪሬን በማጎሳቆል፣ በማቃጠል፣ መቀበሪያ ቦታ በመከልከል ተባብሶ እያለና ሙሴአቸው ይህ ከፋፋይ ህገ-መንግስት ወይም ሞት ብሎ እያለ ህዋሓት ተቀበር ብሎ ጭፈራ እንኳን በብዙ ድካም የሚመጣን እውቀት ይቅርና እንድ ፊደል ያልቆጠረ ሰው ከተፈጥሮ ተምሮ «የወለደ  አይሞትም፡ እራሱን ተክቶአልና»  የሚለውን ጥበብ ተነጥቀው ሳይ እንደሀገር መከራችን ብዛቱ ያሳስበኛል።
ህዋሓት ከመሞቱ በፊት ምንም እንኳን ደህዴንና ብአዴን እድገታቸው ዘገምተኛነት ቢታይበትም ሲጠሩ አቤት፤ ሲላኩ ወዴት የማለት ክህሎታቸው አይቶና ኦህዴድ የአባቱን የህዋሓትን ትርክት፣ ጭካኔ፣ ከፋፋይነት፣ ፀረ አማራነትና ፀረ ኦርቶዶክስነትን ተክኖት፣ ከዚህ ጸረ-ኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ጋር ወደፊት ሲል አይቶና እድሜ ጠግቦ የሞተ እኩይ ድርጅት ነው። ብልጽግና በሚል ስም በልጁ ህያው ሆኖና ቆዳውን ሸልቅቶ አሁንም ህያው ሆኖ ስላለ ህወሓትን ቀበርነው የሚለው ዳንኪራው ላይ ቢበረቱና ብስለት፣ የፖለቲካ እውቀት እያሉ ህዝብን ቁልቁል ማየቱን ቢተውት ሳይሻላቸ አይቀርም።
Filed in: Amharic