>
5:26 pm - Sunday September 17, 3662

እቴጌ ጣይቱና የአድዋ ጦርነት...!!! (ሲሳይ ተፈሪ መኮንን)

እቴጌ ጣይቱና የአድዋ ጦርነት…!!!

ሲሳይ ተፈሪ መኮንን

ተኩሱ ከሌሊቱ 11 ሰአት የጀመረ እስከ 4 ሰአት እንደ ሐምሌ ዝናም አላባራም፡፡ ድምጹም በኖህ ጊዜ ሰማዩ ተነድሎ መሬቱን አጠፋው እንደተባለው ይመስላል እንጂ በሰው እጅ የተተኮሰ አይመስልም፡፡ መድፉም ሲተኮስ ጢሱ የቤት ቃጠሎ መስሎ ይወጣ ነበር፡፡ ከአድዋው ጦርነት እጅግ ጥቂቱን ጻፍኩ እንጂ፣ አይኔ ያየውን ጆሮዬ የሰማውን በሙሉ መጻፍ አይቻለኝም፡፡
በዚያን ጊዜ እቴጌ ጣይቱ በግንባራቸው ተደፍተው፣ በጉልበታቸው ተንበርክከው፣ ድንጋይ ተሸክመው እያዘኑና እየተጨነቁ ወደ እግዚአብሔር ሲጮሁ በንጉሠ ነገሥቱ ክቢ ላይ የመድፍና የነፍጡ እይር እንደ ዝናብ ወረደበት፡፡
እቴጌም ጥቁር ጥላ አስይዘውና አይነ ርግባቸውን ገልጠው በእግራቸው መሄድ ጀመሩ፡፡ ሴት ወይዛዝርቱ፣ የዳግማዊ ምኒልክ ልጅ ወ/ሮ ዘውዲቱና ደንገጡሮች እቴጌን ተከተሏቸው፡፡
የኋላው ደጀን ጦር እንደመወዝወዝ ባለ ጊዜም፣ እቴጌ አይዞህ! አንተ ምን ሆነሃል! ድሉ የኛ ነው! በለው! አሉት፡፡ በዚያ ቀን እቴጌ ጦራቸውን በግራና ቀኝ አሰልፈው የሴቶችን ባህሪ ትተው የተመረጠ የወንድ አርበኛ ሆነው ዋሉ፡፡ የእተጌ ጣይቱ መድፈኞች እቴጌ ከቆሙበት በስተቀኝ ሆነው መልሰው መላልሰው በመተኮስ በመሃል ሰብሮ የመጣውን የኢጣሊያ ጦር አስለቀቁት፡፡ በዚህም ጊዜ የኢጣሊያ ሰራዊት ሽሽት ጀመረ፡፡
እኛም ለጊዜው የፊተኛው ጦር ድል ሲሆን፣ የጦርነቱ መጨረሻ መስሎን ደስ አለን፡፡ ይሁን እንጂ ንጉሠ ነገሥቱ የፊተኛውን ጦር አባራሪውን ተከትለው በሩን አልፈው በዘለቁ ጊዜ እንደገና የኢጣሊያ ጦር እንደ ቅጠል ሆኖ ተሰልፎ ቆየ፡፡ ተኩሱም ከፊተኛው የበለጠ ሆነ፡፡
አጼ ምኒልክም ጦር ጨምረው ወደፊት ወደ ተራራው ከተጓዙ በኋላ ከበቅሎ ወርደው በዋሻው ውስጥ በነበረው 2ሺ የሚጠጋ የኢጣሊያ ጦር ላይ 10፡10 መድፍ ሲጥሉበት በዋሻው ውስጥ የነበረው የጣሊያን ሰራዊት እግዚኦ ብሎ ጮሀ፡፡
የአጼ ምኒልክ አዛዥ አባ ተምሳስ የንጉሠ ነገሥቱን ጥላ ይዞ ነጋሪት እያስመታ፣ አይዞህ በርታ! እያለ ሲያዋጋ ዋለ፡፡ እቴጌ ጣይቱም መጀመሪያ ድል ባደረጉበት ቦታ ቁመው ለተጠማውና ለቆሰለው ውሃ ሲያጠጡ ዋሉ፡፡ እንኳን የኢትዮጵያ ሰው፣ የኢጣሊያ ቁስለኞችም የእቴጌ ውሃ አልቀረባቸውም፡፡
ከቀኑ 9 ሰአት ሲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ሳይመለሱ በርካታ የኢትዮጵያ ሰራዊት ከግንባር መመለስ ጀመረ፡፡ ይሄኔ እቴጌ ንጉሠ ነገሥቱ ሳይመለሱ እንዴት ትመለሳላችሁ፣ በሉ ምርኮኛና ቁስለኛውን እዚህ እየተዋችሁ ወደ ግንባር ተመለሱ ብለው አዘዙ፡፡
የእተጌ እህት ወ/ሮ አዛለች፣ ሰዉ የማረከውንና ቁስለኛውን ይዞ ሲመለስ ባየች ጊዜ፣ ንጉሥህን ጠጅህን ጮማህን ትተህ ወዴት ትመለሳለህ? እያለች ለፈፈች፡፡ የምኒልክ ደግነት እንኳን ወንዱንና ሴቱን መነኩሴውን ጭምር አጀገነው፡፡ እቴጌ ጣይቱና አብረዋቸው የነበሩ ሴቶች ያለስራቸው ታላቅ ስራ ሲሰሩ ውለዋልና፣ ታሪካቸውን ጽፌ አልጨርሰውም፡፡
ንጉሠ ነገስቱ ሳይመለሱ ቀኑ እየመሸ በመምጣቱ፣ እቴጌ ምነው ጦሩ አልተፈታም እንዴ? የሚል መልዕክት ወደ አጼ ምኒልክ ላኩ፡፡ አጼ ምኒልክም በግራ ሲተኮስ እሰማለሁ እንጂ በዚህ ያለው አልቋል ብለው መልእክተኛ በመላክ ወደ ሰፈር ተመለሱ፡፡
እቴጌም የንጉሠ ነገሥቱን መመለስ ባዩ ጊዜ ላይን ድንግዝግዝ ሲል ከጦር ሰፈራቸው ተመለሱ፡፡ በድንኳናቸው በመግባት ዙፋናቸውንና መከዳቸውን እጅ ነስተው በዙፋናቸው ላይ ተቀመጡ፡፡ በጦርነቱ መሃል እንዳልዋሉና እንዳልነበሩ ሆነው ተገኙ፡፡
ታሪክ ዘመን ዘ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፣ ከጸሓፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ሊሚትድ 1959 ዓ.ም፣ ገጽ 262-264
Filed in: Amharic