>
5:18 pm - Monday June 15, 6364

ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም በተሟላ ጤንነት ላይ መሆኑን ልጆቸው ዶ/ር ትእግስት መንግስቱ አረጋገጡ (ወንድወሰን ተክሉ)

ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም በተሟላ ጤንነት ላይ መሆኑን ልጆቸው ዶ/ር ትእግስት መንግስቱ አረጋገጡ

ወንድወሰን ተክሉ

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም ህይወት በሀራሬ ሆስፒታል በ ICU ኮማ ውስጥ ገብተው በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ግብግብ ላይ ናቸው ተብሎ በዲጂ ኢትዮጵያ ሚዲያ የተሰራጨው ዜና ትክክለኛ ያልሆነ ምንጭ የፈጠራ ዜና ነው እንጂ አባቴ በጣም በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ ያሉ ናቸው ሲሉ የኮ/ሉ ሁለተኛ ልጅ የሆኑት ዶ/ር ትእግስት መንግስቱ በስልክ አረጋግጠውልኛል፡፡
የዲጂ ኢትዮጵያን ዜና እንዳነበብኩ ሼር ለመድረግ በመፈለጌ በቅድሚያ የልጃቸውን Confirmation በማስፈለጉ ለዶ/ር ትእግስት መንግስቱ ኃይለማሪያም የአባታቸውን የጤንነት ሁኔታ የታመሙበትን የበሽታ አይነት እንዲገልጹልኝ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ Hi Wonde
My father is well
I have been getting many questions
There is no problem በማለት በቴክስት ዛሬ ከመለሱልኝ በኃላ ቆየት ብለው ስልክ በመደወል በድምጽ «ጥያቄው ከአንተ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሰዎች በኩልም የቀረበ ጥያቄ ነው ሆኖም አባቴ ግን በሙሉ ጤንነት ላይ ሆኖ ቤቱ ያለ ሆኖ ሳለ ሆስፒታል ገብቶ በ ICU ኮማ ውስጥ ገብቶ ለህይወቱ እየታገለ ያለ ነው የሚል መረጃ ከየት አግኝተው በዜና መልክ ሊያሰራጩ እንደቻሉ በፍጹም የማላውቀውና ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው» ሲሉ ነግረውኛል፡፡
ይህ ዜና ከመሰራጨቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ከዶ/ር ትእግስት መንግስቱ ጋር በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የስልክ ቆይታ በነበረኝ ወቅት የአባቷ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማሪያም ጤንነት በጥሩ ሁኔታ ላይ ስለመገኘቱ ነግረውኝም ስለነበረ ትናንትና ማታ በዲጂ ኢትዮጵያ የተላለፈውን የነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ አደጋ እንግዳ ስለሆነብኝ ነበር ዜናውን ለማጋራት እንዳመነታና የልጃቸውን መልስ እንድፈልግ ያደረገኝና ኮ/ሉ በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ ስለመሆናቸው ነው ከልጃቸው አንደበት ማረጋገጥ የቻልኩት፡፡
ዶ/ር ትእግስት መንግስቱ ከሁለትና ሶስት ዓመት በፊትም በተመሳሳይ የተሳሳተ ዜና የአባታቸው ለሞት በሚያሰጋ ህመም ላይ መውደቅ ተዘግቦ የነበረ መሆኑን አውስተው «እኔ ለመላው ኢትዮጵያ በወቅቱ ስለአባታችን ጤንነት ሁኔታ አንዳች ነገር ቢያጋጥም ከማንም በፊት ቀድሜ የምግለጽ ሰው ነኝ በማለት ቃል ገብቼ ነበር» በማለት ከገለጹልኝ በኃላ «ዛሬም ይህንን ቃሌን የማስታውስና የማከብርም ሰው እንደመሆኔ መጠን አባቴ ልህይወቱ አስጊ የሆነ የጤንነት ችግር የገጠመው ሰው ቢሆን ኖሮ ለእናንተ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለማህበራዊ ሚዲያ ጋደኞቼና ወዳጆቼ በቅድሚያ የምገልጽላችሁ ዜና ይሆን ነበር» ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም በተለይ የሲጋራ ማጨስ ልምዳቸውን ካቋረጡና ሙሉ በሙሉ ሲጋራ ማጨስን ካቆሙ በኃላ ለወትሮው አልፎ አልፎ እንኳን የሚታዩ ጥቃቅን የህመም ስሜቶችና ምክልክቶች ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ የጤንነታቸው ሁኔታ ከመቼውም ግዜ በላይ ሙሉ ጤናማ የሆኑ መሆናቸውን  ያወሱት ዶ/ር ትእግስት መንግስቱ «አባቴ እንደማንኛውም የሰው ልጅ ህይወት ለህመምና አልፎም ለህልፈተ ህይወት ቀኑ የደረሰ እለት አንድ ቀን ሊያጋጥመው እንደሚችል ብናውቅም እስካዛሬዋ እለት ድረስ ግን ያንን ምልክት የሚያሳይ ክስተት ፈጽሞ አጋጥሞን (ከጤንነት አኳያ ማለታቸው ነው) ስለማናውቅ አንዳንድ ግዜ ሰዎች ለምን የአባታችንን ጤንነትን ተክትሎ ህይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል እያለ ዜና እንደሚሰራ ፈጽሞ ሊገባን ያልቻለ ክስተት ሆኖብኛል » ሲሉ ይናገራሉ፡፡
የኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም አያት በመቶ ሁለት እድሜያቸው ከዚህች አለም በሞት እንደተለዩ የተናገሩት ዶ/ር ትእግስት መንግስቱ  «እድሜ በቤተሰባችንና በዘራችን ውስጥ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ እድሜ ደግሞ የጄኔቲካል ውርስ ውጤት መሆኑንም ግልጽ ነው፡፡ እናም የአባቴ በዚህ እድሜ ላይ መገኘት ለአብዛኛው ህዝብ የጤና እክል ያለበት ወይም የሚፈጥርበት ነው ብሎ ቢያስቡም በአካል ለምናውቀው ልጆቹና ቤተሰቡ ግን ገና የሃምሳ አመት የእድሜ ባለጸጋ በሚያስመስለው ጥንካሬና ጤንነት ላይ ያለ ነው» ሲሉ በአጽንኦት ነግረውኛል፡፡
ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም በአንድ ወቅት ከሃያ ዓመት በፊት ቃለ መጠይቅ ላደረገችላቸው ጋዜጠኛ ደራሲ ገነት አየለ አንበሴ በሰጡት ቃል «እኔ የእናንተን ሞት አያለሁ እንጂ እናንተ ግን የእኔን ሞት ፈጽሞ አታያትም …» በማለት ለህወሃት ባለስልጣናት ጉዳይ በተናገሩት መሰረት በርካታ የህወሃት አመራሮችና መስራቾችን ህልፈተ ህይወት በህይወት እያሉ ማየት የቻሉ ሲሆን አሁን የቀሩ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ህልፈተ ህይወት በይህወት ሆነው የማየት አምላካዊ ጸጋና ፈቃዱ ይሁንላቸው እያልኩ መረጃውን በፈቃደኝነት ደውለው ላካፈሉኝ የኮ/ል  ልጅ ዶ/ር ትእግስት መንግስቱ አክብሮታዊ ምስጋናዬን እየገለጽኩ ለቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም ፈጣሪ ከአያታቸው የበለጠን እድሜ ከጤንነትና ከጥንካሬ ጋር ያጎናጽፋቸው የሚለውን ልባዊ ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡
Filed in: Amharic