>

የሜጫና ቱላማ መስራቾቹን ጄ. ታደሰ ብሩን ኮል. አለሙ ቂጢሳን ፣ ባሮ ቱምሳን ማን ገደለው?  (ሳሚ ዮሴፍ)

የሜጫና ቱላማ መስራቾቹን ጄ. ታደሰ ብሩን ኮል. አለሙ ቂጢሳን ፣ ባሮ ቱምሳን ማን ገደለው? 
ሳሚ ዮሴፍ

 

* …ዛሬ የኦሮሞ ብልጽግና ውስጥ የተሰገሰጉ ሰዎች ደርግ የኦሮሞን ትግል አጨልሟል ይላሉ ምክንያታቸው ደግሞ የጄነራል ታደሰ ብሩ፣ የኃይሌ ፊዳና የባሮ ቱምሳ መገደል ነው ነው ይላሉ። የኃይሌ ፊዳ ይቆየንና ጄነራል ታደሰ ብሩን መሬት ላራሹን አዋጅ እንዲቃወሙ ወትውቶ ጫካ ያስገባቸው ባሮ ቱምሳ እንደሆነ መረራ ጉዲና ጽፈዋል።
 
*….ለኦሮሞ ሕዝብ ትምህርትና መሠረተ ልማት ለማደራጀት በነ ጄኔራል ታደሰ ብሩ: ኮነሬል አለሙ ቂጢሳ :ማሞ መዘምር ወዘተ በመሳሰሉት ኢትዮጵያዊያኖች የተመሠረተው የሜጫና ቱለማ መሪ ሔዲንግ ሎጎ ይሔ ነበር።ይሔ ትግል ነው በነ ባሮ ቱምሳ ኢብሳ ጉተማና ዳውድ ኢብሳ በመሳሰሉት ተጠልፎና ስሙም ተቀይሮ <<ለኦሮሞ ሕዝብ የምታገል ነኝ >>የሚለው ኦነግ ድል ማጣጣም አቅቶት በየጊዜው በየአንጃዎቹና አማራ ጠል ፖሊሲው እየተጠለፈ ቀና ማለት ያቃተው ስብስብ ሆኖ ይታያል…
“. ፕ/ር መረራ ጉዲና  በመስታወት ቤት ውስጥ የሚኖር በሌሎች ላይ የመጀመሪያውን ድንጋይ ወርዋሪ አይሆንም” 
 
ጥር 1988 ዓ.ም 
ኢጭአትን በደርግ ውስጥ ከነበሩ መኮንኖች ጋር መሥርቶ አንዴ ከዚህ አንዴ ከዚያ ሲል የነበረው ባሮ ቱምሳ ነገሩ እየከረረ ሲሄድ ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ሄዶ እዚያ አካባቢ ከሚንቀሳቀሰው ጃራ አባ ገዳ ጋር ተቀላቀለ። እዚያም ሄዶ ጃራ አባ ገዳን ከሥልጣን ለማውረድ ያሴራል።
የዚህ አስቸጋሪ ሰው ሥራ ያላማረው ጃራም ቀደም ብሎ አብሮት የነበረውንና ለረዥም ጊዜ አብሮት ይሠራ የነበረውን
ባዶ ደቻሳ የሚባል (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረ)
የጉለሌ ልጅ “ይህ ሰው እየከፋፈለን ነው ምክረው” ብሎ ይነግረዋል። ባዶ ደቻሳ ትግል የጀመሩት ለስልጣን  ሳይሆን የኦሮሞን ህዝብ ለማደራጀት መሆኑን፤ እሱው ቤት መጥቶ በሰው ላይ ማሴር ብልግና መሆኑን፤ ውጤቱም አደገኛ ክፍፍልን መፍጠር ሊሆን እንደሚችል ደጋግሞ ቢነግረውም ባሮ ሴራውን ይገፋበታል። በመካከሉም ሶማሊያ አሸንፋ የሚመለሰው የደርግ ሠራዊት ግፊት ተጨምሮበት ተስፋ አስቆራጭ ውጥረት ይፈጠራል።
ይህን የተገነዘበው ባሮ ቱምሳ አዲስ ልብ ወልድ ሲያልም ያድርና “ሥልጣን ላይ በነበርኩበት ጊዜ ጫካ ስገባ ትሰጡኛላችሁ ያልኩዋቸው የቻይናና የምስራቅ ጀርመን መንግሥታት ቃል የገቡልኝን ብዙ ገንዘብና የጦር መሣሪያ መጥቶ ይውሰድ ብለው መልእክት ስለላኩብኝ ይህንኑ ለማምጣት ወደ ውጭ ልሂድ” ይላል። ከማንም በላይ የዚህን ሰው ማንነት መረዳት የጀመረው ባዶ ደቻሳ ባሮ ሌላ ድራማ ለመሥራት ማቀዱን በመገንዘብ “በምንም መንገድ ባሮ ወደ ውጭ መሄድ የለበትም” ይላል። የባሮ ወደ ውጭ የመሄድ ጉዳይ ለስብሰባ ሲቀርበም ባዶ ደቻሳ “የሚባለው  እውነት ከሆነ ሌላ ሰው ተወክሎ ይሄዳል እንጂ ባሮ በምንም ተአምር ወደ ውጭ መሄድ የለበትም” የሚለውን አቋሙን ያጠናክራል
በዚህ ጥያቄ ላይ የባሮ ግልገሎች እነ ዮሐንስ (ሌንጮ) ለታ የፖለቲካ ነፍስ አባታቸውን በመደገፋቸው በጣም የተናደደው ባዶ ደቻሳ ስብሰባ ለቆ ይሄድና መሣሪያ ይዞ በመመለስ
“በኦሮሞ ልጆች ደምና እንባ እስካሁን ነግደሃልና ለዘላለም ግን ስትነግድ አትኖርም” ብሎ ባሮን ረሽኖ ራሱን በመግደል የክብር ሞት ሞቷል።
ከዚህ በኋላ ውጥረቱም ክፍፍሉም በከፋበት ጊዜ ወደ ጅቡቲ የተጓዘው ዮሐንስ (ሌንጮ) ለታ አንድም የፖለቲካ ነፍስ አባቱ በኦሮሞ ልጅ እጅ ትክክለኛ ፍርድ መቀበሉና ርካሽ ሞት መሞቱ ታሪኩን ስለሚያበላሽና በሌላ በኩል ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ የተሻለ ዕድል ከገጠመው እነ ጃራ አባ ገዳ የበላይነት እንዳያገኙ ልክ ባሮ ሲያደርግ እንደነበረው ልብ ወለድ አሉባልታ ማሰራጨት ይጀምራል።
“ባሮን የገደለው ጃራ ነው፤ እስላሞች ሁላችንንም ሊጨርሱን ነበር፤ እኔም አምልጬ ነው የመጣሁት” ብሎ በአንድ ጸሎት ቤት ላደጉትና ከኢትዮጵያ መንግሥት የዜና ማሰራጫ አውታሮች የተሻለ ወሬ የማሰራጨት ችሎታ ላላቸው ዘመዶቹ ይነግራል። እነሱም ከጅቡቲ እስከ ሱዳን፣ ከሱዳን እስከ አውሮፓና አሜሪካ ከዚያም ወደ ሀገር ቤት ይሄንኑ ነጭ ውሸት አውርተው ያስወራሉ። የመጨረሻ ውጤቱም የኦሮሞ ተወላጆች ጃራ በሚመራው “እስላሚክ ኦሮምያ ነፃ አውጭ ግንባር” እና እነ ዮሐንስ ሌንጮ ለታ በሚመሩት “የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር” ተኮለኮሉ። በዚህ ምክንያት እስካሁን የኦሮሞ ልጆች ደም እየፈሰሰ መሆኑ ብቻም ሳይሆን ለነገም የሚተርፍና የኃይማኖትም መልክ ሊይዝ የሚችል የኦሮሞ ልጆች ሁለተኛው አደገኛ ክፍፍል የተፈጠረው የኦሮሞ አዛውንቶች በተደጋጋሚ እነ ጃራንና ኦነግን ለማስታረቅ ሞክረው ያልተሳካላቸውም ጃራ “እነ ዮሐንስ (ሌንጮ) ለታ በኦሮሞ ህዝብ ፊት ወጥተው ዋሽተናል ብለው ካላመኑ እነሱን አምኜ ከእነሱ ጋር አልሠራም” በማለቱ ነበር።
ይህንን ሁሉ ያወራሁት ሙት ወቃሽ ለመሆን ፈልጌ አይደለም። ይሁንና በራሱ አምሳል ኮትኩቶ በየሚሲዮን ጸሎት ቤቶች ያሳደጋቸው ዮሐንሶች ኦነግን በቤተሰብ የጥቅም ሰንሰለት ውስጥ አስገብተው አፍነው በመያዝ ሰዎች በተለይም የኦሮሞ ልጆች የሚታገሉበትን፣ የሚሞቱለትን፣ በእስር የሚንገላቱበትን ዓላማ በቅጡ እንዲገነዘቡ ባለኝ ፍላጎት ነው። ትላንት የጀመሩትን የፖለቲካ ቁማር በስፋት በመቀጠል የኦሮሞ ልጆች በማይታረቁበት ቅራኔ ውስጥ ዘላለም እንዲዳክሩና ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በጋራ ለህዝባቸው እንዳይታገሉ በማድረግ ላይ በመሆናቸው ነው።
ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ እነ ጃራን፣ ከነ ጃራ አልፎ ጀነራል ዋቆ ጉቱን (እዚህ ጋር ፕ/ር መረራን ባገኛቸው ዋቆ ጉቱን ጀነራል ማን እንዳደረገው እጠይቃቸው ነበር)፣ ከእሳቸውም አልፎ አዲስና የተሻለ ድርጅት እንዳይፈጠር ውስጣችንን ያውቁብናል የሚሏቸውን የኦሮሞ ወጣት ምሁራን ከዛሬ መቶ ዓመት በመቶ “ጎበና” ስም (ዛሬ ፕ/ር መረራ ይሄን ጽሑፋቸውን ረስተው ራስጎበናን እና ምኒልክን ይሰድባሉ)  እየኮነኑ የደራ የፖለቲካ ንግዳቸውን ቀጥለዋል።
በተለይ የኦሮሞ ልጆች የችግሮችን ምንጭ ከመሠረቱ እንዲረዱ አይፈልጉም።
“””””በጦቢያ መጽሔት ላይ ከጻፉት የተወሰደ “”””””
 
ከዛሬ 25 ዓመት በፊት ፕ/ር መረራ ጉዲና ጽፈው ነበር። ዛሬስ እሳቸው የት ነው ያሉት????
እነዚህ ዮሐንሶች የተባሉት ኦነጎች የት ነው ያሉት????
አንባቢ ራስህ መርምረህ ድረስበት።
Filed in: Amharic