>

ሀገር ስታምጥ...!!! /ቀለብ (አስቴር) ስዩም/

ሀገር ስታምጥ…!!!

ቀለብ(አስቴር) ስዩም

*…”የኢትዮጵያ የፍትሕ ስርዓት እንደ አክሱም ሐውልት ነው!” ትለናለች ትንታጓና ተምሳሌቷ  ቀለብ(አስቴር) ስዩም! ምን ማለቷ ይሆን?… በቅርብ ቀን በሚወጣው መጽሐፋ ላይ ምላሹን ታገኙታላችሁ። 
* የአገር ፍቅር፣ የእናት ፍቅር፣ የልጅ ፍቅር፣ የትዳር ጓድ ፍቅር “ሀገር ስታምጥ” ውስጥ በመደመም ታነቡታላችሁ። … የአላማ ጽናት፣ ጥቃትና ግፍን አለመሸከም፤ ጀግንነት፤ ትዕግስትና ብሩህ ተስፋ “በአገር ስታምጥ” ውስጥ ነብስ ዘርቶ አጥንትና ስጋ ለብሶ ሲንጎማለል ትመለከታላችሁ። ተገልብጦም ከራሳችሁ ጋር ሙግት ሲገጥም ትፈሩታላችሁ። በአስቴር(ቀለብ) እና ቤተሰቦቿ ጫማ ውስጥ ራስን ከቶ ማሰብ እንዴት ከባድ ነው!!
 
*   *   *
“እኛ አሉ የሚባሉትን ጭልፊቶች ለቅመን ጨርሰናቸዋል፤ አንቺ ከየት የመጣሽ ጭልፊት ነሽ?” 
ከመፅሐፉ የተወሰደ…….
……. አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል አካባቢ ከኋላዬ መጥተው ያዙኝ፡፡  አንደኛው በጥፊና በእርገጫ መታኝ። ሌሎቹ ስልኬን ነጠቁኝ። የያዝኩትን ቦርሳና የትምሕርት ማስረጃ ቀሙኝ። ሁለት ሰዎች መጥተው ተጨመሩ። እየገፈታተሩ በፍጥነት መጥቶ አጠገባችን የቆመው መኪና ውስጥ አስገቡኝ። መኪናው ውስጥ ስገባ ስድስት ሰዎች እየጠበቁኝ ነበር።
አጠቃላይ ዐሥር ሆኑ። አንዳቸውንም አላውቃቸውም። ስገባ ባገኘሁት አጋጣሚ ላያቸው መሞከሬ እንደጥፋት የተቆጠረብኝ ይመስል እንዳላይ ዓይኔን፤ እንዳልጮህም አፌን ሸፈኑኝ።
መኪናዋን አስነስተው አራት ኪሎን ለቀቁ። ወሬያቸው ሙሉ በሙሉ በትግርኛ ስለነበር ምን እንደሚሉ አልተረዳኋቸውም።
እኔን መኪናው ውስጥ በሆዴ ደፍተው አስተኝተውኝ፣ በምንም መልኩ ማየትም ይሁን መናገር እንዳልችል አድርገውኝ ከተማዋን ያዞሩኝ ጀመር። በየመሐሉ ስልኬ በጠራ ቁጥር የሚደወለውን ስም ይመዘግባሉ። ሩቅ መንገድ የሔድኩ ለማስመሰል ሙሉ ቀን ሲያዞሩኝና ሲያሽከረክሩኝ ከዋሉ በኋላ ከምሽቱ 1፡30 ማዕከላዊ ወደሚባለው የስቃይ ቦታ አስገቡኝ፡፡———-
———–በውድቅት ሌሊት ሰብዓዊነት በጎደላቸው ከ5 እስከ 6 የሚደርሱ ወንድ መሪማሪ ነን ባይ አረመኔዎች ለብዙ ጊዜ እንድመረመር ተደርጊያለሁ፡፡ በሰውነት ክፍሌ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰውብኛል። በሚደረግብኝ ምርመራ ምንም ዓይነት ፍንጭ ሊያገኙብኝ ስላልቻሉና በሚያደርሱብኝ አሰቃቂ ምርመራ ፍንክች ማለት ባለመቻሌ እናት አባቴ ያወጠሉኝን ስም በመተው “ጥቁር ድንጋይ“ የሚል ስም ሰጥተውኛል። ለምርመራ በምሔድበት ጊዜ የምጠራው በዚሁ “ጥቁር ድንጋይ” በሚል ጥምር ቃል እስከመሆን ደረሰ።
ጥቁር መባሌን የጥንካሬዬ መገለጫ አድርጌ የተቀበልኩት መሆኑን ሲገነዘቡ፣ ሞራሌን ለመስበር እጅግ አጸያፊ የሆኑ ዘር ተኮር ስድቦችን ይሰድቡኝ ነበር።
“እኛ አሉ የሚባሉትን ጭልፊቶች ለቅመን ጨርሰናቸዋል፤ አንቺ ከየት የመጣሽ ጭልፊት ነሽ?” ብለው ያላቸውን የሥልጣን የበላይነት ብቻ ሳይሆን፣ የሌላውን ሕዝብ ማንነት በማንቋሸሽ አራክሰውኛል። በእነሱ አባባል ጭልፊት ማለት ዐማራ ማለት ነው።
በየጊዜው በሚደረግብኝ ድብደባ ወደ ምርመራ ክፍል ስሔድም ሆነ ወደ ጨለማ እሥር ቤቴ ስመለስ እንኳን ደረጃውን መውጣት መውረድ አልችል ብዬ ፖሊሶች ሁለት እጄን ይዘው እየጎተቱኝ ነበር ከመርማሪዎቹ ዘንድ የሚያደርሱኝ፡፡ ማዕከላዊ ስገባ የዐሥር ወር ልጅ ትቼ ስለነበር የታሠርኩት በእመጫት ሰውነቴ የሚደርስብኝን መከራ ልቋቋመው መቻል አቅቶኝ ነበር። በተለይም ወገቤ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኛል። —————-
——-ወደ ባልደራስ ለእውነተኛና ዲሞክራሲ ፓርቲ ከመግባቴ በፊት ስለነበርኩበት “ኢዜማ” የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ አንዳንድ ነገር ላጫውታችሁ፡-
በዚህ ፓርቲ ውስጥ,,,,,,,
Filed in: Amharic