>
5:26 pm - Wednesday September 17, 6347

ጣልያን ምርኮኞቹን በብልጠት አስለቅቆ እንደገና ኢትዮጵያን ለመውረር ያሴረው ሴራ በአጤ ምኒልክ ጥበብ እንዴት ከሸፈበት?!? 

አ     ድ     ዋ  125ኛ ዓመት

ጣልያን ምርኮኞቹን በብልጠት አስለቅቆ እንደገና ኢትዮጵያን ለመውረር ያሴረው ሴራ በአጤ ምኒልክ ጥበብ እንዴት ከሸፈበት?!? 
ሳሚ ዘብሔረ ኢትዮጵያ

…ኢጣልያኖች ምርኮኞቹን አስፈትተው እንደገና ድጋሚ መልሶ ለመውጋት ያሰቡት ሀሳብ አልሆንላቸው አለ። ከዚህ በኋላ የተጠናከረ ጦራቸው ኤርትራን እንዲጠብቅ ሆኖ ጥቅምት 17 ቀን 1889 ዓ.ም የእርቅ ውል ከምኒልክ ጋር ለ2ኛ ጊዜ ተዋዋሉ። ውሉም የሚከተለው ነበር…
በኢትዮጵያ መንግሥትና በኢጣልያ መንግሥት መሀል የተደረገ የእርቅ ውል ይህ ነው። በቅዱስ ሥላሴ ስም እንጀምራለን።
ጃንሆይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክና በስም መጀመሪያ ኡምቤርቶ የኢጣልያ ንጉሥ ጦርነት ለማስቀረት ድሮ የነበረውን ፍቅራቸውን መልሰው ለማደስ ስለወደዱ ከዚህ የሚቀጥለውን ውል ተዋዋልን። ይህንንም ውል ለመዋዋል ከኢጣልያ መንግሥት ሙሉ ሥልጣን የተቀበለ በሳንሞሪስና በሳንላዛር በኢጣልያ ዘውድ ሊሻን የተሸለመ
ማዦር ዶክተር ሲዛር ኔራሲኒን መርጠው ላኩ። የማዦር ኔራሲኒ ሥልጣን የተስተካከለ መልካም ሆኖ ስለታየኝ የከበረ ማዦር ኔራሲኒን በኢጣልያ ንጉሥ ስምና በጃንሆይ በዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት እርስዎ ተቀምጠው ቀጥሎ የሚጻፈውን ክፍል ሁሉ ተስማምተው ተዋዋሉ።
መጀመሪያ ክፍል 
• በኢትዮጵያና በኢጣልያ የተደረገው ጦርነት ጭራሽ ቀርቷል። እንዲህ ስለሆነ በኢጣልያ ንጉሥና በጃንሆይ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በወራሾቻቸውም፣ በዜጎቻቸውም ለዘላለም እርቅና ፍቅር ይኖራል።
ሁለተኛ ክፍል 
• በ25 ሚያዝያ 1881 ዓ.ም በውጫሌ ሰፈር የተደረገው ውልና በኋላ ታርሞ የተጨመረው ውል ሁሉ ጨርሶ ተፍቋል። እንደተፋቀም ጭራሽ ይቀራል።
(ይሄን ውል የኢጣልያው መልእክተኛ ኮንቲ አንቶኖሊ እንዳይሰረዝ ሲከረከር ጀግናዋ እቴጌ ጣይቱ አይሆንም ሲሉት እስቲ አንቺ ምን እንዲሆን ትፈልጊያለሽ ጽፈሽ አንጪ ሲላቸው “ውሉ በሙሉ ተፍቋል” ብለው ነበር የሰጡት ከጦርነቱ በኋላ የጀግናዋ ቃል ተፈጻሚ ሆነ)
ሦስተኛ ክፍል 
• የኢጣልያ መንግሥት የኢትዮጵያን ነፃነት እራሱን የቻለ ባለ ነፃ መንግሥት መሆኑን ጨርሶ ተቀብሏል።
አራተኛ ክፍል
• እነዚህ ሁለቱ በዚህ ውል የሚዋዋሉ ነገሥታት በሀገሩ ድምበር ነገር ሳይስናሙ ቢቀሩ በእርቁ ቶሎ ለመዋዋልና ለሁለቱም ሀገር የረፍት መልካም ፍቅር ለማድረግ ስለወደዱ እስከ ዓመት ድረስ ጃንሆይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና የኢጣልያ ንጉሥ የመረጧቸው ሽማግሌዎች በፍቅር ተስማምተው የወሰኑን ነገር እንዲጨርሱ ተዋውለናል።
ወሰኑ እስኪወሰን ድረስ ግን ዛሬ ባሉበት በመቆያው ወሰን በመረብና በበለሳ በሙና ወንዞች ላይ ሳይተላለፉ እረግተው ይቆያሉ።
አምስተኛ ክፍል
• የኢትዮጵያና የኢጣልያ መንግሥት ይህን ወሰን ተስማምቱው እስኪጨርሱ ድረስ የኢጣልያ መንግሥት ከዚህ ሀገር ለማንም መንግሥት መስጠትና መልቀቅ አይቻለውም። ዛሬም የኢጣልያ መንግሥት በእጁ ከያዘው ሀገር መልቀቅ ያማረው እንደሆነ ለኢትዮጵያ መንግሥት ይመልሳል።
ስድስተኛ ክፍል 
• የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢጣልያ መንግሥት የጥበብና የንግድ ሥራ ለመርዳት ቢፈልጉ ሁለቱ መንግሥታት ተስማምተው ውሉን ኋላ ማድረግ ይመቻቸዋል።
ሰባተኛ ክፍል 
• ይህ አሁን የተደረገው ውል እነዚህ ሁለቱ የተዋዋሉ ነገሥታት በጥንቃቄ ለሌሎች ነገሥታት ያስታውቃሉ።
ስምንተኛ ክፍል 
• ይህም አሁን ያደረግነው ውል ከዛሬ አንስቶ ሶስት ወር ድረስ በኢጣልያ መንግሥት ፈጽሞ ይታተማል።
ዘጠነኛ ክፍል
• ይህ ዛሬ የተደረገው የእርቅ ውል ተስተካክሎ በአማርኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋ በሁለት ላይ ይጻፋል። ታትሞም ሲያበቃ በኢትዮጵያ ቤተ መንግሥትና በኢጣልያ ቤተ መንግሥት ይቀመጣል።
በዚህ ተስማምተው ጃንሆይ ዳግማዊ ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እርስዎ እራስዎና የከበረ ማዦር ኔራሲኒ በኢጣልያ ንጉሥ ስም ተቀባብለው በየማኅተማቸው ይህን ውል አተሙ።
በጥቅምት 17 ቀን ተጻፈ አዲስ አበባ ከተማ 1889 ዓ.ም 
እዚህ ውል እስከ ዛሬ ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ያልተገለጠ አንድ ታሪካዊ የሆነ አንቀጽ አለ። እሱም አምስተኛው አንቀጽ ነው። አንቀጹ ውስጥ በግልጽ እንደሚታየው የኢጣልያ መንግሥት ከያዘው የኤርትራ ይዞታው ለሌላ የውጭ መንግሥት መስጠት እንደማይችልና መልቀቅም የፈለገ እንደሆነ ኤርትራን ማስረከብ ያለበት ለኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑን ይወስናል። ይህ አንቀጽ በምኒልክ ዘመን ፍጻሜ ባያገኝ እንኳን በልጅ ልጅ ዘመንም ኤርትራ ለኢትዮጵያ እንድትመለስ የሚደነግግ ነው።
ምንም እንኳን ይሄን ውል ምኒልክ ቢዋዋሉም ምርኮኞቹን በሁለት ምክንያት መልቀቅ አልፈለጉም…
1ኛ/ ውሉ ጣልያን ሀገር ሄዶ ማህተም ተመቶበት እስኪመጣ ድረስ
2ኛ/ የእንግሊዝና የፈረንሳይ መንግሥት በዚህ ውል ላይ ያላቸውን አስተያየት ለመጠበቅ ነበር።
የኢጣልያ ህዝብ በምርኮኞቹ ጉዳይ መንግሥትን ወጥሮ ይዞ ስለነበረ መንግሥት ስለምርኮኞቹ ባስቸኳይ መለቀቅና ስለ ካሳ ጉዳይ ከምኒልክ ጋር የሚከተለውን ውል ተዋዋለ።
ለኢጣልያ ወታደሮች ምርኮኞች የሚደረግ ውል ይህ ነው።
ይህን ውል በቅድስት ሥላሴ ስም እንጀምራለን።
በጃንሆይ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና በከበረ ማዦር ኔራሲኒ ከንጉሥ ኡምቤርቶ ሙሉ ሥልጣንን ተቀብሎ የተላከ። ቀጥሎ የተጻፈውን ውል ተስማምተው ተዋዋሉ።
መጀመሪያ ክፍል
• በኢትዮጵያና በኢጣልያ መንግሥት መካከል ዛሬ ስለተደረገው የእርቅ ውል በኢትዮጵያ መንግሥት ያሉ የኢጣልያ ወታደሮች ምርኮኞች ተለቀዋል። ጃንሆይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እነኚህን ምርኮኞች በማፍጠን ሰብስበው ይህ የእርቅ ውል ተጠንቅቆ ታትሞ ሲመጣላቸው ሐረርጌ ላይ ከኢጣልያ መንግሥት ሙሉ ሥልጣን ተቀብሎ ለመጣ ሰው ያስረክባሉ።
ሁለተኛ ክፍል
• እነኚህ የጦር ምርኮኞች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ እንዳይቸገሩ ጃንሆይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የኢጣልያ የቀይ መስቀል ማኅበሮች ጀልዴሳ ድረስ መጥተው እንዲቀበሏቸው ይፈቅዱላቸዋል።
ሦስተኛ ክፍል
• የኢጣልያ ንጉሥ መልክተኞች እነኚህን ምርኮኞች ጃንሆይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በብርቱ አቀማጥለው እሱ ራሱ ስላየ እንዲህም አድርጎ ለማስቀመጥ ብዙ ገንዘብ ስለፈጀ ለእነኚህ ያወጡትን ገንዘብ የኢጣልያ መንግሥት እንዲከፍል ባለዕዳ መሆኑን ተቀብሏል።
ጃንሆይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ግን የዚህን የገንዘብ ኪሳራ የኢጣልያ መንግሥት እንዳወቀ ፈርዶ ሊሰጣቸው ፍርዱን በኢጣልያ መንግሥት ላይ ጥለውታል። በዚህም ውል ተስናምተው ጃንሆይ ዳግማዊ ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እርሳቸው ራሳቸውና የከበሩ ማዦር ኔራሲኒ በኢጣልያ ንጉሥ ስም ተቀባብለው በየማህተማቸው ይህን ውል አተሙ።
በጥቅምት17 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ በ1889 ዓ.ም ተጻፈ 
ምኒልክ ውሉን ቢዋዋሉም አሁንም ምርኮኞቹን አለቀቁም።
የሌሎቹን መንግሥታት አስተያየት ጠብቀው ምንም ተቃውሞ ባለማሰማታቸው አምስት ወር ከአስር ቀን ቆይተው ኔራሲኒ ከኢትዮጵያ ግዛት ከወጣ በኋላ የምርኮኞቹን መለቀቅ ምኒልክ በይፋ አሳወቁ። ይህንንም የእሰረኞቹን መለቀቅ ጅቡቲ ሆኖ ለሚጠብቀው ለማዦር ቴራሲኒ በደብዳቤ አሳወቁት።
ኢጣልያ በ3ኛው የምርኮኞች የውል ክፍል ቃል በገባችው መሠረትና የጦር ካሳ ጭምር አስር ሚሊዮን ሊሬ ለኢትዮጵያ መንግሥት ከፈለች። ይህም ገንዘብ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአድዋ ጦርነት ያወጣውን ወጪ በእጥፍ የሚተካ ነው ይባላል።
ክብር ለአድዋ ጀግኖች!!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!! 
Filed in: Amharic