>
5:18 pm - Monday June 16, 8064

ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ሀውልት ሊቆምላቸው የሚገባ ታላቅ ዲፕሎማት ደረጀ መላኩ (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ሀውልት ሊቆምላቸው የሚገባ ታላቅ ዲፕሎማት

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

እንደመንደርደሪያ


የዛሬውን ጽሁፍ ለማዘጋጀት መንፈሴን የቀሰቀሰው ከጥር ወር አጋማሽ ትንሽ እልፍ ብሎ አንድ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣን የክቡር አክሊሉ ሀብተወልድን ልእለ ስራዎች የሚያጠለሽ አስተያየት በመሰንዘራቸው ነበር፡፡ የተሰጠው አስተያየት በደምሳሳው የሚከተለውን ይመስላል፡፡

 ላም ባልዋለበት…..እንዲሉ  የኤርትራን  ፌዴሬሽን መፍረስን  በቁጥር አንድ ይቃወሙ የነበሩትን ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሊ ሃብተወልድን ልእለ ስራዎች ለማጠልሸት የሞከሩት እንደሚከተለው ነበር፡፡

“ኤርትራዊያን በከፊል ነፃነት ራሳቸዉን ማስተዳደራቸዉ ያልተዋጠለት ‘የጠቅላይ-አግላይ ፅንፈኛ አስተሳሰብ’ አቀንቃኞች ደግሞ ፌዴሬሽኑ ይፈርስ ዘንድ አፄ ኃይለስላሴ አባብሎ አሳምኗል! በ1954 ከኤርትራ ህዝብ ፍላጎት ውጭ ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ ክፍለ ሀገር እንዲትሆን ሲወሰን 30 ዓመታትን የፈጀዉ ጦርነት ተጀምሯል! ከከባድ ሰበዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ በኋላ 1984 ላይ የኤርትራ ህዝብ በሪፍሬንደም ከኢትዮጵያ ተለይቷል! ለዚህ የሚጠየቅ አካል ካለ በነአክሊሉ ሀብተወልድ ይመራ የነበረዉ የጠቅላይ አግላይ ፅንፈኛ አስተሳሰብ አራማጅ ፊዉዳላዊ ጁንታ ይሆናል! የሚል ነበር፡፡ ባለስልጣኑ በሰጡት አስተያየት ላይ ለግዜው የምለው የለኝም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ይህ ፍጹም የተሳሳተ አስተያየት መሆኑን እያስታወስኩ የአሁኑ ትውልድ  የክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉን ልእለ ስራዎችን በሚገባ ለማወቅ እና የህሊና ምስክርነት ለመስጠት ይረዳው በክቡር አምባሳደር ዘውዴ ረታ ( አፈሩን ገለባ ያድርግላቸው›› የተጻፈውን ‹‹ የኤርትረ ጉዳይ ›› የተሰኘውን ዝነኛ መጽሐፋቸውን እንዲያነብ እየጋበዝኩ ወደ ተነሳሁበት ነጥብ እመልሳኋለሁ፡፡

አፈሩን ገለባ ያድርግለትና ያ የምድርጦር የሙዚቃ ኦርኬስትራ ድምጻዊ የነበረው እና አመለሸጋው ጋሼ ታምራት ሞላ  በዛ ጥኡም ድምጹ :-

                                 ማን ነበረ ቆንጆ ማን ነበረ ለማ፤

                                ዳሩ ምን ያደርጋል መሞት አይቀርማ፡፡

ብሎ እንዳዜመው ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ከነግርማ ሞገሳቸው በደርግ የጭካኔ እርምጃ ህይወታቸው ካለፈ ግማሽ ክፍለ ዘመን አለፋቸው፡፡

በሌላ በኩል ጋሼ ጥላሁን በዛ ተስረቅራቂ እና ጥኡም ድምጹ ምን አለ ደጋጉን ዳግመኛ ቢፈጥረው ብሎ ያዜመው እንደ ክቡር አክሊሉ ሀብተወልድ የመሳሰሉትን ታላላቅ ሰዎች ልእለ ስራዎችን ለማስታወስ ይመስለኛል፡፡

ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ማን ናቸው ?

ክቡር ጸሀፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ለጋሲዮን የፕሬስ አታሼ በመሆን ስራ ጀምረው በአገር ውስጥ በልዩ ልዩ መሥሪያ ቤቶች በሚነስትርነትና በመጨረሻም ለ13 ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ለሀገራቸው ነጻነት፣አንድነት፣ እድገትና ብልጽና ለ39 ዓመታት ያገለገሉ አስተዋይ መሪ ነበሩ፡፡

ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ በምሥራቅ ሸዋ አስተዳደር በአድአ ወረዳ ልዩ ስሙ ደምቢ በሚባል ሥፍራ ከአለቃ ሀብተወልድ ካብቴነህና ከወይዘሮ ያደግድጉ ፍልፍሉ መጋቢት 5 ቀን 1904 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ 

ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ የአማርኛ ትምሕርት በአዲስ አበባ በሚገኘው በቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን፣ ዘመናዊ ትምህርት ደግሞ በዳግማዊ ምኒሊክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲማሩ ከቆዩ በኋላ  በ1917 ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምሕርት ወደ ግብጽ ሀገር ተልከው በሊሴ አሌክሳን ድሪ ትምህርት ቤት ትምሕርታቸውን ተከታትለው በ1923 የፈረንሳይን ባኩሎሪያ በማዕረግ ተመረቁ፡፡ ከእዚያም ወደ ፈረንሳይ  አገር ሄደው በሶርቦን ዩኒቨርስቲ ከ1923- 1928 ዓ.ም. ድረስ ሲማሩ ቆይተው በመጨረሻ በሕግ ትምሕርት ሊሳንስ ( ኤል ኤል ቢ) አገኙ፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በፐብሊክ ሎው እና በኢኮኖሚክስ ዲፕሎማ ደ ዶክትራ፣ እንዲሁም በንግድና በፖለቲካ ሳይንስ ሰርተፊኬት ተቀብለዋል፡፡

ክቡርነታቸው በሊሴ አሌክሳንደሪ በትምሕርት ላይ በነበሩበት ጊዜ በግብጽ የኮፕቲክ ፓትሪያርክ በአቡነ ዮሐንስ ለትምሕርት የተወሰዱት የኢትዮጵያ ተማሪዎች ችግር ላይ ስለወደቁ በጊዜው የኢትዮጵያ አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን አንደራሴ ከነበሩትና ከግብጽ ባለሥልጣኖች ጋር በመነጋገር ችግሩ እንዲፈታ አድረገዋል፡፡

ፈረንሳይ ሀገር ሶርቦን ዩንቨርስቲ በትምሕርት ላይ እንዳሉ ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ በመወረሯ 

 በሊግ ኦፍ ኔሽን የኢትዮጵያ ዴሊጌሽን ዋና ጸሃፊ ፣ ከዚያም በፓሪስ በኢትዮጵያ ሌጋሲዮን የፕሬስ አታሼ ፣ ከ1928-1929 ዓ.ም. ደግሞ አንደኛ ጸሐፊና ከ1929ዓ.ም.-1933 ዓ.ም. ጉዳይ ፈጻሚ በመሆን ሲሰሩ ኢጣሊያኖች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ይፈጽሙት የነበረውን ግፍ ለመላው ዓለም በማሳወቅ በአደረጉት ትግል ኢትዮጵያ የአውሮፓውያንን ድጋፍ እንድታገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላም ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ወደ እናት ሀገራቸው ተመልሰው ፣ ከ1935 እስከ 1952 ዓ.ም. በጽሕፈት ሚኒስቴር  ም/ሚኒስቴር ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ም/ሚኒስቴር እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከ1953 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1966 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትርና የጽሕፈት ሚኒስትር ሆነው ከመስራታቸው በላይ በተደራቢነት በ1958 ዓ.ም. የአገር ግዛት ሚኒስቴር ሚኒስትር ነበሩ፡፡

ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ለሀገራቸው ነጻነትና አንድነት ገና በትምህርት ቤት ሳሉና በዚያም በተከታታይ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ካደረጉት ትግል በተጨማሪ ለእደገቷና ለብልጽግናዋ የፈጸሟቸው ተግባራት በርካታ ቢሆኑም ለአብነት ያህል ጥቂቱ ከዚህ ቀጥሎ በአጭሩ ተመልክቷል፡፡

እንግሊዞች ቀደም ብለው ይዘዋት የነበረውን ጋምቤላን፣ ፈረንሳዮች ጅቡቲ ጠረፍ አጠገብ ያለችውን ውሃ ያለባትንና ስትራቴጂክ የሆነችውን አፋምቦን እና እንግሊዞች ኦጋዴን ለቀድሞው ብሪትሽ ሶማሌ ላንድ የግጦሽ መሬት ብለው የያዙትን ሪዘርቭድ ኤሪያን እንዲሁም ለማስተዳደር ችሎታ የላችሁም ብለው የያዙትን የምድር ባቡር አስለቅቀዋል፡፡ ኢጣሊያች ሲወጡ ከእንግሊዞች ጋር የነበረውን ስምምነት የእንግሊዞችን የበላይነት የሚያንጸባርቅ በመሆኑ የኢትዮጵያን መብት በሚያስከብር መልክ እንዲለወጥ የሀገሪቱ ወሰን ክልል ( በሶማሊያና በሱዳን በኩል ያለው ሲቀር) ሌላው በሰላም ውሳኔ እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡

ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ጠቅላይ ሚኒሰትር በነበሩበት ወቅት የአንድ ሀገር አስተዳደርና እድገት ሊጎለብት የሚችለው የተጠናከሩ ድርጅቶች ሲኖሩት መሆኑን በመገንዘብ ለእነዚህ መሰረት የሆነው ሕገ መንግስት ተሻሽሎ እንደገና እንዲወጣ ፣ ከዚያም የፍትሐ ብሔርና የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች፣ የጠቅላይ ሚኒስትርና የሚኒስትሮች ስልጣንና ተግባር የሚወስን ሕግ፣ የዳኞች ሹመትና በፍርድ አሰጣጥ ነጻነት ሕግ፣ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ሕግ፣ የመንግስት ሰራተኞች የጡረታ ሕግ፣ አገር አገዛዝ ደንብ፣ የውትድርና አገልግሎት ሕግ፣ ሌሎችም የአስፈጻሚ መ/ቤቶች የሥራ ሂደት የሚያፋጥኑና ሥነ ሥርዓት የሚያስይዙ ሕጎች እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ በልማቱም መስክ የሁለተኛውና የሶስተኛው አምስት ዓመት ፕላን እንዲዘጋጅ ፣ የህብረተሰቡ የስራ ፍላጎት ከፍ እንዲልና የስራ ፈቱ ቁጥር እንዲቀንስ በሰጡት አመራርና በአደረጉት አስተዋጽኦ በመንግስትና በግል ክፍለ ኢኮኖሚ ይገኝ የነበረው  ምርት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት በማሳደግና የሀገር ውሰጥ ፍላጎትን በማርካት ረገድ የታየው ኢትዮጵያ አስተማማኝ አቅጣጫ እንደያዘች የሚያመለክት ነበር፡፡

የአለም አቀፍ ድርጅቶች በሀገር ውስጥ መቋቋም የኢኮኖሚ ጥቅምና ለአገር ክብር እንደሚያስገኝ እንዲቋቋምና ቻርተሩ እንዲፈረም ጽ/ቤቱም አዲስ አበባ እንዲሆን፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጽ/ቤትም አዲስ አበባ እንዲመሰረት አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካ መስኮች በአገር ውስጥ አመራር በመስጠት በሚያካሂዱት የኃላፊነት ሥራ ብቻ ሳይወሰኑ በአያሌ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች ላይ እየተገኙ ታሪካዊና መሠረታዊ የሆኑ ተግባራት አከናውነዋል፡፡

ለአብነት ያህል፡-

ሀ/ ፓሪስ በተደረገው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ የሰላም ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ከሌሎች መንግስታት ጋር በእኩልነት ተካፋይ እንድትሆን በአደረጉት ጥረት በአፍሪካ ውስጥ በቅኝ አገዛዝ ሥር የሚኖሩ አገሮች ነጻነታቸውን እንዲያገኙ፣ ኢጣልያ በቅኝ ግዛት የያዘቻቸውን ሀገሮች እንድትለቅና ለኢትዮጵያ 25 ሚሊዮን ዶላር የጦር ካሳ እንድትከፍል እንዲሁም ኢትዮጵ ውስጥ የሚገኘውን የጠላት ንብረት ኢትዮጵያ እንድትወስድ አስወስነዋል፡፡

ለ/ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር በአሜሪካን ሀገር በሳንፍራንሲስኮ ከተማ በ1937 ሲረቀቅ ኢትዮጵያ የመንግስታት ማህበር መስራች ሀገር እንድትሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገው ይኀው በመሳካቱ ቻርተሩን በሚያዘጋጀው ጉባኤ ላይ ተካፍለው በመጨረሻ ቻርተሩን በኢትዮጵያ መንግስት ስም ፈርመዋል፡፡

ሐ/ ከ1937-1945 አራቱ ታላላቅ መንግስታት የኤርትራን ጉዳይ ለመመርመር በአደረጉት ጉባኤና ከእዚያም በኋላ ለተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ በታየበት ጊዜ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ጋር እንድትቀላቀል ተከራክረው በማሳመን አዎንታዊ የሆነ ውጤት አስገኝተዋል፡፡

መ/ የስዊስ ካናል ችግር በደረሰ ጊዜ የኢትዮጵያ መልእክተኞች መሪ በመሆን በለንደን ጉባኤ ላይ ከተካፈሉ በኋላ ወደ ፕሬዜዴንት ናስር ( የግብጽ መሪ የነበሩ ናቸው፡፡) ከተላኩት አምስት ሀገሮች መልእክተኞች አንዱ ሆነው ተመርተዋል፡፡

ሠ/ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አሥራ አምስተኛ ዓመቱን እስከ አከበረበት ድረስ የኢትዮጵያ መልእክተኞች መሪ በመሆን በስብሰባው ላይ እየተገኙ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኮሌክቲቭ ሴኩሪቲና በተባበሩት መንግስታት ላይ ያላቸውን ጽ እምነት ግንዛቤ እንዲገኝ አድርገዋ፡፡

ረ/ የአፍሪካ ነጻ መንግስታት አራት ብቻ በነበሩበት ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት በ1948 ዓ.ም. በአደረገው ጠቅላላ ጉባኤ በአንድ ድምጽ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ጉባኤውን መርተዋል፡፡ በዚያን ጊዜ አንድ አፍሪካዊ ለዚህ ኃላፊነት ሲመረጥ እርሳቸው በታሪክ የመጀመሪያው ነበሩ፡፡

ሰ/ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ ውስጥ በአደረጋቸው የመሪዎች ስብሰባ ላይ አዘውትረው ተካፍለዋል፡፤በተለይም ከግንቦት 14-17 ቀን 1955 ዓ.ም. በተደረገው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ የሶማሊያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት የጎሳ ጉዳይ አንስተው ባሰሙት ንግግር  ‹‹ የሶማሊያ ዜጎች በኢትዮጵያ፣ በፈረንሳይና  በእንግሊዝ ግዛት ስር ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ያለ ሶማሊያ ሕዝብ ፈቃድ የሶማሊያን መሬት ነጥቃ ወስዳለች፡፡ ›› በማታቸው ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ የቀረበው ክስ መሰረተ ቢስ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ታሪኳ የታወቀና ነጻነቷን ከሶስት ሺህ ዘመን አንስቶ የሕንድ ውቅያኖስን  የሚያካብብ ለመሆኑ ታሪክ እንዲመሰክርላት በታሪክ ውስጥ የሶማሊያ መንግስት የሚባል እንደሌለ፣ በ1942 ዓ.ም. ስለቅኝ ሀገሮች ጉዳይ ተከፍቶ በነበረው ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን መንግስት በመወከል ተገኝተው ሶማሊያ በተቻለ ፍጥነት ነጻነቷን ማግኘት አለባት በማለት እንደተከራከሩ፣ የአገር ጥያቄ ማንሳት የሚቻል ከሆነ ኢትዮጵያ ታሪኳ የሚፈቅድላትና የጂኦግራፊ አቀማመጥ ( ሁኔታዋ) በሚመሰክርላት መሰረት ሶማሊያ ራስዋን ከኢትዮጵያ ግዛት እንደ አንዷ አድርጋ እንደምትጠይቅ ሆኖም ኢትዮጵያ ከመሬቷ አንዲት ጋት ( ጣት)  እንደማትሰጥ ይህንንም አይነት ፈለግ አንደማትከተል አስረድተው በማናቸውም ሀገር ጉዳይ ውስጥ ማንም ጣልቃ እንዳይገባ ፣ ጠቅላላ ወሰን እንዲከበር፣ አለመግባባቶች በሰላም መንገድ እንዲያልቁ ለአፍሪካ አንድነት ጥረት እንዲደረግ ኢትዮጵያ አጥብቃ ስለምትጠይቅ የሶማሊያ መንግስትም በዚህ ዓለማ ተመርቶ እንዲሰራ ያላቸውን ምኞት በመግለጽ ሰፊ መልስ ሰጥተዋል፡፡

ሰው በሥራው እንደሚታወቅ ሁሉ ክቡርነታቸው ለኢትዮጵያ አንድነት፣እድገትና ብልጽግና በትምህርት ላይ ከበሩበት ጊዜ ጀምሮ ለአደረጉት አስተዋጽኦ በ1950 ዓ/ም የብላቴን ጌታነት፣ በ1953 ዓ/ም የጸሐፊ ትእዛዝነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እንዲሁም ከኢትዮጵያና ከውጭ አገሮች ልዩ ልዩ መንግሥታት ማለትም 

ሀ/ ከኢትዮጵያ መንግሥት የንግሥት ሳባ፣የሥላሴ፣ የዳግማዊ ምኒሊክና የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ኮርዶን ሊሻኖች

ለ/ ከ29 ሀገሮች ማለትም በጠቅላላው ከ40 በላይ ኒሻኖች ተሸልመዋል፡፡

ክቡር ጸሐፊ   ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ማዳም ኮሌትን በሕግ አግብተው ሲኖሩ  ፣ በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም.በተፈጸመባቸው የግፍ ግድያ በተወለዱ በ62 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ 

የግል ማስታወሻ፡- ለእውነት መቆም ያስከብራል፡፡የ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉን አርአያነት መከተል ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም

አንድ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለስልጣን ከላይ ከተጠቀሱት ባለስልጣን ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ  መሥራያቤታቸውን የለቀቁ ሰሞን በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ እንዲህ ብለው ነበር… “ኢትዮጵያ አገራችን ካሏት በአገር ፍቅር ስሜት ከታነፁ አንጋፋ ተቋማት መካከል አንዱ በሆነውና እና አክሊሉ ሃብተወልድና ከተማ ይፍሩ የመሳሰሉ አገር ወዳዶችና ስመ ጥር መሪዎችን ባፈራው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመድቤ አገሬን በፍቅር በማገልገሌ ሁልጊዜም ኩራት ይሰማኛል።” እሳቸው አክሊሉ ሃብተወልድን አገር ወዳድ ብለዋቸዋል፡፡

ትልቅ ሥራ አበርክተው የሄዱትን የኢትዮጵያ መሪዎች ማክበር ጨዋነት እና ታላቅነት ነው፡፡ ቀደሙ ታላላቆችን ማክበር ከተሳነን ታሪክ አልባ እንሆናለን፡፡  ይህም ብቻ አይደለም አንገታችንንም እንደፋለን፡፡ ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ከሀገርም አልፈው በአለም ደረጃም በሥራቸው የታወቁ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር እንደነበሩ የአሁኑ ትውልድ ማወቅ ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡  እሳቸው እኮ አንዱን ከሌላው የማያበላልጡ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።

ኢትዮጵያ እንደማንኛውም አገር ታሪክ አላት። ታሪክ ተሰርቶ የተቀመጠ የቆየ ስራ ነው። ማየት እንጂ መቀየር የማንችለው። ሲያሻን ለእኛ ጥቅም ብለን ወደኅላ ሄደን የምናስተካክለው አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የማይሞከር ነገር ስለሌለ ወደ ኅላ ሄደን የተሠራውን ሁሉ እኛ በምንፈልገው መልክ ለማስቀመጥ ሙከራ ለማድረግ የሚባዝኑ ሰዎች መኖራቸውን ሰዎች አይተን ታዝበናል፡፡ አዝነናል። ወደፊት እንደመሄድ ወደ ኋላ  ምን አመጣው?

ጥላቻ ከሁሉም በላይ እራስን ነው የሚጎዳው። ለሀገር የመሥራት አጋጣሚ ስታገኙ እባካችሁ ተጠቀሙበት። እናንተም ወደፊት ስማችሁ በጥሩ ሊነሳ ይችላል። ባሉበት ጊዜ ከተቻለ የበለጠ ሠርቶ ማለፍ ነው እንጂ ያለፉትን ታላላቅ የኢትዮጵያን ልጆች መንካት የራስን ጉድለት በአደባባይ ማሳየት መሆኑን ማን በነገራችሁ። እኔም ሆነ ሌላው የሚታየን ይሄው ነው።

እስቲ እንደ ምታሟቸው አባቶቻችን እስከ ዛሬ ድረስ ወደር የሌላቸውን እንደ እነ ኢትዮጵያ አየር መንገድን; አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ; የአፍሪካ ህብረት; ወዘተ የመሳሰሉትን ለመሥራትና እነሱ እንዳደርጉት እናንተም ለሚቀጥለው ትውልድ ለማበርከት ሞክሩ። እንደ አባቶቻችን አያቶቻችን እና ቅድመ አያቶቻችን በሥራ እንጂ በንግግር ግዚያችሁን አትጨርሱት። የኢትዮጵያ ህዝብ ከናንተ የሚጠብቀው የጎደለውን እንድታሟሉለት እንጂ ወደኅላ ሄዳችሁ ታሪክን እንድትቀይሩለት አይደለም።

እንደ መደምደሚያ

 • የአክሊሉ ጥፋት ምንድን ነው ? የአክሊሉ ሀብተወልድ ጥፋት ምናልባትም እንደ ጥፋት ከተቆጠረ ከሌሎች የአጼ ሀይለስልሴ ከፍተኛ ባለስልጣናት  ጋር ሆነው ንጉሱ ዲሞክራቲክ አካሄድ ተከትለው እንዲሄዱ ግፊት ለማድረግ አለመቻላቸው ይሆናል፡፡ ከዚህ ባሻግር ኢትዮጵያን በአለም የዲፕሎማቲክ አደባባይ ያስከበሩ ታላቅ የዲፕሎማቲክ አታሼ ነበሩ፡፡  ሌላ ምን ይባላል ? በየትኛው ችሎት ማን ጠበቃ ይሆነዋል? ክቡር  አክሊሉ ሀብተወልድ በህይወት ዘመናቸው ኢትዮጵያዊ ግዴታቸውን ተወጥተው ያለፉ ታላቅ ኢትዮጵዊ ነበሩ እንጂ በተለይም በኢትዮጵያ ላይ በደል አድረስው ያለፉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ ታሪክ አይሽፈጥም፡፡ ክቡር አክሊሉ ሀብተወልድ ወደር የሌለው አስተዋጽኦ ባያደርጉ ኖሮ  የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣የኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት ፣ የወንጀለኛና የፍታብሔር ሕጎች ፣ የውጭ ፖሊሲዎቻችን እና ሌሎችም ተቋማት በነ ጆርጅና ሄነሪ እየተመሩ የባርነት ስነ ልቦና ጌጣችን ይሆን ነበር ተብሎ ቢጻፍ ቡራ ከረዩ የሚል ይኖር ይሆን ?
 • ” እናትና ወንድሜን ግደሏቸው እንጅ ኢትዮጵያን አልክድም ” በማለት ከዲፕሎማሲ ተጋድሎ ባሻገር ለኢትዮጵያ በገቢር ሊሞት ወደ ጎሬ ከአርበኞች ጋር ሊቀላቀል የወሰነና ከድል በኋላ ብቻውን ያለ ጸሐፊ ኢትዮጵያን ከጠላት የተከላከለ ዓለም አቀፍ ጀግና ነው ። ይኸን መካድ እንዴት ሰውነት ይቻለዋል? 
 • አክሊሉ ሀብተወልድ ከሰራቸው በጥቂቱ
 • ግብፅንና የመንን አርፉችሁ ካልተቀመጣችሁ ጦር እናዘምትባችኋለን በማለት አርፈው እንዲቀመጡ አስጠንቅቋል ።
 • ራሽያን በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ክብር አዋርዷታል ።
 • ፈረንሳይን ቅኝ የተገዛችሁ ስለሆናችው ስለ ነጻነት አታወሩም በማለት በአደባባይ ስለ ኢትዮጵያ ክብር ንቋታል ።
 • የታላቋን እንግሊዝ የፖለቲካ ፊትአውራዎችን ፈትኖአቸዋል 
 • የተባበረችው አሜሪካን መሪዎች እቅድ በተደጋጋሚ አስቀይሮአል ።
 • በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ላይ የዓለምን መንግስታት በማስደነቅ ቁጭ ብድግ አስድርጓል።
 • አረቦችን ፣ላቲን አሜሪካኖችን ፣አውሮፓዎችን ባየር እና በመርከብ እየበረረ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲሰለፋ በብሩህ አእምሮው አሳምኖአቸዋል።
 • ****
  • 700 ሰአታት በአየር ላይ ስለ ኢትዮጵያ በሯል ።
  • ገና በ19 ዓመቱ ኢትዮጵያን በተባበሩት መንግስታት ላይ ወክሎአታል ።
  • እየታመመ በዶክተሮች እየተጠበቀ ስለ ኢትዮጵያ ጥቅም ተሟግቷል ።
  • የኢትዮጵያን አየር መንገድ ፣ ንግድ ባንክ በራሳችን ልጆች እንዲዘወሩ መሥርቷል ።
  • የኢትዮጵያን ሕገ መንግስት፣ የወንጀለኛ መቅጫ ፣ የፍታብሔር፣ የንግድ ፣ የባህር ህጎችን አስረቅቆአል… 
  • የአፍሪካ ህብረት አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን ሀሳቡን ከማመንጨት ጀምሮ ታግሎአል ።
  • ጣሊያኖችን በአውሮፓ ምድር እረፍት ሲነሳቸው ትልልቅ ማባበያ ቢሰጡት አልፈልግም ሲላቸው እናትና ወንድምህን እንገድልብሀለን ሲሉት ከብዙሀን እናት ኢትዮጵያ አይበልጡም ብሎ መልስ ሰጥቷቸዋል።
  • ጋምቤላ ፣ኦጋዴን ፣አፋምቦን የኢትዮጵያ ግዛት ሆነው ይቀጥሉ ዘንድ ካለ እንቅልፍ በአየር እየበረረ በባህር እየተጓዘ የእንግሊዞችን ሴራ የበጣጠሰ የጭንቅ ቀን ልጅ መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል
 • -በአለም ህዝቦች ፊት ። ስለ ኤርትራ ብቻውን የቆመና በድል ያጠናቀቀ የምንግዜም ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት ነው ።
  • በተባበሩት መንግስታት ፊት ተናገረ “እኛ መቼም ወገን የሌለን ትንሽ ሀገር ነን የምንጠብቀው ፍትህ ነው ” አያለ የጮኸ ።
   • አክሊሉ ምንም ቢሳቢስቲን ንብረት የሌለው ሚኒስቴር ነበር እንደውም ሚስቱ በጠና ስትታመምበት ለህክምና ብር በማጣቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 600ብር ተበድሮ ከደሞዙ ላይ በየወሩ እየተቀነሰ ከፍሎአል… 
   • አክሊሉ ሀብተወልድን ለየት የሚያደርገው በሀገር ጉዳይ ቁፍጥን ፣ምርር ፣ድርቅ ፣ጅግን፣ ፅንት የሚያደርገው በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ለድርድር የማይቀመጥ ኩሩ መሆኑ ነው ። 
  • ምን ዋጋ አለው ልጅነቱን የሰጣት ሀገሩ ግን ለውለታው ሽልማት የግፍ እና አጉል አሟሟትን ሸለመችው… ይህም ሳያንሰው ገድሉ ለትውልድ እንዳይነገር የሰራቸውን ድንቅ ስራዎች ሳይቀር የውጭ ጉዳያችን በአርካይቭ ውስጥ ደበቀው ። 
   • እባክህን የውጭ ጉዳይ ጽፈት ቤት ከሺ ገጽ በላይ የሚሆነውን የአክሊሉን ገድል ስለ ሀገር የከተበውን የእጅ ጽሁፍ አውጡልንና ጀግና እንፍጠር ? ለበርካታ የውጭ ሀገር ሰዎች መንገድ በስማቸው የሰየመችላቸው አዲስ አባባ አክሊሉን ለምን ዘነጋችው  በእውነቱ ለመናገር ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን ጨምሮ ሌሎችም እንደ እነ  ፣ አቶ ከተማ ይፍሩ፣ ፕሮፌሰር አክሊሉ ለማ፣ ሳይንቲስት ጌታቸው ፣ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ጀኔራል ታደሰ ብሩ፣ ዶክተር ሀይሉ አርአያ  ወዘተ የመሳሰሉትን ጨምሮ ታላላቅ የኢትዮጵያ ልጆች በስማቸው ሀውልት ሊቆምላቸው የሚገባ የኢትዮጵያ ባለውለታ ናቸው፡፡
   • በተለይ ለክቡር አክሊሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሃውልት ሊያቆምለት ይገባል ! !
 • የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሃውልት ሊያቆምለት ይገባል !
 • በስሙ መንገድ ወይም ተቋም ሊሰየምለት ይገባል! 
 • ግን እኛ ምንድነው የሆንነው? ምን አይነት እርግማን ነው የተጠናወተን? ለማናቸውም ሰላም፡፡ ‹‹ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እዜአብሔር ትዘረጋለች፡፡
Filed in: Amharic