>

ለ60 ዓመታት የመድረክ ድምቀት ለሆነው አሊ ቢራ የምስጋናና የእውቅና መርሐግብር ተካሄደ...!!!

ለ60 ዓመታት የመድረክ ድምቀት ለሆነው አሊ ቢራ የምስጋናና የእውቅና መርሐግብር ተካሄደ…!!!
የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ

 (ኢ ፕ ድ )
ጠንክረው ከሠሩ ሁሉን ነገር ማሸነፍና ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ አስታወቁ። በኦሮሞ ኪነጥበብ ውስጥ እጅግ ተወዳጅና ትልቅ ቦታ ይዞ ለ60 ዓመታት የመድረክ ድምቀት ለሆነው አሊ ቢራ የምስጋናና የእውቅና መርሐግብር ተካሄደ፡፡
የምስጋናና የእውቅና መርሐግብሩ ላይ እምባ እየተናነቀው ንግግር ያደረገው የክቡር ዶክተር አሊ ቢራ ፣ ጠንክረው ከሠሩ ሁሉን ነገር ማሸነፍና ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አስታውቋል ። “ለዚህ ለላቀ ክብር እበቃለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበርም ብሏል
ስሠራ የነበረው ለኦሮሞና ለሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ካለኝ አክብሮት እና ለጥበብ ካለው ፍቅር የተነሳ ነው ያለው ዶክተር አሊ፣ የክቡር ሽልማቱ እንዲሁም በሕይወት ታሪኩ ላይ ያተኮሩ መጽሐፍት መዘጋጀቱ ከታች ለሚመጡ አርቲስቶች የሞራል ስንቅ እንደሚሆን አመልክቷል፡፡
 “የምስራቁ ዋርካ…!!!”
እ.ኤ.አ በ1977 መጀመሪያ አካባቢ አሊ ከአይቤክስ ባንድ ጋር ኮንትራት መፈራረሙን ተከትሎ የዛምቤዚ ክለብንና የዲ አፍሪክ ሆቴልን ለቆ በራስ ሆቴል ስራ ጀመረ፡፡ በወቅቱ የደንበኞ ቁጥር በመቀነሱ ምክንያት የአይቤክስ ባንድ በራስ ሆቴል የሚያቀርበውን ዝግጅት ቅዳሜ ማታ ብቻ ለማድረግ ተገዶ ነበር፡፡ ማህሙድ አህመድንና ሌሎቹ ስመ-ጥር ሙዚቀኞችን ያቀፈው አይቤክስ ባንድ አሊን ማግኘቱ የተቀዛቀዘውን የሆቴሉን ደንበኛ በማነቃቃት ገቢው ከፍ እንዲል ማድረግ እንደሚችል በማመን ነበር 1000 ብር የወር ደመወዝ ሊከፍሉት የተስማሙት አሊ የስራ ስምምነቱን ከመቀበል ባለፈ በአጭር ጊዜ ውስጥ በ200 ብር የአይቤክስ ሙዚቃ መሳሪያዎችን አክሲዮን መግዛት ቻለ፡፡
እ.ኤ.አ በ1979 የአሊና የአይቤክስ ባንድ ወዳጅነት ጠንክሮ “አማሌሌ” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ለእርሱ አራተኛ ከባንዱ ጋር የመጀመሪያ የሆነውን አልበም ለገበያ በቃ፡፡ የአልበሙ መጠሪያ የሆነው “አማሌሌ” ዘፈን አሊ ባደገበት በምሥራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሚዘወተር ባህላዊ ዘፈን ሲሆን፤ አሊና ማህሙድ አህመድ በኦሮምኛና በአማርኛ እየተቀባበሉ በዘመናዊ መልኩ ሊጫወቱት ችለዋል፡፡ አይቤክስ ሙዚቃ ቤት የአልበሙ አሳታሚና አከፋፋይ ሲሆን በወቅቱ ኦሮሞዎች ስራውን የተቀበሉበት የደስታ ስሜት ዛሬ ድረስ በህይወት ያሉ እማኞች በመገረም ያስታውሳሉ። “የሰዉ አቀባበልና ከአልበሙ ሽያጭ የተገኘው ትርፍ ከጠበቅነው በላይ ነበር” ይላል የሙዚቃ ቤቱ ባለቤት አቶ ጣሃ አህመድ (የማህሙድ አህመድ ወንድም) ስለአልበሙ ሲያስታውስ፡፡ የአልበሙ ሽያጭ አስጨንቆት የነበረው ሙዚቃ ቤት የካሴቱን ዋጋ ከተለመደው 15 ብር ወደ 12 ብር እንዲወርድ አድርጎ የነበረ ሲሆን ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ቁጥሩ እጅግ የበዛ ህዝብ አልበሙን በእጁ ለማስገባት በመፈለጉ ማዳረስ እንኳን አልተቻለም፡፡ የመግዛት አቅምና አጋጣሚውን ያገኘ አልበሙን ተረባርቦ ገዛ፡፡ ያልቻለው ደግሞ አንዱ ከአንዱ እየተዋዋሰ አልበሙን ይኮመኩም ያዘ፡፡“አማሌሌ” አልበም በወቅቱ የነበረውን ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ከፍቅርና ከባህል ጋር ደባልቆ እያላቆጠ ለአደባባይ ቢያቀርበው የብዙዎችን ጆሮ አጠመደ፤ ከብዙዎች አንደበት አልጠፋ አለ፡፡
…እ.ኤ.አ 1979 የአይቤክስ፣ ዳህላክ እና ዋቢ ሸበሌ ባንዶች ያለፈ ታሪክ ከል የለበሰበት ዓመት ነበር፡፡ ሱዳኖች የባንዶቹን መሳሪያ ተጫዋቶች ሀገራቸው ወስደው እንዲጫወቱ ስላግባቧቸውና ስምምነት ላይ ስለደረሱ ሶስቱም የሙዚቃ ቡድኖች ነፋስ እንዳየው ገላባ ብትንትን ብለው ፈረሱ። ይሄን ተከትሎም አንዳንድ የአይቤክስና የዳህላክ ባንድ አባላት ተሰባስበው ዋልያስ ባንድ በሚል ስያሜ በሂልተን ሆቴል መስራት ጀመሩ፡፡ ማህሙድ አህመድም ባንዱን ተቀላቀለ፡፡ ለአሊ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት የአይቤክስ ባንድ አባላት ወደ ሂልተን ሄደው ስራ እንደጀመሩ በእሱ ምትክ ተክሌ ተክለእግዚ ቡድኑን እንዲቀላቀል አደረጉ። ከእነዚህ የሙዚቃ ቡድኖች የተረፉት ሌሎች ሙዚቀኞች በመሰባሰብ ሌላ ባንድ መስርተው በራስ ሆቴል ለመስራት ሀሳብ አቀረቡ፡፡ የራስ ሆቴልም አሊን የሚቀላቅሉት ከሆነ ብቻ ሀሳባቸውን እንደሚቀበል አስታወቀ፡፡ ሙዚቀኞቹም በመስማማታቸው ሙሉቀን መለሰ /ከዳህላክ ባንድ/፣ ዳዊት ሰንበታ /ቤዚ ጊታር ተጫዋች/፣ ግርማ ወልደሚካኤል /ሳክስፎን ተጫዋች/፣ ሽመልስ በየነ /ትራምፔት ተጫዋች በጋራ ሆነው ኢትዮ ስታር ባንድን መሰረቱ፡፡ ኢትዮ-ስታር ባንድ ከራስ ሆቴል ኩኩ ሰብስቤ፣ ግርማ ጭብሳና ሌሎች ዘፋኞችን ጨምሮ በመያዝ ጅቡቲ፣ የመንና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ
በመዘዋወር የሙዚቃ ስራውን ማሳየት ችሏል። በጥቅሉ አሊ በራስ ሆቴል ለ7 ዓመታት የሰራ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 3ቱን ዓመት ከአይቤክስ ባንድና ቀሪውን 4 ዓመት ደግሞ ከኢትዮ-ስታር ባንድ ጋር አሳልፏል፡፡
Filed in: Amharic