>

የአቶ ግርማ ሞገስ ለገሰ ግድያን አስመልክቶ ከኢዜማ የተሰጠ መግለጫ!!

የአቶ ግርማ ሞገስ ለገሰ ግድያን አስመልክቶ ከኢዜማ የተሰጠ መግለጫ!!


የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በሀገራችን በሁሉም አካባቢዎች አባላትን በማደራጀት እና መዋቅሮችን በመዘርጋት በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንዲሁም የሀገር አንድነት እና ቀጣይነትን የማረጋገጥ ሂደት ውስጥ አወንታዊ አስተዋፅዖ እያደረግን ከመቆየታችን በተጨማሪ አጠቃላይ የሀገራችንን ፖለቲካዊ ባህል ለመቀየር የበኩላችንን ጥረት ስናደርግ የቆየን መሆኑ ይታወቃል። በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ከማኅበረሰቡ ጋር ለመወያየት፣ አባላትን ለመመልመል እና ለማደራጀት በምናደርገው ሙከራ ውስጥ ሥራችንን ለማደናቀፍ እና ተስፋ ለማስቆረጥ የመንግሥትን መዋቅር ጨምሮ የተለያዩ ኢ-መደበኛ አካላት ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በምናደርገው እንቅስቃሴ ላይ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ረጅም ጊዜ እና ትልቅ ትዕግስት እንደሚያስፈልግ በማመን ችግሮቹን ከማጉላት ይልቅ ችግሩን እና ፈተናውን ተቋቁመን በንግግር እና በውይይት ለመፍታት ጥረት ስናደርግ ቆይተናል።
የሚደርሱብንን ጫናዎች በመቋቋም የዘረጋነውን ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር እና የኢትዮጵያን ሕዝብ የተጠራቀሙ ችግሮችን የሚፈቱ በባለሙያዎች የተዘጋጁ ፖሊሲዎች ይዘን የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ዝግጅታችንን ባጠናቀቅንበት የመጨረሻ ሰዓት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቢሾፍቱ ከተማ አድአ ምርጫ ወረዳ 1 የኢዜማ መዋቅር ሊቀመንበር የነበሩት ግርማ ሞገስ ለገሰ እሁድ የካቲት 7 ቀን 2013 ዓ.ም በጥይት ተመተው ሕይወታቸው አልፏል።
ከዚህ በፊት በቢሾፍቱ ከተማ የምናደርገው እንቅስቃሴ ላይ የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሙን እና አባላቶቻችን ላይ ማዋከብ ሲያጋጥመን ነው የቆየው። በከተማው ከነዋሪዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ፈልገን በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ በከተማው አስተዳደር እምቢተኝነት ምክንያት መሳካት አልቻለም። የምርጫ ወረዳ መዋቅራችን የሚጠቀምበት ጽሕፈት ቤትም ለመክፈት ብዙ ውጣውረድ ብናልፍም ከከተማው አስተዳደር በሚደረግ ጫና መሳካት አልቻለም። በከተማው ኢዜማ ከነዋሪዎች ጋር ሊያደርግ የነበረውን ስብሰባም ሆነ ጽሕፈት ቤት ለመክፈት ይደረግ የነበረውን እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምትነት ለማስተባበር ሲሠሩ የነበሩት አቶ ግርማ ነበሩ። ከዚህም የጎላ እንቅስቃሴያቸው ጋር በተያያዘ በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይደርስባቸው ነበር።
በቢሾፍቱ የሚገኘው የኢዜማ መዋቅር በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ችግሮች በዋናው ጽሕፈት ቤት እገዛ እንዲስተካከል አቤቱታቸውን ቀደም ብለው አስገብተው ነበር። ይህንኑ መሰረት በማድረግ ከከተማው እና ከክልሉ ኃላፊዎች እንዲሁም ከገዢው ፓርቲ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ሙከራ አድርገን ነበር። ሙከራችን የነበረውን ችግር ማቃለል አልቻለም። እንደውም ችግሩ ተባብሶ የሁለት ልጆች አባት እና የቤተሰብ ኃላፊ እና የኢዜማ የአድአ ምርጫ ወረዳ 1 ሊቀመንበር የነበሩት ግርማ በጥይት ተመተው መተኪያ የሌለው ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የኢዜማ የቢሾፍቱ መዋቅር ለኢዜማ ዋናው ጽሕፈት ቤት ካስገባው አቤቱታ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በከተማው እንቅስቃሴ ለማድረግ ያጋጠማቸውን ችግር እና እየደረሰ ያለውን ወከባ ገልፀው አስፈላጊውን እንዲያደርጉ በደብዳቤ ጠይቀው ነበር።
የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ከዚህ ቀደም የኢዜማ ዕጩ ተወዳዳሪ የሆነን ሰው መኖሪያ ቤት በፈተሸበት ወቅት የወሰዳቸውን የፓርቲው መገልገያ ሰነዶች እንዲመልስልን ስንጠይቅ ውክልና ያለው ሰው እንድናሳውቅ በጠየቀው መሰረት አባላችን ግርማ ሞገስን ጉዳዩን እንዲከታተሉ እና ንብረቶቻችንን እንዲቀበሉ ወክለን የላክነውን ደብዳቤ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ የካቲት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ማሕተም እና ፊርማ አስፍሮ ተቀብሎን ነበር። ይህ በእንዲህ እያለ የአባላችን መገደልን ተከትሎ በፍጥነት ወደድምዳሜ ከመሄድ ይልቅ በጥንቃቄ ዝርዝር መረጃዎችን ለማሰባሰብ ጥረት በምናደርግበት ወቅት የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ጉዳዩን ተከታትሎ በሕግ የተጣለበትን ፍትህን የማስከበር ሥራውን ከመወጣት ይልቅ የአባላችን መገደልን አስመልክቶ የከተማው ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ታሪኩ ለገሰ ለፋና፣ ኢቲቪ፣ ዋልታ እና ኦቢኤን ቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ ግርማ የኢዜማ አባል እንደሆነ እንደማያውቁ በመካድ የግድያውን አቅጣጫ ለማስቀየር የሄዱበት ርቀት እና ከዚህ በፊት በከተማው የፓርቲያችን እንቅስቃሴ ላይ እና አባሎቻችን ላይ ይደርስ ከነበረው መዋከብ እና እንግልት ጋር ተደምሮ ግድያው የተቀነባበረ እንደሆነ ያመላክታል።
የሕግ የበላይነት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን እንዲሰፍን የሚደረገው ትግል የብዙዎች መራር ትግል እና መስዕዋትነትን የጠየቀ እንደሆነ ይታወቃል። አባላችን ግርማ ሞገስን ጨምሮ ከዚህ ቀደም ስለእኩልነት እና ፍትህ ሲሉ ዋጋ የከፈሉ ኢትዮጵያዊያን መስዕዋትነት ቁጭት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመመሥረት ለምናደርገው ትግል ተጨማሪ ብርታት ይሆነናል እንጂ በዚህ ምክንያት በፍፁም ወደኋላ አንልም። እየሞትንም ቢሆን ዴሞክራሲዊት ኢትዮጵያን ከመገንባት የሚያቆመን ምንም ኃይል የለም፡፡ ይህ ለማንም ግልፅ ሊሆን ይገባል።
ቀጣዩ ምርጫ ነፃ እና ፍትሃዊ እንዲሆን መሟላት ከሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ በሚደረግባቸው አካባቢዎች በነፃነት መንቀሳቀስ፣ ለማኅበረሰቡ አማራጫቸውን ማቅረብ መቻል እና ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በምርጫው ውስጥ ያለምንም ፍርሃት መሳተፍ መቻላቸው እንዲሁም ከምርጫው ጋር በተያያዘ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ለማንም ሳይወግኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በገለልተኝነት ማስተናገድ መቻላቸው ይገኝበታል። በምርጫ ቅስቀሳ ዋዜማ አባላችን ላይ የተፈፀመው ግድያ እነዚህ መስፈርቶችን በተመለከተ ብዙ መሠራት ያለባቸው የቤት ሥራዎች እንደሚቀሩ በግልፅ ያሳየ ነው።
ኢዜማ የዓባላትችን ግርማ ግድያ ተከትሎ፣
1. መንግሥት የጓዳችንን ሕይወት የቀጠፉትን ወንጀለኞች አድኖ ሕግ ፊት ባስቸኳይ እንዲቀርብ እንጠያቃለን፣
2. ቀደሚ ሲል አቶ ግርማን ጨምሮ በአባሎቻችን ላይ ወከባን ማስፈራሪያ ያደርጉ የነበሩት የቢሾፍቱ የፓርቲና የመንግስት ሀላፊዎች የምርመራው አካል እንዲድሆኑ እንጠያቃልን፣
3. ጉዳዩን ቀድሞ እንዲያውቁ የተደረጉት የክልሉም ሆኑ የፓርቲው ከፍተኛ ሃላፊዎች ግድያውን እንዲያወግዙ እንጠያቃለን፣
በኛ በኩል ይህንን የማጣራት ሥራ በሚመለከት ማገዝ የምንችለውን ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን። የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግሥት ይህን ማድረግ ሲችል ብቻ ነው ለሰላማዊ እና ፍትሀዊ ምርጫ ከልቡ የተዘጋጀ መሆኑን ማወቅ የምንችለው።
ለአባላችን ግርማ ሞገስ ለገሰ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች እና የትግል አጋሮች ልባዊ መጽናናትን እንመኛለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
Filed in: Amharic