>

“ስንጀምርም ስንጨርስም በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ውስጥ ሆነን ነው...!!!” የአብን ሊቀመንበር ረ/ፕ በለጠ ሞላ

 

“ስንጀምርም ስንጨርስም በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ውስጥ ሆነን ነው…!!!”

የአብን ሊቀመንበር ረ/ፕ በለጠ ሞላ


ጌትነት ምህረቴ

በአንድነት ሀይል ተሰልፎ በብሄር ፖለቲካ የተደራጁ ሀይሎችን ማስረዳትና መግባባት አስቸጋሪ መሆኑን ነዉ የተረዳነው!

ፕሮፌሰር በለጠ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት ፣ አማራ በሰፊዋ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች መኖሩ ብቻውን አማራው እንዳይደራጅ ምክንያት ሊሆን አይገባም።ለአማራው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሌላው ህዝብ ዘላቂ ጥቅም ሲባል አማራ መደራጀት አለበት፡፡

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለውን አማራ መብቶቹን ማስጠበቅ እና ጥያቄዎቹን መመለስ ለአሮሞ ህዝብ ጥቅም ተገቢ እንደሆነ ለማስረዳት ጭምር እንደ አማራ መደራጀት አስፈላጊ መሆኑን ያመለከቱት ፕሮፌሰር በለጠ፣ በአንድነት ሀይል ተሰልፈን በብሄር ፖለቲካ የተደራጁ ሀይሎችን ማስረዳትና መግባባት አስቸጋሪ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ለዚህም እንደ አማራ ተደራጅተን፣ እንደ አማራ መሞገትና ማስረዳት ይጠበቅብናል ያሉት ፕሮፌሰር በለጠ፣ ይህ ማለት ግን ከኢትዮጵያዊነት መሸሽ አይደለም። ስንጀምርም ስንጨርስም በኢትዮጵያዊነት እሳቤ ውስጥ ነን ብለዋል፡፡

የነበረው ስርአት የአማራን ህዝብ ታሪክ በጨቋኝነት የሚፈርጅ፣አማራ በሌሎች ህዝቦች በጥርጣሬና በጨቋኝነት እንዲታይ ያደረገ እንደነበር አመልክተው፣ በአደባባይ ሲነገር የነበረ የሀሰት ትርክት ነበር ብለዋል። ትርክት ብቻ ሳይሆን ህገ መንግስቱም ከዚህ መንፈስ አንጻር የተቃኘ እንደሆነ ህግጋቶቹ፣ ተቋማቱ በዚሁ መንፈስ ይሰሩ እንደነበር ጠቁመው።

ይህም በአማራው ላይ መገለል እንዳደረሰ ያመለከቱት ፕሮፌሰር በለጠ ፣መገለሉ አማራው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ወሳኝ እንዳይሆን ማድረጉን አስታውቀዋል።በዚህም የአማራው ህዝብ ጥቅሙ እንዳይረጋገጥ ተደርጓል።የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዳይመለሱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአማራ ልጆች መደራጀታቸውና ተደራጅተው መታገላቸው ዜናው ለብዙዎች አስደጋጭ እንደነበር አመልክተው፣ ከኢትዮጵያዊነት የመሸሽ ለብሄር ፖለቲካው እጅ መስጠት፤ ህወሓት በአሰመረው መስመር የመጓዝ አይነት ተደርጎ ተተርጉሞ እንደነበር አመልክተዋል። በተጨባጭ አገሪቱ ላይ ያለው ማደራጃ መርሁ የብሄር ፖለቲካ መሆኑን ባለመረዳት አብን መመስረቱ ከኢትዮጵያዊነት የመሸሽ ስጋት አድርገው የተመለከቱት አሉ፡፡ ይህን ሀሳብ እኛም እንረዳዋለን” ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አማራው እንዳይደራጅ የሚፈልግ ሀይል በርካታ መሆኑን ያመለከቱት ፕሮፌሰር በለጠ፣በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተዋናይ የሆኑ ሀይሎች አማራው እንዲደራጅ አይፈልጉም ነበር፡፡ለምሳሌ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም በጉባኤ አብን ስንመሰረት አንዳንድ የትግራይ ሚዲያዎችና ድረ ገጾች ደርግ በአዳራሽ ተመሰረተ ብለዋል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የእኛን ስም የማጥፋትና የመታገል ስራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሌሎችም የብሄር አደረጃጀቶች አማራው እንዳይደራጅና የፖለቲካ ስራ እንዳይሰራ የሚፈልጉ ሀይሎች ከጅምሩ ጀምሮ እኛን በመፈረጅ ህዝቡ በእኛ ላይ እምነትና መተማመን እንዳይኖረው ሰፊ ስራ ሰርተዋል፡፡ አንዳንድ የአንድነት ሀይሎችም አማራው በብሄር መደራጀቱ ችግር ይፈጥርብናል በሚል አብን ጽንፈኛ፣ ፋሽሽትና ከኢትዮጵያ ተገንጣይ ነው በሚል የተለያዩ ስሞችን በመስጠት ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ ሲነዙብን ቆይተዋል ሲሉም ተናግረዋል።

በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አንዳንድ በጽንፈኝነት ሊያስፈርጁን የሚችሉ ድምጸት ያላቸው ንግግሮችን አድርገን ሊሆን ይችላል፡፡እንዲህ አይነት ነገሮች ተደምረው እውነተኛ ፍላጎታችን ሌላ ሆኖ እያለ ኢትዮጵያዊነታችን ፈጽሞ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ሳይሆን እነዚህ ፕሮፓጋንዳዎች በእኛ ላይ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ሌላ ስዕል እንዲይዙ አድርጓቸው ነበር፡፡እንደዚህ አይነት ተግዳሮቶች ነበሩ።ዛሬ ላይ ግን የመጣንበት የሁለት ዓመት ከመንፈቅ ጉዞ በእርግጥም ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ጊዜ ከፊት ቆመን ኢትዮጵያን የማዳን ስራዎችን እንደሰራን ማንም የሚገነዘበው ነው ብለዋል ፡፡

በዚህም ከመንግስት ጭምር ምስጋናን አግኝተናል። ወሳኝ በሆኑ ወቅቶች ላይ የወሰድናቸው የፖለቲካ አቋሞች በእርግጥም ሀቀኛ ኢትዮጵያዊ ሀይል እንደሆንን ማሳየት አስችሏል፤ በዚህም አጋጥ መውን የነበሩ ተግዳሮቶችን አልፈናል ብዬ መናገር እችላለሁ ብለዋል ፡

Filed in: Amharic