>

አገዛዙ መቸም ቢሆን በምንም ተአምር ነጻ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ እንደማያደርግና ላድርግ ቢልም ፈጽሞ ሊያሸንፍ እንደማይችል ልንገራቹህ??? (አምሳሉ ገኪዳን አርጋው)

አገዛዙ መቸም ቢሆን በምንም ተአምር ነጻ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ እንደማያደርግና ላድርግ ቢልም ፈጽሞ ሊያሸንፍ እንደማይችል ልንገራቹህ???
አምሳሉ ገኪዳን አርጋው

አገዛዙ በመጭው ምርጫ ተቃዋሚዎችን ያለ አንዳች እንቅፋት ወይም ገደብ፣ ወከባና አፈና እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው ለመመረጥ እንዳይችሉ ለማድረግና አጭበርብሮ “አሸነፍኩ!” ለማለት በሚገባ መዘጋጀቱን የምርጫ ቦርድ ተብየው ሲሠራቸው ከሰነበተው ከእያንዳንዱ ሥራዎቹ በሚገባ የተረዳን ቢሆንም አገዛዙ ካላጭበረበረ ወይም ኮሮጆ ካልገለበጠ በስተቀር በምንም ተአምር ቢሆን በነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ማሸነፍ የማይችልበትን አንድ ምክንያት ብቻ ልንገራቹህ፦
አገዛዙ “መሬት የመንግሥት ነው አይሸጥም አይለወጥም!” የሚልና “ይሄ ድንጋጌ በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ካልሆነ በስተቀር ፈጽሞ አይቀየርም!” ሲልለት የኖረው ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ አለው፡፡ አገዛዙ ለውጥ በሚለው ድራማው ዘመንም ይሄንን ድንጋጌ በምንም ተአምር ቢሆን እንደማይቀይረው አቶ ዐቢይ ከሸገር ራዲዮ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ማስታወቁ ይታወሳል!!!
ልብ በሉ እንግዲህ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ከገጠር እስከ ከከተማ ያለው በሙሉ መሬት የግሉ እንዲሆንና ሲፈልግም መሸጥ መለወጥ የሚችለው ንብረቱ እንዲሆን ጽኑ ፍላጎትና ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ብዙ የታገለበትና ዋጋ የከፈለበት ብርቱ ጥያቄው ነው!!!
ተቃዋሚዎች ቢመረጡ መሬትን የግል እንደሚያደርጉ ምርጫ በመጣ ቁጥር በምረጡኝ ዘመቻቸውና በምርጫ ክርክር መድረኮች ማኒፌስቷቸውን ሲያቀርቡ የምንሰማው ጉዳይ ነው!!!
እናም ተቃዋሚዎች መሬትን የግል እንደሚያደርጉ እየገለጹ ባሉበት ሁኔታና የኢትዮጵያ ሕዝብም ገጠር ከከተማ መሬት በፈለገው ጊዜ የሚሸጠውና የሚለውጠው የግል ንብረቱ እንዲሆን የዘመናት ጥያቄውና ጽኑ ፍላጎቱ በሆነበት ሁኔታ በምንም ተአምር ቢሆን ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል ኮሮጆ ገልብጦ ካልሆነ በስተቀር “በመቃብሬ ላይ ካልሆነ በስተቀር መሬት የግል አይሆንም!” የሚለው አገዛዙ በነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ተወዳድሮ ሊያሸንፍ ይቅርና አንዲት ድምፅ እንኳ ከሕዝብ አያገኝም!!!
አገዛዙ “አሸነፍኩ!” ካለ ኮሮጆ ገልብጦ መሆኑን የሚያረጋግጠው ቀላሉ አመክንዮ በመሬት ጉዳይ ላይ ያለው የማይለወጥ እብሪተኛና አንባገነናዊ አቋሙና የሕዝቡ ጽኑ ፍላጎትና የዘመናት ጥያቄ ፈጽሞ የማይጣጣም፣ የማይስማማ፣ የሚቃረን መሆኑ ነው!!!
አገዛዙ መሬትን ፈጽሞ ለድርድር በማያቀርብበት ሁኔታ “የመንግሥት ነው አይሸጥም አይለወጥም!” የሚልበት ምክንያት ደግሞ በሕዝብ ተወዶ ሊመረጥ የሚችልበት ላሕይ፣ ውበትና ምግባር እንደሌለውና በዚህም ምክንያት መቸም ቢሆን በሕዝብ ሊመረጥ እንደማይችል በሚገባ ስለሚያውቅ ነው መሬትን በእጁ አድርጎ በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝብ 85% የሚኖርበትንና “ማኅበራዊ መሠረቴ ነው!” ነው የምለውን ገበሬውን ወይም የገጠሩን ሕዝብ “እኔን ካልመረጥክ መሬትህን እቀማሀለሁ!” በሚል ማስፈራሪያ ሳይወድ በግዱ እንዲመርጠው እያደረገ ለዘለዓለም ለመኖርና ሲፈልግ ደግሞ ከመሬቱ ማፈናቀልና መሬቱን ቀምቶ መሸጥ የሚፈልገውንም መሬት ያለ ችግር አፈናቅሎ ለመሸጥና ለራሱ ሰዎችም ለማደል እንዲመቸው ነው!!! በዚህም መሠረት እንደምታውቁት ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲጫወት ቆይቷል!!!
በመሆኑም አገዛዙ መቸም ቢሆን በምንም ተአምር በነጻ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ፈጽሞ ሊያሸንፍ ስለማይችል በቀጣዩ ምርጫም ልምድ ያካበተባቸውን የማጭበርበሪያ መንገዶችንና አዳዲስ የማጭበርበሪያ መንገዶችንም በመጠቀም እንዲሁም ኃይልን አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው ቦታ ሁሉ ተጠቅሞ “አሸነፍኩ!” የሚል መሆኑን ቅንጣትም ቢሆን አትጠራጠሩ!!!
ስለዚህ ተቃዋሚዎች ከአጫዋችነት ወይም ከአጃቢነት የዘለለ ሚና አይኖራቸውም ማለት ነው፡፡ አገዛዙ ለውጥ የሚል ድራማ አምጥቶ አፈ ቀላጤውን አቶ ዐቢይ አሕመድን ሀገሪቱንና ዓለምን እንዲዞር በማድረግ ሕዝቡን ከሀገር ቤቱ እስከ ዳያስፖራው ድረስ በሀገሪቱ ነጻ የሕግ አስፈጻሚና የሕግ ተርጓሚ ተቋማት ተገንብተው ማንም የማይገለልበት ወይም ሁሉንም ያካተተ ፍጹም ነጻ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ የሚደረግ አድርጎ በመናገር ሕዝቡን በእርጎ ባሕር ላይ እያስዋኘ ያጃጃለበትና ያቄለበት ስንት የተባለለት ምርጫ “ነጻ ይሆናሉ!” የተባሉት ተቋማት በጽንፈኛ ኦሮሙማ ተጠምቀው ተስፋው ሁሉ እንደጉም በኖ በቦታው ደግሞ አስጨናቂ ሥጋት ነግሦ መጨረሻው ይሄ ሆነ ማለት ነው!!!
አገዛዙ በዚህኛው ምርጫ ግፋ ቢል ሊያደርግ የሚችለው ምን መሰላቹህ እንደ መጨረሻዎቹ 4ኛውና 5ኛው ሁለት የውሸት ምርጫዎች 100% እና 99% “አሸንፌያለሁ!” ማለቱን ይተውና ለቀቅ አድርጎ ዋና ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ ከሚባሉት ቅጥረኞቹ አመራር አመራሮቹን ወይም ዋና ዋናዎቹን ያስገባና ምርጫው ነጻና ፍትሐዊ የነበረ ለማስመሰል ይሞክራል፡፡ ያውም በጣም ከቸረ ነው እንጅ “ከ200% አሸነፍኩ!” ብሎ የተረኝነትን ሪከርድ በምርጫውም በመስበር ያስደንቀንም ይሆናል!!!
እስከ ሁለት መቶ የፓርላማ ወንበር ድረስ ለተቃዋሚ ቅጥረኞቹ ቢሰጥ እንኳ መንግሥት የመመሥረቱ ዕድል የእሱ ስለሚሆን በምርጫ 1997ዓ.ም. ተቃዋሚዎች ፓርላማ ገብተው ወሬ ከማሞቅ የዘለለ ሚና ውሳኔ የማስለወጥና የመወሰን ወይም ፍላጎትን የማስፈጸም ሚና እንዳልነበራቸው ሁሉ በቀጣዩ የውሸት ምርጫ አገዛዙ የሚያስገባቸው ተቃዋሚዎችም ወሬ ከማሞቅ የዘለለ ሚና አይኖራቸውም ማለት ነው!!!
እናም የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ አገዛዝ ስር እስካለ ጊዜ ድረስ መቸም ቢሆን ምንም ተስፋ እንደሌለው አውቆ ለስርነቀል ለውጥ ቆርጦ መነሣት አለበት!!!
Filed in: Amharic