>

ደርጉ ብልጥግና…  !!! በዘመድኩን በቀለ

ደርጉ ብልጥግና…  !!!

በዘመድኩን በቀለ

… ብልጽግና ቁጭ ደርግ ራሱን ነው። ኢዜማ ደግሞ መኢሶን። ቀጥሎ የሚገመተው ደርጉ ብልጥግና መኢሶኑን ኢዜማ ቀርጥፎ አጣጥሞ ይበላዋል። ይበላሃል ጅቦ ። ኢዜቲ ሆይ ከምር እውነቴን ነው ” ቱ ዘመዴ ምንአለ በዪኝ ደርጉ ብልጥግና ሃም አድርጎ ይበላሻል። ጠብቂ።
… ደርጉ ብልጥግና የዋዛ አይደለም… እጅግ ሲበዛ ቀመር አዋቂ ነው። ወለጋ ላይ ወሎዬዎችን አርዶ እየበላ ደሴ ላይ ወሎዬዎችን የድጋፍ ሰልፍ የሚያስወጣ ዥግና ነው። በፕሮግራም ተቃዋሚዎቹን ሁሉ በየተራ አርዶ ጠብሶ የሚበላም በላተኛ ነው። መጀመሪያ ኃይለኛውን ተቃዋሚውን እየሳቀ፣ እየተቅለሰለሰ ወዳጁ ያደርገዋል። በአደባባይ አቅፎ እየሳመ፣ ራስ ጠጉሩንም እያሻሸ፣ ፎቶ አብሮ እየተነሣ ያቀርበዋል። ለጃዋር በኦሮሚያ ስም፣ ለብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ ስም እየማለ ሁለቱም የፈለጉትን፣ መስማት የሚሹትን እየነገረ ያቀርባቸዋል። ከዚያ አለሳልሶ፣ አዘናግቶ ይበላቸዋል። ሃም ነው።
… ዓይኑ እያየ እኮ ነው አራዳ ነኝ ባዩን ከእኔ በላይ ላሳር ባዩን ጃዋርን ራሱን እያሻሸ፣ አቅፎ እየሳመ፣ እንደፈለገው እንዲፏልል የመዝለያ ሜዳ ሰጥቶት እንደ እንቦሳ ጥጃ እንዲፈነጭ ካደረገው በኋላ የበላው። አሜሪካ ተቀምጦ ለቁጥጥር እንዳያስቸግረው አሜሪካ ድረስ ሄዶ ወደ ኢትዮጵያ አመጣው። ከዚያ በሚጥሚጣ እያጣቀሰ በላው። ጃዋር በደርጉ ተበልቷል።
… ኦነግን ማስፈራሪያ ነበር። ለኦሮሞ እንደ ምልክት የሚታይ ነበር። አንዲት ቀበሌ ነፃ አውጥቶ ባያውቅም አስመራ ተቀመጦ በመፎከር ያሸብር ያስደነግጥ ነበር። ደርጉ ግን ኦነግን አስመራ ድረስ ሄዶ ጀነጀነው። የአቀባበል ሥነ ሥርዓቱን አደመቀለት። በመስቀል አደባባይ በሬ፣ በቡራዩ ሰዎች አረደለት። ደምቀብቶ፣ ደም አሻግሮ አስገባው። ቤት ለመሪዎቹ፣ ጽሕፈት ቤት ለድርጅቱ ሰጠው። ቆይቶ ግን ደርጉ ኦነግን በላው። መሪው የቁም እስረኛ፣ ፓርቲውን እንደ ጣቃ ጨርቅ ተረተረው። አሁን ኦነግ የለም። ደርጉ አደገኛ ነው።
… ቁርስ ላይ ኦነግን፣ የሻይ ሰዓት ላይ ኦብነግን በለስላሳ የቀመቀመም ነው ደርጉ። ኦፌኮን ምሳ ላይ በአዋዜ፣ ሰማያዊን መቅሰስ፣ ባልደራስን የቡና ቁርስ አድርጎ የበላ ነው ደርጉ። የደርጉ ማስተር ማይንድ በፈርኦን ቤት ያደገ ፈርኦን ነው። አቢቹ ይበላል አይገልጠውም። ተናግሮ የማይደክመው፣ ፎቶ ነፍሱ የሆነ ቄሮ የቄሮም አለቃ የሆነ ምርጥ በላተኛም ነው።
… ደርጉ አደገኛም፣ አስብቶ አራጅ ቂመኛም ነው። ለአሳዳጊ የጡት አባቶቹም ያልራራ። እያዋዛ እያሳሳቀ ቀርጥፎ የበላቸውም ጀግና ነው። በህወሓት እንኳ ( ስለት ነበረብኝ። የስለቴ ነው የደረሰልኝ) ደጺንም ሂዊኒም ነው አጣጥሞ የበላቸው። ደርጉ… ለወዳጁ ለለማ መገርሳም አልራራም። መጀመርታ በአማሪካና በወዳጅ ሃገራት አስመክሮ፣ አስጠንቅቆም ከፊቱ ገለል እንዲል አስደረገ። ኋላ ላይ ለማ ሄጵ በማለቱ ሲቀጥል በጨው አሽቶ፣ በበርበሬና በቅቤ ለውሶ ዘልዝሎ በባዶ ቤት እንደ ቋንጣ አስጥቶ ንፋስ እንዳያገኘው አጅሎ አሽጎት፣ አሻግቶትም ጥግም አስይዞ ነው የበላው።
… ደርጉ የዋዛ አይደለም። … እስክንድርን ከዓይኑ ፊት አርቆ ለክፉ ቀን የረሃብ ዘመን ከመጣ ብሎ በጎተራ ቃሊቲ አካባቢ በመጋዘን በጎተራ አስቀምጦታል። ወይ እዚያው አልያም ከዚያ አውጥቶ የሆነ ቀን ያስበላዋል። ይበላዋልም። ልደቱና ይልቃልን ፓርቲያቸውን በቁሙ አፍርሶ ዋይ ዋይ አሰኝቶ በውኃ ጥም ጉሮሮአቸውን ካደረቀ በኋላ ምን ሊያደርጋቸው እንደሚችል የሚያውቀው ራሱ ደርጉ ብቻ ነው። ኦኦ ደርጉ ጃንሜዳ ሆድ ነው። በልቶ አይጠረቃም።
… አሁን ደግሞ ደርጉ በዐብንም ላይ ጎምጅቷል። ጆፌም ጥሏል። ሊበላትም የፈለገ ይመስላል። ሰሞኑን ዥግራዬም ነሽ እያላት ነው አሉ አጅሬ ደርጉ እሜይቴ ዐብንን። ጫንቃውን እንዲያይ፣ ሻኛውንም በታዬ ደንደአ እያስገመተ ነው። ቆይቶ የዐይንሽ ቀለም አላማረኝም። ልበላሽ ነው ሳይላት አይቀርም። በዐብን የሌለ ነው የተከየፈባት ብሎኛል አንድ የዶሮማነቂያ ጎዶኛዬ። ደግነቱ ዐብን ዐማራ መሆኑ በቀላሉ ላይታረድ ይችላል እንጂ ደርጉ ማንንም አይምርም። ( ዶር አምባቸው፣ ጄነራል አሳምነው፣ አቶ እዘዝ፣ አቶ ምግባሩ፣)  ነፍስ ይማር።
… በመጨረሻም ደርጉ ሁሉንም ከበላ በኋላ … ወዳጁን ኢዜማን፣ ሮድማፕ የሠራችለትን ኢዜማን፣ ስንት መከራ ያየችለትን ኢዜማን፣ ከህዝቡ ጋር አቃቅሮ አስጠምዶ ካራቃት በኋላ አጣጥሞ አርዶ ሊበላት ዳር ዳር እያላት ነው። ከአሁኑ በነቆራም በከዘራም ጀምሯታል።” የደርጉ ብልጥግና ካድሬዎች ሳይቀሩ ኢዜማ ላይ አፋቸውን በትልቁ መክፈት ጀምረዋል። በቅርቡ ኢዜማን ደርጉ መብላት ይጀምራል።
… ኢዜማም ከወዲሁ መላ እያበጀች ነው። ልሣኗ የነበረውን ኢሣትን ለሁለት ከፍላ አንዱን አዲስ አበባ አንዱን አማሪካ አድርጋ መጪውን ጊዜ ልትጠብቅ ነው። ከሁለት ያጣ እንዳትሆን መላ እየዘየደች ነው። አንዳርጋቸው ጽጌ የአማሪካው የኢሳት ቦርድ የተደረገው በምክንያት ነው። ጠብቁ ከጥቂት ቀናት በኋላ የዲሲ ግብረ ኃይል ፍሪ እስክንድር ነጋ ባይል ቱ ምን አለ በሉኝ። ዶላሩ ስለሚጠርባት ኢሳት በቅርቡ የቀድሞዋ እሳት ትሆናለች። ውዝግቡ በዚያ ቤት ጦፏል። የገሌ መጨረሻው ይሄው ነው።
… አማሪካም ሆነች ኤርትራ አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ምርጫቸው ደርጉ ብልጥግና ብቻ ነው። ብልጥ-ግና ብቻ። አከተመ። ደርጉን በምርጫ ማሸነፍ የማይሞከር ነው። ባይሆን የአሁኑ ምርጫ እንደ ዕቁብ ይቆጠርና የመጀመሪያውን ዕጣ ለደርጉ ቢሰጠው የሚሻል ይመስለኛል። የዕቁቡ ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳም ከአቶ ነጋ እና ከጋሽ አራጌ ልጆች ለአብዲሳና ለፈይሳ ልጆች የምትቀርብ ይመስለኛል። ይመስለኛል ነው ያልኩት። እናም ዕቁብተኞቹ የለደርጉ የዕቁቡን የመጀመሪያ ዕጣ በፈቃደኝነት ይልቀቁለትና ከመሞት መሰንብቱ ሳይሻላቸው አይቀርም። ይህን ያለው ደግሞ የምርጫ 8 የወረዳ 9 የቀበሌ 18 ዕጩ ተመራጩ አቶ ጠከሴማጱሩ ፈቖጿጨዿ ናቸው። ያለበለዚያ ደርጉ የሌለ ጢባጢቤ ነው የሚጫወትብህ።
… ነቆራ አንድ ፦ የዓሰሎጠሚዶኮ ዐቢይ አሕመድ እንዲህ አለ። “ይህ ሰነድ ድርሰት አይደለም። ብዙዎች ድርሰት እያዘጋጁ ነው፡፡ (በሾርኒ እነ ኢዜማን ማለቱ ነው) ሆኖም ፖሊሲ ድርሰት መሆን አይችልም። ማንፌስቶም ድርሰት አይሆንም፡፡ ለአንድ ዓመት የሚዘጋጅ ጉዳይም አይደለም፡፡ በሰፊ የመረጃ ማሰባሰብ፣ መተንተንና ከዚያ ተምሮ ለነገ የሚሆን ዐበይት ጉዳዮችን አካትቶ ለገባነው ቃል ኪዳን የምንሄድበት ሰነድ ነው፡፡ በመሆኑም ከወርና ከሁለት ወር በኋላ እኔ ፖሊሲ አለኝ ማለት ብቻውን ትርጉም አይኖረውም፡፡ እናም ፖሊሲ ድርሰት ሳይሆን ቃል ኪዳንን መወጫ ሰነድ ሆኖ መዘጋጀት ይኖርበታል።” ብለው ኮሎኔሎ ለኢኮኖሚስቱ መልእክታቸውን አስተላልፈውለታል።
• እናም ቀጥሎ ደርጉ ብልጥግና መኢሶንን ኢዜማን ይውጠዋል። ሰልቅጦ፣ ቀጥቅጦ ይበላዋል። ኢሳትም እሳት ልሁን ብሎ ይፍጨረጨራል። ወዶ ገብ ገሌ አሽከሩ ሁሉ በልብ ድካምና በደም ብዛት ይሰናበታል። በመጨረሻም ደርጉ ወይ ምርጫ ብሎም ነገር የለም ሊልህ ወይ ደግሞ የመጀመሪያውን ዕጣ ለእኔ ስጡኝ ብሎ ሁላ ሊጠቀልልህ ይችላል። አከተመ።
… ከዚህ በፊት በደርጉ ለተበላችሁ፣ አሁንም በደርጉ እየተቀጠፋችሁ ያላችሁ፣ ወደ ፊትም በተጠባባቂነት ልትበሉ የተዘጋጃችሁ በሙሉ ነፍስ ይማር።
Filed in: Amharic