>
5:26 pm - Wednesday September 17, 2988

ታሪክን የኋሊት:-  ርዕሲ ምድሪ /ምፅዋ  - የካቲት 9/1982 ዓ.ም ተወልደ በየነ(ተቦርነ)

ታሪክን የኋሊት:-

 ርዕሲ ምድሪ /ምፅዋ  – የካቲት 9/1982 ዓ.ም
ተወልደ በየነ(ተቦርነ)

የመጣው ይምጣ! ከሞት ውጪ የሚመጣ የለም! ነገሩ ከአቅም በላይ ከሆነ ሻዕቢያ ዓይኔን ማየት ቀርቶ ሬሣዬንም አያገኛትም! እድሜ ለቀይ ባህር ውሃ! የቀይ ባህር ዓሳ ይቀብረኛል!
የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጣሉብኝ አደራ ከድንጋይ በላይ ይከብደኛል ። በመሆኑም ጠላት ከአቅም በላይ ከሆነ እንደ አጼ ቴዎድሮስ ሽጉጤን እጠጣለሁ፡፡
የካቲት 9 ቀን 1982 ዓም ምጽዋ ከተማ ለተከማቸው አብዮታዊ ሠራዊትና አመራሩ ክፉ ቀን ነበረች ። ሻዕቢያ ደግሞ እንደ ልደት ቀን ይቆጠረዋል ። ምክንያቱም የሻዕቢያ ተዋጊ የድል ባለቤት ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ምፅዋ ከተማን የረገጠው በዚች ዕለት ነውና ።
ሻዕቢያ በ1970 ዓ.ም ከጀብሃ ተዋጊዎች ጋር በመሆን አብዛኛውን የኤርትራ ግዛት ተቆጣጥሮ ነበር፡፡ አሥመራ ባሬንቱ ምፅዋና ዓዲ ቀይህ ከተማ የነበሩትን የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት ደምስሶ እነዚህን ከተሞች መቆጣጠር አልቻለም፡፡በመሆኑም የሃያ ስምንት ዓመታት ምኞቱን ሻዕቢያ በምፅዋ እውን ያደረገበት ቀን የካቲት 9 ቀን 1982 ናት፡፡
ጄኔራል ተሾመ ተሰማ የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ከጠዋቱ 1፡30 ሰዓት ላይ በምፅዋ ከተማ ርዕሰ ምድር በተባለ አካባቢ በከባድ መሳሪያ በፈራረሱ ቤቶች ጥግ ሆነው የተወሰኑ የጦር መኮንኖችንና ባለሌላ ማዕረግተኞችን ሰብስበው ንግግር አደረጉ፡፡
ሻዕቢያ ያለ የሌለ ሃይሉን ተጠቅሞ በእጅ ቦምብና በክላሽ በአሁኑ ሰዓት የከተማ ውስጥ ውጊያ በማድረግ ላይ ነው፡፡ ሻዕቢያ የከባድ መሳሪያ ድብደባ አቁሞ በእግረኛ ብቻ ለመዋጋት አዲስ ተዋጊ ሃይሉን በመኪና እያመላለሰ ዕዳጋ ከተማ ላይ እያከማቸ ነው፡፡ በአዲስ ጉልበት ተዋግቶ ምፅዋን ለመያዝ ቆርጦ ስለመነሳቱ ጥርጥር የለውም፡፡
እኔ የሚፈለግብኝን አደራ ተወጥቻለሁ፡፡ ከጥር 30 ቀን 1982 እስከ ዛሬ የካቲት 9 ቀን 1982 የሞት ሽረት ትግል አድርጌያለሁ፡፡ የሻዕቢያን የጥፋት ዓላማ ለመግታት ያላደረኩት ጥረት የለም፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የራስን ሕይወት በክብር ከማጥፋትና ለኢትዮጵያ ጀግኖችና ታሪክ ጸሃፊዎች ታላቅ ተምሳሌት ከመሆን ሌላ አማራጭ የለኝም፡፡ ጀግንነት ማለት በሁሉም መልክ ለጠላት ምቹ ሆኖ አለመገኘት ማለት ነው፡፡
በዚች የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕር በርና ዓለም ዓቀፍ ወደብ በሆነችው በምፅዋ ከተማና በቀይ ባህር ጠረፍ ላይ ቆሜ ሽጉጤን ለመጠጣት ዝግጁ ሆኜያለሁ፡፡ በዕውነት እኔ ዛሬ በሞት ብሸነፍም በታሪክና በመጭው የኢትዮጵያ ትውልድ ፊት አልሸነፍም፡፡ የአፄ ቴዎድሮስን ዕድል በማግኘቴም በጣም እኮራለሁ፡፡ እኔ አሁን የተዘጋጀሁለት ሞት ዘላለማዊ ክብርና ሕይወት ይሰጠኛል ፡፡ በሻዕቢያ ተማርኬ የሻዕቢያን መሪዎች ዓይን ማየት ግን የሞት ሞት ነው፡፡
አፄ ቴዎድሮስ በእንግሊዞች እጅ ወድቀው ከመዋረድ ሞትን መርጠው የራሳቸውን ህይወት መቅደላ ላይ አጠፉ፡፡ እኔ ደግሞ በተራዬ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የተሰጠኝን የጄኔራልነት ማዕረግ ሳላስደፍር ለመንግስትና ሕዝብ በገባሁት ቃል ኪዳን መሰረት አቅሜ የፈቀደውን ያህል ተዋግቼና አዋግቼ ሻዕቢያን አራግፌያለሁ፡፡
እንደ ጦር መሪም እንደ ተራ ተዋጊም ሆኜ ክላሺንኮቭ ጠመንጃ ይዤ ተፋልሜያለሁ፡፡ አሁን ግን ለመጨረሻዋ መስዋዕትነት ህይወቴን ለማጥፋት የቀሩኝ ጥቂት ደቂቃዎች ናቸው፡፡
 ጎበዝ ስሙኝ ይህ የአደራ መልዕክቴ ነገ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይደርስ ይሆናል፡፡ ምናልባት አምላክ ካለ ከእናንተ አንዱ መልዕክቴን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ያደርስ ይሆናል፡፡ ዛሬ ሻዕቢያ ምፅዋን ተቆጣጥሬያለሁ በማለት የዓለምን መገናኛ ብዙኃን እንደሚያጨናንቅ ጥርጥር የለውም፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሀገሬና ሕዝቧ ትልቅ አደጋ ነው፡፡
በቀይ ባሕር በራችን በኩል ብዙውን ጊዜ ወረራ ፈጽመውብናል፡፡ በተደጋጋሚ ያሳፈርናቸውና ፊት ለፊት ያልቻሉን ምዕራባውያን ሀገሮችና ዓረቦች ዛሬ የሻዕቢያን ጊዜያዊ ድል ሰምተው ይፈነጥዛሉ፡፡ ምናልባትም የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ድንበር የሆነውንና ለዘመናት በአባቶቻችን የደም ዋጋ ፀንቶ የቆየውን የባህር በራችንን ለመዝጋት እንዲሁም ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ባሕር አይደለም በማለት በምድር ተወስነን እንድንቆይ ይደረግ ይሆናል፡፡ይህ ደግሞ የሞት ሞት ነው፡፡
ይሁን ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ ሁሉም ነገር ከቁጥጥሬ ውጪ ሆኗል፡፡ ከሙታን አለም መጥቼ ማረጋገጥ ባልችልም የፈለገ ጊዜ ይጠይቅ እንጂ ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ የባህር በር አልባ ሆና በኢምፔሪያሊስቶችና ጋሻጃግሬዎቻቸው ተሸንፎና እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም፡፡
ይህ ከሆነማ የአፄ ዮሐንስ የቀይ ባህር ተጋድሎ እና የጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ እንዲሁም የኔን ጨምሮ የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት ደምና አጥንት የኢትዮጵያን ትውልድ ሁሉ እስከ ዘለዓለሙ ይፋረዳል፡፡ኢትዮጵያ ሀገሬ የጀግኖች መፍለቂያና ገናና ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡
በመሆኑም ጀግናው ሕዝቧ ሕዝባዊ የባህር በሩ በሻዕቢያ ተይዞና የጠላቶቹ መፈንጫ ሆኖ አይቀርም፡፡ የፈለገ ጊዜ ይቆይ እንጂ ሻዕቢያ ምፅዋን እንደያዛት ለዘለዓለም አይኖርም ጊዜውን ጠብቆ የኢትዮጵያ ጀግና ጠላቱን ደምስሶ ምፅዋን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያስረክብ እምነቴ የጸና ነው፡፡ አሉና ትንሽም ፋታ ወሰዱ፡፡
 የጄኔራል ተሾመ ዓይን የቆሰለ ነብር ዓይን መስሏል ከንፈራቸው በውሀ ጥም ደርቆ ቅርፊት ይዟል፡፡ ፊታቸው በደረቅ ላብ ዥንጉርጉር ሆኗል፡፡ ለረዥም ሰዓታት ከምግብ በመራቃቸው ሆዳቸው ከወገባቸው ተጣብቋል፡፡
በተሰበሰበው አባል ውስጥ በሰፈነው ጸጥታና ዝምታ መሃል እናንተ አብዮታዊ መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረግተኞች! ስሙኝ አንድ ምሳሌ ልንገራችሁ፡፡ አሉ ጄኔራል ተሾመ ቆጣ ብለው፡፡
አንድ ሰው ቤት ሲሰራ የሚሰራው ቤት በርና መስኮት አሉት፡፡ አንድ ሰው ደግሞ ሞተ እንበል፡ መቃብሩ በርና መስኮት የለውም፡፡ በርና መስኮት የሕይወት ምልክቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ያለ ሀገር ነጻነትና ያለ ባሕር በር ብልጽግና ስለሌለ የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕር በር ተነጥቆ የሚኖር ሕዝብ አይደለም፡፡ ከሻዕቢያ ጀርባ ሆነው ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ አይደለም የሚሉ ሀገሮችና ጋሻጃግሬዎቻቸው ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ፍላጎታቸው የኢትዮጵያ ሞት ነው፡፡
ይህ ምሳሌ ከገባችሁ የባሕር በር የሌላት ሀገር ሞቶ ከተቀበረ ግለሰብ የምለየው በትንሹ ነው፡፡ ምክንያቱም የባሕር ሀብት ከማጣቷም በላይ ምርቷን ወደ ውጪ ለመላክ የግዴታ ወደብ ስለምትከራይ ለወደብ ክፍያ የምትከፍለው የገንዘብ ወጭ ዜጎቿን ያደኸያል፡፡
በአኳያው ጠላቶቿንና ባለወደቦቹን ያበለጽጋል፡፡ ይህ ዕድል ለኢትዮጵያ እንዳይደርሳት ቀይ ባሕርን የኢትዮጵያ ትውልድ ይፋረድ፡፡ ቀይ ባህር ለኔ ዘላለማዊ ቤቴ እንዲሆን ወስኛለሁ፡፡ ደስተኛና እድለኛ ጄኔራል ነኝ ። እኔ ብሞት ታሪኬ አይሞትም ። የእኔ ታሪክ በእንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ህሊና ውስጥ እንደሚኖር እገምታለሁ፡፡ ቻው! ቻው! ማንም ሰው ወደ እኔ እንዳይጠጋ አሉና ጄኔራል ተሾመ መኮንኖቹን ከሰበሰቡበት ቦታ ተፈናጥረው ወደ ቀይ ባሕር ጠረፍ አመሩ፡፡
የባሕሩ ጠረፍ ከስብሰባው ቦታ በግምት ከስልሳ ሜትር አይበልጥም በፍጥነት ወደዚህ ባሕር ጠረፍ ገሰገሱ፡፡ ክላሺንኮቭ ጠመንጃቸውን አቀባብለውና  አውቶማቲክ ላይ አድርገው በቀኝ እጃቸው ጨብጠዋል፡፡ በጄኔራል ተሾመ ተሰብስበው የነበሩ የአብታዊ ሰራዊት አባላት ተደናግጠው ከተቀመጡበት ተነስተው ቆመው የጄኔራሉን የመጨረሻ ፍጻሜ ለማየት እየዘገነናቸው እንባ በእንባ ሆኑ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ህይወታቸውን ለማጥፋት የክላሽንኮቭና የሽጉጥ መጠበቂያ ከፍተው የጄኔራል ተሾመን ምሳሌነት ለመከተል ተዘጋጁ፡፡
ጄኔራል ተሾመ ከምጽዋ ወደብ በስተቀኝ ከሚገኘው ወታደራዊ ወደብና መደብር ላይ ሲደርሱም ለቀይ ባሕር መገደቢያ በተሰራ ግንብ ጠርዝ ላይ ጀርባቸውን ወደ ቀይ ባሕር ፊታቸውን ወደ ምፅዋ ከተማ ሰድርገው ቆሙ፡፡ ቀጥለውም በእጃቸው የነበረውን ክላሺንኮቭ ጠመንጃ ወደ ቀይ ባሕር ወረወሩት፡፡
ከዚያም በወገባቸው ታጥቀውት የነበረውን ኮልት ሽጉጥ አወጡና የሽጉጡን አፈሙዝ በአፋቸው ጎርሰው የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡10 ሰዓት ሲሆን ቃታውን ሳቡት፡፡ የሽጉጥ ተኩስ እንደተሰማ ወደ ጀርባቸው በቀይ ባሕር ውሃ ላይ ወድቀው ሰጠሙ፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት ተሸቀዳድመው ባሕር ጠረፉ ላይ ደርሰው የጄኔራሉን አስከሬን ሲመለከቱ ከጭንቅላታቸው የሚፈስ ደም በቀይ ባሕር ውሃ ላይ ቀልቶ ይታይ ጀመር፡፡
ወዲያውም ይህን የጄኔራል ተሾመን ሞት በምስክርነት ቆመው ካዩት መካከል ከ150 የማያንሱ የጦር መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረግተኞች በሽጉጥ በእጅ ቦምብና በክላሽ ጠመንጃ ህይወታቸውን አጠፉ……..
የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም
ምንጭ : ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ – አይ ምፅዋ
ክብር ለጀግናው ለቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት!
Filed in: Amharic