>

የኢትዮጵያን ሕዝብ በመጨፍጨፍ ከዓላማው ማሰናከል አይቻልም...!!! ታሪክ ምስክር ነው...!!! (ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ የታሪክ ተመራማሪ)

የኢትዮጵያን ሕዝብ በመጨፍጨፍ ከዓላማው ማሰናከል አይቻልም…!!! ታሪክ ምስክር ነው…!!! ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ የታሪክ ተመራማሪ
ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ የታሪክ ተመራማሪ

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የታሪክ ተመራማሪ እና መምህር ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ያለቁበትና በወራሪው የጣሊያን ወታደሮች የተፈጸመው የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ጭፍጨፋ በሕዝቦች ዘንድ ሽብር በመፍጠር ድልን የመቀዳጀት ዓላማ የነበረው ነው።
ድርጊቱን በቅርቡ በጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የተቀነባበረውን የማይካድራው የዘር ጭፍጨፋም ከየካቲት 12ቱ ጭፍጨፋ ጋር በዓላማ ደረጃ ያላቸውን ተመሳሳይነት እንዳለው የጠቆሙት ፕሮፌሰር ሹመት ፣ እነዚህ ሁለት ድርጊቶች ያነገቡትን ዓላማ ያላሳኩ እና ውጤታቸውም ከታሰበው በተቃራኒ መሆኑን ገልጸዋል።
የየካቲት 12ቱ ጭፍጨፋ ዋነኛ ዓላማ ሕዝቡን ለማስፈራራትና ትግሉን ያስቀጥላሉ ተብለው የታመነባቸው ክፍሎች በማጥፋት የጣሊያንን ተቀባይነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የኢትዮጵያውያንን ትግል ጨርሶ ለማዳፈን ያለመ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ሹመት ፣ በተመሳሳይ መታወቂያ እና ቋንቋ እየተለየ ዜጎች የተጨፈጨፉበት የማይካድራው ጥቃት በተጨፍጫፊው ሕዝብ ዘንድ ፍርሃትና ሽብር በመፍጠር ድሉን ለመንጠቅ የተደረገ ጥረት መሆኑን አመልክተዋል ።
ከምንም በላይ ሁለቱም ክስተቶች አንድ የሚያደርጋቸው ደግሞ ሕዝብ በማንነቱ ተለይቶ የተገደለባቸው ሁነቶች ከመሆናቸውም በተጨማሪ ሁለቱ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች የመነጩት ከፈጻሚዎቹ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን አርበኞች ወራሪውን የጣሊያን ጦር አምርረው ጫካ የገቡት ከየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በኋላ ነው ያሉት የታሪክ ተመራማሪው፣ ክስተቱ የጣሊያን ጦር ባልጠበቀው መንገድ የኢትዮጵያውያንን ትግል ማነቃቃቱን አመልክተው ፣ ጭፍጨፋው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የንዴት እና የመቆጨት ስሜት ስላሳደረ ክስተቱ የኢትዮጵያውያንን ትግል ከማዳከም ይልቅ የበለጠ እንዲስፋፋ እና መራር የሆነ የነጻነት ትግል እንዲካሄድ እገዛ ማድረጉን አስታውቀዋል።
 እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፣ የማይካድራው ጭፍጨፋም አብዛኛው ዳር ቆሞ ይመለከት የነበረው ሕዝብ ይህንን ዘግናኝ ጭፍጨፋ በመመልከት ነግበኔ በማለቱ እንዲሁም ‘ይሄ የአረመኔ ስራ ነው፤ ማንም ሰብዓዊ ፍጡር ይህንን ዘግናኝ ሁኔታ ቆሞ መመልከት የለበትም’ በማለት በህወሓት ላይ የበለጠ ቆርጦ እንዲነሳና ሁለተኛ እድል እንዳያገኙ ለማድረግ ከዳር እስከዳር ሕዝቡን ያስተባበረ ክስተት ሆኖ አልፏል።
የህወሓት የጥፋት ዓላማ ቀድሞውኑ የታወቀ ቢሆንም የማይካድራው የዘር ጭፍጨፋ የያዘው አገር አጥፊና አውዳሚ ዓላማ በግልጽ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኛን ዓላማ ትክክለኛነት እና የተጻራሪው ኃይል አውዳሚ ሀሳብ ለማስረዳት መሞከር ያለብን ቢሆንም እነሱን ለማስረዳት ስንጥር ብዙ እድሎች ሊያመልጡን ይችላሉ ያሉት ተመራማሪው፣ወሳኙ ጉዳይ እኛ ኢትዮጵያውያን ከእንዲህ አይነቱ ክስተት ራሳችንን አውጥተን ከፍ ላለ እና አሸናፊ ለሚያደርግ ዓላማ እንድንሰለፍ በቂ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ነው ብለዋል ።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁኔታውን በአግባቡ ባለመረዳት ሊጯጯህ ፤ እንደ ማይካድራ ያሉ እጅግ ዘግናኝ ክስተቶች በአግባቡ ላይረዳው ይችላል፤ ወይም አቃሎ ሊመለከታቸው እንደሚመለከተው ጠቁመው ፣ የኢትዮጵያውያን እጣ ፈንታ የሚወሰነው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚኖረው ግንዛቤ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን በሚያዳብሩት ብስለት ነው መሆኑን አመልክተዋል ።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማይካድራውን አይነት ክስተት እንዳይፈጠር ሊከላከልልን እንደማይችል ያስታወቁት ፕሮፌሰር ሹመት ፣ እኛ ያጣመምነውን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያቃናልን እንደማይችል አስታውቀዋል ።
በ1929 ዓ.ም ከሰላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በጣሊያን ወራሪ የተጨፈጨፉበት ቀን ዘንድሮ ለ84ኛ ጊዜ እየታሰበ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2013
Filed in: Amharic