>

ማን ላይ ጣታችንን እንጠቁም??? (አሣፍ ኃይሉ)

ማን ላይ ጣታችንን እንጠቁም???

አሣፍ ኃይሉ
 
/ከሐረሩ የልዑል ራስ መኮንን ሐውልት ማፍረሶች በስተጀርባ ያሉ አንዳንድ ታሪካዊ እውነቶች!/ 
 
ይድረስ ለአቻምየለህ ታምሩ፡- 

 

እንደተለመደው ፀሐፊውን (በራስ መኮንን ኃውልት ፈረሳና በአድዋው ድል ምጸታዊ አከባበር ላይ ያሰፈረውን የውግዘት ጽሑፍ ) አድንቄ፣ የዚህን የታሪክ ማፍረስ ድርጊት በተመለከተ የግድ መታየት ያለባቸውን ጥቂት ታሪካዊና አሁን እየተከናወኑ ያሉ ዳራዎችን አንስቼ ጥቂት ነገር ማከል ፈልግኩ፡፡ የሐረር ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ሁሉ ከወያኔ ወደ ሥልጣን መምጣት ጋር በቀጥታ የተገናኙ ናቸውና – ጊዜ ሳልፈጅ ከዚያ እጀምራለሁ፡፡
 
‹‹ሽግግር መንግሥቱ›› በሚባለው የወያኔ አገዛዝ ጅማሮ ላይ – የሁሉም ብሔር-ብሔረሰቦች ማዕከል ናቸው ተብለው የተለዩ ሶስት የኢትዮጵያ ከተሞች ‹‹የቻርተሩ ነጻ ክልሎች›› ተብለው ተቀመጡ፡፡ እነዚህ የቻርተሩ ሶስት ነጻ ከተሞች ድሬዳዋ፣ አዲስአበባና ሐረር ነበሩ፡፡ 
 
በመሐል ግን በ1984/85 ላይ ወያኔ ሐረርን ለኦነግ በከፊል በመስጠት፣ ከሐረር የቻርተሩ ነጻ ከተማነት ጎንለጎን ልዩ የኦሮሚያ አስተዳደር የሚል ተቀጽላ አስተዳደር አበጅታ በእጅ መንሻነት ልትሰጠው ዳር ዳር ብላ ነበር፡፡ ኦነግ የወያኔን ጉባዔ ረግጦ ባይወጣ ኖሮ ምናልባትም ሐረር እንደ እጅ መንሻነት ኦሮሚያ ለሚባለው ክልል ተላልፋ የምትሰጥ ገጸበረከት ትሆን እንደነበር ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም ኦነግ ከወያኔ ጋር ጦር ተማዞ ተደመሰሰ፡፡ 
 
በ1987 ወያኔ ህገመንግስቱን አስፀድቆ ኢፌዲሪ በሚል ስም ኢህአዴጋዊ አገዛዙን በኢትዮጵያ ላይ ዘረጋ፡፡ ሲዘረጋ በቻርተሩ ነጻ ክልል ከተባሉት 3 ከተሞች መሐል – አዲስአበባና ድሬዳዋን ወደ ፌደራሉ መንግሥት ከተማነት ሲያዞራቸው ሐረርን የፌዴራል ከተማ ከመሆን አገዳት፡፡ እና በሐረር ለኦነግ ተብሎ የተቋቋመውን ልዩ ዞን ሙሉ በሙሉ ለኦፒዲኦ ሰጥቶ – ሐረርን የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) ለሚባለው እና ለኦፒዲኦ የሞግዚት አስተዳደሮች አሳልፎ ሰጣት፡፡ ህዝቡስ? 
 
ህዝቡ የመንግሥት ሠራተኛው ወይ በአደሬው ወይ በኦሮሞው አስተዳደር ሥር ግባ ተባለ፡፡ ሥልጣኑ ሁሉ ለሁለቱ ‹‹ብሔሮች›› ተደለደለ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ‹‹የክህደት ቁልቁለት›› በሚል መጽሐፋቸው ላይ ያን 20 ፐርሰንት ያልሞሉት አደሬዎች በህገመንግሥቱ እውቅና ተችሯቸው 80 ፐርሰንቱን ከተለያየ ብሔር የተውጣጣ የከተማ ሕዝብ የሚገዙበትን ክልላዊ መዋቅር ከደቡብ አፍሪካው የእንግሊዞች አፓርታይድ ጋር አነጻጽረው ገልጸውት ነበር፡፡
 
ጥያቄው ድሬዳዋና አዲሳባ የፌዴራል ከተሞች ሲደረጉ፣ ሐረሪ ለምን ቀረች ነው? በትንሹ 7 ተያያዥ ምክንያቶችን አነሳለሁ፡-
 
1ኛ/ ሐረር ወያኔን በቁሟ ሲያስቃዣት የኖረው የመንግሥቱ ኃይለማርያም (የኦጋዴን አንበሣ) መናገሻ ነች፤ 
 
2ኛ/ ሐረር ከምኒልክ እስከ ራስ መኮንንና ተፈሪ መኮንን ድረስ – እና እስከ ደርግ ዘመነመንግሥት ማብቂያም የቀጠለውን ‹‹የኢትዮጵያዊነት የጋራ ሀገር ምስረታ›› ፕሮጀክት ቀዳሚ ማዕከልም፣ ሥኬታማ አብነትም ሆና ተገኘች – እና ያንን ለወያኔ ጠባብ አገዛዝ የማይመች የኢትዮጵያዊነት መሠረት ወያኔ ፈነቃቅላ ማጥፋት ነበረባት፤ 
 
3ኛ/ 1983 ግንቦት 20 ላይ አዲስአበባ በወያኔ ከተያዘችም በኋላ ሐረር ላይ ተሰልፈው ወያኔን አላሳልፍም በማለት ሐረርንና ከሐረር በመለስ ያለውን የጂጂጋና ኦጋዴን ግዛት ሁሉ ለወያኔ አላስረክብም ብሎ የተዋጋውን የሐረርን ህዝብ ለመበቀል ነው፤ 
 
4ኛ/ ምጽዋን ለወያኔ-ሻዕቢያ አሳልፎ እንደሸጠ በሰፊው ለሚነገርለት ለአደሬው የደርግ ዘመን ጄነራል (ጄኔራል አሊ) ውለታ መክፈያነት የተደረገ የጦር ካሳ ክፍያ ነው፤ 
 
5ኛ/ እንግሊዞች ከባልፎር ዲክለሬሽን በፊት በፓለስታይን ያደርጉት እንደነበረው – አረቦች በሚበዙበት ቦታ እስራኤሎችን፣ እስራኤሎች በሚበዙበት ቦታ አረቦችን አስተዳዳሪ አድርገው እየሾሙ ነዋሪውን እያባሉ አገዛዛቸውን እንደቀጠሉት – በሐረርም ወያኔዎች አናሳውን አደሬን በብዙሃኑ ላይ ሾማ እያባላች መግዛት እንደምትችል በመቆመር ነው፤ 
 
6ኛ/ በወያኔ ነገዳዊ ህገመንግሥት አወቃቀር የእስልምና መልክ ያላቸው ክልሎች መብዛት (መመጣጠን) የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ግባቸው አንዱ አካል ነበረ – ስለዚህ ሐረሪ በስም የሙስሊም ክልል ተብላ ከትልልቆቹ ክልሎች ጋር መደመሯ ለፖለቲካዊ ግብ ተፈለገ፤
 
7ኛ/ በወያኔ ህገመንግሥታዊ አወቃቀር ምንም የምትተማመንበት ወያኔን የሚያሰጋ የራሷ ኃይል የሌላት ለአናሳዎቹ አደሬዎች የተሰጠችው ክልል በወያኔ ዘመን ሁሉ ‹‹እንደ ክልል›› ወያኔ ያላትን ሁሉ እንደገደል ማሚቶ እያስተጋባች ከመኖር ሌላ አማራጭ የሌላት የወያኔ ‹‹ባሉሽካ›› (ሳተላይት ስቴት) እንድትሆን ስለተፈለገ ነው (እውነትም ሰርቷል፣ ወያኔዎች ጥቂት ሲያንገራግጩ 50/50 ለአደሬና ለኦሮሞ የተካፈለው የክልሉ ምክርቤት ለኦሮሞዎች ተላልፎ እንደሚሰጥባቸውና ክልልነታቸው እንደሚያበቃ እየተነገራቸው መለስ ጉንፋን ሲይዘው እያስነጠሱ ኖረዋል)፤ 
 
ሌሎችም ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ላሁኑ ይህ ገለጻ ስለ ሐረሪ ክልል አፈጣጠር ለማስረዳት በቂ ይመስለኛል፡፡ አሁን ደግሞ የአሁኗን ሐረርና የሐረሪ ክልል የምትባለዋን እንያት፡፡ 
 
አሁን ላይ ሐረሪን እንያት፡፡ የኦሮሙማው መሪ አብይ አህመድ መንግሥት ሆኖ መጥቶባታል፡፡ ኦሮሙማው በሞኖፖል ሐረርጌን በሙሉ፣ እና አብዛኛውን ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮታል፡፡ አንዱ ታዛቢ በቅርቡ እንዳለው የኦሮሙማው ኃይል ‹‹ታንኩም ባንኩም በእጁ ነው››፡፡ በድሬዳዋ ሆነው ወለም ዘለም የሚሉትን ሶማሊዎችንም ‹‹የወያኔው አጋር አብዲ ኢሌ ሶማሊ ክልልን ሊገነጥል ነው›› በሚል ሰበብ ገና ከጅምሩ በመከላከያ ሀይል ተጠቅመው ድራሹን አጥፍተውታል፡፡ 
 
በአሁኑ ሰዓት ሐረሪ የምትባለው ክልል ዙሪያዋን በኦሮሙማው (በተለይ የኦነግ መሠረት በሆነው) ሀይል ተከብባ መተንፈሻ መፈናፈኛ አጥታለች፡፡ የሐረሪዋ የራሷ የከተማዋ መማክርት ራሱ 50/50 ለአደሬና ለኦሮሞ ተከፍሎ ሚዛኑ አየር ላይ እንደተንጠለጠለ ነው፡፡ በሐረር ከተማ ከሚገኘው የምሥራቅ ዕዝ እስከ ሶማሊ ድረስ ያለው የኢትዮጵያ ጦር በኦሮሙማው እጅ ነው ያለው – ባሰኘው ላይ ይተኩሰዋል፣ ባሰኘው ላይ ያዘምተዋል፣ ያሰኘውን ይዳምጥበታል፡፡ በዚህ ላይ የሀረር ከተማ (ማለትም የሀረሪ ክልል) ግማሹ መስተዳደር የሚተዳደረው በኦሮሚያ ዞን ሥር ነው፡፡ 
 
በአሁኑ ሰዓት ከወያኔም ዘመን በከፋ መልኩ የሀረሪ ክልል ምን ያህል መተንፈሻ ያጣች በኦሮሙማው እጅ ውስጥ ያለች ጉልበት አልባ ወፍ (ከወፍም የቀለለች የኦሮሙማው መጫወቻ እፉዬ-ገላ) መሆኗን የምናውቀው አብይ አህመድ ሐረሪን ሊጎበኝ ሲሄድ ‹‹አብይ አህመድ – ዳግማዊ አል ነጃሺ›› ብለው ለታላቅ አቀባበል መሰለፋቸውንና በመልሱ የጀጎሉ ግንብ ምስል በአድራጊ ፈጣሪው ኦሮሙማው መንግሥት በተቀየረው የኢትዮጵያ የብር ኖት ላይ ወጥቶላቸው ስናይ ነው፡፡ ያ ለተመልካች ቀላል ቢመስልም መልዕክቱ ከዚያ በላይ ነው፡- ‹‹ሐረሪ ሆይ፤ በኦሮሙማው አዲስ አገዛዝ ህልውናሽ እንደሚቀጥል ማረጋገጫችንን እነሆ ተቀበዪን፣ ፀባይሽን ብቻ አሳምሪ!›› የሚል ቃልኪዳን ጭምር ነው፡፡ 
 
የሐረር ከተማን የልዑል ራስ መኮንን ሐውልት እንዲፈርስ አደሬዎች የቆየ ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም ሳያደርጉት ኖረዋል፡፡ በጀጉላ ሆስፒታል ውስጥም ያለውን ሐውልት እንዲሁ፡፡ አሁን ጊዜው የኦሮሙማው ነው፡፡ በእነአብይ አህመድ ሙሉ የመንግሥት ድጋፍና ሽፋን የሚቸራቸው የኦሮሙማው ቄሮአዊ ኃይሎች ታሪካዊዎቹን ‹‹የነፍጠኛ አማራ›› ሐውልቶች የማፈራረስ የተግባር ውጥን ይዘው መጡ፡፡ እና ሊያፈርሱ ተሰማሩ፡፡ 
 
እና የአደሬዋ ሐረሪ (የ50%ቷ የከተማዋ አስተዳደር) በምን ትንፋሿ፣ በምን አቅሟ፣ በምን ሥልጣኗ፣ በማንስ ፈቃድ፣ እንዴትስ አድርጋ የወያኔን አልጋ ወራሽ ባለዙፋኑን የኦሮሙማ መንግሥት ብትንቅና ብትደፍር ነው – በአፍራሾቹ ላይ ጥይት የምትተኩሰው?? – በፍጹም! አታደርገውም! አትሞክረውም! ከቶውኑም አታልመውም! ጭንቅላቷ ላይ የኦሮሙማው ቃታ የተደገነባት ተላላኪ ክልል ያን አታደርግም፡፡ ግን አንድ ነገር ታደርጋለች፡፡ 
 
የሀረሪ አደሬዎች ሊያደርጉ የሚችሉት፣ ወይም ሐረሪ ልታደርግ የምትችለው ነገር፡- የከተማውን የጸጥታ አስከባሪ ኃይሏን በኦሮሙማው በተወጠነለት የሐውልት ማፍረሱ ትርዒት ላይ አሰማርታ ከህዝቡ የሚነሳ መቋቋምና ተቃውሞ ቢኖር – ያንን ማንኛውንም ኃይል ተጠቅማ ለመደምሰስ በቦታው ትገኛለች፡፡ የከፋ ነገር ቢመጣ ከ1 ኪሎሜትር ባነሰ ርቀት በካምፕ ለሰፈረው የኦሮሙማው ንብረት ለሆነው የመከላከያ ኃይል የድረሱልኝ ጥሪ ታደርጋለች፡፡  
 
እና በተግባር እንደሆነው – የሐውልት ፈረሳው በሠላም ሲጠናቀቅላት – በታላቅ እፎይታ – የአደሬ መሪዎች ከበው የሚቀመጡበት የደስታ ዱአ ጠርታ – የአወዳይ ጫት ይዛ ትቀመጣለች፡፡ አላህዋን እያመሰገነች፡፡ ወደድንም ጠላንም በሀረሩ የልዑል ራስ መኮንንን ሐውልቶች ማፍረስ ሂደት የነበረው ባክግራውንድ፣ እና በትክክል የሆነው ይኸው ነው፡፡ 
 
ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ይህን እውነታ የተገነዘበ አዋቂ ሰው በሐረሪ መሪዎች (እፉዬ ገላዎቹ አደሬዎች) ላይ ብቻ ጣቱን አይቀስርም! ከእነሱም በከፋ መልኩ – እና ከእነሱ በስተጀርባ ሆነው – የታሪክ ድለዛና ክለሳውን እያስፈጸመ ያለው – የጊዜው የወያኔ ተረካቢና የነገዳዊቷ ኢትዮጵያ ባለአደራ – በአብይ አህመድ የሚመራው – (እና ‹‹ባንኩም ታንኩም በእጁ የሆነው››) የኦሮሙማው መንግሥት ነው! 
 
ይህ መልዕክቴ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣ በተለይም ለምሁራን፣ ታሪክ አጥኚዎች፣ እና የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሂደት በጽኑ ለምትከታተሉ ሁሉ ይደርስልኝ ዘንድ ከልብ እመኛለሁ፡፡ አቻምየለህን (ጊዜ ሰጥቶ ሙሉ ትንታኔውን ገና ያላስቀመጠ ቢሆንም) ስለ ውግዘቱ ስል ግን አመስግኜ እሰናበታለሁ፡፡ 
 
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
Filed in: Amharic