>

የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን አሳዛኙ ሁነት እና ዝምታችን! ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን አሳዛኙ ሁነት እና ዝምታችን!

ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


እንደ መንደርደሪያ

በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ላይ የሚወርደውን መአት እንዳለሰማን ሆነን በታላቅ ጸጥታ ውስጥ ከተዶልን የሚደርሰውን በደል እና አሳዛኙን መራር ሁነት እንደተቀበለነው ይቆጠራል፡፡

የፍትህ ጥሰት ሲኖር ዝምታ ( ዝም ብሎ መወዘፍ) አርበኝነት አይደለም፡፡ በተቃራኒው የፍትህ መነፈግ ሲከሰት ለምን ብሎ መሞገት ግን የአርበኝነት ስሜት ነው፡፡ ሁላችንም ብንሆን፣ ከደቂቅ እስከ ሊቅ፣ ከሃብታሙ እስከ መናጢ ደሃው፣ ከወጣቱ እስከ አዛውንት የእድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሁሉ የፍትህ መዛባት ሲከሰት መጥፎ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ሆኖም ግን ምንም አይነት እርምጃ አንወስድም፡፡ ምንም አንናገርም፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ሌሎች ግለሰቦች ፍትህ እንዲያስከብሩልን እንጠብቃለን፡፡ በጥቂት ሰዎች መስእዋትነት ፍትህን እንመኛታለን፡፡ ሆኖም ግን ዝንተ አለም እናነባታለን እንጂ አናገኛትም፡፡ እኛ ሁል ግዜ በጸጥታ ( በዝምታ) እንቀመጣለን፡፡ ምክንያቱም ዝምታ ቀላል ስራ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ ዝምታ እንደ መስማማት ይቆጠራል፡፡ ምንም ካልተናገርን፣ ምንም ካልሰራን፣ በደልን አሜን ብለን እንደተቀበልን ይቆጠራል፡፡

“It’s not unpatriotic to denounce an injustice committed on our behalf, perhaps it’s the most patriotic thing we can do.” E.A. Bucchianeri, Brushstrokes of a Gadfly “All too often, when we see injustices, both great and small, we think, That’s terrible, but we do nothing. We say nothing. We let other people fight their own battles. We remain silent because silence is easier. Qui tacet consentire videtur is Latin for ‘Silence gives consent.’ When we say nothing, when we do nothing, we are consenting to these trespasses against us.”                                                                

(Boxane Gay,Bad feminist )

  1. የመለየት ነጥብ (Point of departure )

በዛሬው ዘመን ኢትዮጵያውያን ባልተነገረ ስቃይና መከራ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የጎሳ አምበሎች፣  ፋሺስት ጎሰኞች፣ ያልታወቁ ነፍሰ ገዳዮች፣ ከእብድ ውሻ የከፉ ጨካኞች የሚፈጽሙት እከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት እጅጉን አሳሳቢ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንደተሰማው በአንዳንድ የኢትዮጵያ ግዛቶች ( ጉራፈርዳ፣ ቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል መተክል ዞን፣ ምእራብ ወለጋ ዞን ወዘተ ወዘተ) የሰው ህይወት መቅጠፍ፣ ኢሰብአዊ ድብደባ፣ አለህጋዊ አግባብ እስር እየተለመደ መጥቷል ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡ ይህን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ጊዜ በጉራፈርዳ ወረዳ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የሚያሳዩ ዜናዎችን ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዜናው መሰማቱን ብዙዎቻችን የሰማን ይመስለኛል፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠጠር ጥቅምት 11 ቀን 2020  የአማራ መገናኛ ብዙሃን የሰብአዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸውን ኢትዮጵያዊ ዜጎች የሰጡትን ቃል መሰረት አድርጎ ባስተላለፈው ዜና መሰረት ከ11 በላይ ዜጎች ባልታወቁ ነብሰ ገዳዮች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸውን የሚያሳይ ዜና መዘገቡን አስታውሳለሁ፡፡

በሌላ በኩል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሐምሌ 5 ቀን 2020 ላይ የእንግሊዙ የዜና አውታር ቢቢሲ የመንግስት ምንጮችን ዋቢ በማድረግ በዘገበው መሰረት በሻሸመኔ፣ ምእራብ አርሲ፣ ዝዋይ ሀይቅ አካበቢ በመቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች መገደላቸውን፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ  መኖሪያ ቤቶች፣ ከ200 በላይ የንግድ ተቋማት ( ፋብሪካዎችና ትምህርት ቤቶችን ይጨምራል) ተቃጥለው ወደ አመድነት መቀየራቸው የቅርብ ግዜ አሳዛኝ ትዝታ ነው፡፡ ከወደሙት የንግድ ተቋማት መሃከል በአለም ላይ ስመጥር እና ዝነኛ የሆነው ሀይሌ ገብረስላሴ፣ የአለምና ኦሎምፒክ የረጅም ርቀት ሻምፒዮኑ ሀይሌ  ንብረት የሆነው ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ይገኝበታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ቁጥራቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በደረሰባቸው ጥቃት ተፈናቅለው በቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ እነኚህ ሁሉ የተፈጸሙት በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ መሆኑን ስናስብ የኢትዮጵያን እድል አሳዘኝ ያደርገዋል ( እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሰኔ 29 2020 የአርቲስት ሀጫሉን ግድያ ተከትሎ ባሉት ሁለት ቀናት ውስጥ አሳዘኙ ሁነት መከሰቱን ልብ ይሏል፡፡)

ከላይ በተጠቀሰው ተመሳሳይ ሳምንት የአልጀዚራ የዜና አውታር፣ የጀርመን ድምጽ ራዲዮና የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ የመንግስትን የዜና ምንጮች ዋቢ በማድረግ በዘገቡት መሰረት የሟቾችን ቁጥር ወደ 298 ከፍ አድርገውት ነበር፡፡ እንደ ጎ0ርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ፣ በእለተ እሁድ መስከረም 13 2020 በቤኒሻንጉል ክልል መተክል ዞን ውስጥ ነዋሪ የነበሩ ወደ 80 የሚጠጉ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ብረት ባነገቱ ተጣቂዎች መገደላቸውን በታላቅ ሀዘን እናስታውሰዋለን፡፡  ይህ ኢሰብአዊ ድርጊት የተፈጸመባቸው የሟቾች ስም እና ማንነት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር የተነገረ መራር ሀቅ ነው፡፡ ይህንኑ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ቃለ ምልልስ ያደረጉት የቤኒሻንጉል ክልል አፈቀላጤ ከማረጋገጣቸው ባሻግር የሰውን ህይወት ያጠፉት ቡድኖች ጸረ ሰላም ሀይሎች ናቸው ሲሉ ነበር ለተጠቀሰው መገናኛ ብዙሃን የገለጡት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር መስከረም 25 ቀን 2020 አየር ላይ የዋለው የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአካበቢውን ባለስልጣናት ጠይቆ ባቀረበው ዘገባ መሰረት በተመሳሳይ ስፍራ ከ14 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፣ ከ 4 በላይ ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውን ተሰምቶ ነበር፡፡ ያሳዝናል፡፡

ሆኖም ግን ይሁንና የመንፈሳዊና የሀይማኖት አባቶች ጩሀት የት ነው ያለው ? ድምጻቸው የት ይገኛል ? ( በነገራችን በቅርብ ግዜ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ምድር ስለተፈጸመው አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ያሰማውን ኡኡታና ጩሀት መዘንጋት የለብንም፡፡) የአብዛኞቹ የሲቪልና የሙያ ማህበራት ድምጽ የት ይገኛል ? ( በጣም ጥቂቶች የመብት አስከባሪዎች ድምጽ ጩሀታቸውን ማሰማታቸውን መዘንጋት አይገባም፡፡) ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊ የሀይማኖት አባቶች እና የሰብአዊ መብት አስከባዎች በኢትዮጵያ ምድር የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲጣሱ ድምጻቸውንና ጩሀታቸውን በእውነትና ማስረጃ ላይ ቆመው ማሰማት መንፈሳዊ ግዴታቸው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የሰው ልጅ ህይወት ክብር ያለው ነው፡፡ የሰው ህይወት በዘፈቀደ መጥፋት አይገባውም፡፡ የሰው ልጅ የመኖር መብት መከበር ያለበት ተፈጥሮአዊ መብት ነው፡፡ ማንም ሊሰጠን፣ ሊነፍገን አይገባውም፡፡

በአንድ ሀገር ላይ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ወይም አንዲት ሀገር በብሔራዊ ሀዘን ላይ ስትዶል ((In a disaster or national tragedy ) የሃይማኖት አባቶችና የሲቪል ማህበረሰቡ መሪዎች በፊትለፊት ሰልፍ ላይ መገኘት አለባቸው፡፡ እነርሱም በህብረተሰቡ መታመን አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የተቸገረውን የሚረዱና መንፈሱን የሚያበረቱ ፣ እንዲሁም የሚያክሙም ናቸው፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆን ይገባቸዋል፡፡ (They are also expected to be the voice of the voiceless)

ምንም እንኳን የሃይማኖት አባቶች ስራ እንደየ የእምነት ተቋሞቻቸው ቀኖና  ( ወይም ፍልስፍና) መሰረት መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት ቢሆንም፣ እንዲሁም በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋ የተጎዱትን ኢትዮጵያውያን ዜጎች ማጽናናት ቢሆንም ሰዎች የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጸምባቸው ድምጻቸውን ከፍአድርገው ማሰማት መንፈሳዊ ግዴታቸው ይመስለኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሲቪል ማህበረሰብ አባላት በተለይም በሰብአዊ መብቶች ማስከበር ዙሪያ የቆሙት መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ትምህርት ማህበረሰቡን ከማስተማር ባሻግር የሰብአዊ መብቶች ሲጣሱ ዝምታቸውን በመስበር ኡኡታቸውን ማሰማት ሙያዊ ግዴታቸው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ( በነገራችን ላይ እንደ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤን የመሰሉ የሰብአዊ መብት አስከባሪ ድርጅቶች ላለፉት ሃያ ዘጠኝ አመታት በኢትዮጵያ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ እንዲሁም የህግ የበላይነት እንዲከበሩ ላደረጉት አስተዋጽኦ ታሪክ ስፍራውን የሚነሳቸው አይመስለኝም፡፡ በቅርቡ ደግሞ ማለትም ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ መንግስታዊው የሰብአዊ መብት አስከባሪ ድርጅት፣ የሰሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚያደርገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ) ስለሆነም በኢትዮጵያ ምድር የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፉትን፣ ኢሰብአዊ ድርጊት የሚፈጽሙትን  እኩያንን ሁሉ ማውገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በቂ ማስረጃዎችን ከሰባሰቡም በኋላ በህግ የሚጠየቁበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ስላለው አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ሁኔታን በተመለከተ እነርሱ ( የሃይማኖት አባቶችም ሆኑ የሲቪል ማህበረሰቡ መሪዎች ወይም አባላቶቻቸው ) መወያየት አለባቸው፡፡ መወያየት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ሰላምና አንድነቷ የተጠበቀ ሀገር እንድትሆን በፊት መስመር ሆነው ታሪካዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ሳስታውስ በአክብሮት ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለድምጽ አልባዎች ድምጽ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡( They are also expected to be the voice of the voiceless ) ውሸትን አሽቀንጥረው በመጣል ከእውነት ጋር ወዳጅ መሆን አለባቸው የሚለውን መልእክቴን ሳቀርብ በታላቅ አክብሮትና ትህትና ነው፡፡

ምንም እንኳን ይሁንና ዋነኛው የሃይማኖት አባቶች ሥራ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት ቢሆንም፣ ሰዎች ከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ሲዶሉ፣ መከራ ሲገጥማቸው ማጽናናትና መንፈሳዊ ጥንካሬ እንዲኖራቸው መምከር ማስተማር ቢሆንም ሰላማዊ ኢትዮጵያዊ አፈር ገፊ ዜጎች በአረመኔዎች ጥይት ተገድለው ሲወድቁ የሃይማኖት አባቶቸ  ከፊትለፊት ሆነው ግድያውን ማውገዝ መንፈሳዊ ግዴታቸው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ብቻ ኢትዮጵያዊ ዜጎች በሀይወት የመኖር ተፈጥሯዊ መብታቸው እንዳይገሰሰ የሀገሬው መንግስት ጥበቃ ማድረግ እንዳለበት በብዙ መልኩ ውትወታ ማድረግ አለባቸው፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ አባላትም የየድርጅቶቻቸው አላማና ተግባር የተለያየ ቢሆንም ተፈጥሮአዊ መብት የሆነው በህይወት የመኖር መብት እንዲከበር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት የዘውትር ስራቸው መሆን አለበት፡፡ የሰብአዊ መብት የሚጥሱ መንግስት አካላቶችም ሆኑ ሌሎች ያልታወቁ ቡድኖች አባላት በህግ አግባብ እንዲቀጡ ለማድረግ አበርክቷቸው የትዬየሌሌ ነው፡፡ በዛሬዬቱ ኢትዮጵያ ሰማየ ሰማያት ላይ በሚናኘው የፖለቲካ ምህዳር ላይ የሚናኙ የፖለቲካ ሃይሎች  ሰላማዊ ፖለቲካዊ ጉዞ መምረጣቸው ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ መንግስትም ቢሆን ለሁሉም የፖለቲካ ተፎካካሪዎች በሚመጥን መልኩ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት አለበት፡፡  ፍትህን እና እውነትን ያስቀደመ ብሔራዊ እርቅ ፣እንዲሁም የሰለጠነ ፖለቲካ   በኢትዮጵያ ምድር እውን እንዲሆን ይህን ተከትሎ ነጻ ገለልተኛ፣ ፍትሃዊና ርእታዊ የምርጫ ውድድር ይዘጋጅ ዘንድ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማህበረሰቡ መሪዎች እና የሙያ ማህበራት መሪዎች በታሪክ ፊት ቆመዋል፡፡ መንፈሳዊ ወኔ ታጥቀው ይህን ለማድረግ ህሊናቸው ከወሰነ እና ውጥናቸው ከተሳካ  በታሪክ ዝንተ አለም ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ ለማናቸውም እግዜአብሔር ይርዳን ይርዳቸው፡፡

በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በትግራይ ክልል በርካታ ሰዎች መገደላቸው፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ኢትዮጵያዊ ዜጎች እትብታቸው ከተቀበረበት መንድር መፈናቀላቸው፣ ለአመታት አፈር ገፍተው ደክመውና ጥረው ያፈሩት ንብረት መውደሙ ወይም መዘረፉ ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል፡፡ በተለይም ከላይ የጠቀስኳቸው ተቋማት መሪዎች በእጅጉ ሃላፊነታቸው የሰፋ ነው ባላቸው አቅም እና እውቀት ተጠቅመው ዜጎች ዳግም አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይደርስባቸው ኢትዮጵያ መንግስት ውትወታቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ  ብጹነታቸው አቡነ ማቲያስ፣ ሼክ ሀጂ ኡመር እድሪስ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዜዴንት ( the grand mufti of Ethiopia and the president of the country’s Islamic Affairs Supreme Council )  በኢትዮጵያ በህይወት የመኖር መብት እንዲከበር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በየጊዜው ስለማሰማታቸው ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ከመከሰቱ በፊትና የሰብአዊ መብት ጥሰት ከተፈጸመ በኋላም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የሰብአዊ መብቶች እንዳይጣሱ ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ ደግሞ በማስረጃ የተደገፉ መግለጫዎችን በማውጣት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ መንግስትንና የኢትዮጵያን ህዝብ በማሳሰብ የሚታወቅ የሰብአዊ መብት አስከባ ድርጅት መሆኑን ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በቅርብ ግዜ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚያደርገው ውትወታ አድናቆትን የሚያስቸረው ነው፡፡

  1. የሃይማኖት እምነት በኢትዮጵያ፣ ውጥረት እና ግጭትን ለመከላከል መንግስት የሚያደርገው መከላከል ( ቁጥጥር)

በዚች ነጥብ ላይ እኔ የራሴን መላምት ወይም ሃሳብ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ አንባቢው ደግሞ የበለጠ የመወያያ ሃሳቦችን ያነሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እኔ የማነሳው ሃሳብ ሁነኛ መፍትሔም ነው ለማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የሃሳብ ሻማ ለመለኮስ እንደሆነ አንባቢውን አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ ባሻግር የጽሁፉ  ዋና አላማ የሃይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማህበራት መሪዎች እንዴት የአባላቶቻቸውን ፍላጎት እና ምኞት ላይ ተመስርተው ማንቀሳቀስ ይችላሉ የሚለው ነጥብ ላይ ሃሳብ ለመጫር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከመቼውም ግዜ በላይ የሃይማኖት አባቶችና የሲቪል ማህበረሰቡን መሪዎች ምክር የምትሰማበት ግዜ መስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኝ ሀገር ሆና ትታየኛለች፡፡ እኔ ማንንም ለመውቀስ አይደለም ይህን ጽሁፍ ያዘጋጀሁት ( የሀይማኖት አባቶችንም ሆነ የሲቪል ማህበረሰቡን መሪዎች ማለቴ ነው፡፡) በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ አጽንኦት ሰጥቼ ማሳሰብ የምፈልገው ጉዳይ ግን በዚህ እጅግ አሳሳቢ የታሪክ  ነጥብ ላይ የሚገኙትን እነርሱ ( የሀይማኖት አባቶችና የሲቪል ማህበረሰቡ መሪዎች፣የሀገር ሽግሌዎች ወዘተ ወዘተ )  የኢትዮጵያ መጻኢ እድል መልካም እንዲሆን  የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማሳሰብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የገጠማት ምርጫ ከዳቦና ኬክ አንዱን መምረጥ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በህልውና ፈተና ላይ መውደቋን ለአንድም ሰከንድ መዘናጋት የለብንም፡፡

በእኔ አስተያየት አብዛኛው የእስልምና እና ክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች በኢትዮጵያ የዘር ጭፍጨፋ አልተከሰተም ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎችን ደግሞ ከፋፍለህ ግዛ በሚል የፖለቲካ አስተምህሮ አይመሩም ብለው የሚያምኑ ይመስለኛል፡፡

I have little doubt that the overwhelming majority of the Muslims and Christians are against the genocide and the political elites’ divide and rule strategy.

አብዛኞቹ የኦርቶዶክስ፣ እና ካቶሊክ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች፣ የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ የኢትዮጵያ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ( ፔንጤኮስታል እንደ ድርጅትና እንድ ግል አማኝ) አባላት ሁሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለፍትህ ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ ዛሬም ለፍትህ እና የህግ የበላይነት የሚታገሉ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ግፍን አሜን ብሎ ላለመቀበል፣ ከሰማእትነት አኳያ ልዩነት ነበር፡፡ ዛሬም አለ፡፡ ዝርዝር ውስጥ አልገባም፡፡ለአብነት ያህል አቡን ጴጥሮስ ሰመእት ሆነው ያለፉ የሃይማኖት አባት ነበሩ በማለት በድፍረት መጻፍ ይቻላል፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2014 ሆስቲን የተባሉ ምሁር ባቀረቡት ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ የሃይማኖት ልዩነት እየሰፋ ነው ፡፡ ይህ የሃይማኖት ልዩነት ደግሞ ለግጭት ቦይ የሚከፍት፣ በሰዎች ማህበራዊ ህይወት ላይ ተጽእኖ የሚያሳርፍ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ስፍር ቁጥር የሃይማኖት ተቋማት መስፋፋታቸውን የሚታየው በትላልቅ ከተሞች ብቻ ሳይሆን በትናንሽ ከተሞች ጭምር ነው፡፡ በማናቸውም ከተሞችና መንደሮች ጭምር የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ምልክትን ማየት ይቻላል፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል

“Full Gospel Believers 5 Church” (ሙሉ፡ወንጌል፡አማኞች፡ ቤተ፡ክርስቲያን, Mulu Wängel Amañočč BetäKrəstiyan), “Paradise Church” (ገነት፡ቤተ፡ ክርስቲያን, Gännät Betä-Krəstiyan), “Light of Life Church” (ሕይወት፡ብርሃን፡ቤተ፡ ክርስቲያን, Ḥəywät Bərhan Betä-Krəstiyan), “Deliverance Church” (አርነት፡ቤተ፡ ክርስቲያን, Arənnät Betä-Krəstiyan), እና ሌሎች እጅግ በርካታ የቤተክርስቲያ ስሞችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1960 በወጣው የሲቪል ኮድ ህግ ቁጥር 321 መሰረት የሃይማኖት ተቋማት ህጋዊ መሰረት ማግኘት እንደሚችሉ ማወቁ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለማናቸውም ሚስተር ሁስተን በእንግሊዘኛ የጻፉት የበለጠ ገላጭ ስለሆነ እንደወረደ አቀርበዋለሁ፡፡

. According to Haustein (2014) there is a new religious factor in Ethiopia, which attracts considerable public attention, invites dispute, influences social behavior, and has produced new Amharic phrases. It is visible in the multitude of church signs in any town or even small villages, displaying names like “Full Gospel Believers 5 Church” (ሙሉ፡ወንጌል፡አማኞች፡ ቤተ፡ክርስቲያን, Mulu Wängel Amañočč BetäKrəstiyan), “Paradise Church” (ገነት፡ቤተ፡ ክርስቲያን, Gännät Betä-Krəstiyan), “Light of Life Church” (ሕይወት፡ብርሃን፡ቤተ፡ ክርስቲያን, Ḥəywät Bərhan Betä-Krəstiyan), “Deliverance Church” (አርነት፡ቤተ፡ ክርስቲያን, Arənnät Betä-Krəstiyan,” Based on these constitutional provisions, the legal framework for the registration of associations, already set up by the 1960 Civil Code and the “Legal Notice No. 321” of 1966, was now put into practice, allowing and mandating the official registration of all religious bodies.

ግራም ነፈሰ ቀኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ ሃይማኖት የእምነት በዋነኝነት እንዲሁም ሁሉም በኢትዮጵያ ምድር የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበረሰብና የሙያ ማህበራት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን፣ የሀገሪቱ አንደነቷና ሉአላዊነቷ ተከብሮ እንዲኖር፣ አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቅ የምርጫ ውድድር የተመረጠ እና የሰለጠነ መንግስት በኢትዮጵያ ምድር እንዲበቅል ታሪክ ታላቅ አደራ ሰጥቷቸዋል፡፡ መንፈሳዊ ወኔ በመታጠቅ ኢትዮጵያን ይታደጓት ይሆን ? ጊዜ የሚያሳየን ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል ፖለቲካን ለፖለቲከኞች በመተው የሁሉም ሃይማኖት አባቶች ሁሉ መንፈሳዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ሳስታውስ በታላቅ ትህትና ነው፡፡ እዚች ላይ ሁሉም የሃይማኖት አባቶች ከፖለቲካው ወላፈን ነጻ ናቸው ወይም ተጽእኖ ውስጥ ናቸው  ብሎ ለመጻፍ ማስረጃ ስለሚያስፈልግ በዚሁ አልፈዋለሁ፡፡ ወይም ለግዜው የምለው የለኝም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና  በየእምነት ተቋማቱ የየእለት ተግባራት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ለመሆን ቢያንስ ለህሊናቸው ቃል መግባት ያላባቸው ይመስለኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥንታዊ ገዳማትና ታሪካዊ የእምነት ስፍራዎች ለቱሪዝም ሚያስገኙት ገቢ መዘንጋት የለበትም፡፡ በተለይም እንደ አክሱምና ላሊበላ አብያት ክርስቲያናት፣ የባሌ ሶፍ ኡመር ዋሻ፣ የሀረር ግንብ ወዘተ ወዘተ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እቅም መጠንከር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ሰለሆነም አቅማቸውን በመጠቀም በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ አብርክቶቻቸው የትዬየሌሌ ነው፡፡ ያለችን አንድ ሀገር ናት፣ የተወለድነው እትብታችን የተቀበረው፣ በዚችው ኢትዮጵያ በምትባል ጥንታዊት ሀገር ምድር ውስጥ ነው፡፡ ያደግነው፣ የተማርነው፣ በመጨረሻም ለወግ ማእረግ የበቃነው በኢትዮጵያ ሀገራችን ላይ ነው፡፡ ስለሆነም የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ቢኖረንም፣ በሃይማኖት ፍልስፍና ብንለያይም በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ጉዳይ አንድ መሆን አለብን፡፡ በስንቱ ጉዳይ ተላያይተን እንችለዋለን፡፡ ሰንደቅ አላማ የአንድ ሀገር አርማ በመሆኑ ኢትጵያውያን ሁሉ እኩል ክብር ልንሰጠው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ሰንደቅ አለማ ጉዳይ የኢትዮጵያውያን ጉዳይ እንዲሆን የሁሉም የሃይማኖት ተቋማት አባቶች፣ መሪዎች ምእመኖቻቸውን ( ወይም ተከታዮቻቸውን ) ለማስተማር መንፈሳዊ ግዴታ ለባቸው ይመስለኛል፡፡ ድሮ ጥንት አጼ ሀይለስላሴ እኮ ‹‹ ሀይማኖት የግል ሀገር የጋራ ናት ›› ብለው አስተምረውን ነበር፡፡ አጼ ሀይለስላሴ ይህን የሀይማኖት ነጻነት ሲያጎናጽፉ የሀይማኖት ተቋማት እንደ አሽን እንዲፈሉ ብቻ የነበረ አይመስለኝም፡፡ ሁላችንም ለኢትዮጵያ ታማኝነታችንን ሳንለቅ የፈለግነውን እምነት እንድንከተል ይመስለኛል፡፡ እየሆነ ያለው ግን ተቃራኒው ሃሰብ ነው፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በሀይማኖታዊ ክብረ በአላት ላይ በቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ወይም አውድ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በመስቀል፣ እንዲሁም በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ ከጀግኖች አባቶቻችንና አያቶቻችን ጋር  የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እና ታቦት ተሸክማ አብራ በመዝመት ለከፈለችው መስእዋትነት ታሪክ በወርቅ ቀለሙ ጽፎ ያስቀመጠው እውነት ብቻ ሳይሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደ ጅረት ፈሶ አሁን ባለንበት ጊዜ ድረስ ደርሷል፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሙስሊም ወንድሞቻችን ለሰንደቅ አላማችን መከበር ከፈሉት መስእዋትነት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የታላቁ አፋር ህዝብ መንፈሳዊ መሪ የነበሩት ሱልጣን አሊሚራ ‹‹ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እንኳን እኛ ግመሎቻችን ያውቁታል›› የሚለው ዘለአለማዊ ንግግር በኢትዮጵያውያን አይምሮ ውስጥ ምንግዜም ቢሆን የሚደውል ነው፡፡የደጃች ኡመር ሰመርተርም ተጋድሎ በወርቅ ቀለም ተጽፎ የተቀመጠ ነው፡፡ በጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሱማሊያና ኢትዮጵያ ስልታዊ ጠቀሜታ ባለው ድንበር ላይ የሚገኘው የአፋር ህዝብ ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከማክበር አኳያ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ተምሳሌትነቱ አሌ አይባልም በተለይም በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ላይ ጥያቄ አለን ለሚሉ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችን ጥያቄአቸው ከባድ ህጸጽ እንዳለበት የሚያመላክት ነው፡፡ ለመማር ህሊናቸው ዝግጁ ከሆነ ማለቴ ነው፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ኢትዮጵያውያን ከግጭት ወጥተን በሰላም እና አንድነት እንድንኖር ከሚያስችሉን ቁምነገሮች መሃከል አንደኛው የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ነው፡፡ የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ከመያዙ በፊት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ‹‹ አሻቦ መቋጠር ›› እንዳዋለው አቶ ገብረመድህን አርአያ የተባሉ የሕውሃት መስራችና አባል የነበሩ ሰው ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ከሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ማዳመጤን  አስታውሳለሁ፡፡ የማእከላዊ መንግስቱን ስልጣን ከያዙም በኋላ ቢሆን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ላይ ሌላ ምልክት በማድረግ የቀደመውን ሰንደቅ አላማ ወደ ጎን ገሸሽ አድርገውታል፡፡ ከዚህ ባሻግር ምንም ምልክት የሌለበትን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ የሚይዙ ኢትዮጵያውያን ላይ ተጽእኖ ያሳድሩባው ነበር ፡፡ ወደ ወህኒ አምባም ሲወረውሩ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ክብረ በአላት ላይም የቀደመው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ እንዳይሰቀል ተጽእኖአቸው የጎላ ነበር፡፡ የወያኔ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በነጻነት ይዞ መንቀሳቀሰ ቢፈቀድም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የቀደመውን የኢትዮጵያ ባንዲራ ይዞ መገኘት ለእንግልት ይዳርጋል፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2017 ጄፍ ዳይመንት( jeff Daimnt  2017 ) የተባሉ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑ ጠበብት ባቀረቡት ጥናት መሰረት ‹‹ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ውጪ ከፍተኛ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ያለባት ሀገር ናት፡፡ በማናቸውም መለኪያ ኢትዮጵያዊ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች፣ በምስራቅ አውሮፓና መካከለኛው አውሮፓ ከሚገኙት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ይልቅ ሃይማኖተኛ እና ለሃይማኖታቸው ቀኖና በይበልጥ ተገዢ ናቸው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘው ይህቺ ሀገር ከ45 ሚሊዮን በላይ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ይኖሩባታል፡፡ ኢትዮጵያ ከሩሲያ በመለጠቅ ከአለም ካሉት ሀገራት የበለጠ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ የሚኖሩባትም ሀገር ናት፡፡ ሁሉም የኦርቶዶክስ ኢትዮጵያውን እምነት ተከታዮች ማለትም ወደ ዘጠና ፐርሰንት የሚሆኑት ሃይማኖት ጥሩ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ በሌላ በኩል በ13 የአውሮፓ ሀገራት በሚኖሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ በተደረገ ጥናት መሰረት 34 ፐርሰንቱ ብቻ ናቸው ሃይማኖት ጥሩ ነው የሚል መልስ የሰጡት፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች በተለይም ያለፈው የወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያን ለማዳከም የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ማዳከም በሚል ሴጣናዊ ስልት በብዙ ባጅቷል፡፡ የወያኔ አንጋሽ እና እንደ ፈለጉ ይናገሩ የነበሩት አቦ ስብሃት ሳይቀሩ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን አክርካሪውን መተነዋል ሲሉ በአደባባይ መናገራቸውን በሀዘን እናስታውሰዋለን፡፡ በነገራችን ላይ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መዳከም ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ታሪክ፣ ባህልና ማህበራዊ ምስቅለቅሎሽ የመጨረሻው መጀመሪያ ስለሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በብርቱ ልንጨነቅበት የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ሳስታውስ በታላቅ ትህትና ነው፡፡ ኢትዮጵያ በከባድ አጣብቂኝ ውስጥ መሆኑን ተረድተን ከገባንበት ማጥ ለመውጣት  አንድነታችንን ማጠንከር ይገባናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት  የኢትዮጵያን ታሪክ፣ እጽዋት፣ ባህል፣ የሀገር አስተዳደር፣ የህዝብን አንድነት ጠብቃ የቆየች መሆኑን ኢትዮጵያውያን ሁሉ መዘንጋት የለብንም፡፡

ማጠቃለያ ምን ይበጀናል ?

 ኢትዮጵያ ከገባችበት አስቸጋሪ የታሪክ አጋጣሚ ወይም መስቀለኛ  መንገድ  ኢትዮጵያ በቀና እንድትሻር ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ከሲቪል ማህበረሰቡ መሪዎች ምን እንጠብቅ ? 

1ኛ. አንዳንድ ሴረኞች በተለያዩ የሃይማኖት እና ጎሳዎች መሃከል ግጭቶች እንዲቀጣጠሉ ምክንያቶች መሆናቸውን መገንዘብ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊ የሃይማኖት አባቶች ፣ ኢትዮጵያዊ የሲቪል ማህበራት መሪዎች፣ የሙያ ማህበራት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች በኢትዮጵያ ምድር የሚከሰቱ ግጭቶች ( በተለይም ጎሳና ሀይማኖት ተኮር በሆኑት ላይ)  ምክንያቶቹ ምን እንደሆኑ፣ እነማን ለግጭቶች ተጠያቂዎች እንደሆኑ ለማወቅ ጥናት ማድረግ፣ መወያየት አለባቸው፡፡

2ኛ. የሀይማኖት መሪዎቻችንን ድምጽ በእጅጉ እንፈልገዋለን፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ሀይማኖት ተቋማት አባቶች ወይም መሪዎች በህዝብ ዘንድ የተከበሩ ስለሆኑ ይመስለኛል፡፡ የሀይማኖት አባቶች ከምንግዜውም በላይ ስለ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መቻቻል ሰርክ አዲስ ህዝብን ማስተማር አለባቸው፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች በበኩላቸው የሰብአዊ መብት፣ የዲሞክራሲያዊ መብቶችና የህግ የበላይነት እንዲከበሩ መንግስትን በተለያዩ መንገዶች መወትወት የዘውትር ተግባሮቻቸው መሆን ይገባቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

3ኛ. የሀይማኖት ተቋማት መሪዎችም ሆኑ የሲቪል ማህበረሰቡ  መሪዎች ፍትህ ሲጓደል ዝምታ ከመረጡ በምንም አይነት ተቀበይነት የለውም፡፡ በተለይም መጪው የምርጫ ውድድር ለሁሉም የፖለቲካ ተፎካካሪዎች እኩል የመጫወጫ ( ውድድር) ሜዳ እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ከወዲሁ በብርቱ መስራት አለባቸው፡፡ የምርጫ ውድድሩ ጤናማ እንዲሆን የእነርሱ የገለልተኝነት ሚና መተኪያ የለውም፡፡ ሀገራችን ዲሞክራቲክ የምርጫ ውድድር እንድታካሂድ በብዙ መድከም አለባቸው፡፡

4ኛ. በእኔ አስተሳሰብ የሀይማኖት አባቶች እጅግ የታወቀ ሚና አላቸው፡፡ 

የሃማኖት አባቶች የተሰጣቸው ሃላፊነት መንፈሳዊ ተግባራትን ብቻ መከወን አይመስለኝም፡፡ እውነተኛ የሀይማኖት አባቶች ፍትህ ሲጓደል ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ ለፍህትህ መከበር እንዲቆም መናገር፣ ማስተማር፣ መወትወት መንፈሳዊ ግዴታቸው ነው፡፡ በሌላ የሳንቲሙ ግልባጭ ያሉት የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች፣ የሙያ ማህበር መሪዎች ወዘተ ወዘተ ከትላልቅ የሆቴል ቤት ኮክቴል ጫጫታ በመውጣት የኢትዮጵያ ህዝብ ለፍትህ መከበር እንዲቆም በተለያዩ ዘዴዎች መሞከሩ ታሪካዊ ሀላፊነታቸው ነው በማለት ሳስታውስ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡

5ኛ. በታወቁት የሃይማኖት ተቋማት፣ በሲቪል ማህበረሰቡ እና በሙያ ማህበራት ውስጥ ጎሰኝነት ስር እንዳይሰድ ሁላችንም በቀና መንፈስ ቁጭ ብለን መነጋገር ያለብን ይመስለኛል፡፡ የተጠቀሱት ተቋማት የሰው ልጆችን ሁሉ በእኩልነት መንፈስ ማገልገል ግዴታቸው መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጀውን የሚያውቅ ታላቅ ህዝብ ነው፡፡ በሃይለኞች የፊጥኝ ታስሮ አድሎአዊነትን፣ ኢፍትሃዊነትን፣ ግፍን አይፈልገውም፡፡ ይህ በእንዲህ በኢትዮጵያ ግዛት የእኩልነት መብት በብዙ ስፍራዎች እየተጣሰ በመሆኑ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ሰማይ ነክቷል፡፡ በርካቶች በሚያገኙት ወርሃዊ ደሞዝ ብቻ ኑሮን ማሸነፍ ተስኗቸዋል፡፡ የጥቂቶች ኑሮ መሻሻል ብዙሃኑን ህዝብ የሚወክል አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያ ሀይማኖት፣ ባህል፣ ታሪክ እንደሚስተምረን የውጪ ወራሪዎችንና ቅኝ ገዢዎችን አሳፍረን መመለሳችንን ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ለሚበቅሉ ጨቋኞችና የፍትህ ጣሾች ግን ለም መሬት ሆነን ዘመናትን አሳልፈናል፡፡ ይህ ግን ዛሬ ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ወደ አደገኛ ገደል ውስጥ ሁላችንንም ጭልጥ አድርጎ ይዞን የሚገባ ነው፡፡ ስለሆነም ለእኩልነትና ፍትህ መከበር ሲባል አንድነታችንን ማጥበቅ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ይሆናል፡፡ በተለይም በመጪው ምርጫ ውድድር ላይ ከሚካፈሉ የፖለቲካ ሃይሎች መሃከል፣ የሚበጀንን ለመምረጥ ሁለት ሶስት ጊዜ ማሰብ፣ ማሰላሰል የሰውነት ባህሪ ነው፡፡ 

6ኛ. ምንም እንኳን በሀይማኖት ተቋማት መሃከል የሀይማኖት ቀኖና ወይም አስተምህሮ ልዩነት እንዳላቸው ቢታመንም ፣ በኢትዮጵያ ምድር ፍትህን ለማስከበር፣ ፍትህ በጉልበተኞች እንዳትረገጥ፣ ደካሞች ፍትህ እንዳይነፈጉ በአንድነት መቆም አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም የሲቪል እና ሙያ ማህበራት የቆሙላቸው ዋና ዋና አለማዎች የተለያዩ ቢሆንም ለፍትህና ለነጻነት ጥያቄዎች መከበር ሲባል የህብረት ችቦ መለኮስ አለባቸው፡፡ ለህግ የበላይነት፣ ለሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የሚታገሉት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያዎችና ጠበቆች ማህበር፣ ቪዥን ኢትዮጵያ ለዲሞክራሲ ( ቪኮድ) ወዘተ ወዘተ በሌሎች የሲቪል ማህበራት መደገፍ አለባቸው፡፡ ሁሉም የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎችና አባላት በፍትህ መከበር ጉዳይ ላይ ያለ ይሉኝታ መተባበር አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚሀ ባሻግር ኢትዮጵያውያን ሁሉ በኢትዮጵያ ምድር ፍትህና ነጻነት እንዲሰፍን አንድነታችንን ማጠንከር አለብን፡፡ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን የመሰሉ ስመጥር ምሁራን በህይወት በነበሩበት አበክረው እንዳስገነዘቡን ለዲሞክራሲና ፍትህ እውን መሆን ይህ አሁን ያንበት ጊዜ መልካም እድላችን ነው፡፡ በተለይም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተንተከተከ ያለው የጎሳ ጥቃት ዛሬውኑ መላ ካላበጀንለት መጥፊያችን ይሆናል ብዬ በብርቱ እሰጋለሁ፡፡

7ኛ. የተከበራችሁ የተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት መሪዎች ወይም የሀይማኖት አባቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጎሳንና ሀይማኖት ወይም ፖለቲካን መሰረት ያደረጉ ግድያዎችን በአንድ ድምጽ ካለወገዛችሁ የምትወቀሱት ወይም የምትዳኙት በኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ አይደለም፣ በታሪክም ብቻ አይደለም የምትዳኙት፡፡ በእግዚአብሔር ፊትም የምትዳኙ ይመስለኛል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ እና የሙያ ማህበር መሪዎችም ብትሆኑ ለፍትህ መከበር ለመቆም መንፈሳዊ ወኔ ከከዳችሁ በታሪከ፣ በኢትዮጵያ ህዝብና ለህሊናችሁም ተጠያቂ መሆናችሁ አይቀሬ ሀቅ ነው፡፡

በዛሬዬቱ ኢትዮጵያ ለተለያዩ የሀይማኖት ቀኖናዎች፣አስተምህሮ፣ በአንድ ሀይማኖት ተከታዮች መሃከል ለሚደረግ የስልጣን ግብግብ ቦታ የለም፡፡ በሲቪልና ሙያ ማህበራት መሪዎችና አባላት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት መሃከል  ለስልጣን ጥማት ማርኪያ ሲባል ለሚጎነጎን የሴራ ፖለቲካ ቦታ የለም፡፡ የዛሬዬቱ ኢትዮጵያ የህለውና አደጋ ላይ የምትገኝ አሳዛኝ ሀገር ናት ተብሎ ሃሳብ ቢቀርብ ስህተት አይመስለኝም ወይም ክፉ መመኘት አይደለም፡፡ ችግር አለ ከተባለ ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣት የሃሳብ መንሸራሸር እንዲኖር ይረዳል፡፡ በነገራችን ላይ ትግሉ በመጥፎ እና ጥሩ መሃከል ቢሆንም፣ በህይወትና በሞት መሃከል ቢሆንም ይህ የመቅደም እና የመቀደም ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡

ሰይጣናዊ ተግባር ሲፈጸም እንዳላየን ዝምታ ከመረጥን፣ ይህን ክፉ ድርጊት በአይምሮአችን ውስጥ እንቀብረዋለን፡፡ በአካባቢያችን ይህን ክፉ ድርጊት የሚያሳዩ ምልክቶች ይጠፋሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ይህ ሰይጣናዊ ተግባር ከብዙ አመታት በኋላ በብዙ ሺህ እጥፍ ጨምሮ ይከሰታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢሰብአዊ ድርጊት ፈጻሚዎችን፣ ፍትህን የሚያዛቡትን ሰው መሳይ አውሬዎችን በፍትህ አደባባይ እንዲቆሙ ካላስገደድናቸው መጪውን ትውልድን ብቻ ሳይሆን የምንጎዳው የፍትህን መሰረት ሙሉበሙሉ እናናጋዋለን፡፡ ያለችን አንዲት ሀገር ናት፣ የምንኖረውም በዚችው ሀገር ነው፡፡ ስንሞትም የምንቀበረው በዚችው ሀገራችን ነው፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ የሚገኙ ሰላማዊና ህጋዊ የፖለቲካ ሀይሎች ሁሉ በመጪው የኢትዮጵያ ሀገረ አቀፍ የምርጫ ውድድር ላይ በነጻነት ስለመሳተፋቸው፣ደጋፊዎቻቸውን በነጻነት ስለማስተማራቸው ፣ እጩዎቻቸው በነጻነት ስለመንቀሳቀሳቸው በገለልተኝነት መከታተል፣ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ የሲቪል ማህበረሰቡ መንፈሳዊ እና ህሊናዊ ግዴታ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች እሮሮ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠው ለማድረግ የሲቪል ማህበረሰቡ ሚና እጅጉን ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በኢትዮጵያው የምርጫ ውድድር ላይ ሁሉም የፖለቲካ ተፎካካሪዎች በነጻነት መንቀሳቀስ መቻላቸው መጪውን ግዜ ከስጋት ዳመና ይገፈዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለማናቸውም አምባገነኖችን፣ፍትህ የሚረግጡትን፣ ሙሰኞችን፣ አድሎአዊ አሰራር የሚፈጽሙ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ተጠያቂ ካልሆኑ የፍትህ መሰረት ሙሉበሙሉ እንደሚናድ አሌክሳንደር ስሎዝሄኒስትየን የተሰኘው ጠበብት ‹‹ The Gulag archepilago (1918- 1956 )

በተሰኘው ስራው ላይ ያሰፈረውን እውነት በመጥቀስ እሰናበታለሁ፡፡ አቤቱ አምላኬ ሆይ የኢትዮጵያን ክፉ አታሳየን፡፡

“In keeping silent about evil, in burying it so deep within us that no sign of it appears on the surface, we are implanting it, and it will rise up a thousand fold in the future. When we neither punish nor reproach evildoers, we are not simply protecting their trivial old age, we are thereby ripping the foundations of justice from beneath new generations.

Alexander Slozhenitsyn The Gulag archepilago (1918- 1956 )

 

Filed in: Amharic