>

የአማራ ክልል ባለሥጣናት ሆይ ወዴት አላችሁ? (የአራት ኪሎው ዘንዶ አማራን ውጦ አይጠግብም!) - አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)

የአማራ ክልል ባለሥጣናት ሆይ ወዴት አላችሁ?

(የአራት ኪሎው ዘንዶ አማራን ውጦ አይጠግብም!)

አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)


አራት ኪሎ የተገሸረው ዘንዶ እምብርት የለውም፤ በመሆኑም መቼም ቢሆን አይጠግብም፡፡ ቀለቡም የሰው ሥጋና ደም ነው፡፡ ካለደም ግብር ዘንዶው እስትንፋስ የለውም፡፡ ዘንዶ በተፈጥሮው ርህራሄና ምሕረት አያውቅም፡፡ ይህ ወጣት ዘንዶ ትናንሽና ጎረምሳ ዘንዶዎችንና እጅግ መርዛማ ኮብራዎችን በተለይ ኦሮምያ በሚባለው አካባቢ አሠማርቶ ኢትዮጵያን የማጥፋት ተልእኮውን በተሣካ ሁኔታ እያከናወነ ነው፡፡ ዘንዶው የዓዞ ዕንባ በማፍሰስ የተዋጣለት ነው – “ሩህሩህ ነው፤ ኢትዮጵያን ይወዳል፤ …” እየተባለ በተከፋይ አክቲቪስቶቹና አሽቃባጮቹ ይደሰኮርለታል – ውስጡን ለቄስ፡፡ ዓዞ የዕንባ ዕጢው በማላመጫው አካባቢ በመሆኑ ባላመጠና በበላ ቁጥር ዕንባው ሳይወድ በግዱ ዱብ ዱብ ይላል፤ በዚያም ምክንያት ነው የዓዞ ዕንባ የሚባለው – ለሚበላቸው እንስሳት ያዘነ እንደሚመስል በመጠቆም ግን የሀሰት አዘኔታ መሆኑን ለማሳየት ይመስላል የብሂሉ ሞራላዊ መልእክት፡፡ ዓለም አቀፉ የጨለማው ገዢ ኃይል በመረጃ፣ በሞራልና በቁሣ ቁስ እንዲሁም በገንዘብ የሚደግፈው ይህ ዘንዶ በእስካሁኑ ሁኔታ ምንም ነገር ሳያደነቃቅፈው ሀገራችንን እንጦርጦስ የማውረዱን ግዳጅ ለተጨማሪ የኖቤል ሽልማት በሚያበቃውና ላኪዎቹን በሚያስደስት መልክ እየተወጣ ነው፡፡

በመጀመሪያ አሮጌውን ጌኛ ሕወሓትን ከጨዋታ ሜዳ አወጣና መቀሌ ወተፈ፡፡ ቀጥሎ ብአዴንን እርስ በርስ አራኮተና ለዘንዶው ኦሮሙማዊ ዓላማ እንቅፋት ይሆናሉ ብሎ ያሰባቸውን አምባቸውንና አሣምነውን የመሰሉ ለሀገር ተቆርቋሪ አማሮች በልዩ ሥልት በማጨድ ከጨዋታው ሜዳ አገለለ – የሚገርም ልጅ ማለቴ ዘንዶ ነው! ቀጠለና ብልጣ-ብልጡ ሕወሓት ያጣውን ሥልጣንና የሀብት ውቅያኖስ በተሳሳተ ሒሣባዊ ቀመር ተመርቶ ለመቆጣጠር በጀመረው የጅል ሥራ ምክንያት በዘንዶው ወጥመድ ገባና አያ ዘንዶ ወያኔን ቀርጥፎ በመሰልቀጥ ጉድ ሠራት – ለነገሩ ወያኔን ማን እንደቀጠቀጣትና ትዕዛዙም ከየት እንደሆነ የምናውቅ እናውቃለንና ወደዚያ አሁን አንገባም፡፡ ራሱን መጠበቅ የማይችለውና በዘር የተከፋፈለው መከላከያ ነው ካላችሁም መብታችሁ ነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ታሪክ ራሱ ይመሰክራል፡፡ ብቻ ወያኔም ጦሷ ለምስኪኑ ትግራዋይ እስኪተርፍ ድረስ አሣሯን በላችና በቆፈረችው ጉድጓድ ሰተት ብላ ገባች፡፡

ዘንዶው አንድ ዕረፍት አገኘ፡፡ ግን ጥሩ ዕረፍት ለማግኘት ቀደም ሲል በጅምር የተወውን የአማራ ጉዳይ ዕልባት መስጠት ነበረበት ወይም አለበት፡፡ ስለዚህም ንጹሑን ገበሬ አማራ በመተከልና በወለጋ፣ በሐረርና በደቡብ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ …. በግልጽና በሥውር በኦነግ ሸኔና በተራ የመንደር ውስጥ ሽፍቶች ከማስጨፍጨፍ በተጓዳኝ የአማራን ክልል ደንገጡሮች እርስ በርስ እያናቆረ ክልሉን የኦሮሙማ አሽከር ማድረግ ነበረበት፤ እንደሚሰማው ከሆነ የክልሉ ባለሥልጣናት ዐይጥና ድመት ሆነው ብዙዎቹ ለአማራው ሣይሆን ለአዲሶቹ ጌቶቻቸው አድረዋል፡፡ ይህ አደገኛና አሳሳቢም ነገር ነው፡፡ አማራ በወያኔ የተደቆሰው አንሶት ሊያውም የራሴ በሚላቸው ልጆቹ ለሁለተኛ ጊዜ ለከፋ የዕልቂት ድግስ መዳረጉ ይቅርታና ምሕረት የሌለው ወንጀልና ኃጢኣት ነው፡፡ ጎማው ከተነፈሰው የትግራይ ወያኔ ቀጥሎ ለዘንዶው አፄያዊ አምባገነን ሥልጣን ተቀናቃኙ አማራው እንደሆነ የተጠራጠረው ዘንዶው የአማራን ክልል ዕረፍት ካልነሳና የራሱን ሰዎች በክልሉ አስተዳደር ካልመደበ እንቅልፍ የለውምና ያንን በማድረግ ሂደት ላይ ተጠምዶ ይገኛል፡፡ እመኑኝ! ትክክለኛ ቀኑንና ሰዓቱን ማወቅ ባንችልም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዘንዶው አናቱ ይመታል፤ ይሞትማል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ብዙ ዕልቂት አለ፡፡ ይህ ዘንዶና አፎምያን ሊውጥ የነበረው እሳት የሚተፋው ደራጎን አንድ ናቸው – ሁለቱም ካለ የሰው ደም ግብር ሕይወት የላቸውም፡፡ የአራት ኪሎው ዘንዶ የደም ግብር ሲቀርብለት ደስታና ፈንጠዝያው እጅግ ልዩ ነው፡፡ በማስመሰልና በሀሰት ንግግር ደግሞ በዓለም (in the entire Universe!) አንደኛ ነው፡፡ እኔ ይህን አውቃለሁ፡፡ የ“ሰባበርናቸው”ንና የ“ቁማሩን በልተናል” ፖለቲካ የማይረዳ ዜጋ የለዬለት ደንቆሮ ነው፡፡ 

ጥቂት ጥያቄዎችን እንጠይቅ፡፡ አሁን የአማራ ክልል መስተዳድር የት ነው? ምንስ እየሠራ ነው? አማራን እያስተዳደረ ያለው ማን ነው? ባለሥልጣቱ መሀል ምን ዓይነት አንደርብ ገባና ያምሳቸው ያዘ? ዐርባና ሃምሣ ሚሊዮን አማራ በጥቂት የኦሮሙማ አክራሪ ኃይሎች መዳፍ ሥር የገባው በምን መተት ነው? ክልሉ የሚታወቅበት ፍጹም የማያንቀሳቅስ የተወሳሰበ ቢሮክራሲ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? አገኘሁ ተሻገር የተባለው የመለስ አምላኪ አሁን የት ነው? ሌሎቹ የክልሉ ባለሥልጣናትስ ምን ዓይነት አፍዝ አደንግዝ ተዞሮባቸው ነው የትሮይ ፈረስ ሆነው የቀሩት? እውነት ብል(ጽ)ግና የሚባለው አዲሱ ፕሮቴስታንታዊ ኢሕአዲግ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአማራ የሚጠቅም ሆኖ አግኝተውት ይሆን ህዝብን በግዳጅ ለድጋፍ ሰልፍ የሚያስወጡት? ለመሆኑ የያዙት መንገድ ጤናማ ነው ብለው ያስባሉ? “ሆድ እንዳሳዩት ነው” ይባላልና በአፋጣኝ ከሆድ አምላኪነት ወጥተው ወደ ሕዝባቸው ይመለሱ – “ሕዝባችን ነው” ካሉ፡፡ ያኔ ነው ኢትዮጵያም ከንፍር ቁስሏ የምትድነው፡፡ ኃጢኣትና ወንጀልም በንስሃና በጽድቅ ሥራ ይደመሰሳልና ባለፈ ዕኩይ ሥራቸው እያፈሩ በካፈርኩ አይመልሰኝ ኢትዮጵያን ከሚያጠፉ ወገኖች ጋር ከሚተባበሩ አሁንም ከረፈደም ቢሆን ተጸጽተው ይመለሱ፡፡ ሕዝቡም ይቅር ባይ ነው፡፡ 

አዎ፣ ብዙ ነገር እንሰማለን፤ እናያለንም፡፡ የአማራ ባለሥልጣናት ነገ ጊዜ ካለፈ በኋላ እንደጲላጦስ እጃችሁን ብትታጠቡ ከታሪካዊ ፍርድ አታመልጡም፡፡ የዛሬ የሞላ ቀፈት ለነገ ስንቅ አይሆንም፡፡ ዛሬ የተጎሰረ ሆድ የነገን የኅሊና እርቃን አይሸፍንም፡፡ ከመነሻው እስከመጨረሻው የሆነውንና እየሆነ ያለውን ወደፊት የሚሆነውም ጭምር ፈጣሪ በምናብ እያሳየን የለፈለፍንና አነስተኛም ቢሆን መስዋዕትነትን የከፈልን ብዙ አለን፡፡ ጩኹ ተብለን ከጮኽነው አንድም የቀረ የለም – የቀረው የቀረው ብቻ ነው – ያንንም እናንተም ታውቁታላችሁ፡፡ የዘንዶው ራስ ሊቀጠቀጥ ኢትዮጵያም አፈር ልሳ ከሙታን መንደር ልትነሳ ቀኑ ቀርቧል፡፡ እስከዚያው የሚገደል ይገደላል፤ የሚራብ ይራባል፤ የሚታሰርና የሚሰቃይም ይታሰራል፤ ይሰቃያልም፡፡ በጨለማ ያልታጀበ ንጋት ታይቶ አያውቅምና መቻል ነው፡፡ 

Filed in: Amharic