>
5:01 pm - Monday December 2, 6469

በኦነጋውያን የተወረሱት የመንዙ አማራ ፊታውራሪ ገበየሁ ተክሌ የግድም ወርቅ (አቻምየለህ ታምሩ)

በኦነጋውያን የተወረሱት የመንዙ አማራ ፊታውራሪ ገበየሁ ተክሌ የግድም ወርቅ 

አቻምየለህ ታምሩ

 

* …. ታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ሰላሌ ላይ በዐቢይ አሕመድ ተመርቆ በተከፈተው «የሰላሌ ኦሮሞ የባሕል ማዕከል» ውስጥ ተወርሶ በኦሮሞ ብሔርተኞች ኦሮሞ ተደርጓል…
 
* ኦነጋውያን ከዚህ በፊት አድዋን አስመልክቶ ሲያራምዱት የኖሩት ፖለቲካ በቻሉት መጠን ድሉን ማራከስና ማጣጣል፤ አልፎም ሁለት ቅኝ ገዢዎች ማለትም ኢትዮጵያና ጣሊያን ኦሮሞን ቅኝ ለመግዛት ያካሄዱት ጦርነት አድርጎ ማቅረብ ነበር። ይህን ባለፉት 46 ዓመታት ሲያራምዱት የኖሩት ፖለቲካ ሞክረውት፣ ሞክረውት አልሆን ሲላቸው አሁን ደግሞ መቼም እዚያ ቤት ሀፍረት ብሎ ነገር የለም 180 ዲግሪ ተገልብጠው ሁለት ቅኝ ገዢዎች ኦሮሞን ቅኝ ለመግዛት ያካሄዱት ጦርነት ሲሉት ሲሉት የኖሩትን ጦርነት ድሉ የኛ ነው፤ መሪዎቹም እኛ ነን እያሉን ነው። ድሉንም የነሱ ለማድረግ ኦሮሞ ያላደረጉት የአማራ የጦር አዝማች የለም።    
ከሻምበል አበበ ቢቂላ [የአበበ ወላጅ አባት የጅሩ አማራ የሆኑት አቶ ደምሴ ዓለሜ እንደሆኑ ከዚህ በፊት ስለ ሻምበል አበበ ታሪክ የጻፍሁትን ልብ ይላሏ] ቀጥሎ የኦሮሞ ብሔርተኞች የመውረርና የመውረስ ፖለቲካ ሰለባ ከሆኑት ታላላቅ ሰዎች መካከል የአድዋው ጀግና ፊታውራሪ ገበዬሁ ተክሌ ቀዳሚው ናቸው። ታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ሰላሌ ላይ በዐቢይ አሕመድ ተመርቆ በተከፈተው «የሰላሌ ኦሮሞ የባሕል ማዕከል» ውስጥ ተወርሶ በኦሮሞ ብሔርተኞች ኦሮሞ ተደርጓል። ለኦሮሞ ብሔርተኞች ሰውንም ይሁን ቤትን፤ ምድሩንም ይሁን ሰማዩን ለመውረስና ለመውረር እውነት፣ ታሪክና እውቀት አያግዳቸውም። ይህም በመሆኑም  በእንጀራ አባቱ የሚጠራው በእናቱ የመንዝ አማራ፤ በአባቱ ደግሞ የጅሩ አማራ የሆነው የአቶ ደምሴ ዓለሜ ልጅ  ሻምበል አበበን ኦሮሞ አድርገው ወርሰውታል።
እንደ ሻምበል አበበ ቢቂላ ሁሉ የኦሮሞ ብሔርተኞች ታላቁን አርበኛ ፊታውራሪ ገበዬሁ ተክሌን ወርሰው ኦሮሞ ሲያደርጉት የፊታውራሪው የቤተሰብ ታሪክ አላስጨነቃቸውም። ፖለቲካቸው የዝቅተኛነት ደዌ የተጠናወተው የመውረርና የመውረስ በሽታ ስለሆነ ትልቅ የተባለን ሰው ኦሮሞ ካላደረጉ ሰው ሆነው የሚቆሙ አይመስላቸውም። መንግሥት ነኝ በሚለው አካል ተመርቆ በተከፈተው የባሕል ማዕከል ውስጥ ኦሮሞ ተደርገው ስለቀረቡት ሰዎች ማንነትና ታሪክ በባለሞያ ለማስጠናት ሙዝ የመላጥ ያህል እንኳ ሙከራ አላደረገም፤ እንዲደረግም አይፈልግም። የማጣራት ሙከራ የማይደረገውም እውነቱ/ውጤቱ የኦሮሞ ብሔርተኞች የማይፈልጉት ሆኖ ስለሚገኝ ብቻ ነው።
በኦሮሞ ብሔርተኞች ተወርሶ ኦሮሞ የተደረገው የአድዋው ጀግና ፊታውራሪ ገበዬሁ የተወለዱት በዳግማዊ ምኒልክ የትውልድ ስፍራ መንዝ አንጎለላ ውስጥ ነው። የአባታቸው ስም ተክሌ ነው።  የአያታቸው ስም ደግሞ የግድም ወርቅ ነው። ፊታውራሪ ገበዬሁ ተክሌ የግድም ወርቅ  ወደ አድዋ ከመዝመታቸው በፊት የእቴጌ የጣይቱ ጉልት ገዢ፣ የአድአ፣ የምንጃርና የአንኮበር አስተዳዳሪ ነበሩ። በአድአ ወረዳ  ደብረ ዘይት ከተማ ቃሊቲ ሰፈራ በሚባለው ቦታ የሚገኘው የዳሎታ ሚካኤል  ቤተክርስቲያን ያሳነጹት ፊታውራሪ ገበዬሁ ናቸው።  ይህ ተመዝግቦ የምናገኘው ታሪክ ነው። የፊታውራሪ ገበዬሁ የቤተሰብ አባል የሆነችው ማሕሌት ገበዬሁ የቅመ አያቷ የፊታውራሪ ገበዬሁ አባት ስም ክንዴ እና ካሳ እንደሚባልም በውስጥ መስመር በጽሑፍ የላከችልኝ የቤተሰብ ታሪክ ይገልጣል። በነገራችን ላይ ማሕሌት ገበዬሁ የፊታውራሪ ገበዬሁ አራተኛ ትውልድ ስትሆን ባሁኑ ወቅት “የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ” የጽሕፈት ቤት ሰራተኛ ናት። ኦነጋውያን ምን ይሉኝ የማያውቁትና የማያፍሩት ስለሆኑ የፊታውራሪ ገበዬሁ ዘሮች ሞተው ሳያልቁ  የፊታውራሪው ቤተሰብ ጉዳይ  ቅንጣት ታህል እንኳን ሳያስጨንቃቸው የጀግናውን  ታሪካቸው ከልጆቻቸው ቀምተው ሲወርሱ  አያስጨነቃቸውም።
የአድዋው ጀግና  ፊታውራሪ ገበዬሁ የአራት ልጆች አባት ነበሩ። አራቱ ልጆቻቸው ባራምባራስ በላይነህ ገበዬሁ፣ ወይዘሮ ይመኙሻል ገበየሁ፣ ቀኛዝማች ደገፉ ገበዬሁ  እና ፊታውራሪ መድፉ ገበዬሁ ይባላሉ። የባልደራሷ ማሕሌት ገበዬሁ የወይዘሮ ሐረገወይን ደገፉ ገበዬ የልጅ ልጅ ናት። የፊታውራሪ ገበዬሁን አራት ልጆች አባታቸው አድዋ ከተሰው በኋላ በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ያሳደጓቸው  አቴጌ ጣይቱ ናቸው። አራቱም የፊታውራሪ ልጆች አዲስ አበባ ውስጥና  በዙሪያ ብዙ ርስት ነበራቸው።
ፊታውራሪ ገበዬሁ ተክሌ የግድም ወርቅን  ኦሮሞ ለማድረግ ገበየሁ ጉሩሙ የሚል ተረት የፈጠረው ሻዕብያው ተስፋዬ ገብረአብ ነው። የኦሮሞ ብሔርተኞች ፊታውራሪ ገበዬሁ ተክሌን  ፊታውራሪ ገበዬሁ ጉሩሙ እያሉ የሚጠሩት ተስፋዬ ገብረአብ ያስተማራቸውን ይዘው ነው። ተምዝግቦ የምናገኘው የጦር አበጋዙ ትክክለኛ ስም ግን  ፊታውራሪ ገበየሁ ተክሌ ነው። ፊታውራሪ ገበየሁ ስማቸው ፊታውራሪ ገበየሁ ተክሌ ስለመሆኑ ምንጭ የሚፈልግ ቢኖር የጳውሎስ ኞኞን «ዐጤ ምኒልክ» መጽሐፍ ገጽ 167 ይመልከት።
እንግዲህ! መቼም በኦነጋውያን ዘንድ ሐፍረት ብሎ ነገር የለም የንጉሥ ሣሕለ ሥላሴን ከተማና የዳግማዊ ምኒልክን የትውልድ ቦታ አንጎለላን የኦሮሞ ነች ብለው ካልሰለቀጧትና ንጉሥ ሣህለ ሥላሴንና  ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክንም ኦሮሞዎች ናቸው ብለው ካልወረሷቸው በስተቀር በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የትውልድ መንደር አንጎለላ የተወለዱትና በአርባ ቀናቸው ዳግማዊ ምኒልክ ክርስትና በተነሱባት አንጎለላ ኪዳነ ምሕረት ክርስትና የተነሱትፊታውራሪ ገበየሁ ተክሌ የግድም ወርቅ ኦሮሞ ሊሆኑ አይችሉም!
የመንደራቸው ልጅ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ በዓድዋው ዘመቻ የሸዋን ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ እንድትከት ብለው ሲያውጁ የቀዳሚው ጦር አበጋዝ የነበሩት ፊታውራሪ ገበየሁ “በጦርነቱ ስዋጋ በጥይት ብወድቅ የተመታሁት ጀርባዬን ከሆነ ስሸሽ ነው፤ ስለሆነም አሞራ ይብላኝ እዛው ተውኝ፡ አትቅበሩኝ፤ ግንባሬን ከተመታሁ ግን አገሬ ቅበሩኝ አለ» በማለት ወደ አድዋ ዘመቱ። ከወደቁም በኋላ ባሳዩት ጀግንነት “ከነፍጥ ጎበዝ አየሁ፤ ከጀግና ገበየሁ” ተብሎላቸዋል። ጎበዝ አየሁ በዘመኑ አንደኛ የነበረ የጠመንጃ አይነት ነው።
ፊታውራሪ ገበየሁ ግንባሬን ከተመታሁ ብቻ አገሬ ቅበሩኝ ባሉት ቃል መሠረት ከዓድዋ ጦርነት ሰባት ዓመታት በኋላ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ አስከሬናቸውን ከዓድዋ ሥላሴ አስመጥተው በትውልድ ቦታቸው አንጎለላ ንጉስ ሣህለ ስላሴ በሰሯት አንጎለላ ኪዳነ ምህረት አጽማቸው እንዲያርፍ አድርገዋል። ፊታውራሪ ገበየሁ የተወለዱበትም ሆነ አጽማቸው ያረፈበት አንጎለላ ኪዳነ ምህረት በዛሬው ጊዜ ሳይቀር አማራ ክልል በሚባለው የሸዋ ክፍል ውስጥ ይገኛል።
እነ ሰማዩም ምድሩም የኛ ውሸት ማምረታቸውን ወደፊትም ይቀጥላል! እኛ እንዲህ እየተከታተልን ውሸታቸውን ራቁቱን ማስቀረቱን እንቀጥላለን! በቀጣይ ክፍል ስለ ራስ መኮነንና ከሐረር  ስለዘመተው ጦር የፈጠሩትን ተረት እናፈርሳለን!
ከላይ የታተመው ታሪካዊ ፎቶ ፊታውራሪ ገበዬሁ በጦር ሜዳ ሳሉ ቼኪ በተባለ የጣሊያን ጎብኚ የተነሳ ምስላቸው ነው።
Filed in: Amharic