⇐ ለክቡር ልጅ ዳንኤል መስፍን፤
የኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበር ፕሬዚዳንት፡፡
የማክበር ሰላምታዬን እያቀረብኩ፤ ስለ ተላከልኝ ማስፈንጠሪያ «ኢትዮጵያ እሳት ያለበትን» ልባዊ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚም፤ አባትህ፤ የተከበሩ ራስ መስፍን፤ ኢትዮጵያ በፋሺሽት ኢጣልያኖች በተወረረችበት ጊዜ ስላበረከቱት የጀግንነት አስተዋጽኦ አድናቆቴን መግለጽ እወዳለሁ፡፡ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማርልን፡፡ በተጨማሪም፤ ስለ የፋሺሽት ኢጣልያ የጦር ወንጀል እንዲሁም በአሁኑ ዘመን ስለ ተከሰተው አሰቃቂ እልቂት ላቀረብከው ገለጻ አመሠግናለሁ፡፡
ፋሺሽት ኢጣልያ፤ በቫቲካን ያልተቆጠበ ድጋፍ፤ በኢትዮጵያ ለፈጸመችው እጅግ ከባድ የጦር ወንጀል፤ ይኸም፤ የአንድ ሚሊዮን ሕዝብ መጨፍጨፍ (ከዚሁ ውስጥ፤ በ3 ቀኖች ብቻ፤ አዲስ አበባ ከተማ፤ የ30000 ሰው ግድያ)፤ የ2000 ቤተ ክርስቲያኖች፤ የ525000 ቤቶችና የ14 ሚሊዮን እንስሶች ውድመት፤ የብዙ ንብረቶች ዝርፊያ፤ ወዘተ፤ ኢትዮጵያ የሚገባትን ፍትሕ ሳታገኝ ቀርታለች፡፡ 30000 ሕዝብ የተጨፈጨፈባት ሊቢያ $5 ቢሊዮን ካሣ ከኢጣልያ ማግኘት ችላለች፡፡ ኬንያ ከእንግሊዞች፤ ኢንዶኔዚያ ከኔዘርላንድስ፤ ሌሎች ሐገሮችም የሚገባቸውን ፍትሕ ማግኘት ችለዋል፡፡ ቫቲካን አይሑዶችን፤ የሩዋንዳንና የላቲን አሜሪካን ሕዝቦች ይቅርታ ለምነው ኢትዮጵያን ግን ችላ እንዳሉ ነው፡፡ እንዲያውም ከ500 በላይ የሆኑ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ቅርሶች በቫቲካን ቤተመዛግብት፤ በሮም ከተማ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ ለበለጠ ዝርዝር ከዚህ ጋር የተያያዙትን ሰነዶችና http://www. globalallianceforethiopia.net መመልከት ይጠቅማል፡፡
ስለዚህ፤ ይህ ከባድ የፍትሕ ጉዳይ፤ የኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበርም ልዩ ጉዳይ (“mandate”) መሆን ስለሚገባው፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመመካከር፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሚበጅ ሥልት፤ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ በማክበር አሳስባለሁ፡፡
የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳን፡፡
ኪዳኔ ዓለማየሁ፡፡