‹‹ መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን እየሰራን ነው››
አቶ አንዷዓለም አራጌ የኢዜማ ምክትል መሪ
(ኢ ፐ ድ)
መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ፓርቲያቸው ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ አስታወቁ።
ምክትል መሪው በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ የተሳካ ብሔራዊ ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው። መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ፓርቲያቸው ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ነው።
ሁሉም ፓርቲዎች ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ያሉት አቶ አንዷዓለም ፣ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሀገሪቱ ሳይሳካ የቆየውን የዴሞክራሲ ሥርዓት እውን ለማድረግ እንደ ሀገርም ሆነ ትውልድ እጃችን ላይ የወደቀ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ኢዜማ በተግባር የሚገለፅ ማንነት ለማሳየት ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ አቅሙን አሟጦ እየሰራ ነው ያሉት ምክትል መሪው፤ እኛ ለመማርም ለማስተማርም ዝግጁ ነን፤ ይህን ስንል በኢትዮጵያ ትክክለኛ የዴሞክራሲ ምርጫ እንዲካሄድ ካለን ፅኑ ፍላጎት የመነጨ በመሆኑ ነው። እኛ የፖለቲካ መሪዎች ብቻ ሳንሆን የሞራል መሪዎችም መሆን ይጠበቅብናል ብለዋል።
ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ኢዜማ የራሱ የሆነ የመግባቢያ ሰነድ አዘጋጅቶ ለአባላቱ እንዳሰራጨ የጠቆሙት አቶ አንዷዓለም ፤ ሥርዓትን በተከተለ መንገድ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የሌሎችን ተወዳዳሪዎች የመመረጥ እድል፣ የህዝቡን የመምረጥ መብት እንቅፋት እንዳይፈጥሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የምርጫ ጉዳይ የጋራ የሆነ ትልቅ የሀገር ፕሮጀክት መሆኑን ያነሱት አቶ አንዷዓለም፤ ኢዜማ ይህን መልካም አጋጣሚ መሰናክል እንዲገጥመው ፈፅሞ አይፈቅድም። ሌሎች ፓርቲዎችም ለሰላማዊ ምርጫው አበክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።