>
3:56 pm - Friday March 31, 2023

በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ የታሰሩ የአማራ ባለሃብቶች ወደ ነቀምት ተወሰዱ...!!! (አማራ ሚዲያ ማዕከል)

በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ የታሰሩ የአማራ ባለሃብቶች ወደ ነቀምት ተወሰዱ…!!!

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ/

*…. በኦነግ ሸኔ እና በኦሮሚያ ልዩ ኃይል በግፍ የተገደለ እና ትጥቅ የተዘረፈ አማራ ሆኖ እያለ አሁን ላይ አማራ እየታደነ በግፍ መታሰሩ ያለንበትን ጊዜ በእጅጉ አሳሳቢ እና መፍትሄ ሊፈለግለት የሚገባ መሆኑን በግልፅ ያመለክታል ….!!!
ከየካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ 01 ቀበሌ መንደር 10 በት/ቤት ግቢ የታሰሩ በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ 27 የአማራ ባለሃብቶች ከቀናት የእስር ቆይታ በኋላ በዛሬው እለት የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ነቀምት እንደተወሰዱ ተነግሯል። የታሳሪዎችን ቁጥር ከፍበ የሚያደርጉም አሉ።
ከጊዳ አያና ወረዳ የደረሰን መረጃ እንዳመለከተው በቀይ ቦኔት ለባሽ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣በፌደራል ፖሊስ፣በኦሮሚያ ልዩ ኃይልና በሚሊሻ እየተመረጡ በት/ቤት ታጉረው የሰነበቱ የአማራ ባለሃብቶች ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ወደ ነቀምት ተወስደዋል።
አንዳንዶቹ ምንጮች ነቀምት አሉን እንጅ በትክክል ወደተባለው ቦታ ይሁን ወደ ሌላ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፤ ወደ አካባቢው አቅንቶ ለመጠየቅም አስቸጋሪ ነው ብለዋል።
በኦነግ ሸኔ እና በኦሮሚያ ልዩ ኃይል በግፍ የተገደለ እና ትጥቅ የተዘረፈ አማራ ሆኖ እያለ አሁን ላይ አማራ እየታደነ በግፍ መታሰሩ ያለንበትን ጊዜ በእጅጉ አሳሳቢ እና መፍትሄ ሊፈለግለት የሚገባ መሆኑን በግልፅ ያመለክታል ብለዋል።
የሰሞኑ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ትጥቅ ለማስፈታት በሚል ሰበብ በአካባቢው ነዋሪ በሆኑ አማራዎች ላይ የፈፀመው ግድያና ዝርፊያ ከኦነግ ሸኔ ጋር አብረው ነው የሚሰሩ የሚለውን ለሚጠራጠሩት አሳማኝ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
ከየካቲት 1 እስከ የካቲት 3 ቀን 2013 ኦነግ ሸኔ በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና እና በሊሙ ወረዳዎች በአማራዎች ላይ ግልፅ ጦርነት በመክፈት የጨፈጨፈና የአፀፋ ምላሽም የተሰጠው ሲሆን የካቲት 7 ደግሞ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መመታት የተበሳጩ የአካባቢው የመስተዳድር አካላት የኦሮሚያ ልዩ ኃይልን በማስመጣት አማራዎችን ጦር መሳሪያ እንዲነጠቁና እንዲዘረፉ አድርገዋል፤ በርካቶችንም አስገድለዋል።
 በኦሮሚያ ልዩ ኃይል አማካኝነት በወጣቱ ባለሃብት በዋሴ በላይ የተፈፀመው ግድያና በወንድሙ እና በአጎቱ ላይ በኦሮሚያ ፖሊስና ሚሊሾች የተፈፀመው አሰቃቂ እስርና ድብደባ ከሁሉም የከፋ እና አሳዛኝ እንደነበር ነዋሪዎች አውስተዋል።
ስለሀገር፣ስለወገን፣ስለሰብአዊነት የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በግፍ እየተገደለ፣ እየታፈነ፣ እየተፈናቀለና እየተዘረፈ ላለው አማራ አንዳች መፍትሄ እንዲፈልጉ ጠይቀዋል፤ ድምጻችን አሰሙልን ሲሉም ተማፅነዋል።
ከክልሉ ውጭ ያለው አማራ በተለይም በመተከል እና በኦሮሚያ ክልል በጅምላ እየተገደለ፣ እየተፈናቀለ፣ከህጻን እስከ ትልቅ እየታገተ፣ እየተዘረፈና ከሰው በታች ሆኖ ክብሩ ተዋርዶ ያለማንም ሃይ ባይ ክፉኛ እየተፈተነ ያለበት ጊዜ መሆኑ ግልፅ ነው።
Filed in: Amharic