>
5:13 pm - Monday April 19, 4641

የጉድ ሀገር ገንፎ እያደር ይፋጃል! (አሰፋ ሀይሉ)

የጉድ ሀገር ገንፎ እያደር ይፋጃል!

አሰፋ ሀይሉ

‹‹የሐረሩ የልዑል ራስ መኮንን ኃውልት ወደ ወጥቤትነት ተቀየረ! የፊንፊኔውስ የአፄ ምኒልክ ኃውልት ወደ ምንነት ሊቀየርልን ይሆን የታቀደው?›› 
ይሄ የፈረሰው የሐረሩ የራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ ኃውልት መከዳ ነው፡፡ ወያኔ 27 ዓመት ስትገዛን የቱንም ያህል ጥላሸት ልትቀባው ብትሞክር፣ የቱንም ያህል ሀገር ምድሩን በጡትና በሰማዕታት ኃውልት ብትገጠግጥ፣ የቱንም ያህል የብሔር ፖለቲካዊ ዳንኪራ ስትደልቀብን ብትኖር፣ በዚህን ያህል የድፍረት ደረጃ ግን ታሪካችንን በአደባባይ እንዲህ ለማፈራረስ አልተዳፈረችም! አሁን እየሆነ ያለው ለከት ያጣ የምን ታመጣላችሁ የአደባባይ ነውረኝነት ነው! የአድዋው ጀግና ታሪካዊው የራስ መኮንን ኃውልት ፈርሶ፣ ፔዴስታሉ (የኃውልቱ መከዳ) የባቄላ ፉል የሚቀቀልበት ወጥ ቤት ተደርጓል፡፡ ለፉል ሕዝብ ከዚህ በላይ የሚገባው ታሪክ የለም፡፡ ነው መልዕክቱ? ያሳዝናል፡፡
እና ይገርማልም፡፡ ይገርማል በእውነት፡፡ ይገርማል ብቻ ሳይሆን ይህን ያክል ዓይን ያወጣ ድፍረትን የወለደው ምን እንደሆነ በእውነቱ አስቦ ማግኘት ያዳግታል፡፡ ምናልባት የሆነ የአጥፍቶ ጠፊ መንፈስ በላያቸው ላይ ተዘርቶባቸው እንደሆነ አንድ ነገር ነው፡፡ አሊያ ግን የድፍረታቸውን ምክንያት ፈልጎ ማግኘት ግን ያዳግታል በእውነቱ፡፡
የዚህ የ7ኛው ንጉሥ የእሣት ላይ ጨዋታ፣ የልጅ እያሱን ልክ ያለፈ ቅብጠት ያስታውሰኛል፡፡ ልጅ እያሱ የምኒልክን የአድዋ ጀግኖች በችሎት ‹‹የአባቴ ሙክቶች›› እያለ ይሳለቅባቸው ነበር፡፡ የሀገሪቱን አስተዳዳሪዎችና ባላባቶች ‹‹ካሰኘኝ አንጋልዬ ብሸናባቸውስ ምን ያመጣሉ?›› እያለ በአደባባይ ይሳለቅባቸው ነበር፡፡ ፍጻሜውን ታሪክ ነው የሚያውቀው፡፡ የአሁኑም ተረኛ አንጋልዬ ብሸናባችሁስ ምን ታመጣላችሁ? ነው እያለን ያለው? ለዚህ ሾርት ሚሞሪያም ህዝብ ዳቦና የትምህርት ቤት ምገባ መች አነሰው? ታሪክ የለህም፡፡ ነጻነት የለህም፡፡ ማንነት የለህም፡፡ የኢህአዴግ ሙክቶቼ፡፡ የብልጽግና አህዮቼ፡፡ እንዳሰኘኝ እጋልብባችኋለሁ፡፡ ነው እየተባልን ያለነው?
ታሪክ ራሱን ይደግማል ብቻ ሳይሆን ይደጋግማል፡፡ ይህ አይቀርም፡፡ የሚያሳዝነው ከታሪክ አለመማራችን ብቻ ነው፡፡ የዚህችን ጥጋብ መጨረሻ ማየት ነው፡፡ ግን የሚሆነው ላይቀር፣ ነገራችን ሁሉ እንዲህ ‹‹የጉድ ሀገር ገንፎ እያደር ይፋጃል›› ሆኖ መቅረቱ ያሳዝናል፡፡ በአንዱ ገንፎ ስንቃጠል፡፡ ያው ገንፎ ደግሞ፣ ደጋግሞ እያቃጠለን መኖር ሆኗል የኛ ህይወት፡፡ ስንቃጠል ስለማንጮህ በህይወት ያለን የመሰላቸው አልመሰለኝም፡፡ ዝም ብለናል፡፡ ግን አለን፡፡ ታሪካችን በላያችን ላይ እየፈራረሰ ነው፡፡ ደፍረውናል፡፡ ወረውናል፡፡ ነበር ያለው መንጌ?
‹‹ያገቡሻል፣ ይፈቱሻል›› እንዳለችው ዘፋኟ፣ የኛ ነገር መደፈርና መወረር ብቻ ከሆነ ሰነባበተ፡፡ እነዚያ ደፍረውን ወረውን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የሚያፈራርሱንና አንጋለው የሚሸኑብን፣ ያን ባለማወቃችንና ባለማስታወሳችንም ሾርት ሚሞሪያችንን ለዓለም በአደባባይ የሚለፍፉልን መጡ፡፡ ግን አለን? ጀግንነት በደማችን ይንተከተካል? አሁንም እንኳን እናት ሀገራችንን አፍሪካችንን የሚያለብስ የሀገር ፍቅራችን በውስጣችን አለ? አሳዩን፡፡ ፕሩቭ አድርጉልን፡፡ መሰለኝ እየተባልን ያለነው፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ልብ እና ልቦናችንን ይቀስቅስ፡፡ የጀግኖች አባቶቻችንን ትኩስ ትንፋሽ ያውሰን፡፡ ለክብራችን መቆምን ይስጠን፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡
⇑Image: Abiy Ahmed’s legacy; a recently desecrated and crumbled Adwa hero Prince Makonnen Woldemichael Gudisa’s historical equestrian statue in Harar, a city in Eastern Ethiopia, has turned into a street side barbeque kitchen. Photo from Ras Awash on Facebook Timeline, Feb. 27, 2021.
Filed in: Amharic