ብልፅግና መሪውን «ሸጦ» ምን ያተርፋል?
በፍቃዱ ሀይሉ
ብዙዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ሰው ተክለ ቁመና ተደግፈው የሚቆሙ ናቸው። ብዙዎቹ የፓርቲዎቹ ደጋፊዎችም ፓርቲዎቹን የሚከተሉት ሊቀመንበሮቻቸውን ብለው ነው። ለዚህም ይመስላል ፓርቲዎቹ ሊቀመንበሮቻቸውን እንደዋዛ አይቀይሩም፤ የሊቀመንበር ለውጥ ጉዳይ ፓርቲዎችን ይሰነጥቃል። ብዙዎቹ በአንድ ወቅት ጠንካራ ይመስሉ የነበሩ ፓርቲዎች መሪዎቻቸውን በአንድም በሌላም መንገድ ካጡ በኋላ ግርማ ሞገሳቸውን ያጣሉ ወይም ይከስማሉ። ብልፅግና ፓርቲም እንዲህ አንድ ሰው ላይ መንጠልጠልን መርጧል፤ ምን ያህል ያዋጣዋል?
ብልፅግና ፓርቲ ዐቢይ አሕመድን በየሰበብ አስባቡ ለማንገሥ ሲፍጨረጨር ማየት የተለመደ ነው። በተለይ ከመስከረም ወዲህ የለየለት የአንድ ሰው ተክለ ቁመና ግንባታው ተጧጡፎ ቀጥሏል። በምርጫው መራዘም ምክንያት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥልጣን መስከረም ላይ ያከትማል የሚል ክርክር በመነሳቱ ምክንያት የአዲስ አበባ ወረዳዎች ደጃፍ ላይ “ምርጫችን አንተው ነህ” ብለው ለጥፈው ነበር። ብልፅግና ከኢሕአዴግ በወረሰው ባሕል መሠረት ለፓርቲ እና መንግሥት መለያየት እምብዛም አይጨነቅም። የሚገርመው የመንግሥታቸው ሥልጣን መስከረም ላይ ያከትማል የሚለው መከራከሪያ አንድ ዐቢይ አሕመድን ብቻ የሚመለከት አይደለም። ነገር ግን ከፍተኛ ሕዝባዊ ድጋፍ ያላቸው እርሳቸው ናቸው በሚል ፓርቲያቸው እሳቸውን ብቻ ዒላማ ያደረገ ጥቃት እንደተሰነዘረ በማስመሰል እሳቸውን የማግነኑን ሥራ በተጋነነ መልኩ ገፍቶበታል።
የምርጫውን መቃረብ አስታኮ ይመስላል፣ ፓርቲው በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎችም “ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የድጋፍ ሰልፍ” ጠርቶ ነበር። የብልፅግና ደጋፊ ሚዲያዎች “ሰዎች በራሳቸው ፈቃድ የወጡበት” ብለው ያወደሷቸው እነዚህ ሰልፎች ላይ ፎቷቸው ላይ አወዳሽ ጽሑፎች ታትመው አደባባይ ወጥተዋል።
ከሰሞኑ ደግሞ የብልፅግና ደጋፊዎች እና መሪዎች የትዊተር ዘመቻዎችን እያቀላጠፉ ነው። ከትላንት በስቲያ ምሽት ላይ በነበረው ዘመቻ ከተመረጡ ሀሽታጎች መካከል አንደኛው #DrAbiyIsCleaningTPLFMess፣ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሕወሓትን ቆሻሻ እያፀዱ ነው እንደማለት። ምንም እየተሠራ ይሁን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብቻቸውን ጠቅልለው እንዲወስዱት ማድረግ የኋላ ኋላ ፓርቲውን ያከስረዋል።
ዝና ምን ያህል ይታመናል?
ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ ሳር ቅጠሉ አወድሷቸዋል። ከማኅበራዊ ሚዲያ እስከ ታክሲ እና ባጃጆች ፎቷቸውን አጊጠውበት ነበር። እንደ መሲሕ የቆጠሯቸው አሉ። አንድ ነገር እንዳይሆኑ የሳሱላቸውም ነበሩ። እየሰነበቱ ሲሔዱ ከፊሎች ብቻ እምነታቸውን አጠናክረው ሲቀጥሉ፣ ከፊሎቹ የፖለቲካው ጡዘት አስፈርቷቸው ሒሳዊ ድጋፍ እየሰነዘሩ የፖለቲካውን መጨረሻ ሲጠባበቁ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ጠንካራ ነቀፋ እየሰነዘሩባቸው ነው። አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው። የዐቢይ አሕመድ ዝናና ተቀባይነት ከቀደመው ግዜ እጅግ አሽቆልቁሏል።
የብልፅግና ወላጅ ኢሕአዴግ በአንድ ሰው ዝና እና ብልሐት ላይ ብቻ ለመንጠላጠል ይሞክር ነበር። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፖለቲካዊ ቁመና ከፓርቲው ቁመና በላይ ገንኖ እንዲወጣ ሲደረግ ነበር። በተለይ ከ1993 የሕወሓቱ «መሰንጠቅ» በኋላ መለስ ዜናዊ ብቸኛው ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ሲወጡ መለስ እንደ መሲሕ ተስለው ነበር። ከ1997 በኋላ የመለስ ዜናዊን ፎቶ በትልልቅ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ በከተማው መሐል ማየት የተለመደ ነበር። እንደ ሕዳሴው ግድብ ያሉ የስኬት የሚመስሉ ዜናዎች ጋር በሙሉ ሥማቸው ተያይዞ እንዲነሳ ያደርጉ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ፓርቲያቸው በቀድሞው ጥንካሬ ቆሞ መቀጠል አልቻለም። ምክንያቱም የሁሉም ስኬት እና ጥንካሬ ብቸኛ መለኪያ ተደርገው የተሳሉት ሰው ከምስሉ ሲጠፉ ፓርቲውን ሰብስቦ የሚያቆየው ሌላ ምክንያት አልነበረም። ይህም ኢሕአዴግን በቀድሞ አካሔዱ እንዳይቀጥል አድርጎ፣ አክስሞታል።
ብልፅግና ተቃዋሚ ቢሆን?
የብልፅግና ፓርቲ መሪ “ፕሬዚደንት” ነው የሚባለው። ይህንን ብዙዎቹ የፓርቲው ደጋፊዎች ያውቃሉ ብዬ መገመት ይቸግረኛል። ፓርቲው የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎችን አክስሞ ራሱን ብልፅግና ፓርቲ ብሎ ከሰየመ በኋላ፣ ያለው አሠራሩ እጅግ ምሥጢራዊ ሆኗል። የቀድሞው ኢሕአዴግ ከሚታማበት ችግሩ አንዱ የተማከለ-ዴሞክራሲ በሚል ሰበብ የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ የወሰነው ጉዳይ በመላ አባላቱ እና በመላ አገሪቱ ያለምንም ቅሬታ ተፈፃሚ እንዲሆን ማድረጉ ነው። አሁን ግን የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ የፓርቲው ፕሬዚደንት ብቻ እስኪመስል ድረስ የውሳኔ ማዕከሉ ደብዛው ጠፍቷል። በቅርቡ የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ባደረገው ስብሰባ የሰማነው አንድ ጉዳይ ቢኖር የፓርቲው አባላት አንድነታቸውን አጥተዋል የሚል ግምገማ እንዳደረጉ ነው።
የብልፅግና ፓርቲ ንዑስ አመራሮች ሐሳባዊ አንድነት እንዳጡ ለመገመት የማኅበራዊ ሚዲያ ኃይለ ቃል ልውውጦቻቸውን ማየት በቂ ይመስላል። ታዲያ እኒህ አንድነት ያጡ ፖለቲከኞችን በአንድነት ያቆማቸው ምንድን ነው ብለን ከጠየቅን የምናገኘው መልስ ገዢ ፓርቲነት የሚለው መልስ አይጠፋንም። ከባሕሪያቱ ተነስቼ ብልፅግና ፓርቲ ተቃዋሚ ቢሆን ኖሮ በጣም ደካማ ተቃዋሚ ፓርቲ ይሆን ነበር ብዬ እገምታለሁ።
የብልፅግና ፓርቲ ንዑስ መሪዎች የሚያስተሳስራቸው የፖለቲካ አጀንዳ ባለመኖሩ ጠቅላይ ሚኒስትርን ዐቢይን ሸጦ ለማትረፍ ሽር ጉድ ማለታቸው ላያስገርም ይችላል። ነገር ግን አዋጭ አይደለም። የአንድን ሰው ፖለቲካዊ ቁመና ላይ የሚገነባ ፖለቲካ መጨረሻው መፍረስ መሆኑ መታወቅ አለበት።