>

አድዋን ስታወሱ ጊዮርጊስን አትርሱ...!!!!  (ታደለ ጥበቡ)

አድዋን ስታወሱ ጊዮርጊስን አትርሱ…!!!!

 ታደለ ጥበቡ

በክብረ ነገሥት መረጃ መሠረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጽላቱ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ13ኛው መክዘ በዐፄ ዓምደ ጽዮን (1307-1336 ዓ.ም.) ነው። 
በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም ውስጥ ለብዙ አመታት የነበሩት አባ ልዑለ ቃል የተባሉ መነኩሴ ከደማስቆ (ሶርያ) ደብረ ይድራስ ከሚባለው ገዳም አምጥተው ለዐፄ ዓምደ ጽዮን እንዳስረከቡና ንጉሡም ቤተ ክርስቲያን እንዳሰሩ፤ ገድሉም ከዐረብኛ ወደ ግእዝ እንደተተረጎመ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከዐፄ ዓምደ ጽዮን በኋላ ከ1422-1425 ዓ.ም. የነገሠው የቀዳማዊ ዳዊት ልጅ የሆነው ተክለ ማርያም (ሕዝብ ናኝ) የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አሰርተው ነበረ። ይኼ ቤተ ክርስቲያን የተሰራው ሰሜን ሸዋ፣ ሞረትና ጅሩ ከእነዋሪ ከተማ አጠገብ “#ደይ” እየተባለ ከሚጠራው  ጠረጴዛማ ተራራ ላይ ሲሆን ቤተ መንግሥቱም  እዚሁ ተራራ ላይ ነበረ። ዛሬም የቤተ መንግሥቱ ፍርስራሽ ይገኛል።
ዐፄ ዓምደ ጽዮን ከአስር በላይ ታላላቅ ጦርነቶችን አድርጓል። አስሩንም ጦርነቶች በድል አድራጊነት ሲያጠናቅቅ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፅላት ተለይቷቸው አያውቅም።
በ1426 ዓ.ም. “ቆስጠንጢኖስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብሎ ተጉለት #ደጎ ላይ የነገሰው የቀዳማዊ ዳዊት የመጨረሻ ልጅ ዘረዓ ያዕቆብ በ1437 ዓ.ም. አሕመድ በድላይን ድል ያደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስን ፅላት ይዞ ነበረ።
ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክም ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም. ወደ አድዋ ሲዘምቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ይዘው ነበረ።
የካቲት 22 ለ23 አጥቢያ ከጧቱ  11:00 ሰዓት አድዋ ላይ ጦርነቱ ጀመረ።ዐበዚህን ጊዜ በጦርነቱ መሀል ድንቅ ተአምር ታዬ። ይኸውም ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ቀስተ ደመና ነው። በቀስተ ደመናው ውስጥ ደግሞ መልኩ አረንጓዴ የሚመስል ጢስ ወጣ። ጢሱም ውስጥ የነጎድጓድ ድምጽ ተሰማ። ታላቅም ሽብር ሆነ። ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ተገለጠ።
ከዚህን በኋላ የኢጣሊያን  ወታደሮች መዋጋት አልሆነላቸውም። መሳሪያ የያዙበት ሰይፍ የጨበጡበት ክንዳቸው ዛለ። በግንባራቸውም ፍግም እያሉ ወደቁ። ምድር ጠበበቻቸው። የኢትዮጵያ አርበኞች ፈጇቸው። የተረፉትንም ማረኳቸው። ቀኑም የካቲት 23 1888 ዓ.ም. ዕለተ ጊዮርጊስ ነበር።
ተርፈው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት የኢጣሊያ ወታደሮችም ከኢትዮጵያ አርበኞች መሀል አንድ ወጣት በነጭ ፈረስ ተቀምጦ ሰራዊታቸውን እንደፈጀባቸው ገለጡ። የድሉ ምንጭም የእግዚአብሔር ሀይልና ኢትዮጵያዊን ለሃይማኖታቸው ለነጻነታቸው የነበራቸው ቀናዒነት እንደሆነ የራሳቸው የኢጣሊያ ታሪክ ጽሐፊ የነበረው ኮንቲ ሩስኒ በሮም አደባባይ መሰከረ።
የኢትዮጵያ ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክም ለፈረንሣዊው ሙሴ ሞንዶን ከጻፉለት የምሥራች ደብዳቤ እንዲህ ብለው ነበር
 የምሥራች በእግዚአብሔር ቸርነት የየካቲት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዕለት ኢጣልያንን ድል አድርጌ መታሁት፡፡ በጨረቃ ሲገሰግስ አድሮ እሰፈሬ ድረስ መጥቶ ገጠመኝ፡፡ አምላከ ኃያላን ረድቶኝ ፈጀሁት፡፡ ደስ ብሎኛል ደስ ይበልህ”
እንደገና መጋቢት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ዐፄ ምኒልክ  ለሩሲያው ንጉሥ ት‘ዛር ኒቆላዎስ 2ኛ በጻፉት ደብዳቤያቸው “እንደ አውሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ጠብ መፈለጋቸውን ሳያስታውቀኝ፣ እንደ ወምበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሰግስ አድሮ ሲነጋ ግምባር ካደረው ዘበኛ ጋር ጦርነት ጀመረ፤ ጥንት ከአሕዛብና ከአረመኔ አገራችን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከእኛ ባይለይ በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረግሁት›› በማለት ድሉ የእግዚአብሔር መሆኑን አስረግጠው ተናግረው ነበር፡፡
Filed in: Amharic