>

‹‹በእያንዳንዱ ዜጋ ልብ ውስጥ የዓድዋ ሐውልት ሊገነባና ሊታተም ይገባዋል››  (ተባባሪ ፕሮፌሰር ተፈሪ መኮንን )

‹‹በእያንዳንዱ ዜጋ ልብ ውስጥ የዓድዋ ሐውልት ሊገነባና ሊታተም ይገባዋል›› 
ተባባሪ ፕሮፌሰር ተፈሪ መኮንን  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም መምህርና የታሪክ ተመራማሪ
(ኢ ፕ ድ ) 
የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምልክት ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር የአሸናፊነት ዓርማ የሆነው የዓድዋ ድል ሐውልት በእያንዳንዱ ዜጋ ልብ ውስጥ ሊገነባና ሊታተም እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም መምህርና የታሪክ ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተፈሪ መኮንን አስታወቁ፡፡
ተባባሪ ፕሮፌሰር ተፈሪ የካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሚከበረውን 125ኛው የዓድዋ ድል በዓልን አስመልክተው በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ የዓድዋ ድል የተገኘው ኢትዮጵያውያን በመካከላቸው የነበረውን የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የአካባቢና የመሳሰሉ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያዊነታቸውን አስቀድመው በቆራጥነትና በጀግንነት ተዋግተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለሀገር ሉዓላዊነትና ነጻነት ሲሉ ከልዩነታቸው አልፈው አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ከምባታ፣ ሐዲያ የመሳሰሉት በአንድ ጉድጓድ ውስጥ መቀበራቸውን የጠቆሙት ተባባሪ ፕሮፌሰር ተፈሪ፤ ያንን በማድረጋቸው አገራችንን ነጻነቷና ክብሯ ተጠብቆ እንዲቀጥል ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
‹‹አባቶቻችን በዓድዋ ያስመዘገቡት አንፀባራቂ ድል ለመላው ጥቁር ሕዝብ፣ ለአፍሪካውያንና ለሌሎችም ጭቁን የዓለም ሕዝቦች አርዓያ ሆነዋል፣ ኢትዮጵያንየነፃነት ቀንዲል አድርገዋታል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ከዚያኛው ትውልድ የሚማረው ብዙ ነገር አለ›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በፍቅር፣ በነጻነትና በክብር የመኖር ሥነ ልቦናና ስሜት እንዳላቸው በዓድዋ ላይ አሳይተዋል ያሉት መምህሩ፤ አባቶቻችን የአገርን ነጻነት በማስጠበቅ ለሌሎችም ተስፋ መሆን የቻሉት በነበራቸው የአገር ፍቅር ስሜት በመነሳሳት መሆኑን ጠቁመዋል።
Filed in: Amharic