>

ለኢትዮጵያችን አርቀን እናስብ!!! (ALARM!!!) - ዶ/ር ኤልያስ ገብሩ አዕምሮ

ለኢትዮጵያችን አርቀን እናስብ!!! (ALARM!!!)

ዶ/ር ኤልያስ ገብሩ አዕምሮ

…አሁን ላይ ያለው የሃገሬ ፖለቲካ እጅግ አደገኛ አካሄድ ላይ ይገኛል። መንግስት አረመኔያዊ ግፍ ዜጋው ላይ ሲፈፀም በቶሎ ባለመድረሱ የአዲስ አበባ ህዝብ ቁጣው ገንፍሏል። በቋንቋና ብሔር ተለይቶ ሰው ሲጠቃ ግን የአሁኑ የቡራዩ ክስተት የመጀመሪያው አይደለም። በሱማሌ ክልል 100,000 ገደማ የኦሮሞ ብሔር ያላቸው ኢትዮጵያውያን መፈናቀላቸውና ብዙዎች መገደላቸው፤ ሲቀጥልም በጅጅጋ ከተማ የሚኖሩ ዜጎች “መጤ ናችሁ!” ተብለው መገፋትና መገደላቸው የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው። ድርጊቱ በጉጂ፣ በሃዋሳ፣ በመስቃን፣ በቀቤና እና ወ.ዘ.ተ… ሲደረግ እንደነበር ማንም አይረሳውም። ንፁህ ወገንን መግደል፣ አካል ማጉደልና ማፈናቀል ተደጋግሞ ተከስቷል። አዲስ አበቤዎች ምን አልባትም የቡራዩ ጉዳይ በልጦ የተሰማችሁ ችግሩን በቅርበት ምስክር ሆናችሁ ስላያችሁት ይሆናል። የወጣችሁት ተቃውሞ ግን እጅግ አስፈላጊ ነው።
    አንድም ሰው ቢሆን “ሃገር አለኝ፤ ሰፈሬ ነው!” ብሎ ተወልዶ ካደገበት ቦታ መብት የለህም ተብሎ መደብደብ፣ መገደልና መባረር የለበትም። ከዚያም አልፎ ሴቶች በገዛ ሃገራቸው ክብራቸው ተገፎ ሲደፈሩ አይቶ ስራውን ለመውቀስና ለመቃወም አንጎል ያለው ሰው መሆን ብቻውን በቂ ነው። ይህንን ስራ የሰሩ ሰዎች እራሳቸውንም ሆነ እንወክለዋለን የሚሉትንም ቡድን አዋርደዋል። ህዝብም ይሄን ድርጊት እንደ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው ተፀይፎ ቢቃወምና ድምፁን ቢያሰማ ሊተኮስበት አይገባም። መንግስትም እያለባበሰ ከማለፍ ይልቅ ቁርጠኛ ውሳኔ ሊወስድና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከዚህ በኋላ ከሚኖርበት ስፍራ በብሔሩና ቋንቋው ምክንያት እንደማይፈናቀል ዋስትና ሊሰጠን ይገባል።
… መካድ በማንችለው ደረጃ በዚህ ዘመን ላይ ያለ ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በብሔር መሰረት ላይ በቆሙ ፓርቲዎች ታቅፎ ይገኛል። ከነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ህወአት፣ ኦነግ፣ ደህዴን እና ግን. 7 ናቸው። በድፍኑ ስናየው የኢትዮጵያ ዋና ዋና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ብሔረሰቦች ደግሞ ኦሮሞ፣ አማራ እና ትግራይ ናቸው። ወደድንም ጠላንም የማንሽረው በእነዚህ ብሔሮች መካከል የሃሳብ ልዩነት አለ። እውነት እውነቱን ስንነጋገር ብዙሃኑ አማራ ንጉስ ሚኒሊክን የኢትዮጵያዊና ጥቁር ህዝብ ታሪካዊ ጀግና ንጉስ ብሎ ያከብረዋል፤ ታማኝ በየነንና ገዱ አንዳርጋቸውን ጀግናዬ ይላል። ይህ የብሔረ አማራ ሃሳብ የማይዋጥለት ብዙሃኑ ኦሮሞ በበኩሉ ንጉስ ሚኒሊክን እንደ አፍሪካ ናዚ አይቶ የአሁኖቹን የኦሮሞ አክቲቪስቶች  ጃዋር መሐመድና በቀለ ገርባ እንዲሁም የኦነግ አመራሩን ዳውድ ኢብሳ ጀግናዬ ብሎ አንግሷል። ወያኔ እያለ ሌላው ቢወቅሰውም ብዙ የትግራዋይ ሰውም ግን መለስ ዜናዊን ይወዳል፤ ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና ዶ/ር አርከበ እቁባይንም ጀግኖቼ ብሎ ይጠራችዋል። ሃሳቡ ሲጨመቅ አንዱ የሚጠላውን ሌላው ይወዳል ማለት ነው። እናም አሁን ያለንባት ኢትዮጵያ እውነታዋ ይሄ ነው። ስለዚህም ከዚህ ክፍፍል ወጥተን ኢትዮጵያዊነትን የምናቀነቅን ሰዎች ይህንን እውነታ በሚገባ መረዳት አለብን። ብሔርን መስደብ፣ ያ ብሔር እንደ “Icon” የሚያያቸውን ሰዎች ማንቋሸሽ እመኑኝ ኢትዮጵያን መቀመቅ ይከታታል እንጂ አይጠቅማትም።
…. ስለዚህም፤ አሁን ላለው ችግር ስር ነቀል መፍትሄ ይሆናሉ ያልኳቸውን 10 ነጥቦች እነሆ!
1ኛ፤ ቡራዩም ላይ ይሁን ሻሸመኔ
ቀቤናም ይሁን ጅግጅጋ ላይ ወንጀል የሰሩ ሰዎች ለህዝብ ይፋ በሆነ መንገድ ፍርድ ያግኙ። (ሰው ገለውና ንብረት አውድመው ፎቷቸውን እንደ ጀብዱ የለጠፉት ግልብ ወንበዴዎች የእጃቸውን ያግኙ!)
2፤ ከላይ ያየናቸውን የሃሳብ ልዩነቶች በመደመር እሳቤ አንድ ለማድረግ ቆሞ የብዙሃኑን ድጋፍ ያገኘውና ሁሉንም ለማስማማት ከማንም በላይ አቅም ያለው ዶ/ር አብይ አህመድና ክቡር ዶ/ር ለማ መገርሳ እና እነ ገዱ አንዳርጋቸው የህዝቡ ብሶት ለከት ማለፉን አውቀው ቆፍጠን ይበሉ፤ የህግ የበላይነትን በተግባር ያስከብሩ።
3፤ ቄሮ ፣ ፋኖና ዘርማን መሰል ተቋማት ህጋዊ መዋቅር ኖሯቸው ለሰሩት ጥሩ ነገር እንዳሞገስናቸው ሁሉ በእነርሱ አርማና መለያ ወንጀል ሲሰራም ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ይሁኑ፤ ጥሩ ቄሮዎች ባህርዳር ድረስ ሄደው እንቦጭ እንደነቀሉት ሁሉ ህዝብን አንድ በሚያደርጉና ለሃገር እድገትም በሚጠቅሙ ነገሮች ላይ እንዲሳተፉ ይደረግ።
4፤ እንደነ ጀዋር አይነት ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች በእነርሱ ስር ባሉ ወጣቶች ስም የተፈፀመውን ድርጊት ያውግዙ፤ ህዝቡንም በይፋ ይቅርታ ይጠይቁ። (ይቅርታ መጠየቅና ለሰላም መቆም ትልቅነት ነው።)
5፤ እውነት ለሀገር ነው የቆምነው፤ ለትውልድም እናስባለን የሚሉ ከሆነ ታማኝና ብርሃኑ ከጀዋርና በቀለ ገርባ ጋር ተቀራርበው በመነጋገር ለህዝብ  አብረው መግለጫ ይስጡ። (እነ ሃጫሉና ቴዲ አፍሮም ግንቡን ያፍርሱ።)
6፤ “ከእንደዚህ አይነት ወንጀሎች ጀርባ እጁ አለ!” የሚባለው አካል እጁ ተጎትቶ ይምጣልንና ፊቱን እንየው። ይህ አካል እውነትም ካለ ነፍሰ ገዳይና ሃገር አጥፊ ነውና ለመቅጣት መለሳለስ አያስፈልግም።
7ኛ፤ ከቡራዩም ይሁን ከሌላ የኢትዮጵያ ስፍራዎች ለተፈናቀሉ ሰዎች እየተደረገ ያለው እርዳታ ተጠናክሮ ይቀጥል። በፍጥነትም ወደ ቦታቸው ተመልሰው፣ ደህንነታቸው ተጠብቆ የሚኖሩበት ሁናቴ ይመቻች።
8፤ ተቃውሞ በሰልፍም ይሁን በፌስቡክ የምናደርግ ሰዎች ብሔርን ለይቶ የሚያጠቃ ስድብና ነቆራችንን እናቁም። (እንደዛ የሚሳደብ ጋጠወጥ አካውንት ያለው ሰው ሲያጋጥመንም በብሎክ እናሰናብተው።)
9፤ እንዋደድ፣ እንፋቀር፣ ሥለ ሀገር ህልውና ከስሜታዊነት ወጥተን አርቀን እናስብ። ያለፈውን ነገር እያነሳን “እኔ እንዲህ ሆኛለሁና ሌላውም ይቅመሰው” የሚል አስተሳሰብ እናፍርስ።
10፤ ውጊያው የስጋ ብቻ ሳይሆን የመንፈስም ነውና በፀሎታችን እንበርታ፤ በዱዓችን እንታገስ። የኢትዮጵያን አምላክ ሳናሰልስ እንጠይቀው!
.         .
… ይህ ካልሆነ ግን በዲሞክራሲ ስም የህፃናት ደም እንደ ጎርፍ እንደፈሰሰባቸው፤ የእናቶች ዋይታ ሰሚ እንዳጣባቸው፤ ከተሞች ከነውብ ፎቃቸው ወደ ትብያነት እንደተቀየሩባቸው፤ ፎቶው ላይ እንዳሉት የአረብ ሃገራት ሊያደርገን የሚችል የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ልንገባ እንደምንችል አርቆ ማሰብ ያስፈልጋል። ብልህ ሰው ከጎረቤቱ ይማራል! እነርሱም ከጥቂት አመታት በፊት በሰላም ይኖሩ የነበሩ ህዝቦች መሆናቸውንም አንዘንጋ። እባካችሁን ብሔር ሳልለይ ልለምናችሁ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም አርቀን እናስብ፤ ለልጆቻችን ቂም በቀልና ጥላቻን አናውርስ። “እኔ ብዙ ነኝ!… እኔ የጀግና ልጅ ነኝ! እኔ ጉልቤ ነኝ!” ብሎ ነገር አያዘልቀንም። የሃገርህን ሰው መግደልም ይሁን ጉልበትህን ማሳየት ደግሞ ጀግንነትን ሳይሆን አላዋቂነትን ነው የሚያሳያው።
… አንድነታችን ብቻ ነው ሚያዋጣን!!
Filed in: Amharic