>

"የምንታገለው በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚያጭበረብረውን ሃይል ነው...!!!" - የባልደራስ የፖለቲካ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻ

“የምንታገለው በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚያጭበረብረውን ሃይል ነው…!!!”

የባልደራስ የፖለቲካ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻ
አዲስ አድማስ

 “ባልደራስ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ድምጽ ለመሆን ነው”
• የታሰሩ መሪዎቻችንን ዓላማ ለማሳካት የበለጠ እንታገላለን
• አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናት የሚልን አስተሳሰብ ነው

ዋነኛ ትኩረቱን አዲስ አበባን ራስ ገዝ ወይም ክልል ለማድረግ አልሞ የሚንቀሳቀሰው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ)፤ ለቀጣዩ አገራዊ ምርጫ የሚያደርገው ዝግጅት ምን ይመስላል? አላማና ግቡ ምንድን ነው? በምርጫ ዝግጅት ወቅት  የገጠሙት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? በምርጫው ቢያሸንፍ ምን ለማድረግ አስቧል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ  የፓርቲውን የፖለቲካ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻን፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

 ባልደራስ የተቋቋመው በምን አላማ  ነው?
እንደሚታወቀው ለውጡ ከመጣ ሶስት ዓመት ሊሞላው  ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ይነሱ የነበሩ  የልዩ ጥቅምና  ተያያዥነት ያላቸው ጥያቄዎች፣ በከተማው ነዋሪ ላይ ስጋት ፈጥረውበት ነበር፡፡ ያንን ስጋት እንደ አማራጭ የፖለቲካ ሃይል፣ ለመቅረፍና የአዲስ አበባ ድምጽ  ለመሆን ነው ባልደራስ  የተቋቋመው፡፡
ቀጣይ ግቡ ምንድን ነው? ምን ለማግኘት ነው የሚንቀሳቀሰው?
በዋናነት የከተማው ነዋሪ ራሱ በመረጠው አስተዳዳደር እንዲመራና የራሱ የፖለቲካ ሥልጣን እንዲኖረው ነው የሚታገለው፡፡ ከዚያ አልፎ ከተማ አስተዳደሩ የሚያስተዳድረው ግዛተ መሬቱ ሊከበርለት ይገባል፡፡  አዲስ አበባ ማንም ልዩ ጥቅም የማይሰጥበትና ማንም ልዩ ጥቅም የማይቀበልበት  መኖሪያ እንድትሆን ነው ዋነኛ ግቡ፡፡
“ግዛት መሬቱ ሊከበርለት ይገባል” ሲባል ምን ማለት ነው?
የኛ ግልጽ አቋም አዲስ አበባ ራሷን የቻለች ክልል ትሁን ነው፡፡ ክልል የማድረግ ዋነኛ ዓላማ ይዘን ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ ክልል ሆና ፌደራል መንግስቱ መቀመጫ ሊያደርጋት ይችላል፡፡ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም ዋነኛ መቀመጫቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡ ክልል ሆና ራሷን በራሷ ታስተዳድር ነው፤ የፓርቲያችን አቋም፡፡
የአዲስ አበባ ግዛተ ወሰን የምትሉትና በእናንተ በኩል የምታቀርቡት የቱን  ነው?
የአዲስ አበባ ከተማ መስራቾች ከተማዋን ሲመሰርቱ ለብዙ ነገር ነው ያሰቡት። ለኢኮኖሚ እንዲመች፣ ለማህበራዊና ለፖለቲካዊ ሁኔታ ፋይዳ እንዲኖረው፤ ከዚያም አልፎ ራሱን በራሱ ማስተዳደር በሚችልበት አግባብ መሰረት ነው ያዋቀሩት፡፡ አዲስ አበባ መጀመሪያ ላይ ሰበታን፣ሱሉልታንና አቃቂን ጨምሮ ያካተተ ነው፡፡ እኛ በሚገባ የድሮ የግዛት ወሰን ካርታ አቅርበናል፡፡ ኦሮሚያ የሚባል ግዛት እኮ ከዚህ ቀደም አልነበረም፡፡ ትናንት ኦነግና ህወኃት የፈጠሩት ነው፡፡ አዲስ አበባ ግን ከጥንትም የነበረ ነው፡፡ ካርታውም ወሰኑም ተቀመጧል፡፡ ኦሮሚያ ከ83 በፊት አልነበረም፤ አዲስ አበባ ግን ነበር፡፡ ካርታውም በሚገባ ተሰርቶ የተቀመጠ ነው። ጣልያን ሳይቀር ግዛቷን በሚገባ አካሎ፣ ማዕከሉ አድርጓት ሲያስተዳድር ነበር፡፡ አዲስ አበባ ለኢኮኖሚ ታስቦ የገጠር መሬት ሁሉ ነበራት፡፡ ገበሬዎች ነበሯት፡፡ እኛም እነዚህ ግዛቶቿ የተከበሩላት የአዲስ አበባ  ክልልን እውን ለማድረግ ነው የምንታገለው።
ፓርቲያችሁ ምን ዓይነት ርዮተ ዓለም ነው የሚከተለው? የፖሊሲ ዝግጅቶቹስ ምን ይመስላሉ?
እኛ በቀኝ ዘመም የፖለቲካ  አስተሳሰብ ነው የምንመራው፡፡ ገበያ መር የኢኮኖሚ መንገድ ነው የምንከተለው፡፡ ባለሃብት ግለሰቦች በንግድና ኢንቨስትመንቱ ሙሉ ድርሻ እንዲኖራቸው፣ መንግስት ጠቃሚ በሆነ ዘርፍ ላይ ብቻ እንዲገባ የሚል ሃሳብ ይዘን ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ ፖሊሲዎችንም የቀረጽነው በእነዚህ መሰረቶች ላይ ነው፡፡
አዲስ አበባ ላይ መሰረት አድርጋችሁ የምትንቀሳቀሱ እንደመሆናችሁ፤ ለአዲስ አበባ የተለየ የቀረፃችሁት የፖሊሲ አማራጭ ምን ይሆን?
እኛ አዲስ አበባን የምንረዳት እንደ አንድ የአስተዳደር ዋና ከተማ ብቻ አይደለም። የአፍሪካ መዲና ነች፡፡ ከአፍሪካ መዲናነት አልፋ በአለምም ከጥቂት ከተሞች መካከል የምትጠቀስ ነች፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ብቻ ሳትሆን የአለምም ከተማ ነች፡፡ ሰፊ ሃብት ያላት ከተማ ናት፡፡ ንግድ አንዱ ነው፡፡  ለቱሪዝም  የሚጋብዝ ሙሉ መስብህ የተቸራትና “ኑ ጎብኙኝ” ብላ የምትጣራ ከተማ ናት፡፡ ከዚህ አንጻር አዲስ አበባ መጠቀምም ባለባት መጠን መጠቀም አለባት፡፡ ነዋሪዎቿም ከዚሁ መጠቀም አለባቸው፡፡ ከተማዋ የተለያዩ ባህሎችንና ትውፊቶችን የምታንጸባርቅ ጭምር ናት፡፡ ስለዚህ የእኛ የፖሊሲ ቅኝት  ከዚህ አንጻር የሚታይ ይሆናል፡፡ ፖሊሲያችንን እያዘጋጀን ያለነውም ከዚሁ መነሻ ሲሆን በአገር ውስጥም በውጭም ያሉ፣ ሰፊ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ነው፡፡
የምርጫ ተሳትፎአችሁ በአዲስ አበባ ላይ ብቻ የተወሰነ ነው ወይስ….?
እኛ አዲስ አበባ መሰረታችን ይሁን እንጂ ውድድሩን የምናደርገው በመላው ሃገሪቱ ነው፡፡ አሁን ከመኢአድ ጋር የጀመርነው ጥምረት አለ፡፡ እሱ ሲቋጭ ሰፊ መሰረት ይዘን መንቀሳቀስ ያስችለናል፡፡ ከሌሎች ጋርም የጀመርናቸው የጥምረት እንቅስቃሴዎች በሂደት ላይ ናቸው፡፡ እነሱ ውጤታማ ሲሆኑ ሰፊ መሰረት ይዘን እንቀሳቀሳለን። እንደ ዘመናዊ ከተማ የፖለቲካ ፓርቲ  ደግሞ  ደረጃውን የጠበቀ፣ የሰለጠነ የምርጫ እንቅስቃሴ እንከተላለን፡፡ ከዚህ አንጻር ነገ እሁድ ለየት ያለ የምርጫ ቅስቀሳ ታላቅ የመክፈቻ ፕሮግራም ይኖረናል፡፡
ፓርቲያችሁ በዚህ ምርጫ ምን ውጤት ለማግኘት ነው ያለመው?
የመጀመሪያው፣ በአዲስ አበባ ም/ቤት ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ፤ በፓርላማ ያሉትን የአዲስ አበባ ወንበሮች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚያስችለንን አደረጃጀትና ሰፊ ዝግጅት አድርገናል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ማሸነፍ የመጀመሪያ አላማችን ሲሆን፤ ጎን ለጎን ግን ያንን ማስፈጸም የሚያስችለንን አቅም ለማግኘት ቢያንስ በደቡብ፣ አማራ ክልልና በድሬደዋ ከእኛ ጋር መስራት ከሚችሉ ጋር እየተባበርን አብረን እንሰራለን፡፡ አዲስ አበባ ላይ ለፓርላማው 23ቱም ወረዳዎች ላይ እጩዎች አቅርበናል፡፡ ለአዲስ አበባ ም/ቤት ደግሞ 138ቱም ላይ በቂ እጩዎች አዘጋጅተናል፡፡
የፓርቲው ሊቀ መንበርና ሌሎች አባላት መታሰር በዚህ ምርጫ ላይ ያለው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው? እንዴት ልትወጡት አቅዳችኋል?
የመሪዎቻችን መታሰር በጣም ያስቆጨናል፤ በአስቸኳይ እንዲፈቱም እንፈልጋለን፡፡  ከእስር እንዲፈቱ  በተለያየ አግባብ ትግል እናደርጋለን፡፡ በዚህ መሃል በዋናነት እነሱ ይዘው የተነሱት አላማ አለ። ያንን አላማ ከግብ ማድረስ ነው ትልቁ ትኩረታችን፡፡ ምክንያቱም የታሰሩበትም አላማ ይሄው ነው፡፡ ግንባራችንን ሰጥተን የታሰሩለትን አላማ ከግብ ለማድረስ እንቀሳቀሳለን፡፡ ነገር ግን የመሪዎቻችን መታሰር ጎድቶናል፡፡ ያንን ጉዳት ተቋቁመን፣ በበለጠ እልህ አላማቸውን ለማሳካት እንታገላለን፡፡ በዚህ መርህ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡
አዲስ አበባ ላይ ዋነኛ ተፎካካሪያችሁ ማን ይሆናል ብላችሁ ታስባላችሁ?
እኛ ተፎካካሪ አለን ብለን አናስብም። ምክንያቱም አላማችን ራሱ የተለያየ ነው። እኛ ሪፈረንደም  (ህዝበ ውሳኔ) ነው የምናደርገው ብለን  እናምናለን፡፡ የኛ ጥያቄ የሪፈረንደም ነው፡፡ መሰልቀጥ ወይም ተቻችሎ በጋራ የሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን  ገንብቶ  የማለፍ አማራጮች ቀርበው፣ ህዝበ ውሳኔ የሚሰጥበት እንዲሆን ነው የምናስበው፡፡ እኛ በዚህ ደረጃ ተፎካካሪ አለን ብለን አናስብም፡፡  ጉዳዩ የሪፈረንደም (ህዝበ ውሳኔ) ነው፡፡
የመሰልቀጥ ስጋት አለ ብለዋል፡፡ ማን ነው ሰልቃጩ?
“አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት” የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናት የሚለውን እውነታ የሚክድ ነው፡፡ ይህንን አስተሳሰብ ነው ሰልቃጭ የምንለው፡፡ እኛ የምንታገልለት #አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናት; ለሚለው አስተሳሰብ ነው፡፡
በቅርቡ በኦሮሚያ በተጠሩ የጠ/ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፎች ላይ ስማችሁ በክፉ ተነስቷል፡፡ ከአካባቢው የኦሮሞ ህዝብ ጋርም ግጭት ውስጥ እንደገባችሁ ተደርጎ ሲነገር ተሰምቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ  የእናንተ ግምገማ ምንድን ነው?
ይሄ አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ እንደ ህዝብ፣ ከኦሮሙማ የሰልቃጭነት አስተሳሰብ ጋር አይገናኝም፡፡ ህዝቡ አንድን አካል ካልዘረፍኩ፣ ካልበዘበዝኩ አይልም። ከዚያ ይልቅ የፖለቲካ ስልጣን ላይ ወጥተው በስልጣናቸው ተጠቅመው፣ መሬቱን ለመዝረፍ የሚፈልጉ ናቸው ግጭት ውስጥ ሊገቡ የሚችሉት እንጂ ህዝቡ ከእኛ ጋር ግጭት የለውም፡፡ ካድሬዎች ግን አዎ ይጋጩናል፡፡  እኛም የምንታገለው እነዚህን ሀሳቦች ይዘው የሚንቀሳቀሱትን ነው፡፡ ስለዚህ ከህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ቅራኔ የለንም፤ አይኖረንምም፡፡  ከዚህ በፊት በትግራይ ህዝብ ስም  የሚያጭበረብር ቡድን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚያጭበረብር ሀይል አለ፡፡ ያንን ሀይል ነው የምንታገለው፡፡
በቀጣዩ ምርጫ  ዋናው ፈታኝ ሁኔታ የምትሉት ነገር  ምንድን ነው?  ጠ/ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ነፃ  ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ  ለማካሄድ ቃል ገብተዋል፡፡ በተግባር ይፈፀማል የሚል እምነት አላችሁ?
ጠ/ሚኒስትሩ የሚሉት እዚህ ሳይሆን አሜሪካ ያለውን ዲሞክራሲ ነው፡፡ እሳቸው ለመሰልቀጥ የሚደረግን እንቅስቃሴ በቃላት እያስመሰሉ፣ ሌላውን በባዶ እጅ ለማስቀረት የሚያደርጉት ነገር፣ የተነቃበት ነው፡፡ እኛ ሁሉም ገለልተኛ ናቸው ስላሉን አንታለልም።
በምንም ሁኔታ ወገባችን አይጎብጥም፤ ግንባራችን አይፈታም፡፡ ምክንያቱም መራራ ትግል ላይ ነን፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የሚገጥመንን ፈተና አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
በምርጫው ከቀናችሁና የአዲስ አበባ ም/ቤትን ከተቆጣጠራችሁ የመጀመሪያ ተግባራችሁ ምን ይሆናል?
የመጀመሪያ ስራችን አዲስ አበባ፣ የአዲስ አበባውያን መሆኗን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይሄም በአዲስ አበባ ህዝብ  ድምጽ ይረጋገጣል፡፡ ከዚያ በኋላ ክልል እንድትሆን እናደርጋለን። ለዚህም በየደረጃው እንቅስቃሴ ወደ  ማድረጉ በቀጥታ እንገባለን ማለት ነው፡፡

Filed in: Amharic