>

የአድዋ ድል  ብሎ ነገር የለም፤አልነበረምም።   ኢትዮጵያ የት ሄዳ? (ዐቢይ ኢትዮጵያዊ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ)

የአድዋ ድል  ብሎ ነገር የለም፤አልነበረምም።   ኢትዮጵያ የት ሄዳ?

  ዐቢይ ኢትዮጵያዊ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ


ይህ የ”አድዋ ድል”ብሎ የመጥራት ስያሜ ላለፉት አርባ አራት ዓመታት የተለመደ ሲሆን አባባሉ በፍጹም ስህተት ነው፤በግድፈቱ የተፈፀመው ጥፋት ደግሞ ሆን ተብሎ እና የተንኮል ሴራ መሆኑን፤ወደ ውስጥ ስንመረምረው፣በተጨባጭ ሐቅ እናረጋግጣለን።ይህንንም ያልኩበት ምክንያት ጉዳዩ የስያሜ ብቻ ሳይሆን፤በፖለቲካዊ መሰሪነት በአድዋ ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን የተቀዳጀነውን የአሸናፊነት ውጤት፣አገራዊ ዋጋ ለማሳጣት እና የጉዳዩን ባለቤትነት ቀስ በቀስ የሚሸረሽር አገላለጽ ስለሆነ ነው።

    የ”ኢትዮጵያ ድል” ከአድዋ ጦርነት የተገኘ ነው ስንል፤ምሥክራችን ደግሞ በነገረ-ነፍስ ታሪክ እና ዕውነት ናቸው።የጦርነቱ ባለቤት የሆነው አካል ምንጊዜም የሽንፈቱም ሆነ የድሉ ባለቤት እርሱ ብቻ ነው የሚሆነው።ከዚህ መሠረታዊ ሐቅ ተነስተን ተንትነን ስንመለከተው የጦርነቱ ባለቤት በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ስትሆን፣በዚያ በኩል ደግሞ የሮማው ሥርወ-መንግሥት ነው፤የሚገጥሙትም ሁለቱ አገሮች ናቸው።ምክያቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአገርነት የተመዘገቡት ለጦርነት የተፈላለጉት ሁለቱ አገሮች ናቸው፤የጦርነታቸውም መነሻ ሰበብ በቆዳ ልዩነት የበላይ የመሆን ፍላጎትና ጉልበትን የመጠቀም ውርደት ነው።ስለጣሊያን ወረራ እና የኢትዮጵያዊነት ድል ብዙ የተነገረ ስለሆነ ዝርዝሩን ደግሞ እዚህ ማንሳቱ አስፈላጊ አይደለም።
በዚህም   ምክንያት ስያሜው ከተፋለሰ ትርጓሜው ሌላ አቅጣጫ ይይዛል፤ለምሳሌ በአድዋ ጦርነት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መስዋዕት የከፈለበት ውጊያ ነው።በዚህ የሐቅ እይታ ውስጥ ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ፤ኢትዮጵያውያን እና የሌላው አገር ሰዎች።ታዲያ ሁለቱም የሕብረተሰብ አካላት ኢትዮጵያውያን በአድዋ ጦርነት ላይ ያገኙትን ድል ያለአድራሻው ሲጠሩት ይሰማል።ይኸውም አድዋ በትግሬ ክፍለ ሐገር የሚገኝ አውራጃ ሲሆን፣የሮማውያኑ የመጨረሻ የሽንፈት መቃብራቸው ማረጋገጫ ቦታ ነው እንጂ ከኢትዮጵያን ግዛት ፈርጥጠው እስኪወጡ አልተለቀቁም።
ስለዚህ የአድዋው ጦርነት(the battle of Adowa)የኢትዮጵያን ድል (Ethiopian Victory)ውጦ በጦርነት ስም ከአርባ አራት ዓመታት በላይ፤የአድዋ ድል ሲባል ፣ታሪኩን ያረሳሱ መስሏቸው ነበር።የዛሬ ስምንት ዓመታት በእነ መሐመድ ካሳ የተጀመረው የአድዋ ጦርነትን አሸናፊነት እና የኢትዮጵያን የድል በዓል ማክበር እንደገና ተጀምሮ ይኼው በመቶ ሃያ አምስተኛው ዓመታት የኢትዮጵያ የድል በዓል ላይ በማይታመን ሁኔታ ሱሰኛ የተባለው የኢትዮጵያ ወጣት፣በዕምነቱ በርትቶ ቤተክርስቲያን እና መስጊድ እየተሳለመ ወደፈጣሪው ሲመለስ ተዓምር ታይቷል።ከዚህም በእነሰርፀ በጥናት ከመቃብሮቹ ተፈልቅቀው እንዲናገሩ የተደረጉም መረጃዎችም እየተግተለተሉ መሆኑን በዐይናችን ስናይ እጅግ የሚበረታቱ መሆኑን እንረዳለን።
በተለይም በመምህር ሰረፀ ፍሬስብሃት የተሰባሰቡት የዕውቅ ምሁራን ሰነዶች ለምርምር ስራዎቻችን ከፍተኛ አስተዋጾ ይኖራቸዋል፤በዘመኑ ከነበሩ አዋቂዎች መምህር ጽጌ፣በዘመናችን ከነበሩት መካከል ደግሞ እንደነጋድራስ ኃይለየሱስ፣እንደ አፈወርቅ ገብረየሱስ፣ከታሪክ መጽሃፍ ከሰበሰቡትም እንደኡስታዝ አቡበከር ያሉ፣ፕሮፌሰር ዓበባው፣ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ፣ብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል፣ ፕ/ሮ ስርገወ  ሀብለ ስላሴ
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፣ እኛን ወግነው ደግሞ የአድዋን ጦርነት አሸናፊነት ይገልጻሉ፤ጆርጅ በርክሊ ግን በነገረኝነቱ የታወቀና ከጦርነቱ የሚያገኙትን ድሎች በባለሙያ እንዲዘግብ ለማድረግ የተመረጠ ነው።
ታዲያ ጋዜጠኛው ጆርጅ በርክሊ ሂስቶሪያን እና  የኢትዮጵያን ድል ገና ከጠዋቱ የአድዋ ጦርነቱ ሳይጠናቀቅ በትክክል ገምግሞ ቀጣይ ሴራውን በጋዜጣ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መርዶውን ያወጣው ሰው እርሱ ብቻ ነው።ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ከቅንነታቸው የተነሳ በከይሲዎች ይጠለፋሉ።
ለምሳሌ የውጫሌውን ውል ተፈራራሚዎች ሁለቱም ትርጉም ለሁለቱም ወገኖች ነው የሚደርሳቸው አምኖ ከመሰረቱ መቀበል ስህተት ላይ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል። ከነዚህም አንዱና በማንም ተነስቶ የማያውቀው ከድላችን በኋላ የተጠነሰሰልን ሴራ ኢትዮጵያን የድሉ ባለቤትነቷን ሥያሜ ለማሳጣት የሚደረገው ሚሥጥራዊ የመፈቅፈቅ ዘመቻ ነው።ዘመቻውም ሲታይ ዘመቻ በፍጹም አይመስልም፤በጣም አጉልቶና አርቆ ለሚያስተውል ግን ፥በሎጎ፣በተንቀሳቃሽ ምስልና በፎቶ ግራፎች፣በበራሪ ወረቀቶች በሌሎችም የኪነ ጥበብ ዘርፎች ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን የባለድል ስያሜ:- በተዘዋዋሪ መንገድ ኢትዮጵያ ስሟ እንዳይነሳ በሚፈልጉ በተለይም ባለፉት ሃያሰባት ዓመታት የተሞከረው ጥፋት ከግምት ውስጥ ገብቶ እና ኢትዮጵያ ብዙ ጠላቶች እንዳሏት ልብ ተብሎ፤ሴረኛው ኢጣሊያዊ ጋዜጠኛ ጆርጅ በርክሊ የአድዋ ድል የሚለው ጥገኛ ሐረግ ፍጹም ሆን ተብሎ የተሰራጨና የኢትዮጵያን ሥም ለማደብዘዝ የተደረገ መሆኑ ታውቆ በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል።
በአንጻሩም መባል ያለበት ያኔውኑ ከአድዋ ጦርነት በኋላ ሜጆር ፐርሃም እንደዘገበው የኢትዮጵያ ድል የተገኘው ከአድዋ ጦርነት መሆኑን በመግለጽ ነው፤የውጤቱ ባለቤት         የጦርነቱ ባለቤት መሆኑን በመግለጽ የሽንፈቱም ሆነ የድሉ ባለቤት፣እንደውጤታቸው የሮም እና የኢትዮጵያ መንግስታት ናቸው፤በዚህም መሰረት ሮም ሽንፈቷን ጠቅልላ ስትፈረጥጥ፣ኢትዮጵያም የድሏን ዋንጫ ከእግዚአብሔር ተቀብላለች።
ነገር ግን ፖለቲከኛውና ሴረኛው ኢጣሊያዊ ጋዜጠኛ ጆርጅ በርክሊ ሽንፈቱን ተቀብሎ “የአድዋ ድል” የሚለው
 የጥገኛ ሐረግ መርዝ ጥሎብን ሄዷል፤ ለኢትዮጵያ የድል ታሪክ ግን ተገቢም አይደለም መባልም የለበትም ምክንያቱም፦
፩ኛየጦርነቱ ባለቤት ኢትዮጵያ እንጂ አድዋ አይደለም፤ጎጃም ላይ ጠላት ቢሸነፍ የጦርነቱ ቦታ ይገለጽ እንጂ ድሉ በማን ሊጠራ ነው በባለቤቱ ብቻ።
፪ኛ በተለይ የአድዋን ጦርነት በጥልቀት ስንመረምር ድፍን ኢትዮጵያዊያን በቀጥታ የተሳተፉበትና የተሰዉባት ጦርነት በግልጽ ይታወቃል።የአክሱም ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው እንዳለው ጎጠኛ መልስም የሰጠው ምሁር አልሰማሁም፤ምናልባት የብረት ባለቤት ስለሆነ ጦሜን ልደር ብለው ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ፣በአሁኑ ጊዜ ተራ ማንነታቸው በአደባባይ በውጊያ እንደተጋለጠው፤እናም የኢትዮጵያዊነት መቀነቱ ነው፣ከታሪክ አለማወቁ እንጂ ኣኮሱም ላይ የነበሩት የተለያዩ የኢትዮጵያ ጎሳዎች እንደነበሩ ቢታወቅም አገዎችን የሚቀድም አልነበረም፤ስያሜውም ኣገውኛ ነው።
፫ኛ በተለይ የባንዳ የልጅልጆች በኢትዮጵያ እና በዓለም ላይ የተዘሩና እነርሱም ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው የድላችንን ስያሜ እንዳያጨማልቁት መንገድ ላለመክፈት ነው፤በተለይ የኣኮስምን ስያሜ ስናጠና የአገው እንደነበረና ትርጉሙ የውሀ ሹም ማለት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
፬ኛ ለሌሎችም የኢትዮጵያ ድሎች ምዝገባ በቂ የሆነ የታሪክ ጥበቃ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስገንዘቢያ ምሳሌ ስለሆነ ነው።
ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ድል በኢትዮጵያውያን የተገኘ በአድዋ እና በሌሎችም የጦርነት ቀጠናዎች መሆኑ ቢታወቅም የአድዋ አውራጃ ድርሻ የጦርነቱ መቃብር ብቻ ነው፤የኢትዮጵያውያን ድርሻ ደግሞ ድሉ ሲሆን አጠራሩም በሐቅ ላይ የተመሠረተ የባለቤትነት ውጤት ነው። 
Filed in: Amharic