>

"ካ ራ ማ ራ...!!!" (ዳንኤል በቀለ)

“ካ ራ ማ ራ…!!!”

ዳንኤል በቀለ

በ1966 ዓ.ም ሶማሊያ የአረብ ሊግን ተቀላቀለች። በወቅቱ የሶማሊያ መሪ የነበረው ሜጀር ጄኔራል ሲያድ ባሬ ኢትዮጵያን ወረረ። ጦርነቱ የተጀመረ ሰሞን የሲያድ ባሬ [ዚያድ ባሬ] ጦር በሶቪዬት ኅብረት ይደገፍ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ከዩናይትስ ስቴትስ ጋር ወዳጅነት አለው። በወቅቱ በቀዝቃዛ ጦርነት ውስጥ የነበሩት ሶቪዬት ኅብረትና አሜሪካ ምሥራቅ አፍሪካ ገቡ።
ፕሬዝደንት አብዲራሺድ አሊ ሸርማርኬን በመንፈቅለ-መንግሥት ፈንግሎ ሥልጣን የጨበጠው የዚያድ ባሬ መንግሥት ድንበር ማስፋፋት ዋነኛ ዓላማው አደረገ። ወሳኟ ቦታ ደግሞ – ኦጋዴን።
ኦጋዴን ሠፍሮ የሽምቅ ውጊያ ያካሂድ የነበረው የምዕራብ ሶማሌ ነፃ አውጭ ግንባር የኢትዮጵያ ጦር ላይ ጥቃት ሠነዘረ። የጦርነቱ መባቻ ተደርጎ የሚቆጠረውም ይህ ጥቃት ነበር። በመቀጠል የዚያድ ባሬ ጦር በሶቪዬት ኅብረት የጦር መሣሪያ ታግዞ ወደ አጋዴን ገሰገሰ።
በወቅቱ ከንጉሡ አገዛዝ ወደ ወታደራዊው ደርግ የተሻጋገረችው ኢትዮጵያ በይፋ ራሷን ማርክሲስት ስትል አወጀች፤ ወዳጅነቷም ከሶቪዬት ኅብረት ጋር ሆነ። አሜሪካ ደግሞ ድጋፏን ለሶማሊያ አደረገች።
ሁለቱ አገራት ወደ ቀለጠ ጦርነት ገቡ። በወቅቱ የሲያድ ባሬ መንግሥት ኩባውያን የኢትዮጵያውን ጦር ደግፈው እየተዋጉ ነው ሲል ወቀሰ። ይህንንም ለማሳመን ሲሉ የኩባ ወታደሮች መያዝ ጀመሩ። የዚያኔ ነው ኩባዊው ወታደር ካርሎስ ኦርላንዶ ተይዞ ለጋዜጠኞች መግለጫ እንዲሰጥ የተገደደው።
የዚያድ ባሬ መንግሥት ወራራውን አጠናክሮ በጅግጅጋ በኩል ደንበር አልፎ ገብቶ ብዙ ጥፋት አደረሰ። የንፁሃን ዜጎች ሕይወት ተቀጠፈ። አልፎም ወደ ሐረር ገሰገሰ። ይሄኔ ነው የኢትዮጵያ ክተት የታወጀው። ሐረር ላይ 40 ሺህ ገደማ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ጠበቀው። ተጨማሪ 10 ሺህ የኩባ ጦረኞች ከኢትዮጵያ ጎን ነበሩ።
የኢትዮጵያ ጦር የዚያድ ባሬን ጦር አሳዶ ከመሬቱ አስወጣ። የመጨረሻው ውጊያ የነበረው ካራማራ ላይ ነበር። በወቅቱ በዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታገዘው የኢትጵያ ጦር በሰማይ በምድር ጥቃቱን በማጠናከር የሶማሊያ ጦርን ድባቅ መታ።
ጦርነቱ ሲጀመር ኢትዮጵያ 10 በመቶ ብቻ የኦጋዴን መሬት በእጇ ነበር። ጦርነቱ ካራማራ ተራራ ላይ ሲያበቃ ኦጋዴን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ተያዘች።
በካራማራ ጦርነት በርካቶች ተሰውተዋል። በቀጣናው ያለውን ድርሻ ለማስፋት ኢትዮጵያን የወረረው ሜጀር ጄነራል ሲያድ ባሬ ከሽንፈቱ በኋላ ተቀባይነቱ እየሟሸሸ መጣ።
ታላቋ የሚል ቅጥያ የነበራት ሶማሊያም ከኦጋዴን ጦርነት በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት መታመስ ጀመረች። ሲያድ ባሬ 1983 ዓ.ም ከሥልጣን ተወግዶ ወደ ናይጄሪያ ሸሸ። ሕልፈተ ሕይወቱም ለአራት ዓመታት በስደት በቆየባት ናይጄሪያ ሆነ።በጦርነቱ ኩባ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ የመንና ምሥራቅ ጀርመንን ጨምሮ ሌሎች አገራት አጋርነታቸውን ለኢትዮጵያ አሳይተዋል። ከ16ሺህ በላይ የኩባ ወታደሮች በውጊያው እንደተሳተፉ መዛግብት ያሳያሉ። የኢትዮ-ሶማሊያ የኦጋዴን ጦርነት የብዙሃን ሰላማዊ ዜጎችን ቢቀጥፍም፤ ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች ጅግንነታቸውን ያሳዩበት እንደሆነ በታሪክ ይወሳል።
ለአንድነቱ
ድሉ እንዲሰምር የነፃነቱ
ወጣ ወረደ : ሄደ ነጎደ ሠራዊቱ ::
አለኝ አደራ
የተቀበልኩት :ከጀግኖች አውራ
እንድትኖር : ሀገሬ ታፍራ ተከብራ
ብሎ ተነሳ : ህዝባዊው ሰራዊት
ጉዞ ጀመረ
እየዘመረ
እንዲያበራ
የነፃነት ድል : የአንድነት ጮራ
አውለበለበ የድል ባንዲራ
እንዲያበራ ::
—————————–
ሀገሬ
መመኪያ ክብሬ
አትደፈርም ዳር ድንበሬ
ነፃነቴ
ውርሱ የአባቴ
ተደፍሮ ማየት : አልሻም መብቴ
ብሎ ነጎደ : ህዝባዊው ሠራዊት
ጉዞ ጀመረ
🎖ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለጀግኖቹ የካራማራ ሠማእታት ይሁን !!!
Filed in: Amharic