>

ያላነበበውን መጽሐፍ የሚጠቅሰውን  የአረናውን አምዶም ገብረ ሥላሴን "በሊቃውንት ፊት ጥቅስ?!?" በሉልኝ...!!!    (አቻሜለህ ታምሩ) 

ያላነበበውን መጽሐፍ የሚጠቅሰውን  የአረናውን አምዶም ገብረ ሥላሴን “በሊቃውንት ፊት ጥቅስ?!?” በሉልኝ…!!!   

አቻሜለህ ታምሩ

አንድ ወዳጄ የወያኔ ይቅርታ የአረና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆነው አምዶም ገብረ ሥላሴ  “ስለ ወልቃይት ታሪክ ጽፏልና መልስ ስጥ” የሚል መልዕክት ዛሬ ጧት ልኮልኝ አነበብሁት።  አምዶም ስለ ትግራይ ታሪክ ያሳያል ብሎ  ብሎ በፊስቡኩ የለጠፋቸው ገጾች እንግሊዝ አገር ውስጥ የግላንጎና ጋለወይ የሚባሉ ክፍለ ሀገሮች ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ማይክል ሩሴል “Nubia And Abyssinia” በሚል የጻፉትን በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እ.ኤ.አ. በ1844 ዓ.ም.  ያሳተሙትን መጽሐፍ ነው።
ይህንን የማይክል ሩሴልን መጽሐፍ ሳያነቡ በወረራ የያዟቸውን የጎንደርና የወሎ ወረዳዎች ለማጻናት ሲሉ እንደ ታሪክ ምንጭ በመጠቀም አምዶም ገብረ ሥላሴ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ በፊት የፈንቅል ሊቀመንበር ነኝ ሲል የነበረውን ሰው ጨምሮ በርካታ የትግሬ ብሔርተኞች ይህንን መጽሐፍ ሳያነቡ እዚህም እዚያም ሲለጣጥፉት እመለከት ነበር።
የማይክል ሩሴልን “Nubia And Abyssinia” መጽሐፍ የትግሬ ብሔርተኞች ሳያነቡ ነው የሚጠቅሱት ያልሁት ያለ ምክንያት አይደለም። መጽሐፉን ቢያነቡት ኖሮ ወልቃይትን፣ ጠለምትን፣ ጠገዴንና ሁመራን የትግሬ ለማድረግ የሚጠቅሱት ይህ የአማራና የትግሬ ተፈጥሯዊ ወሰን የተከዜ ወንዝ እንደሆነ ከሶስት አራት ጊዜ እንደጠቀሰ ያውቁና ተከዜን “የትግሬና የአማራ ተፈጥሯዊ ወሰን” ሲል የገለጸው ይህ የሚጠቀሱት መጽሐፍ ወራሪዎች ስለመሆናቸው በማስረጃነት የሚቀረብ እንጂ ይገባናል የሚሉትን የሚደግፍ አለመሆኑን ይረዱ ነበር።
አምዶም የጠቀሰው “Nubia And Abyssinia”  የማይክል ሩሴል መጽሐፍ  መግቢያ ላይ እንደተገለጠው  ደራሲው መጽሐፉን የጻፉት ስኮትላንዳዊው ጀምስ ብሩስ፣ ሔንሪ ሳልትና ናትናኤል ፒርሰን ኢትዮጵያን ጎብኝተው የጻፏቸው መጽሐፍት በዋና የታሪክ  ምንጭነት በመጠቀም ነው። እነዚህ ተጓዦች ስለ ወልቃይት ታሪክ በዘመናቸው የሰጧቸውን ምስክርነቶች “የወልቃትር ጉዳይ” በሚል ርዕስ በጻፍሁት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ በዝርዝር ማግኘት ይቻላል።
የሆነው ሆኖ አምዶም ገብረ ሥላሴ  ሳያነብ ከለጠፋው የማይክል ሩሴል መጽሐፍ  “Nubia And Abyssinia”  የመጽሐፉ ገጽ 5 ገጾችን ያህል ወደኋላ ተመልሶ ቢያነብ ኖሮ በጠቀሰው መጽሐፉ ገጽ 74 ላይ ማይክል ሩሴል “ተከዜ የአማራና ትግሬ ተፈጥሯዊ ወሰን ነው” በሚል የጻፉትን ያገኘው ነበር። በመጽሐፉ ገጽ 115 ላይም ተመሳሳይ የታሪም ምስክርነት ተጽፎ እናገኛለን።
ባጭሩ  የአረናው አምዶም  መጽሐፉን ሳያነብ የጠቀሰው የማይክል ሩሴል “Nubia And Abyssinia”  መጽሐፍ ገጽ 74 ላይ “ተከዜ የአማራና ትግሬ ተፈጥሯዊ ወሰን ነው” በሚል የተጠቀሰው የታሪክ ምስክርነት  ከታች ተያይዟል። ከዚህ በተጨማሪ  በዚሁ አምዶም በጠቀሰው የማይክል ሩሴል መጽሐፍ ገጽ 115 ላይ ትግራይ ተከዜን ተሻግሮ እንደሚገኝ የጻፉት ተያይዟል።
እንግዲህ! አምዶም ሳያነብ በጠቀሰው የማይክል ሩሴል “Nubia And Abyssinia”  መጽሐፍ መሰረት  እንኳን ብንሄድ ተከዜ የአማራና ትግሬ ተፈጥሯዊ ወሰን ስለሆነ የትግሬ ብሔርተኞች ተከዜን ተሻግረው ይገባናል የሚሉት አጽመ ርስት እንደሌላቸው ሊያውቁ ይገባል እንላለን።
በተረፈ ያላነበበውን መጽሐፍ የሚጠቅሰውን አምዶም ገብረ ሥላሴን  «ከመጠምጠም መማር ይቅደም» ፤ «ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት» ፤ “በሊቃውንት ፊት ጥቅስ” የሚሉትን  የአያቶቻችን ጥልቅ ምክር በመለገስ ተስናብቻለሁ።
Filed in: Amharic