ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ
እኔ በሀገር ጉዳይ እንኳን ከማላውቀው በብሄር ብቻ ከምዛመደው ሰው ይቅርና ከእናቴ ልጅ ጋር እንኳ ልጣላ፣ ደም ልቃባ እችላለሁ። በትክክለኛ እና እውነተኛ ምክንያት (just cause) ለሀገር መቆም፣ ለዚህም መሞት ያለ፣ የነበረ እና ወደፊትም የሚኖር ነው።
በመሰረቱ ጦርነት ከማንም ጋር ልክ አይደለም፣ አይመረጥም፣ አውዳሚ ነው። ምርጫ ሲጠፋ የሚገባበት ጉዳይ ነው። የጦርነት ቦቃ የለውም።
ወንድም ከወንድሙ የሚጋደልበትም የርስበርስ ጦርነትም እንደ ለሉኣላዊነት የሚደረግ ከጠላት ጋር ጦርነትም የማይፈለግ ነው። ወንድም ከወንድሙ የተላለቀበት የርስበርስ ጦርነት በአስከፊነቱ መታወስ አለበት። እንዳይደገም የውስጥ ፖለቲካን አካታች በማድረግ ነፃነትና ዴሞክራሲን በማስፋት ማስወገድ ይቻላል። የሌላ ሀገር ወረራን ግን ወይ ተንበርክኮ ሀገርን አሳልፎ መስጠት ነው አልያም ምርጫየለሽ ትግል አድርጎ የሀገርን ሰንደቅ አስከብሮ በድል ለሀገር መቆም ነው። ኢትዮጵያ ሁልጊዜ የኋለኛውን በመመረጥ አንድነቷን እና ሉአላዊነቷን አስከብራለች። ነገም ታስከብራለች፣ ለዚህም እኔን ሙክታር ኡስማን ከጠራችኝ በደስታ ለሀገሬ መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ ነኝ። የእናቴ ልጅ ቢሆንም ለዚህ ርህራሄ የለኝም።
ይህ የእኔ የግል አቋም ነው!
ሆኖም አንዳንድ ሀቆችን ከኢትዮጵያዊ ሶማሌ ወገኖች የእይታ ማዕዘን አንፃር ኢትዮጵያውያን ስለኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት መገንዘብ ያለባቸው ነገሮች አሉ። በዚህ ጦርነት የኢትዮጵያ ሶማሌ በሁለት ጅራፍ የግርፋት ሰንበር አለበት።
አንድ፣
በኢትዮጵያ በኩል ከጠላት ጋር እንደሚያብር እየተጠረጠረ የአስከፊ የፕሮፖጋንዳ ሰለባ ከመሆንም አልፎ ከምድርም ከሰማይም የቦንብና የጥይት መዓት ዘንቦበታል። ለጦርነት ማነቃቂያ ይውሉ የነበሩት ፕሮፓጋንዳዎች የኢትዮጵያን ሶማሌ ከዋናዋ ሶማሊያ ያልለየ በመሆኑ ከፍተኛ የስነልቦና ስብራትን በህዝቡ ላይ አድርሷል። ጦርነቱን ተከትሎ በዜግነቱ ላይ ጥርጣሬ አርፎበት ከሀገር የሚገባውን ጥቅም ያላገኘ ህዝብ ነው። ከሃያ አመት በፊት አርባ የጦር ካንፕ እና አንድ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ብቻ የነበረው ህዝብ ነው። አንድም አስፓልት መንገድ የሌለውና መሰረተልማት የማይታሰብበት አካባቢ የተረሳ እና በጎሪጥ የሚታይ ህዝብ ነው። በዚህ ጦርነት የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ያየውን መከራ እና ስቃይ ለሰሚው የሚከብድ ነው። በዚህ ጦርነት ህዝቡ ያለበት ትዝታ መልካም አይደለም። ለዚህ ስሜቱ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በተረፈ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ኢትዮጵዊነቱን ማንም እንዲሰጠው ማንም እንዲቀማው የማይፈልግ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያ አሁን በተቸገረችበት ወቅት ያለኮሽታ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያስመሰክር ህዝብ ነው።
ሁለት፣
በሶማሊያ በኩል “ነፃ ልናወጣችሁ፣ ብንመጣም አታግዙንም ተብሎ በዚያድባሬ ጦርም የተመታ ህዝብ ነው። እናንተ ብታምፁና ከኢትዮጵያ ጋር እንደማትሆኑ እና ሶማሊያን ብትመርጡ የጦርነቱን እድሜ ታሳጥሩት ነበረ ተብሎ ቂም ተይዞበት ከጠላት ጋር አብረሃል ተብሎ የተሰቃየ ህዝብ ነው።
እነዚህን ሁለት ድርብ ሰንበሮችን በገላው ላይ የያዘ ነው የኢትዮጵያ ሶማሌ። ለዚህ ጉዳቱ የትኛውም ወገን ያላወቀለት ህዝብ ነው።
እርግጥ፣ በቋንቋ በሀይማኖት እና በስነልቦና የሚመስለው አካል በአንድ ሀገር አብረን እንኖራለን ብሎ ሲመጣ ቀልቡ ማልሎ ለሶማሊያ በልቡ ያደላ ይኖር ይሆናል። የሚጠበቅ ነው። ይህ በጥቂቱ ተስተውሎ ይሆናል። ሆኖም ይህ ለሶማሌ ሲሆን አዲስ መሆን የለበትም።
በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ እነ ኦነግና ህወሓት ለሶማሊያ አድልተዋል። ኢህአፓ ሳይቀር ከሶማሊያ ጎን በመሆን “ሶማሊያ ታሪካዊ መሬቷን ነው የጠየቀችው” የሚል አቋም ማራመዱ በርካታ ምስክሮች ናቸው።
ይህ ጦርነት ሲታሰብ በርካታ ደስ የማይሉ የታሪክ ጓዞችን ይዞ ይመጣል። የጦርነቱ ውጤት የኢትዮጵያን ህልውና አስቀጥሏል። ለዚህም የተከፈለው መስዋዕትነት የሚያኮራ ነው። ጦርነቱ ግን በአፍሪካውያን መካከል በባህልና መልካዓ ምድር በፍፁም የሚመሳሰሉ ህዝቦች መካከል የተደረገ መሆኑ ከጣልያን ጋር ከተደረገው አድዋ ጋር በፍፁም የሚለይ ነው።
እንዲህ ያለ ጦርነት ከግብፅ ጋር በጉራ እና ጉንደት ላይ ተደርጓል። በቅርቡም ከኤርትራ ጋር ተደርጓል። ከኤርትራ ጋር የአፍሪካ ትልቁ ጦርነት ነው የተደረገው። ይህን ትልቅ ጦርነት ባሰብን ቁጥር አሁን የሚሰማን ፀፀት እንደሆነ ግልፅ ነው። ለሀገራችን በተከፈለው መስዋዕትነትና ድል ሁሉ ኢትዮጵያዊ ይኮራል። ድሉን አመታዊ ዝክር እናውጣለት ቢባል ግን በውስጥም በቀጠናውም ጥሩ አንድምታ አይኖረውም። የካራማራ ድልም ኢትዮጰያ እራሷን የመከተችበት ድል ቢሆንም በሀገሪቱ የሚኖሩ ሶማሌዎች ያሳደረው ጠባሳ ከፍተኛ በመሆኑ ይህን ስሱ ጉዳይ ከኢትዮጰያ ሶማሌ ማዕዘን በኩል በማየት ለህዝቡ ስሜት በአውነታዊነት ለአንድነት ሲባል ቁስሉን መረዳት ያስፈልጋል።
ሌላው ደግሞ
ከብሄርና የመንደር ፖለቲካ በሚያራምድ ማህበረሰብ፣ የሀገርን እሳቤ ከብሄር ጋር እየደባለቀ በሚወዛገብ ማህበረሰብ ውስጥ እንደካራማራ አይነት ድሎችን ፖለቲካ እንድምታውን በማስተዋል የመበሻሸቂያ አጀንዳ መሆኑ የማይፈለግ ነው። በመግቢያዬ እንዳልኩት ይህ የፌስቡክ ማህበረሰብ ሀገር የሚባለውን ከሁሉ በላይ የሆነን ፅንሰሀሳብ ከንዑስ ማንነት አይነቶች ለይቶ የማይከራከር እንዲሁ ግልብ በሆነ ብሽሽቅ ባዶ እርካታ እና ድንፋታ ውስጥ ያለ ነው። ስለብሄሩ አንስተህ ስትሞግተው በእኛ ጉዳይ አያገባህም ይልህና ያንተን ብሄር የሚመለከት ጉዳይ ግን ሲያብጠለጥል ይውላል።
ስለሀገር አንድነት ስትፅፍ ሀገሩ እንዳልሆነች ነገር “ለአማራ ታሽቃብጣለህ” ይልሃል። የጋራ ሀገርን አስፈላጊነተ የሚገነዘብ በጣም ጢቂት ነው። አብዛኛው መደዴ ነው። በእሱ ደረጃ ላለመውረድ መጠንቀቁ እንደለ ሆኖ፣ አንዳንዴ እውነቱን መግለፅ ይገባል።
ኢትዮጵያ..
እንደ ኬንያ .. የኦሮሞ እና ሶማሊ ብሄረስቦች
እንደ ጅቡቲ .. የሶማሊ እና የአፋር ብሄረሰቦች
እንደ ሶማሊያ .. የሶማሊ ብሄረሰብ
እንደ ኤርትራ .. የትግሬ , የአፋር , ኩናማ ብሄረሰቦች
እንደ ሱዳን .. የአኙዋክ , የኑዌር ብሄረሰቦች
መኖርያ ናት ! የአለምም ሀገሮች ይህን ሀቅ ይጋራሉ።
ይህ ማለት እነዚህ ጎረቤት ሃገሮች ቢወሩን እነሱ እና እኛ ጋር የጋራ ብሄረሰቦች ስላሉ እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጣለን ማለት አይደለም .. ደግሞም አልተቀመጥንም:: አንቀመጥምም።
ለዚህም ነው በሁለት መንገድ የፌስቡክ ግሪሳ የቆሸሸ የሚሆንብኝ።
አንድኛው
አንዳንዶቻችሁ ስለኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጦርነት እና እሱን ተከትሎ ለተገኘው ካራማራ ድል ያያችሁበት መነፅር በብሄረሰብ አስተሳሰብ ቆሽሿል:: የምናወራው ስለ ሁለት ሉዓላዊ ሃገሮች ” ኢትዮጵያ ” እና ” ሶማሊያ ” ጦርነት ነበር። ሶማሊያ ብታሸንፍ ጃዋር ዛሬ ዜግነቱ ሶማሊያዊ ነው። ዚያድባሬ በወቅቱ እስከ አዳማ ድረስ ግዛቴ ነው ብሎ ነበረ የሚቀሰቅሰው። ዛሬ የሚፎክርበት የኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያ ሀገረክልል የቀረው በኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ነው።
በኢትዮጵያ እና በዋናዋ ሶማሊያ ያሉ ሶማሌዎችን ድጋፍ በመፈለግ እና የአብይ መንግስትን ለማሳጣት የሀገርን ታሪክ ለገበያ ማቅረቡ አሳፋሪ ነው። ኦሮሞ ለሀገሩ ሉኣላዊነት ያበረከተውን ትልቅ ታሪክ ማሳነስ እና ማራከስ ነው። እንዲህ ላለ አቋም የሚሰጠውም ምላሽ ካራማራን ከሀገር ምልክትነት ወደ የብሄር ብሽሽቅ ቀይሮታል።
ሁለት
አንዳንዶች የጦርነቱን አጠቃላይ ምክንያት ከውጤት በኢትዮጵያዊ ሶማሌ ማህበረሰብ ላይ ጥሎት ያለፈውን ጠባሳ ሳንረዳ፣ በዚህ ጦርነት እንደዜጋ ሶማሌ በጥርጣሬ ሲፈረጅ መኖሩን በመዘንጋት አልያም ባለማወቅ ሶማሌው እንደ አድዋ ድል አይነት በድምቀት እንዲያከብር ይጠብቃሉ። ይህ ስህተት ነው። በባህልና ቋንቋ የሚመሳሰልህ ህዝብን በመልካም ሲወሳ እንጂ እንደ ጠላት ሲፎከርበት ስሜት ይሻክራል። ዘር ከልጓም ይስባል የሚባለው እዚህ ጋ መታወስ አለበት።
የዚህን ማህበረሰብ የዘመናት የመገፋት ታሪኩን ለመቀየር ኢትዮጵያውያን በእጅጉ ለሀገር አንድነት በሚበጅ መልኩ በኢትዮጵያ ያለን ሶማሌ መረዳት እና ማቅረብ ያስፈልጋል። ሶማሌ በኢትዮጵያ የያዘውን ቆዳ ስፋትና የህዝብ ብዛት በማስተዋል ታሪኩን እና ባህልና እሴቱን በማጉላት አለኝታነታችንን ልናሳየው ይገባል።
የሶማሌ ህዝብ የራሱን ድርሻ እንደዜጋ የሚጠይቅ ቅን እና በሀቀኛ ፖለቲካ የሚያምን መሆኑን በመገንዘብ ስሜቱን ከሚያሻክሩ ነገሮች መታቀብ ለሀገር አንድነት ጠቃሚ ነው። ሶማሌ ቁምነገር ላይ ቅጥፈትና ሴራ አያውቅም። ሶማሌ በድሮ ዘውዳዊ ስርዓት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተበድሏል። በደልን ማነሳሳት እና ለፖለቲካ ገበያ ለትርፍ ማዋል አይበጅም የሚል ህዝብ ነው። ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የሶማሌ ስነልቦና ያስፈልጋል።
የሶማሌ ህዝብ
በሙስጠፌ ላይ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን መተማመን እና ፍቅር በሚያጓጓ መልኩ እያየው እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ እውነተኛ ዴሞክራሲ እንዲመጣ የድርሻውን ወደ መሀል በመምጣት ሚናውን ለመጫወት እየተነሳሳ ያለ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያውያን ከሶማሊያዋ በዚያድባሬ ተስፋፊ መንግስት ጋር ያካሄድነው ጦርነትና ድል በዚህ ጦርነት በሁለቱ መንግስታት ሁለት ጊዜ የተገረፈውን ህዝብ ሰንበር አስተውለንለት ለስሜቱ እና ለሰቆቃ እና ስቃይ ያዘለው ትዝታው ትርጉም ብንሰጥ እና ብንረዳው ለሀገር አንድነት ይበጃል እላለሁ።
ማን ያውቃል?
በሀገራችን የሀሳብ ፖለቲካ ሰፍኖ ከብሄርና የመንደር ፖለቲካ ወደ ሀገራዊ የዜግነት ፖለቲካ ከፍ ብለን የጦር ሜዳ ድሎቻችንን በሀገራዊ መነፅር ማየት ስንጀምር ሁሉ ነገር ይቀየር ይሆናል። ያኔ በሚነሳ ሀሳብ ሁሉ ከሚደነፋው ይልቅ በምክንያት የሚሞግት በልጦ ኢትዮጵያ የቀደሟትን ቀድማ ታንፀባርቅ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!