>

የጠቅላዩ የመደበር/የመደመር መንገድ...!!! (ኤርሚያስ ለገሰ)

የጠቅላዩ የመደበር/የመደመር መንገድ…!!!

ኤርሚያስ ለገሰ

*…ከነገ ጀምሮ መንግስታዊ ተቋማት፣ መያዶች፣ ኤምባሲዎች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ ካድሬዎች፣ ጉምቱ የሐይማኖት ሊቀ ሊቃውንት፣ ተደጋፊ ተደማሪዎች፣ ውታፍ ነቃዮች፣ የኢትኖራ ገበሬዎች ማህበር አባላት ፣ የፒያሳ አካባቢ ጐዳና ተዳዳሪዎች በሚወርድላቸው መመሪያ መሰረት ” የመደመር መንገድን” ገፅ በገፅ ካርታ እያጣቀሱ እንደ GPS ይመሩናል። ዘመኑ መነዳት ነውና ለመነዳት እንዘጋጅ!
በነገራችን ላይ መለስ ዜናዊ በየአመቱ አንድ መፅሐፍ እና በየሶስት ወሩ ከ30-40 ገፅ የሚሆን አርቲክል ይፅፍ ነበር። ቢያንስ ለአራት ዓመታት መፅሐፉንም ሆነ አርቲክሎቹን በረቂቅ ደረጃ የማንበብ እድል አጋጥሞኛል።
ከመፅሀፎቹ ውስጥ የፓለቲካ ሳይንቲስት የሆነውን ፍራንሲስ ፉኩያማንና የ8ኛው ሺ ቄሶችን ያብጠለጠለበት፤ The dead end…the new beginning፤ ” የኢትዮጵያ ሚሌኒየምና የህዳሴ ጉዞአችን”፤ ” ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት”፤ “የአመራር ጥበብ” ፣ “ስትራቴጂክ እና ታክቲክ” ” ኢንቫይሮመንትና የዓለም ሙቀት መጨመር” የሚባሉት በጥቂቱ የማስታውሳቸው ናቸው። ታዳያ አንዱም መፅሐፍ ሆነ አርቲክል በግል ስሙ ፎቶው ተለጥፎበት የወጣ የለም። አርቲክሎቹም ቢሆን ታደሰ ገ/ህይወት በመሳሰሉ የብዕር ስሞች የሚወጡ ነበሩ። የመፅሐፉም ሆነ መጣጥፎቹ ባለቤት ፓርቲውና መንግስት ነበሩ። የፓርቲውና መንግስት አቅጣጫ የሚቀዳው ከእነዚህ የሰውየው ጽሁፎች ነበር። እዚህ ላይ አንባቢ ልብ እንዲል የምፈልገው የመለስን መጣጥፎች መንፈስ፣ አገራዊ ፋይዳና ይዘት እየገለጽኩ አይደለም።
በሌላ በኩል የአገር መሪዎች የስልጣን ዘመናቸውን ሲጨርሱ መጽሐፍ በራሳቸው ስም መጻፍ የተለመደና ተገቢ ነው። አገራቸውን እንዴት እንደመሩ፤ አቅደው ያሳኩትን፣ ያላሳኩትን፤ ያጋጠማቸው ችግር፤ እንቅፋቶቹን እንዴት እንደተሻገሩት፤ ለተተኪ መሪዎች የሚያቀርቧቸው ምክረ-ሃሳቦች የሚዳስሱበት ነው። ይሄ ሊበረታታ የሚገባ ነው።
ዓብይ አህመድ እየሄደበት ያለው መንገድ ግን እጅግ ያሸማቅቃል። አነ ደሜክስ፣ዳግማዊት፣ ብናልፌ፣ ሬድዋንና ብፃይ ዛዲግ ለምርጫ ክርክር ሲመጡ በቦርሳቸው አንግበው የሚመጡት በምርጥ ፍቶግራፈር የተነሳ ፎቶ የተለበጠበት መጽሐፍን ነው ማለት ነው? እስቲ ይታያችሁ ደሜክስ መጽሐፉን በቀኝ እጁ ከፍ አድርጎ በማውጣት እያውለበለበ ” መመሪያችን የመደመር መንገድ ነው! እንሰሶች ሁሉ እኩል ናቸው! አንዳንዶቹ የበለጠ እኩል ናቸው! ሀሌሉያ!” ሲል!!
Filed in: Amharic