>

"የህወሓት ጁንታና አጋሮቻቸው ክፍያ በመፈጸም የሀሰት ፕሮፖጋንዳ እያሰራጩ ነው!!!"  (ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኝ - ጄፍ ፒርስ)

“የህወሓት ጁንታና አጋሮቻቸው ክፍያ በመፈጸም የሀሰት ፕሮፖጋንዳ እያሰራጩ ነው!!!”
 ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኝ ጄፍ ፒርስ
(ኢ.ፕ.ድ)

የህወሓት ጁንታና አጋሮቻቸው ለምዕራባውያን የሚዲያ ተቋማትና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ክፍያ በመፈጸም ህውሓት ለበርካታ አመታት ሲሰራ ቆየውን ግፍ በመሸፈንና በወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኝ ጄፍ ፒርስ ገለጹ።
የፖለቲካ ተንታኝና ጸሐፊ ጄፍ ፒርስ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በትግራይ ክልል በአክሱም ከተማ “የጅምላ ጭፍጨፋ” ተፈጽሟል በሚል ያወጣውን ሪፖርት አስመልክተው ባስነበቡት ሰፋ ያለ ትንታኔ ሪፖርቱ ተአማኒነት የጎደለው መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር አያይዘው የህወሃት ባለስልጣናት እና በአውሮፓና አሜሪካ የሚኖሩ ጉዳይ አስፈፃሚ አጋሮቻቸው የሚያናፍሱት የውሸት መረጃ እየተጋለጠ መሆኑንም አብራርተዋል።
ጄፍ ፒርስ እንደሚገልጹት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘጋቢዎች ከኖቨምበር 29 እስከ 30 ባሉት ቀናት በአክሱም ከተማ እንደነበሩ ከተቋሙ ዋና ዳይሬክተር መረጃ ማግኘታቸውን በመጥቀስ በወቅቱ በዓሉ በሰላማዊ ሁኔታ ስለከመከበሩ ዘገባዎች መሰራታቸውንና ምንም ዓይነት የተለየ ክስተት እንዳልነበረ እንዳረጋገጡላቸው አመልክተዋል።
የአምነስቲ ሪፖርት ተጨማሪ ማጣራት ካልተደረገባቸው ለተደራራቢ የፈጠራ ወሬዎች እድል ይከፍታል ብለዋል።
አምነስቲ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች በአብዛኛው መሰረታዊ የሚባለውን የጥናትና ምርምር ዘዴዎች ያልተከተሉ የተዛቡና ለአንድ ወገን በግልጽ የወገኑ ከመሆናቸውም በላይ በአሉባልታ ላይ የተመሰረቱና አሳማኝ ስላልሆኑ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳባቸዋል  ነው ያሉት።
ባለንበት ዘመን ምንም የሚደበቅ ነገር ባለመኖሩ በአክሱም ጅምላ ግድያ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ መቃብሮችንና ሌሎች ማስረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደማይሆን ያስረዱት ጸሃፊው ክሶቹና መሰረተ ቢስ ውንጀላዎቹ ክስተቱን ለአለም ለማሳወቅና ፍትህ ለመጠየቅ የማያስችሉ ፈጠራዎች ሆነዋል ብለዋል።
የምእራባውያን የሚዲያ ተቋማትና ራሳቸውን የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ያደረጉ ድርጅቶች በርካታ ኢትዮጵያውያን ላለፉት በርካታ አመታት በህወሃት አገዛዝ መከራቸውን ሲያዩ ምንም አለማለታቸውን ነው የገለጹት።
በአክሱም ጅምላ ግድያ ተደርጓል በሚል የሚደረገው የስም ማጥፋት ዘመቻ የትግራይ ህዝብ ላይ የስነልቦና ጫና ለመፍጠር የሚያስችል ሙከራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
ጸሃፊው ሙከራው ከተሳካና የአለምን ማህበረሰብ ማሳመን ከቻለ ህወሃት አስቀድሞ ባዘጋጀው የአንድ ለአምስት የቁጥጥር ስርአት አማካይነት ዳግም ሊመለስ እንደሆነ በስፋት በማስነገር ህዝብ እንዳይረጋጋና ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዳይመለስ ለማድረግ እንደሚያስችለው ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
እንደ ኒው ዮርክ ታይምስ ፣ ዋሽንግተን ፖስት ፣ ግሎብ እና ሜል ያሉ ዋና ዋና የዜና አውታሮች ለህወሃት የሰጡትን ሰፊ ሽፋን ያህል ባይሆንም ከኢትዮጵያ አምባሳደሮች የሚደርሳቸውን ምላሾችን በገፆቻቸው ላይ ለማተም ፈቃደኞች ካለመሆናቸውም በላይ ለዲፕሎማቶቹ የስልክ ጥሪዎች ምላሽ አለመስጠታቸው ተአማኒነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከት መሆኑንም አንስተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ህወሃት ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን አውጥተው በአውሮፓና አሜሪካ ቅንጡ የመኖሪያ ቤቶችን የገነቡ ግለሰቦች ያለልክ በሚረጩት ገንዘብ ብዙ የሚዲያና የፖለቲካ ሰዎችን ከጎናቸው በማሰለፍ የአለም ማህበረሰብን ቀልብ ለመሳብ ቢችሉም ለሃገራቸው ያላቸው ፍቅር ቅንጣት ያህል ያልቀነሰ በጣም በርካታ የትግራይ ተወላጆች መኖራቸውን ያስረዱት ጸሃፊው እነዚህ ውሸታም የህወሃት ባለስልጣናትና አጋሮቻቸው ለመረሳት ጥቂት ጊዜ ብቻ እንደቀራቸው መናገር ይቻላል ብለዋል።
Filed in: Amharic