>

ዐብይ ጾም ማለት ምን ማለት ነው?

ዐብይ ጾም ማለት ምን ማለት ነው? ዐብይ ጾም ለምን ዐቢይ ተባለ?

ጾም ማለት ፡- ለዘላዓለም ሁሉንም ሕዋሳት ከኃጢአት መከልከል፣ለተወሰነ ጊዜ እህል ከመብላት ዉሃ ከመጠጣት መታቀብ ወይም ለተወሰኑ ወራት ከጥሉላት ከስጋ ፣ከወተት፣ከቅቤ፣ከእንቁላል፣በአጠቃላይ ከእንሰሳት ዉጤት መከልከል ነው።

የጾም ጥቅም ፦ የሥጋ ምኞትን የምታጠፋ የነፍስን ቁስል የምታደርቅ ለጎልማሶችም ጸጥታንና እርጋታን የምታስተምር ከእንሰሳዊ ግብር ጠባይ የምትከለክልና ሰው መላእክትን መስሎ የሚኖርባት ደገኛ ሥርዓት ነች፡፡

በብሉይ ኪዳን ብዙ ሰዎች በጾም ተጠቅመዋል እግዚአብሔር የጾምን ሥርዐት የደነገገው ገና ከጥዋቱ አዳምን በፈጠረበት ወቅት ነው ፡፡ እጸ በለስን አትብላ ማለት ትዕዛዝ ቢሆንም ትዕዛዙ ግን የጾም ትዕዛዝ ነው አዳምና ሔዋን ይህን የጾም ሥርዐት በመሻር እጸ በለስን በልተው በመገኘታቸው ምን እንደደረሰባቸው በቅዱስ መጽሐፍ ላይ የምና ነበው ነው፡፡
በጾም የተጠቀሙ ቅዱሳን አበው ጾምን የጸሎት እናት የእንባ ምንጭ የጽድቅ መሠረት ደገኛ ሥርዐት በማለት ይገልጻሉ፡፡

ጾም በብሉይ ኪዳን ስንመለከት፦
በሕዝብ ላይ የተቃጣውን መከራ ለማቅለል ተጠቅመውበታል መጽ ኢያሱ 7÷6 -9፣ መጽ አስቴር 4÷16 ፣ትንቢተ ዮናስ 1 ፣ መ.ሳሙኤል ካል 12÷17 ዘዳ 9÷9 -18፣ትንቢተ ኢዩኤል 2÷14 ፣መዝ 34(35) ÷ 13 ትን.ዳን 10÷2 መዝ 108÷ 24

ጾም በሐዲስ ኪዳን

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሥራው ሁሉ መጀመሪያ ያደረገው ጾምን ስለሆነ መሥራቹ ክርስቶስ ነው በሐዲስ ኪዳን ጾም የታዘዘ ስለመሆኑ የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመለከታለን
ማር 2 ÷20 ፣ማር 9÷29 ፣ማቴ 6÷16 ፣ ሉቃ 6÷21 ፣ሐዋ 13÷3 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለጾም ሥርዐትና ደንብ አውጥታለች በዓመት ውስጥ ሰባት የዓዋጅ አጽዋማት እንዳሉና ማንኛውም ክርስቲያን እንኝህን አጽዋማት እንዲጾም ታዛለች እነዚህም አጽዋማት :

  •   ዐቢይ ጾም
  •   ጾመ ሐዋርያት
  •  ጾመ ስብከት (ጾመ ነብያት)
  •  ጸመ ፍልሰታ
  •  ጾመ ድኅነት
  •  ጾም ነነዌ
  •  ጾመ ገሃድ
    ከነዚህ አጽዋማት ውስጥ የምንመለከተው ዐቢይ ጾም ነው።

ዐቢይ ጾም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሥርዓት መሰረት የአዋጅ ፆም የሚባሉ ሰባት አፅዋማት አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም በጊዜው ረዥም ደግሞም በስያሜው የተለየውን አብይ ጾምን እንመለከታለን፡፡

1. ዐብይ ጾም ማለት ምን ማለት ነው

በመጀመሪያ ‹‹ዐቢይ›› የሚለው ቃል ‹‹አበየ›› ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ትርጓሜውም ‹‹ከፍ አለ›› ማለት ነው፡፡
2. ዐብይ ጾም ለምን ዐቢይ ተባለ ዐብይ ጾም ዐብይ የተባለበት ሦስት አበይት ምክንያቶች እንመለከታለን
2.1. ጌታቸን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የጾመው ሥለሆነ ማቴ 4፡2-3
2.2. በቀኑ ቁጥር ከሌሎች አጽዋማት ስለ ሚበልጥ የቀኑ ብዛትም 55 ቀን ነው፡፡
2.3. ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች እንዲሁም ደግሞ ሶስቱ ርዕሰ ኃጢአት የሚባሉት ትዕቢት፣ስስት ፍቅረ ነዋይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ድል የተመቱበት ስለሆነ ይህ ጾም አብይ (ታላቅ) ተብሏል፡፡ ማቴ 4፡3-11 የዐብይ ጾም የተለያየ ስያሜዎች ዐብይ ጾም ከቀኑ ርዝማኔ በተጨማሪ ጾሙ የተለያዩ ስያሜዎች አሉት፡፡
+
° ጾመ ሁዳዴ፡- ሁዳድ ማለት ሠፊ (ትልቅ) የእርሻ ቦታ ማለት ነው፡፡ ይህም ጾም ደግሞ በቀኑ ብዛት ትልቅ (ሠፊ) በመሆኑ የሁዳዴ ጾም ይባላል፡፡
° የካሳ ጾም፡- እንዲህ የተባለበት ምክንያቱ ደግሞ አዳምና ሔዋን በዲያቢሎስ ግዞት እያሉ ክርስቶስ ደሙን በመክፈል (በመካስ) ነጻ ስላውጣቸው የካሳ ጾም ተብሎሏል
° የድል ጾም ፡-ይህም ደግሞ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ጾም ሰይጣንን ድል ያደረገበት በመሆኑ የድል ጾም ተብሏል፡፡
° ጾም አስተምህሮ፡- ይህ ጾም ‹‹ጾም አስተምህሮ›› የተባለበት ምክንያት ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማስተማር የጾመው በመሆኑ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ የተለያዪ ስያሜዎች አሉት ‹‹የመሸጋገሪያ ጾም፣ ‹‹የስራ መጀመሪያ ጾም ››

የዐብይ ጾም ሳምንታት

ዐብይ ጾም በያዘው በ55 ቀኑ ውስጥ 7 ቅዳሜና 8 እሁዶቸን ይዟል የእነዚህ የስምንቱ እሁዶች የተለያየ ስያሜ አላቸው፡፡ ስያሜአቸውንም የሰጣቸው የቤተክርስቲያናችን የዜማው ሊቅ የሆነው ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡
1፣ ዘወረደ
2፣ ቅድስት
3፣ ምኩራብ
5፣ ደብረዘይት
6፣ ገብረ ሔር
7፣ ኒቆዲሞስ
4፣ መጻጉዕ
8፣ ሆሳዕና

ቀደምት ሊቃውንት ሁለት ዓይን የተሰጠን በአንዱ የራሳችን በሌላው የሌላውን ለማየት ነው፡፡ ሁለት ጆሮ የተሰጠን በአንዱ የራሳችንን በሌላው የሌላውን ለመስማት ነው፡፡ ሁለት እጅ የተሰጠን በአንዱ ለመስጠት በሌላው ለመቀበል ነው፡፡ ሁለት እግር የተሰጠን በአንዱ ወደራሳችን በሌላው ወደ ሌላው ለመሄድ ነው ይሉ ነበር፡፡

ከዋክብት የሚያመሰግኑት በስማቸውም የሚጠራቸው: የፀጋው ብዛት የማይታወቅ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለሐዋሪያት እንዲሁም ለቀደሙ አባቶቻችን ምሥጢሩን እንደገለጽክላቸው ለእኛም ግለጽልን። አሜን አሜን አሜን!!!

ወ ስ ብ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር
ወ ለ ወ ላ ዲ ቱ ድ ን ግ ል
ወ ለ መ ስ ቀ ሉ ክ ቡ ር

†† † † ††

Filed in: Amharic