ኢትዮጵያን ከታሪካዊ ጠላቶች ሴራ መታደግ የግድ ነው!
ይታገሱ አምባዬ
ኢትዮጵያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በምዕራባውያን ኃይሎች ከፍተኛ ጫና እየተደረገባት ነው፡፡ በሁሉም የዲፕሎማሲ ግንባሮች እየተደረገ ያለው ጫና በውስጣዊ አንድነትና ጥንካሬ እንዲረግብ ካልተደረገ፣ በተለያዩ ማዕቀቦች በማሽመድመድ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተን አደጋ ማጋጠሙ አይቀሬ ነው፡፡ በታላቁ የዓድዋ ድል መንፈስ መተባበር ካልተቻለ ጫናው ከባድ ነው፡፡ ጭቆናንና በደልን አሜን ብሎ ለመቀበል አሻፈረኝ የሚል መንፈስ የፈጠረውና የሥነ ልቦና ፈውስ የሆነው የዓድዋ ድል በዘመኑ የነበሩ ኃያላን ቅኝ ገዥዎችን ከማሳፈሩም በላይ፣ ቅኝ ተገዥዎችን ለትግል ያነሳሳ ታላቅ ተምሳሌት ነበር፡፡ ለዚህም ነው ከዓድዋ ድል ማግሥት ጀምሮ በተለይ ምዕራባውያን ቅኝ ገዥዎች ይህንን የአይበገሬነት መንፈስ ለመስበር ሲያሴሩ የነበሩት፡፡ ለዚህ ዓላማ ስኬት ደግሞ ኢትዮጵያን በተለያዩ ፈርጆች ማጎሳቆል፣ ደካማ ጎኖቿን እያነፈነፉ ማሳፈር፣ የረሃብና የኋላቀርነት ተምሳሌት ማድረግ፣ በፋሽስት ጣሊያን ዳግም ወረራ ጊዜ ጀርባቸውን በመስጠት ግፍ እንዲፈጸምባት መተባበር፣ የውስጥ ተላላኪዎችን በማደራጀት የማንነትና የእምነት ልዩነቶችን በማጋጋል አንድነትን መሸርሸር፣ እርስ በርስ ማባላትና የመሳሰሉ ሴራዎችን ፈጽመዋል፡፡ በዚህ ወቅት ምዕራባውያንና ታሪካዊ ጠላቶች ከየአቅጣጫው ችግር እየፈጠሩ፣ አንድ መሆን አለመቻል የሚያስከትለው መዘዝ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ዙሪያዋን ለመወጠር እየተደረገ ያለውን ሴራ ለማክሸፍ ከታሪክ መማር ያስፈልጋል፡፡ ከዓድዋ ድል በኋላ ታላላቅ ከሚባሉ ታሪካዊ ክንውኖች መካከል የሚጠቀሰው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አንዱ ነው፡፡ ይህ ግድብ ብሔራዊ ማንነትና ዓርማ ነው፡፡ በግድቡ ምክንያት ኢትዮጵያ ላለፉት አሥር ዓመታት ያህል በግብፅ ተንኮሎች እየተፈተነች ነው፡፡ የዓባይን ውኃ በፍትሐዊነትና በምክንያታዊነት መርህ ለመጠቀም የምታደርገው እንቅስቃሴ፣ ኢፍትሐዊ በሆኑ ምዕራባውያን ዘንድ ድጋፍ እየተቸረው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ እውነትን ይዛ አደባባይ ብትወጣም በግብፅ ደባ መከራዋን እያየች ነው፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ ለመግባት ምዕራባውያን አሰፍስፈዋል፡፡ ለዘመናት ለወራሪዎችና ለተስፋፊዎች አልንበረከክም ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በዘመኑ ኒዮ ኮሎኒያሊስቶችና የውስጥ ተላላኪዎች አደጋ እንዲያንዣብብበት እየተደረገ ነው፡፡ ሱዳን የግብፅን አይረቤ አጀንዳ ተሸክማ ከዘመናት መልካም ጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር ድንበር ጥሳ ፍጥጫ መፍጠሯ፣ ከዓላማዋ ጀርባ የተሸረበው ሴራ ምን እንደሆነ በሚገባ ግልጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው ግንባር በማፍረክረክ፣ እጇን እንድትሰጥ፣ ወይም ወደ የማትፈልገው ጦርነት ጎትቶ ለማስገባት ነው እየተሴረ ያለው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ይህንን አደገኛ ወቅት በጥበብ ለማለፍ ከመተባበር ውጪ አማራጭ የላቸውም፡፡ የየትኛውም ቡድን ሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ፍላጎት ከአገር ህልውና በታች ተደርጎ፣ የታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ ማክሸፍ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በዕውቀታቸው፣ በገንዘባቸው፣ በሐሳባቸውና በተለያዩ መንገዶች ለአገራቸው በአንድነት መቆም ታሪካዊ ግዴታቸው መሆን አለበት፡፡
ኢትዮጵያ ታሪካዊ አገር ናት ሲባል ያለፈችባቸው ዘመናት ውስብስብ እንደነበሩም መዘንጋት አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሩን ነፃነት ለማስከበር ያደረጋቸው ተጋድሎዎች፣ ለመብቱና ለነፃነቱ ያደረጋቸው ፍልሚያዎች፣ የማንነትና የሐሳብ ብዝኃነት ባለመስተናገዳቸው ሳቢያ የተፈጠሩ ግጭቶች፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከሥልጣኔዋ ተለያይታ ለድህነትና ለተመፅዋችነት የተጋለጠችባቸው አጋጣሚዎችም የታሪኳ አካል ናቸው፡፡ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን በአንድነት በመመከት አንፀባራቂ ታሪክ ያላትን ያህል፣ በውጭ ኃይሎች ሴራና በውስጥ ተላላኪዎች ደባ በእኩልነትና በሰላም መኖር እንዳይቻል ተደርጎ ቅራኔዎችና ፍትጊያዎች የተደረጉባት ናት፡፡ ይህች ታሪካዊት አገር ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረችው፣ በሕዝቧ አርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት መሆኑን ግን መቼም ቢሆን መዘንጋት አይቻልም፡፡ ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ የጋራ እሴቶቹን አስከብሮ በአንድነት የኖረው ደግሞ ለአገሩ በነበረው ወሰን የሌለው ፍቅር ነው፡፡ በዚህ ዘመን የአስተዋዩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተምሳሌታዊነትና አገር በቀል ዕውቀት በማከል፣ ኢትዮጵያን ወደ ታላቅነቷ ለመመለስ ይህ ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የምትደምቀው በልጆቿ አንድነት ነውና፡፡ ልጆቿ አንድነታቸውን አጠናክረው በአንድነት ሲነሱ ማንም አይደፍራቸውም፡፡ አንድነታቸው ሲላላ ግን የታሪካዊ ጠላቶች ሰለባ ይሆናሉ፣ ይህም በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ በዚህ መሠረት አንድነታቸውን አጠናክረው በፅናት መቆም አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያዊነት የሚለመልመውና የሚያብበው ቅራኔ ውስጥ ተዘፍቆ በመኖር አይደለም፣ በመግባባት እንጂ፡፡ በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ ለመግባባት የሚቻለው ግን ሐሳብን በነፃነት መግለጽ፣ መደራጀት፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ መሳተፍና በሕግ የበላይነት ሥር በነፃነት መኖር ሲቻል ነው፡፡ ብሔር፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ባህል፣ የፖለቲካ አቋምና የመሳሰሉ ልዩነቶችን በማጦዝ መቃረን የፈየደው የለም፡፡ ነገር ግን ልዩነቶችን ይዞ በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ በአንድነት መቆም ይቻላል፡፡ በብሔሬ፣ በሃይማኖቴ፣ በቋንቋዬ፣ ወዘተ. በደል ደርሶብኛል እያሉ ከማላዘን በመውጣት በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጥላ ሥር የዘመናት ቅሬታዎችን ማስወገድ ይቀላል፡፡ የአሁኗ ኢትዮጵያ ከብሔር ብሔረሰቦች ብዝኃነት በተጨማሪ፣ የአስተሳሰብ ብዝኃነት የሚነግሥባት እንድትሆን ከአፍራሽ ድርጊቶች መታቀብ ይገባል፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠናከረ ዴሞክራሲያዊት አገር ዕውን የምትሆነው በተከፋፈለና ዓይንህን ለአፈር በሚባባል የጽንፈኝነት አራጋቢነት ሳይሆን፣ አገራቸውን ከልብ በሚወዱ አርቆ አሳቢ ዜጎች ነው፡፡ የፖለቲካውንም ሆነ ሌላውን ልዩነት ወደ ጎን በማድረግ በሰከነ መንፈስ ለመነጋገር ሁሉም ወገን ልቡን በቅንነት ይክፈት፡፡ ተረት ከሚመስሉ አደናጋሪ ትርክቶች በመላቀቅ ለአገር ግንባታ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን ይዞ መቅረብ ያስከብራል፡፡ ለአገር ህልውና የሚጠቅመውም እሱ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሁሉም ልጆቿ እናት እንድትሆን የሚያግዙ ፍሬ ነገሮች ላይ ማተኮር ጠቃሚ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ተሞክረው ፍሬ ያላፈሩት ጽንፈኝነት፣ ጥላቻ፣ ሐሜት፣ አሉባልታና ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ፡፡ እንዲህ ዓይነት አላስፈላጊ ነገሮች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል ሳይቀር፣ ብሔር ተኮር ግጭት በመቀስቀስ ወገኖቻችንን የእሳት እራት ነው ያደረጉት፡፡ ኢትዮጵያ ቧልተኞች፣ ግድ የለሾችና ራስ ወዳዶች የሚፈነጩባት መሆን የለባትም፡፡ ለአገራቸው ግድ የሚሰጣቸው ልጆቿ አንገታቸውን ቀና አድርገው ኃላፊነታቸውን የሚወጡባት ልትሆን ይገባል፡፡ በቡድን እየተደራጁ አገርን መዝረፍ፣ ሕዝብን ማስለቀስ፣ ወጣቱን ተስፋ ማሳጣትና ቀውስ መፍጠር ሊያከትም ይገባል፡፡ የዘመኑ ትውልድ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት የሰፈነባት አገር እንድትኖረው ይፈልጋል፡፡ ይህ ምኞቱ ደግሞ ዕውን የሚሆነው ለአገር የጋራ ጉዳይ በአንድነት መሠለፍ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ያመለጡንን መልካም አጋጣሚዎች በቁጭት እያስታወስን፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ዛሬ የመሥራት ትልቅ ኃላፊነት አለብን፡፡ አገር የምትገነባው በመላ ልጆቿ ያልተቆጠበ ተሳትፎ ስለሆነ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ለሚረከቡ ትውልዶች መሠረት መጣል የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ ቤተሰብ የአገር መሠረት እንደ መሆኑ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በአገር ፍቅር ስሜት ማነፅ አለባቸው፡፡ የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ኅብረተሰቡ፣ ወዘተ. በየደረጃው ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ከቤተሰብ እስከ መንግሥት ድረስ ባሉ መስተጋብሮች የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በአገር ፍቅር ስሜት ከተንቀሳቀሱ የአገር ልማት የጋራ ይሆናል፣ እኩልነት ይፈጠራል፣ ፍትሐዊነት የአገር ወግና ባህል ይሆናል፣ ኢትዮጵያዊነትም ይደምቃል፡፡
ከኢትዮጵያችን ረዥሙ የነፃነት ዘመን፣ ከሕዝቡ አንድ ላይ ለአገሩ ዘብ ከመቆምና መስተጋብር፣ ከኅብረ ብሔራዊነትና አሁን እያጋጠመ ካለው መልካም ዕድል መነሻነት አዲስ ታሪክ ለመሥራት መነሳት ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ እውነተኛ የከፍታ ዘመን እንዲረጋገጥ፣ ሕዝባችን በሰላምና በነፃነት የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ፣ የሐሳብ ልዩነቶች በነፃነት እየተደመጡ አገር የዴሞክራሲ ጮራ እንድትሆን፣ ከአሳፋሪውና ከአሸማቃቂው ድህነት ለመገላገል፣ ዜጎች ከስደት ይልቅ በአገራቸው በመረጡት ሥፍራ እየኖሩና እየሠሩ ሀብት እንዲያፈሩ፣ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ወለል ብሎ ተከፍቶ አማራጭ የሚሆኑ ጠንካራ ፓርቲዎች እንዲኖሩ፣ ከግላዊና ቡድናዊ ጥቅሞች ይልቅ የአገር ጥቅም የበላይ እንዲሆን፣ በሕግ የበላይነት ሥር ፍትሕ ለሁሉም በእኩልነት እንዲዳረስ፣ ከተስፋ መቁረጥ ይልቅ ብሩህ ተስፋ እንዲኖር፣ ወዘተ. አጽንኦት መስጠት ይገባል፡፡ በተለይ የአገሪቱ ልሂቃን ከአሰልቺውና ከኋላቀሩ የፖለቲካ ገመድ ጉተታ በመላቀቅ አገራቸውን ያስቀድሙ፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ የሚፈልጉ ዜጎች እንዲህ ማሰብ ሲጀምሩ ትደምቃለች፣ ታብባለች፡፡ በኢትዮጵያ ላይ በምዕራባውያን እየተደገሰ ያለውን ሴራ በአንድነት ማምከን ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያንን የዓድዋ የጀግንነት መንፈሳቸውን በመስበር ለማንበርከክ የሚፈልጉ ኃይሎችን ምኞት ማክሸፍ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን ከታሪካዊ ጠላቶች ሴራ መታደግ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት መሆን አለበት!