>

ተስፋ የተጣለበት ምርጫ እና የተስፋይቱ ምድር ከነዓን! አሰፋ ሀይሉ

ተስፋ የተጣለበት ምርጫ እና የተስፋይቱ ምድር ከነዓን!

አሰፋ ሀይሉ

 

— ‹‹ምርጫ ምርጫ›› ሲሉ የምሰማቸው የሥልጣን ተስፈኞች፣ የሙሴን እስራኤላውያን የሚያስታውሱን ለምንድነው? 
እስራኤሎች ከፈርዖን ባርነት ወጥተው ከነዓንን ለመውረስ 40 ዓመታት ሙሉ ተሰቃይተዋል፡፡ እና በመጨረሻ አጥብቀው በናፈቋት በከነዓን ምድር ደጃፍ ላይ ደረሱ፡፡ ስለዚህ ሙሴ ለመጨረሻው ድል ሕዝቡን ይዞ ከመነሳቱ በፊት፣ ስለ ከነዓን ልምላሜና ድርቀት፣ ስለ ገዢዎቿ ጥንካሬና ድክመት፣ ስለ ቅጽሮቿና ምሽጎቿ፣ ስለ ሰዉና አፈሩ ሁሉ ሰልለው እንዲመጡ 12 ሰላዮችን ላከ – ወደ ተስፋይቱ ምድር ከነዓን፡፡ እና ሰልለው ተመለሱ፡፡
ከ12ቱ መካከል አሥሩ ያመጡት ሪፖርት ከሞላ ጎደል እንዲህ የሚል ነበር፡- ‹‹በፈጣሪ ቃል የተገባችልን ከነዓን ሁሉ ነገሯ እንደተባለው ያምራል፣ ምድሯ ለምለም ነው፣ ዛፎቿ በፍራፍሬዎች የተሞሉ ናቸው፣ አንዱን የወይን ዘለላ ለመሸከም የአንድ ሰው ትከሻ አይበቃውም፣ ማንጎዎቹ የሰው ጭንቅላት ያካክላሉ፣ ሁሉም ነገር እንደተነገረን ነው›› ካሉ በኋላ በመጨረሻ ግን ከነዐንን ስለመውረስ በተመለከተ የሰጡት ድምዳሜ እንዲህ የሚል ነበር፡- ‹‹የከነዓን ገዢዎች እጅግ ጠንካራና ጦረኞች፣ እጅግ ግዙፍና ኃያላን ናቸው፣ እኛ በእነርሱ ፊት ስንታይ ልክ እንደ አንበጣዎች፣ እነርሱ ደግሞ ልክ እንደ ግዙፋን ጭራቆች ናቸው!››፡፡
ከ12 ሰላዮች መካከል ሁለቱ – እያሱና ካሌብ – በሁሉም ባዩት ነገር ከ10ሩ ሠላዮች ጋር ለዩነት አለነበራቸውም፡፡ ከአንድ ነገራቸው በስተቀር፡፡ ልበ ሙሉዎች ነበሩ፡፡ እምነታቸው የጸና፡፡ በኃይልና በጥበባቸው ተስፋ ያልቆረጡ፡፡ በፈጣሪም ተዓምር አጥብቀው ያመኑ ነበሩ፡፡ እና ስለ ጠላቶቻቸው ግዝፈት ያሉት እንዲህ ነበር፡- ‹‹የገዢዎቹ ግዝፈት፣ ፈጣሪ በእነርሱ ላይ ድልን ሰጥቶን፣ ፈጣሪ ምን ማድረግ እንደሚቻለው ሊያስተምረን የተዘጋጁልን የፈጣሪ ተዓምር ሰርቶ ማሳያዎች ናቸው፣ ቆርጠን ከተነሳን በፊታችን የሚቆም ኃይል የለም፣ እንደምናሸንፋቸው እርግጠኞች ነን፣ እናሸንፋለን፣ ቃል የተገባችልንን የተስፋይቱን ምድርም እንወርሳለን፣ አርባ ዓመት ሙሉ የተሰቃየንላትን ከንዓንን ደጃፏ ላይ ከደረስን በኋላ፣ ገዢዎቿን ፈርተን ወደ ኋላ አንመለስም! በእምነት፣ በአንድ ልብ፣ በፅናት፣ ፈጣሪን አምነን፣ የተስፋይቱን ምድር ለመውረስ እንነሳ!›› አሉ በሚገርም ወኔ ተሞልተው፡፡
ሌሎቹ አሥሩ ሰላዮች የሁሉንም ነገር እውነትነት አምነው ተቀብለው እያለ፣ የያዛቸው ፍርሃት ግን ከሚጠብቃቸው ቆራጥ ትግል እንዲሸሹ አደረጋቸው፡፡ ፍርሃት ሰቅዞ ያዛቸው፡፡ ጦርነትን ፈሩ፡፡ ድል የእኛ ሊሆን አይችልም አሉ፡፡ ራሳቸውን እንደ አንበጣ ቆጠሩ፡፡ እና ገና ሳይዋጉ እጅ ሰጡ፡፡
መጨረሻው ብዙዎቻችን የምናውቀው ነው፡፡ ከ12ቱ ሠላዮች መሐል የተስፋይቱን ምድር ለመውረስ የበቁት እነዚያ በእምነታቸው የፀኑት ሁለቱ ብቻ ነበሩ፡፡ በፍርሃትና ተስፋ መቁረጥ ተሸብበው የእስራኤልን ህዝብ ከቃልኪዳን ምድሩ ሊያናጥቡት የቆሙት አሥሩም ሰላዮች በመቅሰፍት ነበር የተመቱት፡፡ አስሩም ሳይውሉ ሳያድሩ ህይወታቸው ተቀጠፈ፡፡ 40 ዓመት በበረሃ ስቃይ ባዝነው – በመጨረሻው የትግል ምዕራፍ እምነት በማጣታቸው፣ በፍርሃት በመራዳቸው የተነሳ – የጎመጇትን ከነዓንን ለማየት ሳይታደሉ ቀሩ፡፡
በጣም የሚገርሙኝ – ገና ከነዓንም ሳይደርሱ ራሱ – በዚያ የ40 ዓመት የእስራኤላውያን የነፃነት ጉዞ መሐል – በተደጋጋሚ ሙሴን – ለረሃብና እርዛት ነው ወይ ከፈርዖን ቤት ያወጣኸን? – ቢያንስ ፈርዖን ቤት እያለን እኮ እያንዳንዱ ቀናችን የሰላም ቀን ነበረ – ቢያንስ ካለፍ ገደም ሥጋና ጮማ እንቆርጥ ነበር – አሁን በረሃብ አለንጋ እየተገረፍን ነው – ጉዟችን በመቅሰፍትና ስቃይ የተሞላ አስመራሪ ሆኖብናል – ስለዚህ ከነዓንን መውረስ አንፈልግም፣ ይቅርብን – የነበርንበት የፈርዖን ባርነት ይሻለናል – ወደ መጣንበት መልሰን፣ ማናውቃት ከነዓን ትቅርብንና፣ ከምናውቀው ፈርዖን ጋር በሠላም እንኑርበት! – እያሉ የሚያማርሩና በሙሴ ላይ ተደጋጋሚ አመጽ የሚቀሰቅሱ ነበሩ፡፡ እነዚህም ከነዓንን አልወረሷትም፡፡
አሁን በኢትዮጵያ የማያቸውን የምርጫ አዳማቂዎች፣ የሥልጣን ተስፈኞችና የሠላም ዘማሪዎችም ደግሜ ደጋግሜ ባሰብኳቸው ቁጥር ደግመው ደጋግመው እነዚያን ሙሴ ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ከንዓንን ሊያወርሳቸው ያወጣቸውን የፈርዖን ናፋቂ እስራኤላውያንና አሥሩን የከንዓን ሰላዮች እየመሰሉኝ ተቸግሬያለሁ፡፡
እነዚህ በጎሰኞቹ መንግሥት ውስጥ ገብተን የሥልጣንና ጥቅም ተቋዳሾች እንሆናለን ብለው የቋመጡ የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች፣ ብዙዎቹ ሲናገሩ የኖሩትን በተመስጦ ሳደምጥ ነወ የኖርኩት፡፡ እና ብዙዎቹ በወያኔ የተተከለው ይህ የጎሰኞች ሥርዓት እስካለ በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ‹‹ምርጫ›› እንደሌለና ሊኖርም እንደማይችል አሳምረው የሚያውቁ ናቸው፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ ያለው ‹‹የጎሰኞች ቅርጫ›› እንጂ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫ›› እንዳልሆነም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡
ህገመንግሥቱ ሀገራችንን የጎሰኞች መፈንጫ ያደረገ ህገመንግሥት መሆኑንም አይክዱም፡፡ እያንዳንዱ የመንግሥት አካልና የሀገሪቱ የፍትህ፣ የዳኝነትና የዲሞክራሲ ተቋማት በሙሉ በጎሰኞቹ ኢህአዴጋውያን ቁጥጥር ሥር እንዳሉም አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ኢህአዴጋውያኑ ስማቸውን ቀየሩም አልቀየሩም ያው የቀድሞዎቹ ጎሰኞች መሆናቸውንም ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ ኢህአዴጋውያኑ ‹‹ምርጫ›› እናድርግ ሲሉ – በትክክል እያሉ ያሉት – ‹‹ያንን ሕዝባችንን በዘር ሸንሽኖ እያባላ ያለውን የወያኔ የጎሰኞች ወንጌል በሠላም ተስማምተን እናስቀጥል!›› ማለታቸው መሆኑንም ጠንቅቀው ይረዳሉ፡፡
እነዚህ የወያኔ-ኢህአዴግን ሥርዓት እንታገላለን ብለው ላለፉ 30 ዓመታት ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩ የኢትዮጵያችን ተቃዋሚዎች – ሀገራችን በጎሰኞቹ መዳፍ ተጨብጣ – ስለ እውነተኛ ምርጫ ማውራት እንደማይቻል ያምናሉ፡፡ ሁሉም በየጎሳ ሰገባው ተሸንሽኖ – ጎሳውንና የጎሳውን ግዛት ነፃ አውጥቶ በመሣሪያና መንግሥታዊ ሠራዊት አለሁ ባይነት ሀገር ምድሩን በጎሰኞች የተቆጣጠረበት ሀገር በትክክለኛ ትርጓሜው ‹‹አንድ ሀገር›› ተብሎ ለመጠራት የማይበቃ፣ እና ሀገራችን መልሰን ‹‹ሀገር›› ለማድረግ ገና ብዙ ፈተና፣ ገና ብዙ ዕዳ፣ እና ገና ብዙ ትግል እንደሚጠብቀንም ከማናችንም በላይ ያውቃሉ፡፡
የኢትዮጵያ የሥልጣን ተስፈኞች (ማለቴ የተቃዋሚ ፖለቲከኞቻችን) በየቦታው የንጹሃን ወገኖቻችን አሰቃቂ እርድ፣ እና የጅምላ ግድያ እንደ አሸን የፈላበት ጊዜ ላይ እንደምንገኝም አያስተባብሉም፡፡ የተለያዩ የጎሳና የነገድ ነፃ አውጪዎች መንግሥት ሆነው የሀገራችንን ብዙውን ድንበር እንደተቆጣጠሩም ዘወትር የሚወተውቱት ጉዳይ ነው፡፡ በጎሰኞቹ ቁጥጥር ሥር በዋሉት የሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተቃዋሚ እንደማይገባ፣ ትንፍሽም ማለት እንደማይችል ያውቃሉ፡፡
በሆሮ ጉድሩ  ላይ ንፁሃን ዜጎች አማሮች እየተባሉ እየታረዱ መሆናቸውን ያውቃሉ፡፡ ደምቢዶሎና ነቀምት፣ ባሌና አርባጉጉ፣ መቀሌና አድዋ፣ ወይም ሐረርና ጂጂጋ ሄዶ ኢህአዴጋውያኑንና ጎሰኛ የአፓርታይድ ሥርዓታቸውን እያወገዙ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ሠላማዊ ሠልፍ ማድረግ፣ በነፃነት መሰብሰብም ሆነ በህዝብ ሚዲያዎች መገልገል በህልም ዓለም እንጂ በእውኑ ዓለም የማይታሰብ መሆኑንም አይክዱም፡፡
የኢትዮጵያችን ነባር ጠላቶች፣ የባንዲራችን ጠላቶች፣ የኢትዮጵያዊነት ፀሮች፣ በወያኔ በተተከለላቸው ጎሰኛ የአፓርታይድ ሥርዓት ተገንነት ራሳቸውን አደራጅተው – ለባለፉት 30 ዓመታት – የኢትዮጵያን ግዛት ሁሉ ከዳር ዳር ተቆጣጥረው እንዳበቁ በትክክል ይገነዘባሉ፡፡ ጎሰኞች መንግሥት ሆነው የኢትዮጵያን ሕዝብ ባንኩንም ታንኩንም የተቆጣጠሩበት ጊዜ ላይ መሆናችንንም አይክዱም፡፡ ወያኔ የዚህ ሥርዓት ዋነኛ ፈጣሪና ጠባቂ ሥለሆነች ወያኔ መቀበር እንዳለባትም አስረግጠው የተማማሉበት ቃል ኪዳናቸው ነው፡፡
እንግዲህ ከላይ ያልናቸውን ሀገራዊ እውነታዎች ሁሉ የሚያውቁ፣ የሚናገሩ፣ የሚሰብኩና፣ የሚያምኑ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በተግባርስ ምን እያደረጉ ነው? ብለን ስናይ የምናገኘው ምስል ተቃራኒውን ነው፡፡ ወያኔን የሚጠሉት ተቃዋሚዎች ወያኔ በፈጠረችላቸውና እንቃወመዋለን በሚሉት የጎሳ ሥርዓት ውስጥ ተንጋግተው ገብተው፣ ምርጫ ምርጫ እያሉ ሲያዳምቁ ነው የምናገኛቸው፡፡ እንፀየፈዋለን በሚሉት ሥርዓት ውስጥ እና ከዋና ከተሞች እልፍ ሳይሉ በሚወራጩባት የምርጫ ከባቢ ውስጥ ሆነው – የኢህአዴጋውያኑን ሃሳዊ የዲሞክራሲ ሆያሆዬ አብረው ሆ እያሉ ሲያጫፍሩና ሲያጋፍሩ ነው የምናገኛቸው፡፡
ህሊናና እውነት፣ ይሉኝታና ሃፍረታቸው ሞቶ ተቀብሯል፡፡ ሁሉንም እውነት አውቀውት፣ ሁሉንም ነገር ተረድተውት አንድ ነገር ብቻ ግን ርቋቸዋል፡፡ ወኔያቸው ከድቷቸዋል፡፡ ይህን የጎሰኞች ሥርዓት ፊት ለፊት ቆሞ ለመቃወም፣ እና ሕዝባቸውን ከጎናቸው አሰልፈው ለመታገል ወኔ አንሷቸዋል፡፡ ስለዚህ ወያኔ ባዘጋጀችላቸው የጎሳ ከረጢት ገብተው እየተንደፋደፉ፣ ወያኔን እየተራገሙ፣ በዚያው ጎሰኛ ህገመንግሥትና ጎሰኛ ሥርዓት ውስጥ ዋኝተው ለመውጣት ይፍገመገማሉ፡፡ በፍርሃት አርቀው ቀብረውት የቆዩትን የሥልጣን አምሮት – አሁን ጎሰኞቹ በከፈቱላቸው ቀጭን ቀዳዳ በኩል ሾልከው እውን ማድረግ ይቻለናል የሚል የፈሪ ሎጂክ ፈጥረዋል፡፡ እውነተኛ ሕዝባዊ ትግል ከማድረግና የሚያምኑትን አይዲያል እውን ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ፣ ወኔ የማይጠይቀውንና ቀላል ሆኖ ያገኙትን ወያኔን እየረገሙ፣ ነገር ግን የወያኔ የዘር ቅርጫ ያመጣላቸውን የሥልጣን ሲሳይ ምራቃቸውን እየዋጡ መጠባበቁን መርጠውታል፡፡
እነዚህ አሁን ‹‹ምርጫ ምርጫ›› ሲሉ የምናገኛቸው ወኔ ቢስ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች – የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 30 ዓመታት ተቋቁሞ ታግሎና ገፍቶ አንገዳግዶት የነበረውን፣ እጅግ የጠላውንና የኮሰኮሰውን ይህን የጎሰኞች ሥርዓት – በውድቀቱ ዋዜማ ላይ ተንጋግተው መጥተው – በህዝቡ የትግል ፍላጎትና ቁጣ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሰው – እኛ አለንልህ ለውጥ መጥቶልሃል ብለው በውሸት ተስፋና ቅዠት ህዝቡን አደንዝወው፣ ለህዝባቸው ግንባር ቀደም ሆነው ለመሰለፍ የደፈሩ ጀግኖችን አሳስረውና አስገድለው – እነሱ ከጎሰኞቹ ጋር ተሞዳሙደውና ተስማምተው – ምርጫ ምርጫ እያሉ – የጎሰኛውን ሥርዓት የሥልጣን ብፌ ለመዝረፍ ክፉኛ ተርበው ማየት ከምንም ውርደት በላይ በከፋ መልክ አንገትን በሀፍረት ያስደፋል፡፡ ያሳቅቃል፡፡ ያሳፍራል በእውነት፡፡
የኢህአዴጋውያኑ ሥርዓት በህዝብ ምሬትና አመጽ ተንገዳግዶ ለመውደቅ አንድ ሀሙስ ሲቀረው – እግር ተወርች ያሰረንን የጎሰኞች ሥርዓት ከላያችን አሽቀንጥሮ – የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘውንና ተስፋ ያደረገበትን ከጎሰኞች የተላቀቀ ሥርዓት እውን ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ ተሰባስቦ በመታገያው ሰዓት – በዚህ ኢህአዴጋውያኑ በሚፍገመገሙበት በመጨረሻው ሰዓታችን ላይ – በፍርሃት ተሸብበው – ወኔያቸው ከድቷቸው – ከጎሰኞቹ ገዢዎች ጋር ገጥሞ ድል ማድረግን በእጅጉ የፈሩት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች – ሁለነገራቸውን እና የህዝባቸውን የዘመናት ፍላጎት ሁሉ ገደል ጨምረው – እጃቸውን አጣጥፈው – ለጎሰኞቹ ገዢዎች እጅ የሰጡበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ መገኘታችን አንገት ያስደፋል፡፡
ወኔ ከድቶናል፡፡ ራሳችንን አንኳሰን፣ እምነት የጣለብንንም ሕዝብ አንኳሰነዋል፡፡ በምንፀየፈው ሥርዓት መውደቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሰን፣ የምንፀየፈውን ሥርዓት አስቀጣዮች ሆነን፣ የክህደት ወንጌል ሰባኪዎችና አስፈጻሚዎች ሆነናል፡፡ የፈጣሪን ሃይል፣ የህዝብን ሃይል፣ የራሳቸውን ሃይል የካዱ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ኃይሎች – የተጠላና የተተፋውን የኢህአዴጋውያን ጎሰኛ ሥርዓት በፍቃደኝነት ተለማምጠው፣ በጎሰኞቹ ምርጫ ከጎኑ ቆመው፣ በሠላምና በልምምጥ እንቀይረዋለን ብለው ተነስተዋል፡፡ ባይቀይሩትም ደንታቸው አይደለም፡፡ የሠላም ሰባኪዎች ሆነዋል፡፡
ኢህአዴጋውያኑ ጎሰኞች ካስፈለጋቸው 100 ዓመት ይግዙን! ሠላማችንን ለምን እናጣለን? ቢያንስ ያገኘናትን ትርፍራፊ ድምጽም ቢሆን ይዘን ብንቀጥል ይሻላል ከጎሰኞቹ ጋር፡፡ ያለው ይኸው ነው፡፡ ወኔው የተሰለበ የፈሪ ቀመር፡፡ የፈሪ ነገር፡፡ የፈሪዎች ወንጌል፡፡ ፍርሃት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ግን ፍርሃት በሀገር ላይ ሲሆን እጅግ ያሳፍራል፡፡ ያሸማቅቃል፡፡ ነውርም ነው፡፡ በፈሪዎች የሚመራ ሕዝብ መቼውኑም ድልን አያይም፡፡ አንገት አስደፊው እውነት ይህ ነው፡፡
ፍርሃትና ወኔ ቢስነት ወደ የትም አያሻግረንም! የሚያሻግረን ዕምነት፣ ፅናት፣ ወኔና ልበሙሉነት ብቻ ነው፡፡ በሕዝባችን፡፡ እና በፈጣሪ ኃይል፡፡
«Fear does not advance the kingdom of God, but faith does. We can “conquer ‘Promised Lands’ when we have regard for our talents and believe in our creative powers. The sin of the spies grows from their failure of self-love and self-respect…Only Joshua and Caleb, who refuse to see themselves as ‘grasshoppers,’ are worthy of entering the Promised Land”» (A Torah Commentary for Our Times, 1993, p. 42).
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic