>

የአንድ ሰው ሰላማዊ ሰልፍ - በሽመልስ ለገሰ...!!! ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ

የአንድ ሰው ሰላማዊ ሰልፍ – በሽመልስ ለገሰ…!!!

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ

ሽመልስ ለገሰ የእነ እስክንድር ነጋን እስር ብቻውን ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት እየተቃወመ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ አቶ ሽመልስ ለገሰ ካለፈው ሰኞ የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሚኖርበት አሜሪካ ብቻውን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እያደረገ ነው። በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች ማለትም እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ከወህኒ ቤት እንዲወጡም በሰላማዊ ሰልፉ ጠይቋል። አመራሮቹ የታሰሩት ለእውነት በመሥራታቸው፣ ለአዲስ አበባ ሕዝብ ሰላምና እኩልነት በመታገላቸው እንደሆነም ጠቁሟል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ብቻውን ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ሽመልስ የመጀመሪያው ሰው እንደሆነ ይገመታል።
በስቴት ዲፓርትመት በር ላይ በየዕለቱ ለአራት ሰዓታት የሚያደርገው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ በመጭዎቹ ቀናትም ይቀጥላል። በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች ሰዎች ሰልፉን እንዲቀላቀሉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ጥሪ አቅርቧል። ሽመልስ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረባቸው ጊዜያትም በአዲስ አበባ የሚደረጉ የዜጎች መኖሪያ ቤቶች ፈረሳን፣ የኦሕዴድ/ብልፅግና የመሬት ወረራን፣ የቅርሶች ውድመትን፣ ሕገ ወጥ የመታወቂያ እደላን እና ሌሎች መንግሥታዊ ውንብድናዎችን ሲያጋልጥና ሲከላከል ቆይቷል። ለዛሬው የፖለቲካ ፓርቲ መሰረት የሆነው የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ጋዜጣዊ መግለጫዎችንና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንዳያካሂድ በአንባገነኖች ሲከለከል በነበረበት ጊዜ ከፊት ሆኖ ሕገ ወጥ ፖሊሶችን በመጋፈጥ ይታወቃል።
Filed in: Amharic