>
5:18 pm - Wednesday June 14, 5200

መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠው የዘር ማጥፋት ወንጀል እና የምርጫ ቦርድ አሻጥር አስመልክቶ ከባልደራስ የተሰጠ የአቋም መግለጫ !

መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠው የዘር ማጥፋት ወንጀል እና የምርጫ ቦርድ አሻጥር አስመልክቶ ከባልደራስ የተሰጠ የአቋም መግለጫ !
1ኛ. ከሁሉ አስቀድመን፣ በአገራችን ምዕራብ ኦሮምያ ክልል፣ ወለጋ ውስጥ፣  በሆሮጉድሩ ወረዳ  ውስጥ ከየካቲት 27 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ በተፈጸመ ጥቃት ከ60 በላይ ንጹሃን  ዜጎች በኦህዴድ/ብልጽግና ይሁንታ እና በኦነግ ሸኔ አድራጊነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ ለሆኑ የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን ባልደራስ ይገልጻል፤ የሟቾችን ነፍስ ፈጣሪ በአጸደ ገነት ያኑርልን፡፡ ለውድ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው  መጽናናትን  እንመኛለን፡፡ ፓርቲያችን በአማራ እና በሌሎች ንጹሃን ዜጎች ላይ ሆነ ተብሎ ለሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ኦነግን ከኤርትራ በረሃ ወደ አገር ቤት ከነትጥቁ እንዲገባ ያደረገው፣ በኦሮምያ ክልል  ጸጥታ መዋቅር ውስጥ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ እንዲካተት ያደረገው እና በመንግሥታዊ ስልጣኑ ሽፋን በመስጠት ለዚህ አሸባሪነት ደረጃ የዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳድር ከማንም በላይ ተጠያቂ እንደሆነ ፓርቲችን ባልደራስ በጽኑ ያምናል፡፡
ይሄንን አረመኔያዊ ወንጀል የፈጸሙ እና እንዲፈጸም ያደረጉ ሁሉ በፈጣሪም ሆነ በምድሩ ሕግ የሚጠየቁበት ጊዜ እሩቅ አይደለም ። ፓርቲያችንም ለዚህ እውን መሆን በትጋት እንደሚሰራ መግለጽ ይወዳል፡፡ በኦሮምያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ሳያቋርጥ ለባለፉት 3 ዓመታት የቀጠለው የዜጎች ሞት እና መፈናቀል ክልሉን እየመራ ያለው ኦህዴድ/ብልጽግና፣ በተረኝነት አገርን ከመዝረፍ ውጪ  መምራት እንደማይችለ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ሃቅ ነው፡፡ ይህ ኃይል  ተጨማሪ ዓመታትን በስልጣን ላይ ሲቆይ አገራችን ኢትዮጵያ  ወደማትወጣበት ውስጣዊ እና አከባቢያዊ ገደል ውስጥ ይዞ የሚገባ ስለሆነ በቃ ሊባል የሚገባበት ምእራፍ ላይ ደርሰናል፡፡
ይህን መሰል በዜጎች ላይ የሚፈጸም ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ንብረት ማውደም እና ዘራፍ ከምንም በላይ መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠው እንዲህ አይነቱ ዕኩይ ተግባር ባለበት ሁኔታ፤ የዘንድሮ ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ መንግስት ጸጥታ የማስጠበቅ እና የዜጎችን ደህንነት ፣ የፖለቲካ ኃይሎች በሰላማዊ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚኖራቸው  እንቅስቃሴ አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑ ፓርቲያችን ይገነዘባል። በተጨማሪ መንግስት እንዲህ አይነቱ ደተኝነት የሚያሳየው በሥልጣን ለመቀጠል ካለው የሥልጣን ጥምኝነት ብሎ ፓርቲያችን ያምናል፡፡
2ኛ. የፓርቲያችን ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ እና ሌሎች ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች በተረኛው ኦህዴድ/ብልጽግና መራሹ መንግሥት ከሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ በግፍ እስር ላይ ያሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እነ እስክንድር ነጋ ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ኦህዴድ/ብልጽግና ምስክሮችን በግልጽ አቅርቦ ሊያስመሰክርባቸው እንዳልቻለ የፍርድ ሂደቱን የሚከታተለው መላው የአገራችን ህዝብ ያውቀዋል፡፡
እነ አቶ እስክንድር ነጋ አላግባብ ለእስር የተዳረጉት የፈጸሙት አንዳች የሚያስጠይቅ ነገር ኖሮ ሳይሆን፣ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ እንዳይሳተፉ ፓለቲካዊ ውሳኔ ተሰጥቶ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ፍርድ ቤቶችን በኃሳብ የበለጠውን ለማጥቂያነት መጠቀምን ከህወሃት/ትህነግ የተማረው ደቀ መዝሙሩ ኦህዴድ/ብልጽግና፣ ከትህነግ አሳዛኝ ፍጻሜ ምንም የተማረው ነገር ስለሌለ ተመሳሳይ የታሪክ ፍጻሜን ለመድገም እየተንደረደረ እንደሆነ የሚያሳይ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ይህ ፍትህ ስርዓቱ መሣሪያነት አመራሮቻቸን ላይ የሚደርሰው በደል ሳያንስ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እነ አቶ እስክንድር ነጋ ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ በባልደራስ ፓርቲ ስም እጩ ሆነው እንዳይቀርቡ የሰጠው ውሳኔ አመራሮቻችንን ከገዢዎች ጋር ተደርቦ እንደማጥቃት አድርገን ቆጥረነዋል፡፡ በእነ አቶ እስክንድር ነጋ የፍርድ ሂደት ላይ የሚሳለቀው ዐቃቤ ሕግም ሆነ ይሄን ሰበብ አድርጎ የመመረጥ መብታቸውን በከለከለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መካከል ልዩነት ለማየት አይቻልም፡፡
ባልደራስ አቶ እስክንድር ነጋን በፓርቲው ስም እጩ አድርጎ በየካ ምርጫ ወረዳ አቅርቧቸው የነበረ ቢሆንም በ20/06/2013 ዓ/ም በተጻፈ ውሳኔ በሕግ ጥላ ስር ስለሆ በእጩነት መቅረብ እንደማይችሉ አሳውቆናል፡፡ ፓርቲው በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት በሕጉ መሠረት አቤቱታችንን ያቀረብንለት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤትም በ29/06/2013 ዓ/ም ለቅሬታችን በጽሁፍ በተሰጠው ውሳኔ በተመሳሳይ መልኩ በእጩነት መቅረብ እንደማይችል ምላሽ ሰጥቶናል፡፡
ነገር ግን፣ የእጩዎችን መስፈርት የሚያስቀምጠው “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር” አ/ቁ. 1162/11 አንቀጽ 31(1)(ሠ) “ማንኛውም ሰው በሕግ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብቱ ያልተገፈፈ” እንደሆነ በእጩነት መቅረብ እንደሚችል በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 20(3) መሠረት የተከሰሱ ሰዎች “በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር” ወይም ንፁህ ሆኖ የመገመት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ይሄ መብትም ዓለማቀፍ ተቀባይነት ያለው እና አሁን ዓለም በደረሰበት ደረጃ ክርክር የሚነሳበት አይደለም፡፡
ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለእነ አቶ እስክንድር ነጋ ብቻ የሚሰራ ሕግ ያለ እስኪመስል ድረስ፣  ያለውን ግልጽ ሕግ ወደጎን በመተው እነ እስክንድር ነጋ በምርጫው እንዳይወዳደሩ የመመረጥ ምብታቸው ላይ እራሱን እንደ ፍ/ቤት በመውሰድ የሰጠው ውሳኔ፣ ቦርዱን እንደተቋም ያለውን ተዓማኒነት በእጅጉ የሚጎዳ እንደሆነ ተረድተናል፡፡ ቦርዱ በ2007 ዓ/ም ከነበረው የፕ/ሮ መርጋ በቃና አመራር ኮምፒውተራይዝድ ከመሆን ባለፈ ያለውን ፖለቲካዊ ጫና ተቋቁሞ ወገንተኝነቱን ለእውነት ብቻ እንደሆነ ለማሳየት ተስኖታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የቦርዱ ውሳኔ፣ የ6ኛውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ እና ገለልተኛነት በጥያቄ ምልክት ውስጥ እንድንከት አድርጎናል፡፡ ይሄ ከብልጽግና ጋር በመናበብ የተደረገ የሚመስለው  የቦርዱ እርምጃ፣ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነ ባልደራስ ያምናል፡፡ በሕግ ጥላ ያሉ ዜጎችን የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ያለምንም የፍ/ቤት ቤት ውሳኔ መግፈፍ የጀመርነውን የዴሞክራሲ ጉዞ ያጨነግፈው እንደሆነ እንጂ የሚያጎለብተው አይሆነም፡፡ ለአቶ እስክንድር ነጋ የተመዘዘ የክልከላ ካርድ ነገ በማናቸውም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ጥርጣሬ የለንም፡፡ በእነ አቶ እስክንድር ነጋ ዴሞክራሲያዊ መብት መገፈፍ ላይ ከገዢው ፓርቲ እኩል ምርጫ ቦርድ የወሰደው አቋም የማይተካ ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ በዚህ ታሪካዊ የስህተት ውሳኔው፣ ቦርዱን እንደተቋም የማውረድ ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ በአገራችን ለሚከሰተው  ችግር ቦርዱ እራሱ አንድ ምንጭ እንደሆነ ፓርቲያችን ያምናል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርቲያችን እየተፈጸመ ያለውን በደል ለሕዝብ ይፋ ከማድረግ ባሻገር፣ ወደ መደበኛ ፍ/ቤት በመወሰድ ለተቋቋሙት ልዩ የምርጫ ችሎቶች በገለልተኛነት ፍርድ እንደሚሰጡ ወይም በገዢው ፓርቲ ረጅም እጅ የተጠለፉ መሆናቸውን መፈተሽ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በምርጫ ቦርድ ያለውን ሂደት በሙሉ ጠብቆ የጨረሰው ፓርቲያችን በቀጣይ ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ የፍትህ ተቋሙን ገለልተኝነት ከወዲሁ ለመፈተሽ ወስኗል፡፡
እስክንድር ነጋ ፣ ስንታየሁ ቸኮል ፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደምሌን ነጻ አስወጥቶ በአገራቸው የፖለቲካ ጉዳይ ተሳታፉ እንዲሆኑ ፓርቲያችን እያደረገ ያለው ትግል ሁሉንም ተቋማቶቻችንን በማጋለጥ ይቀጥላል፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ተከብራ ትኖራለድ 
ድል ለዲሞክራሲ!!!
Filed in: Amharic