>

የእንባው ጀግንነት መጀመሪያ! - የእርዱ ጀግንነት ማብቂያ ደወል - አይሰማም ወይ...???  (አሰፋ ኃይሉ)

የእንባው ጀግንነት መጀመሪያ! – የእርዱ ጀግንነት ማብቂያ ደወል – አይሰማም ወይ…???
አሰፋ ኃይሉ

 

*… ይህቺ «ታላቋ ኦሮሚያ» የምትባል ሀሺሻዊ ምኞት፣ ከአርባጉጉና በደኖ ጀምሮ ሠላማዊ ሰዎችን እያረዱና እርጉዝ እየተለተሉ እንዲኖሩ አድርጋቸዋለች፡፡ ይህቺው «ታላቋ ኦሮሚያ» የተባለች ‹‹ላም-አለኝ-በሰማይ-ወተቷንም-አላይ›› የሆነች የህልም ሀገር – እውነተኛውን የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ አምነው እንዳይቀበሉና በህግና በሥርዓት እንዳይገዙ አድርጋቸዋለች…!
ይሄ ያልታጠቁ ንፁሃንን እየገደለ ‹‹ጀግና ጀግና›› እየተጫወተ ያለው የኦሮሙማው ጨፍጫፊ ቡድን፣ አንድ ቀን እውነተኛው ጦርነት የተለኮሰ ቀን፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ከጎኑ ያሰለፋቸውን የራሱን ጎሳ ወጣቶች ህይወት በጥይት አስበልቶ እንደሚቀበር ሳስብ፣ እየሆነ ካለው ይልቅ፣ ገና ወደፊት ስለሚሆነው ያስጨንቀኛል፡፡
ይህ በኦሮሚያና አጎራባቾቹ ተሰማርቶ ጦርነት ባልዋለበት ባዶ ሜዳ እንደ አይጥ በየሰዉ ጓዳ እየተሹለከለከ የአማራ ንጹሃንን እየፈጀ የሚገኝ አጉራ ዘለል ቡድን፣ እውነተኛ ጦርነትና ጦረኝነት ምን እንደሚመስል፣ ጀግና ማለት ምን እንደሆነ በምሬት እየተንገፈገፈ የሚረዳበት ቀን ሩቅ አይመስለኝም፡፡ በራሱ አራጅ እጅ ፍጻሜውን እያቀረበው እንደሚገኝ ሳይ፣ ነገና ከነገ ወዲያ ጦርነት ሲለኮስ፣ ስንት ነገርን ለራሱና ለደሃ ቤተሰቡ፣ ለሀገሩ ለወገኑ መስራት ይችል የነበረውን ወጣት አብሮት ይዞት መጥፋቱ እንደማይቀር እያሰብኩ እሳቀቃለሁ፡፡
ተባብሶ በቀጠለው የአማራ ንፁሃን ፍጅት በኦሮሙማው ‹‹መንግሥት›› በኩል እየተሰጠ ያለው የጆሮ-ዳባ-ልበስ ምላሽ፣ እና ለጨፍጫፊው ኃይል ሽፋንና አጋዥ የመሆን አዝማሚያ፣ በቅርቡ የመከላከያ ሠራዊቱን በመክፈልና በማፈራረስ፣ ሀገር እመራለሁ ብሎ እየተንደፋደፈ ያለውን ወትሮም ቋፍ የደረሰውን ኢህአዴጋዊ ስብስብ ሳያፈራርስ እንደማይቋጭ፣ ወይ በትክክል የገባው አልመሰለኝም፣ ወይ ደግሞ አውቆ ያ እንዲሆን ተዘጋጅቶ እየሠራ ነው፡፡
አሁን የሚታየው ልኩን ያለፈ ጭካኔና መቅበዝበዝ ሁሉ የሚያሳየው፣ ኦሮሙማዎቹ በወያኔ ዘመን ያለ ከልካይ ሲጋልቡበት የኖሩትን ጋጠወጥ ፀረ-ሀገር የጎሰኝነት ፈረስ፣ ከነሚረጩት የጥላቻ መርዝ ከእጃቸው ላይ ሊቀሙ፣ ጥቂት መንገድ ብቻ እንደቀራቸው እየባነኑ የመምጣታቸውን ጉዳይ ነው፡፡ ከወያኔ ውድቀት ማግስት ከልካይ የሌለው የጎሰኝነት አገዛዛቸው አብሮ ወደ ማክተሚያው እንደሚሄድ እየፈሩ በመጡ ቁጥር፣ በወያኔ ውደቀት የመጸጸትና የመወራጨት ድባብ ውስጥ እየገቡ እንደሄዱ በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡
ገዳዮቹና አስገዳዮቹ፣ አንድ ማወቅ ያለባቸው ነገር፣ ያውም በዘር አማራውን ብቻ እየመረጡ ሠላማዊ ንጹሃን ዜጎችን መግደል፣ ጀግንነት ሆኖ ሌላው እንዲፈራቸውና የያዙትን የዘረኝነት መብት አክብሮ እንዲቀጥልላቸው የሚያደርግ ሳይሆን፣ የተላበሱትን እጅግ አስነዋሪና ወራዳ ሰብዕና አደባባይ በማውጣት – ሁሉም እንዲተባበርባቸው የሚያደርግ መሆኑን ነው፡፡
እነዚህ ኦሮሚያን በቅርቡ እንገነጥላለን ብለው የሚያልሙት የኦሮሞ አክራሪ ቡድኖች፣ እና የኦሮሙማውን መንግሥት ከተቆጣጠሩ የሃሳብ አጋሮቻቸው ጋር በብዙ መልክ እየተናበቡ እንደሚንቀሳቀሱ ከብዙ ግብረአበራዊ ድርጊቶቻቸው ማየትና መረዳት ይቻላል፡፡
የኦሮሞው «ነጻነት» የፖለቲካ ክንፍ በአንድ በኩል የኢትዮጵያን መንግሥት መዋቅር (ባንክና ታንኩን ጨምሮ) ተቆጣጥሮ፣ ሌላውን ሕዝብ ከትግሉ ሜዳ ማዘናጋትና መደለልን ጨምሮ ማንኛውንም ለነጻዋ ኦሮሚያ ህልም እውን መሆን የሚያግዙ ጥርጊያ መንገዶችን ያመቻቻል፡፡
ወታደራዊው ክንፍ ደግሞ በማናቸውም መንግሥታዊ ጭምብል (ፖሊስ፣ ልዩ ሃይል፣ መከላከያ፣ ሚሊሻ፣ ካድሬ፣ ንቅናቄ፣ ህዋሰ፣ ወዘተ.) ተጠቅሞ ያቺን የህልም «ኦሮሚያ» ነጻ የሚያወጣ ጦር እያደራጀ ነው፡፡ እያደራጀ ብቻ ሳይሆን ከኦሮሙማው መንግሥታዊ የፖለቲካ ክንፍ ጋር እየተናበበ ከፍተኛ የህዝብ ተቀባይነት በሚያስገኙለት የንጹሃን አማራ እርዶች፣ የጦር ልምምዶችና የኦነግ ባንዲራ ሥነሥርዓቶች፣ እንዲሁም ግልጽ ግዛቶችን በመቆጣጠር እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሰማርቶ እናገኘዋለን፡፡
እነዚህ የኦሮሞ ተባባሪ ክንፎች – የነፃነት ጉዟቸውን ይጠርግልናል ብለው እስካሰቡ ድረስ – በህልም ግዛታቸው ውስጥ የሚገኝን ማንኛውንም ሌላ ዘር – በተለይ አማራውን – የማፅዳትና የማፈናቀል ተግባርን ጨምሮ፣ ማንኛውንም መስዋዕትነት ከፍለን፣ እጅና ጓንት ሆነን እየተረዳዳን ወዳለምነው «ነፃዋን ኦሮሚያ» የመመሥረት ግባችን እየቀረብን ነው ብለው ነው የሚያስቡት፡፡ ብዙው የኦሮሞ ልሂቅ ጠጋ ብለህ ብትጠይቀው በስሜት ተውጦ የሚነግርህ ከኦሮሚያ ሀገር ምሥረታ የስንዝር ታህል ርቀት ላይ እንደሚገኙ ነው፡፡ ከልሂቁ እስከ ደቂቁ እየተሳተፈበት ያለው የጊዜያችን ‹‹የኦሮሚያ ነፃአውጪ ሰደድ›› ሀገሩን ከአማሮችና ከሌሎች ተቀናቃኞች የማፅዳት እንቅስቃሴ ላይ ተጠምዶ የሚገኘውም ለዚህ የጋራ ህልም ሥኬት ሲባል ነው፡፡
ከዚህ አንጻር – በሀገራችን በሰሜን በኩል – በወያኔ ላይ የተለኮሰው የጦርነት እሳት በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡  አንድም ነገና ከነገ ወዲያ በኦሮሙማው የነጻነት መንገድ ላይ ሊቆም የሚችልን አስፈሪ ወታደራዊ ተቀናቃኝ ኃይል ከሌሎች ጋር ተባብሮ – እና በሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊትና በአማራው ከባድ ኪሣራ – የማስወገድ ጉዳይ ነው፡፡
ወያኔ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይል እንደሆነ ማንም አይክድም፡፡ ምናልባት በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ሃሳብ ላይ ያለው ጥላቻ ከኢጣልያ ፋሺስቶች ራሱ የባሰ ሆኖም እናገኘዋለን፡፡ ፋሺስት ኢጣልያዎች ቢሳካላቸው ኖሮ ህልማቸው ከሶማሊያ እስከ ኤርትራ ያለውን ግዛት አንድ አድርጎ ለመግዛት ነበር፡፡ የወያኔ ሃሳብ ግን ቢሳካለት – ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ሺህ ቦታ ገነጣጥሎ ለመግዛት ነበር ህልሙ፡፡ እና ወያኔ በዚህ በኩል ከፋሺስት ቅኝ ገዢዎችም የከፋ የኢትዮጵያችን ጠላት ነው፡፡
ይሁንና ኦሮሙማዎቹ ወያኔ የቱንም ያህል የኢትዮጵያ ጠላት ብትሆን፣ የብሔር ጡሩንባ ነፍታ በኢህአዴግ ጥላ ስር የሰበሰበቻቸው ጎሰኞች፣ በስብከቱ መሠረት በአደራ የተሰጣቸውን ግዛት ገንጥለው፣ የየራሳቸውን እውነተኛ ሀገር እንመስርት ቢሉ ግን እንደማትቀበላቸው ያውቃሉ፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ጎሳ በየፊናው የየራሱን ግዛት ይዞ በእውነት ቢገነጠል፣ ወያኔ የትግራይን ደረቅ ድንጋይ መሬት ይዛ ስለምትቀርና፣ እንደ ነፃ ሀገር ሌላ ቀርቶ በምግብ እህል ራሷን ችላ መቆም ስለማትችል ነው፡፡
ስለዚህ ወያኔ ለህልውናዋ ቀጣይነት ወዳም ይሁን ተገድዳ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጥገኝነት ውስጥ የገባች ፓራሳይት እስከሆች ድረስ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ተሰባስባ ፈርጥማ አንድ ሀገር እንድትሆን ባትፈልግም፣ እና ኢትዮጵያዊነት ቢያንዘፈዝፋትም፣ ኢትዮጵያ በየጎሳው በእውነት ትገነጣጠል ቢባል ግን ፍጹም ለህልውናዋ አስጊ ስለሚሆንባት አትተባበርም፡፡
ወያኔ የምትፈልገው በእጃዙር በጎሰኞች ስም ሀገሪቱን ከፋፍላ መግዛት ነው፡፡ ለዚያ ደሞ ጠንካራ ወታደራዊ ጉልበቷን ይዛ መቀጠል ትፈልጋለች፡፡ የኦሮሚያን መገንጠል ሀሳብ ታሟሙቃለች፡፡ ትጠቀምበታለች፡፡ ግን በተግባር አትሞክረውም፡፡ አትሞክረውም ብቻ ሳይሆን ያንን ለማስቀረት ከሚሰለፉ ኃይለች ጎን ለመሰለፍ ትገደዳለች፡፡ ወያኔ በ1984 ኦነግን የመታችው በዚህ ቀመሯ ተመርታ ነው፡፡
ስለዚህ በሩቁ መነጽር ከተመለከትናት – ወያኔ ለኦሮሙማው ኃይል ወቅታዊ የጎሰኝነት ርዕዮተዓለሙ አጋር ብትሆንም – ስትራቴጂካሊ ግን መወገድ ያለባት፣ ለወደፊቱም የነጻነት እንቅፋት የምትሆን፣ አደገኛ ጠላት ናት፡፡ ኦሮሙማው ኃይል ወያኔን ለማጥፋት ሲነሳ አንዱ ግቡ ያቺን በህልሙ መንገድ ላይ የምትቆምበትን ስትራቴጂክ ጠላቱን ወያኔን ማስወገድ ነው፡፡ ሌላ ግብም ግን አለው፡፡
ኦሮሙማው ወያኔን ወግቶ ከፖለቲካ ሳይሆን ከወታደራዊ «ሬለቫንሷ» በማስወገዱ ሂደት የሚያገኛቸው ሁለት ግቦችም አሉት፡፡ አንደኛው ግቡ የሀገሪቱን የጦርነት ስበት ማዕከል (ሴንተር ኦፍ ግራቪቲ) ወይም የፍልሚያ ትኩረት – ከኦሮሞሙማው የትግል ሜዳዎች (ከኦሮሚያ) አርቆ ወደ ሰሜን ለመውሰድ የታለመ ‹‹ዲሴፕሸን›› እና ‹‹ዲስትራክሽን›› ታክቲክ ነው፡፡
ሁለተኛ ግብ ደግሞ – ነገና ከነገ ወዲያ የኦሮሚያ ነጻ መንግሥት ህልሙን እውን ለማድረግ በሚነሳበት ወቅት – ከሰሜን በኩል ተቀናጅተው ሊመጡበት የሚችሉትን –  እና ነባሩን የኢትዮጵያ ንጉሠነገሥት ግዛት ለዘመናት እየተፈራረቁ፣ እየተጋገዙ እና እርስ በርስ እየተዋጉም ጭምር ያቆዩትን ሁለት ህዝቦች (የትግራይንና የአማራን ህዝብ) – በቋሚነት የማቃቃር፣ ደም የማፋሰስና፣ ተቀናቃኝ ኃይሎች አድርጎ የማስቀረት ግብ ነው፡፡ ይህ የኦሮሙማውን ኃይል በምን ይጠቅማል?
የሚጠቅመው ከሁለት ነገሮች አንጻር ነው፡፡ አንደኛ ‹‹ኦሮሚያ›› የምትባለው የህልም መንግሥት በእውን ከመመሥረቷ በፊት ለሚደረገው የኦሮሙማው ዘመቻ ይጠቅማል፡፡ ያ ዘመቻ ምንድነው? የወያኔ ወታደራዊ ኃይል መንኮታኮት ከተረጋገጠ በኋላ በአማራው ላይ የሚካሄድ ቀጣዩ ዘመቻ ነው፡፡ ኦሮሙማው በምን ምክንያት አማራውን ለመምታት ይንቀሳቀሳል? ለምሳሌ የወያኔ ኃይል የኦሮሙማው የሩቅ ስትራቴጂካዊ ጠላት የሆነው ከኢትዮጵያ ውጭ መኖር ስለማይችል የኦሮሚያውን የነጻነት ጉዞ ለማሰናከል ስለሚሰለፍ ነው ብለናል፡፡ አማራውስ ለምን?
አማራው ደግሞ ሌላኛው ከኢትዮጵያዊነቱ ሊላቀቅ ያልቻለና የማይችል፣ ለዘመናት ግማሽ ሠላማዊ፣ ግማሽ ወታደር ሆኖ የኖረ፣ በማንኛውም ሰዓት ህዝቡን አስታጥቆ በማንቀሳቀስ ከሌሎች ጋር ተባብሮ የኦሮሙማውን የሀገር ምስረታ ህልም ሊያደናቅፍ የሚችል፣ እና ስለዚህም በረዥም የጦርሜዳ መነፅር ሲታይ በኦሮሙማው ላይ በጠላትነት የሚሰለፍ ስትራቴጂካዊ ጠላት የሆነ ኃይል ነው፡፡
ሁለተኛውስ ጠቀሜታ? ሁለተኛው ነገር ደግሞ – ኦሮሙማው በቀጣይ የነጻነቱ ተገዳዳሪ ኃይል (በአማራው) ላይ ለሚያደርገው ዘመቻ ጥርጊያ መንገድ እያመቻቸ ነው፡፡ ኦሮሙማው ኃይል በአይዲዎሎጂ አጋርነት ከአማራው ይልቅ የሚቀርበውን የወያኔን ወታደራዊ ኃይል እንዴት አድርጎ ድባቅ እንደመታው (እንዳስመታው) እና እንዳንኮታኮተው ለተመለከተ፣ ቀጣዩ ዒላማ ማን እንደሚሆን አይስተውም፡፡ ቀጣዩ የኦሮሙማው ወታደራዊ ኦፕሬሽን የሚያነጣጥረው በአማራው ላይ ነው፡፡
አሁን ላይ ኦሮሙማው ወያኔን በወታደራዊ ጉልበት አንፃር «ኢረለቫንት» ወደ ማድረግ ተቃርቧል፡፡ የወያኔ ጎሰኛ ፖለቲካ ግን ስለሚጠቅመው «ፖለቲካል ሬለቫንሷ» እንዲቀጥልለት ይፈልጋል፡፡ በኦሮሙማው ላይ ችግር የሚደቅንበት ነገ የኦሮሚያን ገንጣይ ኃይሎች በወታደራዊ ጉልበት አጠንክሮ «የታላቋን ኦሮሚያ» ምሥረታ ሲያውጅ፣ በወታደራዊ አቅም ተገዳዳሪ ሆኖ ሊነሳበት የሚችል አካል ነው፡፡ ያ አካል አንዱ ወያኔ ነበር፡፡ ተመቷል፡፡ ቀጣዩ ተገዳዳሪ አካል ደግሞ የአማራው ኃይል ነው፡፡
ኦሮሙማው የአማራውን ኢህአዴጋዊ ኃይል በራሱ ውስጣዊና ውጫዊ ኃይሎች ከማስመታት ባለፈ (ውጫዊ ሲባል ልክ ወያኔን በኤርትራ እንዳስመታው፣ አማራውንም በሱዳን፣ በራሷ ኤርትራና በሌሎች ተጎራባች ኃይሎች ሊያስመታ ይችላል)፣ ነገና ከነገ ወዲያ የኦሮሙማው መንግሥት በጥቅም የደለላቸውን የሀገሪቱን ጎሰኞች ሰብስቦ – የመከላከያ ሠራዊቱን በመያዝ በወያኔ ላይ ያደረገውን ዘመቻ – በአማራው ላይ ለመድገም የሚንቀሳቀስበት ዕድል እጅግ ሰፊ ነው፡፡
ይህን ዝንባሌ ገና ከሩቁ በመረዳት – የትግራዩ ጦርነት ሳይጀመር አንስቶ ጀመርም – ብዙ ሰዎች በእኔ አቋም እስኪገረሙ (እና እስኪደነግጡም) ድረስ፣ የአማራው ኃይል ከኦሮሙማው ጋር በወያኔ ላይ እንዳይሰለፍ በተደጋጋሚ የተቃውሞ ድምጼን አሰምቼያለሁ፡፡
በወቅቱ የትግራዩን ጦርነት የተቃወምኩበት አንዱና ዋነኛው ምክንያቴ – የአብይ አህመድንና በኦሮሙማው ቁጥጥር ሥር የዋለውን መንግሥት ትክክለኛ ባህርይ ከመረዳት የመነጨ ነበር፡፡ አማራው የትግራዩን ጦርነት ከኦሮሙማው ኃይል ጋር አብሮ ተሰልፎ በመዋጋት፣ የልጆቹን ደም አፍስሶ፣ ከሰሜኑ የቅርብ ጎረቤቱ ጋር ደመኛ ጠላት አፍርቶ ሲያበቃ፣ በመጨረሻ ባንኩንና ታንኩን ከተቆጣጠረው ከኦሮሙማውና ከደጋፊ ጎሰኛ ኃይሎቹ በኩል የሚቃጣበትን የተባበረ ጥቃት ለመቋቋም እንደማይችል በማወቅ ነበር፡፡ አሁንም በትንሹ ከወልቃይትና ራያ «ውጡ» እና «አንወጣም» በሚል የኦሮሙማው ኃይል ከኢትዮጵያ መንግሥታዊ ኃይሎች ጋር የቆመ ለማድረግ (ለወደፊቱ ዘመቻው «ሌጂትመሲ» ለመስጠት) እየሞከረ ነው፡፡ የወደፊቱን ዘመቻ «ሊትመስ ቴስት» ካሁኑ ጀምሮታል፡፡
የወያኔ ጦርነት ሲጀመርና በተለይ አማራው «ከመከላከያ ጎን ነን» የሚል ሙሉ ድጋፉን ሲቸር፣ በወቅቱ ፈንጠር ብዬ ቆሜያለሁ፡፡ መቆም ብቻ ሳይሆን በብርቱ ተቃውሜያለሁ፡፡ ‹‹አብይ አህመድ በአማራ ላይ ጦሩን ሲያዘምትስ አሁን የደገፋችሁት ሰዎች ከመከላከያው ጎን ትቆማላችሁ?›› የሚል ጥያቄም በግልጽ ሰንዝሬ ነበር፡፡ ያን ጥያቄዬን እንደ ሟርት የቆጠሩት አልጠፉም፡፡ «በትክክል በአማራው ላይ ጦር እንደሚያዘምት እየነገርከን ነው ወይ?» ብለው የጠየቁኝ ሰዎችም ነበሩ፡፡ መልሴ አዎ ነው፡፡ አዎ፡፡ ይዋል ይደር እንጂ – ኦሮሙማው በወያኔ ላይ ያደረገውን ራሱኑ ዘመቻ – የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊትና እዚህም እዚያም ያሉ ጎሰኛ አጋሮቹን አሰባስቦ – በብአዴን ላይ እንደሚያዘምትበት እርግጠኛ ነኝ፡፡
በጊዜው ቀልድ ይመስል ነበር፡፡ የተቃውሞ ድምጽ ያሰማሁት ለወያኔ አዝኜ አልነበረም፡፡ በፍጹም፡፡ ስለ ወያኔ እውነተኛ ፀረ-ኢትዮጵያዊ ባህርይ ሌሎችን ያስተማርኩ ነኝ፡፡ ነጋሪ የሚያስፈልገኝ ሰው አልነበርኩም፡፡ ከፍ ያለው አደጋ በአማራ ህዝብ ላይ፣ እና በኢትዮጵያችን ላይ የሚመጣው ከየት በኩል እንደሆነ በሩቁ ተመልክቼ ነበር፡፡
ቢያንስ የወያኔዎቹ መኖር፣ የኦሮሙማውን ኃይል ደፍሮ በአማራው ላይ ጦርነት እንዳያውጅ ያስፈራራው ነበር፡፡ ድንገት ልዩነታቸውን ትተው አንድ ላይ ይሰለፉብኛል የሚል ስጋት ስለሚያድርበት፡፡ በተመሣሣይ ምክንያት አጋሩ የሆነውን አማራውን ማስከፋትም ሆነ ማጣት ስለማይፈልግ፡፡ አማራው ሚዛኑ መሐል ላይ ሆኖ አመቺ ስትራቴጂያዊ ጥቅሙንና የሀገሪቱን የሃይል ሚዛን አስጠብቆ መቀጠል ይችል ነበር፡፡ የሚል ዕምነት ነበረኝ፡፡ የወልቃይተና ራያ ጉዳይን የኦሮሙማው መንግሥት በመንግሥታዊ ተቋማቱ አስወስኖ ማስፈጸም ይችል ነበር፡፡ የዚህን ሁሉ ጦስና ሴራ መጨረሻ የምናየው ይሆናል፡፡
ኦሮሙማው ከግዛቱ ውጪ አልፎ በአማራና በትግራይ ላይ ጦርነት መክፈት የማይችል፣ በኢትዮጵያ መንግሥታዊ ኃይል ላይ ጥገኛ የሆነ ኃይል ነው፡፡ አሁን ግን ያ ጥገኝነቱ ገብቶት – በኢትዮጵያ መንግሥት ሽፋን፣ የመንግሥትን መዋቅር ከሞላ ጎደል በብቸኝነት ተቆጣጥሮ፣ የራሱን ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል እየገነባ ነው የሚገኘው፡፡ በአሁን ሰዓት የወያኔ ወታደራዊ ኃይልነት አክትሞ፣ ወታደራዊ ቀብሯ ከተፈጸመ፣ «ምላስ የቀራት» የፖለቲካ ሃይል ብቻ ነው የምትሆነው፡፡ ያ ደግሞ ለኦሮሙማው የሠማይ ምርቃት ነው፡፡
የወያኔ ወታደራዊ አከርካሪ መመታት እውነት ሆኖ ከተፈጸመ (አሁንም በኦሮሙማው ኃይል የፍጻሜ አካሄድና አቋም ላይ ብርቱ ጥርጣሬ ስላለኝ) – በቀጣይ የሚከናወነው የኦሮሙማው ነፃ አውጪ ቡድን  ተግባር – መንግሥታዊ ጦር ሠራዊቱን በማዝመት አማራውን የሚመታበት ምዕራፍ ይሆናል፡፡ ያንንም በድል ካጠናቀቀ፣ በብቸኝነት መንግሥትን የሚቆጣጠርበትና፣ የመጨረሻውን የመገንጠል ህልሙን እስኪያሳካ ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም እንዳሻው እየቀለደ የሚቆይበት የቅድመ-ኦሮሚያ ምዕራፍ ይሆናል፡፡
የኦሮሙማው ረዥም ፀረ-አማራ ዕቅድ ከመተግበሩ በፊት ግን፣ ሁሉም ዓላማውን ከነቃበት፣ ሊከሽፍ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ ይህ ከሆነ፣ የመከላከያ ሠራዊቱን ጨምሮ እውነተኛ ለሀገሩ የሚቆረቆር ኢትዮጵያዊ ኃይል ሁሉ በጋራ ተቀናጅቶ፣ አክራሪውን የኦሮሙማ ተገንጣይ ቡድን፣ እንደልቡ እንዲፈነጭበት በተፈቀደለት ሰፊ የኦሮሚያ ክልል ገብቶ በመምታት፣ ኦሮሚያን ነፃ አወጣለሁ ብሎ እንዳሻው ከፈለገ እያረደ፣ ካሰኘው እየገደለ፣ ካሰኘው ሀገር ምድሩን እየመለመለና ጦሩን እያደራጀ የሚንቀሳቀስበትን የመዋኛ ገንዳውን ማድረቅ የሚቻልበት ዕድል የኖራል፡፡
ያን ማድረግ ከተቻለ፣ ምናልባትም ተንገዳግዶ ሊወድቅ ጫፍ ደርሶ ከነበረው ከወያኔ-ኢህአዴግ ላይ ተረክቦ አንገዳግዶ ሊያቆመው የሚንገዳገደው የወያኔ-ኦነግ አፓርታይዳዊ ህገመንግሥታዊ ሥርዓት አልጋወራሽ ቁማሩ ስለሚያበቃ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጎሰኝነት ከሀገራችን ተወግዶ፣ ከጎሰኝነት ቀንበር ነጻ የሆነች ኢትዮጵያን ለማየት የምንችልበት ዕድል ይፈጠርም ይሆናል፡፡ እስከዚያስ?
እስከዚያ ድረስ ግን የኢትዮጵያዊው አንድነት ኃይል – በተለይም እንደ ዋነኛ ጠላት (‹‹ሞርታል ኤነሚ››) የሚቆጥረው የአማራው ኃይል ማንሠራራት የኦሮሙማውን ትዕግሥት ተፈታትኖ፣ የሚይዝ የሚጨብጠውን አሳጥቶታል፡፡ አሁን እየተቀጣጠለ ባለው ሀገራዊ የብሄርተኝነት ስሜት፣ እና በወጣቱ ልብ ውስጥ እያንሰራራ በመጣው ኢትዮጵያዊ ሀገራዊ አርበኝነት የተነሳ፣ የኦሮሙማው ኃይል በዙሪያው የአደጋ ማቆጥቆጥ ሥጋት ገብቶታል፡፡
ያን ፍርሃቱን በተለያየ መልክ እየገለጸው ነው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ኃውልቶችና ቅርሶች በማፈራረስ፣ ለኢትዮጵያ ባንዲራ ጥላቻውና ብስጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣት፣ ከህጻናት ጭንቅላት ላይ ጥቃቅን ባንዲራዎችን እስከ ማስፈታት የደረሰ መርበትበት፣ እና የኦሮሙማው ወታደራዊ ክንፍ እንደልቡ እንዲፈነጭ በማድረግ በኦሮሚያና አጎራባች ግዛቶች እየተዘዋወረ ንጹሃን አማሮችን እየገደለ፣ እያረደ፣ እያሸበረና እያፈናቀለ እንዲቀጥል ማድረግ፡፡
ይህ ሁሉ የሚያሳየው – የኦሮሙማው ኃይል በፖለቲካ በኩል የአይዲዎሎጂ አጋሩ የሆነውን፣ ነገር ግን በወታደራዊ በኩል ዋነኛ አስፈሪ ስትራቴጂክ ጠላቱ የሆነውን ወያኔን በቀበረ ማግሥት፣ የመገንጠል ህልሙ ዋነኛ ጋሬጣ (ወይም ‹‹ፕራይም ትሬት››) ይሆንብኛል፣ ለነጻዋ «ታላቋ ኦሮሚያ» ምሥረታዬ የማይቀር ወታደራዊ ተገዳዳሪ ይሆንብኛል፣ ብሎ በሚቆጥረው በአማራው ኃይል ላይ፣ እና በአጠቃላይ በኢትዮጵያዊው የአንድነት ኃይል ላይ ያደረበትን ለትልቅ አደጋ የመጋለጥ ስሜትና ብርቱ ፍርሃት (ወይም የመበርገግ ስሜት) ነው፡፡
ኦሮሙማው አሁን በገዛ ድሉ ጭንቀት ውስጥ ሰምጧል፡፡ ምክንያቱም ያላስወገደው አንድ ትልቅ ስትራቴጂካዊ ጠላት ከፊቱ ቆሞ እያየው ነው፡፡ እያሰበው፣ እያሸተተው ነው፡፡ አሁን ኦሮሙማው በብቸኝነት በሚቆጣጠራቸው የኦሮሚያ ግዛቶች (እና በአጎራባች የቤኒሻንጉል ግዛቶች) ውስጥ እያደረገ ያለው፣ ጊዜው ሳይረፍድብን፣ ዕቅዳችን ሳይነቃብን፣ ዕቅዳችን ሳይከሽፍብን፣ የነጻነት እንቅስቃሴ ሜዳችን የሆነውን የኦሮሚያን ግዛት – ነገ ለኢትዮጵያ ተሰልፎ ከሚወጋን ከአማራው የማፅዳቱን ሥራ በፍጥነት አከናውነነት እንጨርስ የሚል የበጀት-መዝጊያ ሩጫ የሚመሰል የእውር-ድንብር የጥፋት ሩጫ ነው፡፡
አሁን የኦሮሙማው የፖለቲካና ወታደራዊ ክንፍ እየተናበበ እየፈፀመው ያለው ድርጊት – የ«ታላቋ ኦሮሚያ» የቅድመ ነጻነት ጥርጊያ ተደርጎ የተቆጠረ – እና በአማራው ላይ ከሚደረገው የመጨረሻ ወታደራዊ ዘመቻ በፊት የሚደረግ – ግልጽ የዘር ማፅዳት ተግባር ነው፡፡
የኦሮሙማው ወታደራዊ ቡድን የአማራውን ዘር እየመረጠ በዘግናኝ ሁኔታ በመጨፍጨፍ – በሌሎች ወደፊት ከአማራው ጋር አብረው ሊወጉት በሚከጅሉ ህዝቦች ዘንድ እንዲፈራ ለማድረግ – በለየለት የሽብር እንቅስቃሴ ውስጥ ራሱን አሰማርቷል፡፡ ይህ መንግሥትም ተቃዋሚውም ሆኖ ከተሰለፈው የኦሮሙማው የነጻነት ህልመኛ ጎራ መጠነ-ሰፊ ድጋፍ እየተቸረው ያለ – እና የኦሮሙማው ኃይል በህዝቡ ዘንድ ራሱን እንደ ዝነኛ ነጻ አውጪ ኃይል አድርጎ ያቀረበበት አሳዛኝና ዘግናኝ ትርዒት ነው፡፡ ይህ የኦሮሙማው የሽብር ተግባር በከፍተኛ ደረጃ በአማራ (‹‹ነፍጠኛ›› እያሉ በሚጠሩት) እርድ፣ ግድያና ማፈናቀል ተደግፎ የሚከወን – የነጻዋ ኦሮሚያ መቃረብ «ህዝባዊ ፕሮሞሽን» ነው፡፡ ያለምንም ማለባበስ – በኦሮሙማው አረዳድና ውጥን መሠረት በአሁን ወቅት እየተከናወነ ያለው – ይህ ነው፡፡
ግን አንድ ያልተረዳው ነገር አለ፡፡ የኦሮሙማው አክራሪ ወታደራዊ ክንፍ፡፡ ይኸውም አማራም ሆነ ሌላ ንጹሃንን ከየጓዳቸው እየለቀመ ሲያርድና ሲገድል በሌሎች ዘንድ ከመፈራት ይልቅ – እጅግ እየተናቀ፣ እየተጠላና እየተነጠለ እንደሚሄድ ነው፡፡ ራሱ ብቻ አይደለም የሚጠላው፡፡ የኦሮሞን ሕዝብም እያስጠላና ለጥቃት እያጋለጠ ነው፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ በኦሮሞ ላይ የጥላቻ «ሴንቲሜንት» እንዲያድርበትና እንዲተባበርበት በራሱ ላይ ለሚቀጣጠል እሳት ነዳጅ እያርከፈከፈ ነው፡፡ የጥላቻና የትብብር አቋም ብቻም አይደለም፡፡ በተለያዩ የኦሮሞ ጎሳ አባላት ላይ በዙሪያቸው ካለው ተጎራባች ህዝብ በኩል ከፍተኛ አደጋን ሊጋብዝባቸው የሚችል አደገኛ የእሳት ላይ ጨዋታም ይሆናል፡፡
The barbaric acts of genocide and mass murder by the Oromuma military wing against unprotected civilian population across the Oromia nad neighboring regions just demonizes and dehumanizes itself, and the very cause it tries to propagate through its acts of terror, and, as a result, builds commonality and common resistance front amongst the rest of Ethiopia’s communities against it, and even against the innocent ethnic Oromo population at large in its extreme sense.
ባጠቃላይ – ለብዙዎቹ በኦሮሙማዎቹ ታጣቂዎች መሬት ላይ እየደረሱ ላሉት ጥፋቶች ዋናዋ ምክንያት – ያቺ በምኞት ዓለም እየዋኙ በሃሳባቸው የፈጠሯት «ታላቋ ኦሮሚያ» የምትባል የኦሮሞ ተናጋሪዎች ብቻ የሚኖሩባት የኦሮሙማ የነጻነት ደሴት ትመስለኛለች፡፡ ይህቺ የሃሳብ ኦሮሞአዊ ደሴት – በሀሺሽ ከመጀንጀንም በከፋ ደረጃ – ቋሚ በሆነ የስካር ስሜት ውስጥ የከተተቻቸውም ይመስለኛል፡፡ ይህች አስካሪ ጋንጃ («ታላቋ ኦሮሚያ») – ኦሮሙማዎቹ ራሳቸውን ነፍጥ እንዲያስታጠቁና ላለፉት ሃያ ምናምን ዓመታት ወያኔ ጠላታችን በሚል የበደለኝነት ሽፋን ለኢትዮጵያ መንግሥት የተሰለፉ ሠራዊቶችን በየሄዱበት ሲወጉና ሲያጠቁ እንዲኖሩ አድርጋቸዋለች፡፡
ይህቺ «ታላቋ ኦሮሚያ» የምትባል ሀሺሻዊ ምኞት፣ ከአርባጉጉና በደኖ ጀምሮ ሠላማዊ ሰዎችን እያረዱና እርጉዝ እየተለተሉ እንዲኖሩ አድርጋቸዋለች፡፡ ይህቺው «ታላቋ ኦሮሚያ» የተባለች ‹‹ላም-አለኝ-በሰማይ-ወተቷንም-አላይ›› የሆነች የህልም ሀገር – እውነተኛውን የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ አምነው እንዳይቀበሉና በህግና በሥርዓት እንዳይገዙ አድርጋቸዋለች፡፡
አሁን ደግሞ ያቺው ኦሮሙማዊ ህልም – «ታላቋ ኦሮሚያ» – የመንግሥታዊው ኦሮሙማ ሰፊ እገዛ ተጨምሮላት – ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ጭምር የታጠቀ – እና በኦሮሚያ ተብዬዋ የወደፊቷ ታሳቢ የነጸነት ምድር ላይ ከአሁኑ በነፃ እንዲንቀሳቀስ የተሰማራውን የኦሮሙማውን የታጠቁ ቡድኖች ፈጥራለች፡፡ ያቺ ህልም ከደፈጣ ጥቃትና ጊዜያዊ ሽብር፣ እንዲሁም አንገትን አሸዋ ውስጥ ቀብሮ ከሚደረግ ስውር የፖለቲካ ሸፍጥ አልፋ – ጥርስ አብቅለው – በመላው ኦሮሚያና አጎራባች ክልሎች እንደልባቸው ያለከልካይ እየተንቀሳቀሱና ጦር እየመለመሉ ያሉትን ወታደራዊ ሰልፈኞች ፈጥራለች፡፡
ባለፉት አርባ ዓመታት በአክራሪ የኦሮሞ ኦነጋዊ አሸባሪ ኃይሎች እየተንቆረቆረላቸው በኖረውና፣ በወያኔ ዘመን ሆነ ተብሎ ሲኮተኮት በኖረው፣ በዚህ ምናባዊ የነጻዋ «ታላቋ ኦሮሚያ» ትርክት የናወዙት ዜጎች ቁጥር ድንበርም ተሻግረዋል፡፡ በኬንያ፣ በዩጋንዳ፣ በሱዳን፣ በኤርትራ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በግብጽ፣ በአሜሪካና በዋና ዋና የአውሮፓ ከተሞች ሁሉ ሳይቀር ተሰራጭተዋል፡፡
እንደሚመስለኝ የኦሮሙማው ኃይሎች በብዙ ነገራቸው የኮረጁት እና እየኮረጁ ያሉት ኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠል የተሳካለትን ሻዕቢያን ነው፡፡ ሻዕቢያ በዘመኑ የኢምፔሪያሊስት-ሶሻሊስት ካምፕ የቀዝቃዛው ጦርነት ፍትጊያ መሀል ታሪካዊ ዕድል አግኝቶ በመፋፋቱና፣ በዚያው ታሪካዊ ዕጣ ፈንታ የሶሻሊስቱን ጎራ የተቀላቀለው የኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግሥት ለውድቀት በመዳረጉ የተፈጠረ የብዙ ምክንያቶች ጥርቅም የሆነ ታሪካዊ ገድል ያለው ተገንጣይ መሆኑ ለኦሮሙማዎቹ ገና የተከሰተላቸው ግን አልመሰለኝም፡፡
የኤርትራ ህዝብ ለዚያ ሁሉ ዘመን የወንድሞቹን ኢትዮጵያውያንን ደም ሲያፈስ ኖሮ፣ እና የራሱንም ወገኖች ደም ሲያስፈስስ ኖሮ ምንም ጠብ ያለለት ነገር ያለመኖሩም ገና ለኦሮሙማዎቹ አልተገለጠላቸውም፡፡ ከሻዕቢያ ጋር የፈጠሩት በወያኔ ጠላትነት ላይ የተመሠረተ ፍቅርም እስከሚመኙት ነጻነታቸው ድረስ የሚዘልቅ «ፍቅር እስከ መቃብር» ታሪክም አድርገው የወሰዱት ይመስለኛል፡፡ የኦሮሞ አክራሪ ቡድኖቹ፡፡
የኦሮሙማው ኃይል – በተለይም እንዳሻው የእርድ ግዳዩን እየጣለ ያለው የኦሮሙማው ወታደራዊ ክንፍ – በዓመታት ስብከት በሃሳብ ከገነባው ሃሽሻዊ «ታላቋ ኦሮሚያ» መንግሥት ሥካሩ በግድ ተቀስቅሶ እንዲወጣ እስካልተደረገ ድረስ – አያያዙ ሲታይ – ገና የብዙ ሺኅ ንጹሃን ዜጎቻችንን ህይወት ሳያጠፋ የሚያቆመው ልጓም ያለው አይመስልም፡፡ ለዚያ ሀሽሻዊ የሀሳብ መንግሥት ምሥረታ ሲሉ ገና የሚያውጁት ጦርነት አለ፡፡ ገና የሚቀጥፉት የብዙ ኢትዮጵያ ህይወት፣ ገና የሚያወድሙት ብዙ የሀገር ሀብትና፣ የሚያደርሱት ገና ብዙ ጉዳት አለ፡፡
እነዚህ በምኞት የተጀነጀኑ ኃይሎች የግድ ከዚህ ለጥፋታቸው ሁሉ ከሚመራቸው ሀሺሻዊ ህልማቸው ተቀስቅሰው እንዲነቁ መደረግ አለባቸው፡፡ እያደረሱ ያሉት ጥፋት የቱን ያህል ራሳቸውን መልሶ እንደሚፋጅ ማየትና መንቃት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ያንን ማድረግ የሁሉንም ኢትዮጵያ ትመለከተኛለች የሚል ቀናዒ ዜጋ ሁሉ ርብርብ የሚጠይቅ ወቅታዊ የተግባር ምላሽ ነው፡፡ ዛሬ ይህን እውነት ያልተረዱ ሁሉ፣ ነገ ከነገ ወዲያ በሚሆኑ ነገሮች በትክክል ይረዱታል የሚል እምነቴ የጸና ነው፡፡
በሌላ በኩል፣ አብዛኛው ከሰካሩ ውጭ የሆነው፣ እና እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹና እህቶቹ የራሱንና የቤተሰቡን ኑሮ ለማቃናት ቀን ከሌት የሚለፋው ለፍቶ-አዳሪው የኦሮሞ ህዝብ፣ እንዲሁም ከ«ታላቋ ኦሮሚያ» ጅንጀናው የነፁ ንፁሃን ኦሮሞዎች ሁሉ፣ በአሁኑ ጊዜ ራሳቸውን ከአጥፊው የኦሮሙማ ኃይል ነጥለው፣ ራሳቸውን ከኦሮሙማው ጥፋት አርቀው፣ አጥፊውን ህልመኛ ኃይል ቦታ ነስተው፣ ከተጽዕኖው መላቀቅ መቻል አለባቸው፡፡ ያንን ማሳየት ካልቻሉ፣ ነገና ከነገ ወዲያ፣ ልክ ትናንት ራሱን ከወያኔ ማላቀቅ ያልቻለው የትግራይ ህዝብ ዛሬ እየከፈለ ያለውን የመሰለ የመከራ ዋጋ፣ እነርሱንም ነገ እንደሚጠብቃቸው ማወቅ አለባቸው፡፡
እስከዚያው ግን የኦሮሙማውን መራር የደም ቀልድ እየተመለከትኩ፣ መካሪ ባይጠፋባቸው ግን ምን ነበረበት? ማለቴን አልተውም፡፡ እባካችሁ ነጻ አውጪ ኦሮሙማዎች፣ እባካችሁ የታላቋ ኦሮሚያ አዋላጅ ነን ባይ አራጆችና ጨፍጫፊዎች፡- ያልታጠቁ ንጹሃንን መግደል የመጨረሻው የአውሬነትና ያለመሰልጠን ማረጋገጫ እንጂ፣ የጀግንነት ማስመስከሪያ አይደለም፡፡ ንጹሃንን መጨፍጨፍ የጦርሜዳ ጀብዱ አይደለም፡፡ ሜዳሊያ አያሰጥም፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ የሚጠየፉት ምህረት የሌለው ዓለማቀፍ ወንጀል ነው፡፡ ብሎ የሚመክር አንድ ሽማግሌ እንዴት ይጠፋል? እያልኩ እገረማለሁ፡፡
ለፍቶ አዳሪ ንጹሃንን ከየቤቱ እየለቀሙ መግደል ወራዳ የፈሪ ተግባር እንጂ፣ ጀግንነት አይደለም፡፡ ጀግንነቱን ወደፊት ለሚጠብቃችሁ የጦር ሜዳ ብትቆጥቡት ይበጃችኋል . . . ፣ በአብዲ ኢሌ አመራር ዘመን – የሶማሌ ልዩ ሃይል «አንድ ሚሊየን ኦሮሞ አፈናቀለብን» እያላችሁ በየዓለምአቀፉ ተቋም ደጅ ስታነቡ፣ ስትጮኹ፣ ስሞታ ስትለቀልቁ የኖራችሁ «የእንባ ጀግኖች» እንደነበራችሁ እንዴት በዚህ ፍጥነት ተዘነጋችሁ? የሚላቸው አንድ እንኳ አስታዋሽ ሽማግሌ ማጣታቸው ይገርመኛል፡፡
ትናንት ከሶማሌ ህዝብ ጋር ያነሳችሁት ጠብ አንድ ሚሊየን ኦሮሞ እንዳፈናቀለ እያያችሁ፣ ዛሬና ነገ ከአማራ ህዝብ ጋር በምታነሱትስ ጠብ ስንት ሚሊዮን ኦሮሞ
ዎችን ያፈናቅልብናል? ብላችሁ ደጋግማችሁ የማሰቢያ ጊዜያችሁ አሁን ነው . . . ፣ የእንባ ጀግንነታችሁ መጀመሪያ፣ እና ንፁሃንን የማረድ ጀግንነታችሁ ማብቂያ ደወል እየተደወለባችሁ መሆኑን ስለምን ልብ አትሉም . . . ? ብሎ የሚናገር፡፡ ብሎ የሚመክር፡፡ ብሎ የሚያስጠነቅቅ፡፡ ብሎ የሚያርቅ፡፡ ብሎ የሚያስታርቅ፡፡ ብሎ የሚያስጠነቅቅ፡፡ አንድ እንኳ አርቆ አሳቢ ሰው፡፡ አንድ እንኳን ምራቅ ዋጥ ያደረገ መካሪ ሽማግሌ፡፡ አንድ እንኳ አባ ገዳ፡፡ እንዴት የላቸውም ግን በመካከላቸው ለእነዚህ ሰዎች?? እያልኩ እገረማለሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ከየቤታቸው እየተለቀሙ በኦሮሙማው ወታደራዊ ክንፍ እየተጨፈጨፉ ያሉ፣ ከፈጣሪ በቀር ጠባቂ የሌላቸውን ንፁሃን አማራዎች ነፍስ፣ ፈጣሪ በገነቱ ይቀበላት!
የምንመካው በፈጣሪያችን በእግዚአብሔር ነው! የኢትዮጵያ አምላክ ደሞ አሳፍሮን አያውቅም!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!  
Filed in: Amharic