አስቀድሜ የማክበር ሰላምታየን አቀርባለሁ፡፡
አሰፋ ታረቀኝ
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እርሰወ እንደ ግሰሰብ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተጋፈጣችሁትን ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ በመሄድ ላይ ያለ ውጥረት የምናየው ነው፡፡ ደግነቱ ብቻወን አይደሉም፤ ሰሞኑን በአሜሪካ ከተሞች፣ በካናዳና በአውሮፓ የታየው የህዝብ ማዕበል ምስክር ነው፡፡ ልክ እንደርሰወ በኢትዮጵያ የወደፊት ዕድገት ላይ የጸና ዕምነት ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ኢትዮጵያን የት ድረስ ይዘዋት ሊሄዱ እንዳቀዱ የተረዱ የውስጥም የውጭም ጸረ ኢትዮጵያ ሐይሎች በሙሉ ሀይላቸው እየተረባረቡ ናቸው፡፡ ከነዚህ ጸረ ኢትዮጵያ ህይሎች መካከል አንዱ ኦንግ የተባለው ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ ድርጅት ማንነት ብዙ ስለተባለ መድገም አስፈላጊ አይደለም፡፡ እያደረሰ ያለውን አደጋ እንደቀላል ማየት የተዘወተረ ስለመሰለኝ ሥጋቴን ለማካፈል ነው፡፡
በወለጋ ክፍለ ሀገር እየፈሰሰ ያለው የሚስኪን፣ ንጹሀን አማርኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን ደም፣ ለኦሮሞ ለራሱ መልካም ይሆናል ወይ? የዕያንዳንዱ ሟች ነፍስ እግዚያብሔር ዙፋን ፊት አበቱታ ታቀርባለች፡፡ እግዚአብሔር ፍርድ ሲሰጥ ወለጋን አያድርገኝ ማለት የማይቀር ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የአማራና የአፋር ልዩ ሀይል፣ ከመክላከያ ሀይሉ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ከትህነግ አጥፊ ሀይል እንደት እንደታደጋት ከእርሰወ አንደበት ሰምተናል፡፡ በተደጋጋሚ የሰለጠነው ግዙፉ የኦሮሚያ ልዩ ሀይል የእነዚያን ምስኪኖች ህይወት መከላከል ተስኖት ነውን? አቶ ሽመልስ አብዲሳና በሥራቸው ያሉ የኦሮሚያ መሪወች፣ በሚያስተዳድሩት ግዛት ውስጥ ህጻናት፣ አረጋውያንና እናቶች እንደንሰሳ ተጎትተው እየታረዱ መሆኑን በዜና እየሰሙ እንደት በሰላም ተኝተው ያድራሉ? ኦንግና መሰሎቹ ኢትዮጵያ የምትባል ሐገር ነበረች፣ አለች፣ ወደፊትም መኖር አለባት ብለው አያምኑም፡፡ እርሰዎ ኢትዮጵያን የሚያዩበት አድማስና የኦነግ ምኞት ለኢትዮጵያ በእጅጉ የተራራቁ ናቸው፡፡ ማን ምን እየሠራ እንደሆነ ይጠፋዎታል ብየ የምገምት የዋህ አይደለሁም፡፡ ሥጋቴን ማጋራት እንዳለብኝ ግን አምኘበታለሁ፡፡ ኦነግ ሦሥት ስልቶችን ቀይሶ እየተንቀሳቀስ ይመስላል፡
- በኦነግ ላይ “ሼኔ” የሚል ቅጥል ለጥፎ ሰላማዊ ነኝ ባዩ በከተማ ማሴር፡ የታጠቀው ክፍል አንድን ጎሳ እየለየ መረሸን
- በኦሮሚያ ብልጽግናና በኦሮሞ ልዩ ሀይል ሥር ተሰግስጎ የዶ/ር አብይን መንግሥት የለውጥ ግሥጋሤ ማደናቀፍ ማለትም በህዝብ ዘንድ ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ድርጊቶችን መፈጸም፤
- አማራን በምጨፍጨፍ ወይ አማራው ተቆጥቶ እንዲነሳና ሐገር እንድትበጠበጥ፣ ያ የማይሳካ ከሆነ አማርኛ ተናጋሪው ህብረተሰብ በዶ/ር አብይ ላይ እምነት እንዳያሳድር ማድረግ ናቸው፡፡
እባክዎን አቶ ሽመልስንና የኦሮሚያ ብልጽግናን ይጥሩና ምን እየሠራችሁ ነው ይበሏቸው፡፡ ኦነጎች ለኦሮሞ ህዝብ ከእግዚያብሔር የሚታዘዝ የቅጣት በትር እያዘጋጁለት መሆኑን የተረዱት አይመስልም፡፡ ለእያንዷ ነፍስ እግዚያብሔር በክብሩ ዙፋን ላይ ሆኖ ይፈርዳል፡፡ ያኔ በደም አፍሳሾች መንደር ዋይታ የሆናል፡፡
“ሰይፍ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ሥፍራው መልስ” ማቴ 26፣ 52-53.