>
5:18 pm - Friday June 15, 2970

የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት ትናንትና እና ዛሬ ( አቻምየለህ ታምሩ)

የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት ትናንትና እና ዛሬ

[ክፍል ፩]
አቻምየለህ ታምሩ

የትናንትናው የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት የእውቀት ባለቤቶች፣ የአገሪቱ ምርጥ ሊቃውንት እና ችሎታ ያላቸው ሰዎች የሚሰበሰቡበት እና ለነገሥታቱ ምክር የሚሰጡበት የእውቀት ማዕከል ነበር። የትናንቱ የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት የእውቀትና የሞያ ባለቤቶች ማዕከል የነበረው ነገሥታቱ ለእውቀት ትልቅ ቦታ ስለነበራቸው፤ ችሎታ ያለውን ሰው ስለሚያቀርቡ፤  በነጻነት የእውቀቱን የምክራቸው ተካሳይ እንዲሆን ስለሚያደርጉ፤ እውቀትን የማይጋፉ፤ አዋቂን የሚያበረታቱና ስለሚሸልሙምም ጭምር ነበር።
በመሆኑም ነገሥታቱ ሞያና ሞያተኛን የሚፈልጉ፤ አዋቂን በእውቀቱ የሚያከብሩና ችሎታ ያለው ሰው በችሎታው አገሩን እንዲያገለግልና እሱም እንዲጠቀም ያደርጉ ስለነበር ከየትኛውም  የአገራችን ክፍል የተገኙ  አዋቂዎች  ወደ ቤተ መንግሥት ይተሙ ነበር። በዐፄ ቴዎድሮስ፣ በዐፄ ዮሐንስ፣ በዐፄ ምኒልክና በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ቤተ መንግሥት ያልደረሰ  የእውቀትና የችሎታ ሰው አልነበረም።
አብዮት መጣ ከተባለ ወዲህ ያለው የዛሬው የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት ግን የእውቀት ሰዎች ድርሽ የማይሉበት መደዴዎች፣ የእውቀት ጾመኞች፣ አዋቂ አያሳየን የሚሉ ደናቁርት፣ በፍቅረ ንዋይና በፍቅረ ስልጣን የተለከፉ ካድሬዎችና በራሳቸው ፍቅር የወደቁ ጸረ እውቀቶች መፈንጫ ሆኗል።
የትናንትናዋ ኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት የአዋቂዎች መሰባሰቢያ ስለነበር ኢትዮጵያ ያጋጠማትን አለማቀፍ ችግር ሁሉ እንደ አክሊሉ ሃብተወልድ፣ ሐዲስ አለማየሁ፣ ሎሬንሶ ታዕዛዝ፣ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ ይልማ ደሬሳ፣ መኮንን ሃብተ ወልድ፣ ወዘተ… አይነት አዋቂ ልጆቿ በእውቀት ባደረጉት ከፍተኛ አለማቀፋዊ ተጋድሎ የምስራቁም የምዕራቡም አለም በኢትዮጵያ ላይ  የተደቀነውን ፈተና አሸንፋ አገራችን የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አፍሪካ የተስፋ አርአያና የነጻነት ጮራ ለመሆን በቅታ ነበር።  ለዚህም ነበር  ክዋሜ ኑክሩማህ «Ethiopia, a land of the wise; the bold cradle of Africa’s ancient rule and fertile school; the beacon of freedom for the black peoples in the world and the repository of Africa’s culture» ሲል የትናንትናዋን ኢትዮጵያን የገለጻት።
የዛሬው ቤተ መንግሥት ግን አዋቂዎችን በሚያሳድዱ፣ ጸረ እውቀት፣ ጸረ ምሁር፣ ጸረ አገርና ጸረ ሀሳብ በሆኑ የራባቸውና ሁሉ ብርቁ ካድሬዎች ተሞልቶ ቤተ መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን አገሩም  ባዶ ስለሆነ አገራችን ተራራ የሚያክል እውነት እያላት ብሔራዊ ክብሯንና ሉዓላዊነቷን  ጫካ ያሉት የፋሽስት ቅሪቶች በአገራችን ላይ አለም እንዲዘምት አያደረጉት ካለው የፕሮፓጋንዳ ጥቃትና የጎረቤት ጠላቶች ወረራ ለመከላከል አልቻለም።
የትናንትናውና የዛሬው የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት እንደ ተቋም ብቻ ሳይሆን በውስጡ በገቡ መሪዎች ችሎታም  ሲመዘንም ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ነው። የአንድ መሪ ትልቅነት የሚለካው አጋሩ አድርጎ በሚመርጣቸው ሰዎች ችሎታ ነው። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዙሪያ የነበሩት የንጉሡ ረዳቶች፣ አማካሪዎችና ሚኒስትሮች ያየን እንደሆነ  ንጉሡ ምን ያህል ብቃት ያለው ሰው መምረጥ የሚችሉ ታላቅ መሪ እንደነበሩ ማየት ይቻላል። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መርጠውት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአለም መድረክ ጭምር ችሎታውን ያላስመሰከረ የንጉሡ ረዳት አልነበረውም። ባጭሩ የንጉሡ ረዳቶች የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለምም ምርጦች ነበሩ።
በተቃራኔው አብዮት ተካሄደ ከተባለ ወዲህ ቤተ መንግሥት ውስጥ የገቡት እነ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ መለስ ዜናዊና ዐቢይ አሕመድ በዙሪያቸው ያሰለፏቸውን ረዳቶቻቸው ያየን እንደሆነ ስለ ምንም ነገር እውቀት የሌላቸው መደዴ ካድሬዎችና የዓለም ምራጮች [ምራጭ ማለት ተመርጦ የወደቀው ለጉዳይ የማይረባው ማለት ነው] ሆነው እናገኛቸዋለን። እነዚህ በገዢዎቹ ዙሪያ የተኮለኮሉት ምራጭ ካድሬዎች የበላዮቻቸው የባሕሪ ታናሽ ወንድምም ናቸው።
በሌላ አነጋገር እነ  መንግሥቱ፣ እነ መለስና እነ ዐቢይ በዙሪያቸው ያሰለፏቸው መደዴ ካድሬዎች የነሱ ነጸብራቅ የሆኑ ካላቸው ታማኝነት በስተቀር እውቀትና ችሎታ በዞረበት ያልዞሩ የአቡጌዳ ሽፍቶች ናቸው። እንደነዚህ አይነት መደዴ ካድሬዎችን ረዳቶቻቸው ያደረጉት የባሕሪ ታላቅ ወንድሞቻቸው እነ መንግሥቱ፣ መለስና ዐቢይም በየትኛውም አገር በመሪ ወንበር ላይ ሊቀመጥ የሚገባው ሰው እነዚህን አይነት ሰዎችን መምሰል እንደሌለበት በመዝገበ ቃላት ጭምር  ለማስተማር በተምሳሌት የሚቀርቡ ጉዶች ናቸው።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መርጠውት በየትኛውም መድረክ ቀርቦ ኢትዮጵያን ያሳፈረ የንጉሡ ረዳት ማቅረብ አይቻልም። የንጉሡ ረዳቶች በሙሉ ኢትዮጵያን ከታላላቆቹ የምስራቅና የምዕራብ ኃይሎች የፖለቲካና የፕሮፓጋንዳ ጥቃት መታደግ ብቻ ሳይሆን በአሸናፊነት ተወጥተው ኢትዮጵያን በአለም መድረክ እንድትከበር ያደረጉ የእውቀትና የችሎታ ሰዎች ነበሩ። ይህ ንጉሡ የነበራቸው የመሪነት ችሎታ የሚያሳይ ነው። በተቃራኒው መንግሥቱ፣ መለስና ዐቢይ መርጠውት ኢትዮጵያን ያላዋረደ፣ ከኃያላኑ ቀርቶ ኢትዮጵያን ከሽፍቶች የፕሮፓጋንዳና የፖለቲካ ጥቃት መከላከል የቻለ አንድ እንኳን ረዳታቸው የሆነ ሰው ማቅረብ አይቻልም። ይህ በግልጽ የሚያሳየው ኢትዮጵያን  ከንጉሡ ውድቀት በኋላ በምን አይነት መደዴዎች  እና ወሮበላዎች እጅ እንደወደቀች ነው።
Filed in: Amharic