>

በአማራ ህዝብ ላይ በሚደረገው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋን አስመልክቶ ከአማራ ማህበር ኦስትሪያ የተሰጠ መግለጫ ! 

በአማራ ህዝብ ላይ በሚደረገው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋን አስመልክቶ ከአማራ ማህበር ኦስትሪያ የተሰጠ መግለጫ ! 
የአማራ ሚዲያ ማእከል 

የአማራን ህዝብ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የሚደረገው ኢሰብአዊ ጭፍጨፋ ያለማቋረጥ ቀጥሏል ። አማራው በሚኖርበት በየትኛውም የኦሮሚያ ክልል ሁሉ አገሬ ብሎ፣  ቤተሰብ አፍርቶ፣  ጥሮ ግሮ ልጆቹን ከማሳደግና ሰላማዊ ኑሮውን ከመኖር ውጭ ሌላ አጀንዳ እንደሌለው እየታወቀ ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ እየታረደና ስጋው ለዱር አራዊት እየተጣለ ፣ የአማራ ዘር ድጋሜ ወደዚች አለም እንዳይመጣ ጽንስ በሳንጃ እየተዘለዘለ ዘሩን የማጥፋት ወንጀል በገሃድ ሲሰራበት ቆይቷል አሁንም እየተሰራበት ይገኛል።  ለማስታወስ ያህል በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳ ቆርቃ ቀበሌ ከ 90 በላይ ንጹሃን ዜጎች በ04 ጥር 2013 ዓ.ም በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል።  በዋዜማው ማለትም በ03 ጥር 2013 ዓ.ም በዚሁ በድባጤ ወረዳ ከ 115 በላይ አስከሬን የተገኘ ሲሆን በየጫካው የወደቀውና ቁጥሩ የማይታወቀው ደግሞ የአውሬ እራት ሆኖ ቀርቷል። ሶስት አይሲዚዎች በአስከሬን ተሞልተው እንደተመለሱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ይህ ሁሉ ሲሆን እንዳላዩና እንዳልሰሙ ጀሮ ዳባ ብለው ድርጊቱን ለማስቆም ምንም አይነት ጥረት ያላደረጉ የአማራ ክልል መስተዳድር፣ የፌደራል መንግስት ፣  የሃይማኖት ተቋማት ፣ የአማራ ምሁራን መማክርት እና ሌሎች  ሲቪክ ማህበራት ሁሉ  ከታሪክ ተጠያቂነት አያመልጡም።
የጎጃም አካል የነበረውን የመተከል አውራጃ ያለህዝብ ፈቃድ ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ማጠቃለላቸው ሳያንስ ፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳ በግልጽ እንደነገሩን ክልሉን ከአማራ ህዝብ ነጻ ለማድረግ  በተወጠነ ሴራ አማራውና አገው እየተመረጠ  ከጥንት ከመሰረቱ ጀምሮ ይኖርበት ከነበረውና  እትብቱ ከተቆረጠበት ቀየው በግፍ እንዲፈናቀልና በአለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ጭካኔ እንዲጨፈጨፍ ተደርጓል ። ሬሳ በላስቲክ እየታሸገ በግሪደር እንደቆሻሻ ተደፍቷል። የሰው ልጅ እጅና እግር ተቆርጦ የከበሮ መምቻ ሆኗል። እርጉዞች ሆዳቸው እየተቀደደ ጽንስ እንዲበላ ሆኗል ። ይህ እንግዲህ ከብዙ በጥቂቱ በዚህ አመት ብቻ የተደርገ ሲሆን ሰሞኑን ደግሞ በወለጋ ሆሮጉድሩ አቤደንጎሮ ወረዳ ደቢስ ቀበሌና ሎሜጭ ቀበሌ በተባሉ ቦታዎች በየካቲት 30 2013 ዓ.ም በአማራ ተወላጆች ላይ በተለይ በሴቶችና በህጻናት ላይ ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ የጭካኔ ጥግ የሰው ልጅ እንደ ግንድ በመጥረቢያ እየተከተከተ ተጨፍጭፏል። ይህ ሁሉ ሲሆን የአካባቢው ባለስልጣናት ፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና የአካባቢው ፌደራል ፖሊስ ከበላይ አልታዘዝንም በማለት ለግድያው ተባባሪነታቸውን አሳይተዋል። እነዚህ ንጹሃን ዜጎች የድረሱልን ሲቃ ቢያሰሙም የደረሰላቸው ባለመኖሩ ህይወታቸው ለህልፈት ተዳርጓል።
ግድያውን ለማቆም መንግስት ምንም አይነት ጥረት አለማድረጉ መላ የአማራን ህዝብ ያሳዘነና ያስቆጣ ጉዳይ ሆኗል። ምንም እንኳን በማንነት ላይ ያነጣጠረ የዘር ማጥፋት ግድያ በአማራው ህብረተሰብ ላይ ሲፈጸም የመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም በተለይ በለውጥ ሰበብ ዶር አቢይ ወደስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ሂደቱ በስልትና በዕቅድ በኦሮሞ ክልል ፕሬዚደንት በአቶ ሽመልስ አብዲሳ መሪነት  እየተከናወነ  ለመሆኑ ማንም የሚያውቀው ሃቅ ነው። እንደሚታወቀው አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ሰበብ በመላው የኦሮሞ ታላላቅ ከተሞች የአማራን ህይወትና ንብረት በማውደም የተሰማራውን የቄሮ መንጋ እንደመሪ ሆነው ያገለግሉ እንደነበር የምናስታውሰው ነው። በምሳሌነት ለመጥቀስ ያህል የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ በሰአታት ውስጥ ከተማዋ ልትወድም እንደምትችል እና ስዎችም በአሰቃቂ ሁኔታ ሊገደሉ እንደሚችሉና ያላቸው የመከላከል አቅም ውሱን መሆኑን ገልጸው ተጨማሪ ሃይል እንዲላክላቸው    ለአቶ ሽመልስ ደውለው ሲያስታውቁ የሰጧቸው መልስ አርፈህ ተኛ እንደነበር ከንቲባው ከስራ ከተባረሩ በኋላ በሰጡት ቃለ መጠይቅ አጋልጠዋል ።
እንደሚታወቀው በለውጥ ሰበብ በኤርትራ በረሃ ለአመታት ሻግቶና በስብሶ የነበረውን የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግምባር ወደ መሃል አገር ከነትጥቁ ጋብዞ በማምጣትና ነፍስ እንዲዘራ በማድረግ የሰራዊቱን ግማሽ በመከላከያ ፣ ግማሹን ደግሞ በኦሮሚያ ልዩ ሃይል በመከፋፈል የቀረው ደግሞ ራሱን ኦነግ ሸኔ ብሎ በራሱ ምክንያት  በየጫካው እንዲሹለከለከ ተደረጓል። ታዲያ ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር እየተናበቡ የአማራን ህዝብ ከምድረ ኦሮሚያ ለማጥፋት በዕቅድ መስራታቸው ነው ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተሩም ሆኑ የአማራ ክልላዊ መንግስት እንዲሁም በታሪክ አጋጣሚ የዚችን አገር እጣ ፋንታ ለመወሰን ስልጣኑ ያላችሁ ሁሉ ይህን ሃቅ ጠንቅቃችሁ ታውቃላችሁ። ጠቅላይ ሚኒስተር ዶር አቢይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠቅላይ
ሚኒስተር እንደመሆናቸው መጠንና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ የመጀመሪያ ስራቸው መሆኑ እየታወቀ ህዝባቸው በተለይ የአማራ ህዝብ አሰቃቂ  የዘር ማጥፋት ጥቃት ሲደርስበት ልባቸው ለምን እንደደነደነ ሊገባን አልቻለም። ዶር አቢይ እያዩ እንዳላዩ፣  እየሰሙ እንዳልሰሙ መሆናቸውና ወንጀሉን በስሙ ለመጥራት መጸየፋቸው ክፉኛ ትዝብት ውስጥ ከቷቸዋል፣  ቢያንስ ለሟች ቤተሰቦች ሃዘናቸውን አለመግለጻቸውም እንቆቅልሽ ሆኖብናል ። አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት መድረክ ሁሉ የአማራን ህዝብ ሲያዋርዱና ቅስም ሲሰብሩ ብሎም በአማራ ህዝብ ላይ ጦርነት የመቀስቀስ ያህል ሲናገሩ እየተሰማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዳቸው ከፍተኛ ቅሬታን አሳድሮብናል ።
በኦስትሪያ የምንኖር የአማራ ማህበር አባላት  በደረሰው ኢሰባዊ ጭፍጨፋ የተሰማንን ከባድ ሃዘን እየገለጽን መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በህይወት የተረፉትን እንዲታደግና ወንጀለኞችን ለህግ እንዲያቀርብ አጥብቀን እንጠይቃለን ።
የሞቱትን ነፍስ ይማር !
ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ይስጥልን !
በኦስትሪያ የአማራ ማህበር ፣  ቪዬና
መጋቢት 3 2013
Filed in: Amharic