>
5:18 pm - Monday June 15, 1131

ጸሀፊውን ቢገድሉትም መጽሀፉን ቢያነዱትም ዛሬም ሚልዮኖች ህሊና ማህደር ውስጥ ተቀብሮ ያለው ኦሮማይ....!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ጸሀፊውን ቢገድሉትም መጽሀፉን ቢያነዱትም ዛሬም ሚልዮኖች ህሊና ማህደር ውስጥ ተቀብሮ ያለው ኦሮማይ….!!!
አሰፋ ሀይሉ

…ወደ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ 50 ጆንያ ጭኖ የደረሰው መኪና እንዲገባ አልተፈቀደለትም ፤ መኪናው የጫነው ነገር ሲታይ ጥበቃዎቹ ግራ ተጋብተው ለሀላፊዎቹ መልዕክት አስተላለፉ ፤ ሀላፊዎቹ 50 ጆንያ ጭኖ የቆመውን መኪና ለማየት መጡ ፤ ነገሩ ግራ አጋባቸው ፤ የመኪናውን ሹፌር ይሄ እኮ ስኳር ፋብሪካ ነው ብለው ነገሩት ፤ አውቃለው! የመጣውት ተልኬ ነው ፤ ጉዳዩን የያዘው ሰው እየመጣ ስለሆነ እሱን ታናግሩታላችሁ አላቸው ። ወዲያውም ሰውዬው መጣ ፤ ከሀላፊዎቹ ጋር ተነጋገረ ፤ መኪናው እንዲገባ ተደረገ ።  ልዩ ጥበቃ ፋብሪካው በር ላይ ቆመ ። ሀላፊው ሸንኮራ የሚፈጨውን አንደኛውን ማሽን ስራውን እንዲያቆም ትዕዛዛ አስተላለፈ ።
 
 ስድስት አውራጆች መጥተው 50 የጆንያውን ዕቃ አወረዱት ፤ ማሽኑ አጠገብም አስቀመጡት ፤ ሀላፊዎቹ ይመካከራሉ ፤ ማሽኑ ቢበላሽ ማን ሀላፊነት ይወስዳል እያሉ ይጠያየቃሉ ፤ ትዕዛዙን ይዞ የመጣው ሰው ጆንያው ሳይፈታ አንድ በአንድ ማሽን ውስጥ ገብቶ እንዲፈጭ ቀጭን ትዕዛዝ ሰጠ ። የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሀላፊዎች ግን እንዳለ ጆንያው ታስሮ ከገባ ማሽኑን ሊያበላሽ ስለሚችል በተናጠል ቢገባ ይሻላል ሲሉ ሀሳብ አቀረቡ ። ትዕዛዙን ይዞ የመጣው ሰው ግን በፍጹም አይፈታም እንዳለ ነው መፈጨት ያለበት አለ። ሀላፊዎቹ አሁንም ተማከሩ ፣ ተማከሩና በቃ ይፈጭ አሉ ። የመጀመሪያው ጆንያ ወደ ማሽኑ ገባ ፣ ተፈጨ ፤ ሁለተኛውም ገባና ተፈጨ ፤ ስኳር ይፈጭ የነበረው ማሽን ወረቀት መፍጨት ጀመረ ። የማሽኑ ባለሞያዎች ወረቀት ወደ ስኳር መለወጥ ጀመረ እንዴ? ብለው ጠየቁ ፤ ግና ምላሽ አላገኙም ። 50 ጆንያ የታሰረ ነገር ወንጂ ስኳር ፋብሪካ ተፈጭቶ አበቃ ።የተፈጨው ወረቀት ደግሞ እንዲቃጠል ተፈረደበት ። ይህ ሁሉ ፍርድ የተፈረደበት ነገር ምንድ ነው? ማለታችሁ አይቀርም ። ይህ ሁሉ ግፍና መከራ እንዲደርስበት የተደረገው ነገር የበአሉ ግርማ “ኦሮማይ” የተሰኘው መጽሐፍ ነው ። መጽሐፉ ገበያ ላይ እንደዋለ ተሰብስቦ ወደ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሄዶ ተፈጨ ፤ ይህም አልበቃ ብሎ ተቃጠለ ። ያም ቢሆን ግን “ኦሮማይ” ዛሬ ላይ ትንሳኤውን አግኝቶ በሁሉም ቤት ለመግባት ችሏል ። 
፨ ምንጭ አዲስ 1879 የሬድዮ ፕሮግራም
ኦ  ሮ  ማ  ይ ን በ ጨ ረ ፍ ታ. . . !
« የድንኳን ከተማው ሺ ደመራ ተደምሮ የተቀጣጠለበት መስሏል፡፡ ጭፈራውና ዘፈኑ ይቀልጣል — እዚህ የትግሬ — እዚያ ያማራ — ወዲህ የኦሮሞ ወዲያ የጉራጌ፡፡ ቀዝቀዝ ያለው አየር ከጭፈራውና ከዘፈኑ ጋር ተዳምሮ መንፈስን ያድሳል፡፡ ቅርብ መስሎ ከሚታየው ጥቁር ሰማይ ላይ የፈሰሱት ከዋክብት በደስታ የሚደንሱ ይመስላሉ፡፡ እና የቀይ ባሕር ማዕበሎችም ያረግዱ ነበር፡፡ አንዳንዴ ማዕበሎቹ ላንዳፍታ ጸጥ ሲሉ በየቦታው የሚነደው እሳት ነጸብራቅ፣ ዘመናዊ ሰዓሊ የሳለው የሕይወት ጥላ የሚመስሉ ዝብርቅርቅ ጥላዎች ባሕሩ ወለል ላይ ይፈጥራል፡፡
« አሁን እንዲያው ከተፈጥሮ የበለጠ ውብ ስዕል የት ይኖራል? እያልኩ የባሕሩን ጠርዝ ይዤ እየተከዝኩ ሳዘግም፣ አንዲት ልጅ ብቻዋን፣ ካንድ ጠርብ ድንጋይ ላይ ቆማ ማዶ — ሰማዩና ባሕሩ የሚሳሳሙበትን አድማስ ስትመለከት አየሁ፡፡ ባሕሩ የቆመችበትን ድንጋይ እያጠበ ይመለሳል፡፡ ከባሕር የሚመጣው ቀዝቃዛ አየር ጠጉሯን እያነሳ አየር ላይ ይነሰንሰው ነበር፡፡ በቀጭን መያዣ ክብ ትከሻዋ ላይ ተንጠልጥሎ ጀርባዋን ገልጦ የሚያሳይ ነጭ፣ አጠር ያለ የበጋ ቀሚስ ለብሳለች፡፡ የባሕርን አምላክ የምታመልክ ነጭ ርግብ መስላ ታየችኝ፡፡ ፎቶግራፍ ማንሻ ምነው በያዝኩ ኖሮ አልኩ፡፡
« ከድንኳኖች መንደር የተተኮሰው ርችት ጥቁሩ ሰማይ ላይ ድንገት ሲፈነዳ በሺ የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ አበባዎች ጨለማው ላይ ረገፉ፡፡ ደንግጣ ዞር ስትል መልኳ ታየኝ፡፡ ከሩቅ ተወርውሮ የሚመጣው የኤሌክትሪክ ብርሀን ትንሽ፣ ትንሽ ያሳያል፡፡ እሷ ትሆን? ወይስ አይደለችም? እያልኩ ተጠጋኋት፡፡ እሷ ነበረች፡፡ «ፊያሜታ!» ፡፡
« ታዲያስ የባሕር አማልክት? » አልኳት፡፡ በረዶ መሳይ ጥርሶቿ የልብ ቅርጽ ካላቸው ከንፈሮቿ መካከል ተፈልቅቀው ወጥተው ብቅ አሉ፡፡ …
« አማልክት ካልከኝ፣ እስኪ ስገድልኝ » አለችኝ፡፡ ጸሎት እንደሚያደርስ ሰው እጆቼን አንድ ላይ አጣምሬ ባንድ ጉልበቴ ፊቷ ተንበረከኩ፡፡
ሳቀችና፣ « አባቴ ይሙት ያበደ ደደብ ነህ፡፡ በሥነ ሥርዓት » አለችኝ፡፡
« አው፡፡ በሥነ ሥርዓት » አልኩ የእሷን አነጋገር አስመስዬ፡፡
« እኔ እንደሱ ነው የምለው አንቴ? አባቴ ይሙት፣ በሥነ ሥርዓት ደደብ ነህ.… »፡፡
        — በዓሉ ግርማ፣ ኦሮማይ፣ ገጽ 200፣ 1975 ዓ.ም ፡፡
የኤርትራ ሴቶች ውብ ናቸው! ልዩ እና ውብ! ባንዲራቸውን ተወው! እርሱን በሁለመናቸው ላይ ውበትን ያፈሰሰባቸው ፈጣሪ አልፈጠረውም፡፡ ጊዜ የፈጠረው ነው! እሱም ቢሆን ግን አያስጠላም! የኤርትራውያን ሴቶች እንደ ሪሃን ናቸው፡፡ መልካም ገጻቸው ከሩቅ የሚያውድ፡፡ የሚስብ፡፡ የሀበሻ አምላክ እጁን ታጥቦ የሠራቸው ውቦች፡፡ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ውበትን ማየት ከፈለግክ፣ የኤርትራ ሴቶችን ተመልከት፡፡ የኤርትራ ፊያሜታዎችን፡፡ ጠያይም ሀበሻዊ ውብ ፍጥረቶችን፡፡ መልካቸው፣ ገላቸው፣ ወይም ፀጉራቸው፣ ዓይናቸው፣ በልኩ የተሠራ ሰውነታቸው ብቻ አይደለም፡፡ ከምንም በላይ ውስጣቸው፡፡ ባህርያቸው፡፡ አፍቃሪነታቸው፡፡ አስተዋይነታቸው፡፡ ነፃነታቸው፡፡ ከፈለጉ እህት፡፡ ከፈለጉ ፍቅረኛ መሆንን አሳምረው የሚያውቁ፡፡ ሁለ ነገራቸው፡፡ ወርቅ የሆነ፡፡ ውብ ፍጥረቶች ናቸው፡፡
ስንቱ የኢትዮጵያ ወታደር ነበር፣ ኤርትራ ለጦርነት ሄዶ፣ ፍቅር አሸንፎት የተመለሰው? እጅግ ብዙ፡፡ የኤርትራ ሴቶች፣ እንኳን በሠላም በፍቅር የቀረባቸውን፣ በጦርነት ተዋክቦ የመጣን ሰው እንኳ በፍቅር አንበርክከው መመለስ የሚያውቁ፣ የፍቅር ደማሞች ናቸው፡፡ ጊዜ ቢያለያየንም፡፡ ጦርነት ቢከፋፍለንም፡፡ ፖለቲካ ቢያራርቀንም፡፡ ፈጣሪ ባልታሰበ መንገድ የተዘጉ ድንበሮችን ከፍቶ ዳግም አቀራርቦናል፡፡ ገና ወደፊት አብረን በፍቅር እፍፍ እንላለን፡፡ ለእነዚህ ውብ የሀበሻ ልጆች፡፡ ለእነዚህ ባለ ውብ ልቦች፡፡ ለቆነጃጅቶቹ ኤርትራውያን እህቶቼ በሙሉ፡፡ የበዛ ክብርና ፍቅር ይሁንላችሁ እላቸዋለሁ፡፡ በዓሉ ግርማ ያርከፈከፈላቸውን የአድናቆትና የመውደድ ጸዓዳ እንደ ሽቶ በደረሱበት እየተከተልኩ ልነሰንስላቸው ያምረኛል፡፡ እናንት የሀባሻ ልጆች፡፡ እናንት የኤርትራ ውብ ልጆች፡፡ እምር እንዳለባችሁ ቅሩ! እንወዳችኋለን፡፡
የፍቅር አምላክ የሀበሻ ልጆችን ሁሉ በያሉበት አብዝቶ ይባርክ!
የኢትዮጵያ አምላክ ፍቅርን ያብዛልን!
መዋደድን ይስጠን!
መልካም ቀዳሚት! 
______________________________________________________
ተጻፈ በአሣፍ ኃይሉ፡፡ ሃሚልተን፣ ኦንቴሪዮ፣ ካናዳ፡፡ «ዋስ» በምትባል አንዲት የኤርትራውያን ሬስቶራንት ውስጥ አረፍ ባልኩበት ከጫርኩት የግል ማስታወሻ፡፡ 2012 ዓ.ም.፡፡ ምስሉ፡- ፎቶ ተነሺዋንም አንሺውንም ያላወቅኩት፣ «Eritrean Beauties – Like Bealu Girma’s Fiameta»፡፡
Filed in: Amharic