>

የሂጃብ አብዮተኞች...!!! አወድ መሀመድ

የሂጃብ አብዮተኞች…!!!
አወድ መሀመድ


*…ወገኔ፣ እኔ በየዋህነት ዘመኔ ሂጃብ የጠመጠመችና የሙስሊም ስም ያላት ሴት ሁሉ ሙስሊም ናት ብዬ አስብ ነበር። 
ትናንት ይሄ ሂጃብ በጠመጠሙ ሴቶች ያሸበረቀው የብልጥግና ፖስተር በዚህ መንደር ሲዘዋወር ተመለከትኩኝና እራሴን ስንቶቹ ይሆኑ ከዚህ መሀል ሙስሊሞች ብዬ ለመጠየቅ ተገድጃለሁ። የሆኑትን ቢሆኑ `ሀይማኖት የግል አገር የጋራ´ ነውና ግድ አይሰጠኝም። ለአገራችን ምን ለመስራት አቅደዋል የሚለው ላይ ቅድሚያ ሰጥቼ አተኩራለሁ እንጂ ሀይማኖታቸውን ምናልባት ምን ይዘው መጥተዋል ከሚለው፣ ከባህሪያቸው፣ ከታሪካቸው፣ ካላቸው የብቃት ደረጃና ከሌሎችም መመዘኛዎች በኋላ የማየው ነው።
ፖስተሩ ከታችኛው ረድፍ በቀኝ በኩል መጀመሪያ ላይ እንዳለችውና በዘመነ ህወሃት ጊዜ ብዙዎችን በማሳነቅና በማስጠፋት እንደምትታወቀው ሀቢባ ዑመር ያሉ አንዳንድ ከይሲዎች ላይጠፉበት ቢችሉም፣ ብዙዎቹ ጤነኞች ናቸው ብሎ በመውሰድ የሴቶች ተሳትፎ በዚህ ደረጃ ማደጉ ይበል ያሰኛል። ነገር ግን ሂጃብ በመጠምጠማቸውና የሙስሊም ስም በመያዛቸው ብቻ ሙስሊም ናቸው ብሎ የሚያምን ሰው ካለ፣ እኔ በፊት እንደነበርኩት የዋህና በግ ነው ማለት ነው። በተለይ በብልጥግና ዘመን፣
የቀድሞ የሻሸመኔዋን ከንቲባና በኋላ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት የነበረችውን ጠይባ ሀሰንን ታስታውሷታላችሁ አደል? ጠይባ ሀሰን ከዚህ በፊት እንደፃፍኩባት ጴንጤ ናት። ጠይባ ሀሰን በሻሸመኔ ሙሉ ወንጌል ሰባኪም እጇን ወደ ላይ በማወራጨት የምትጨፍርና ብዙዎችን ወደ እምነቱ የሳበች ጴንጤም ናት። ጠይባ ሀሰን ለማ መገርሳን በመገልበጥ ወንበሩን ለመያዝ ስታደባ ተደርሶባት ከተባረረችና ወደ አሜሪካ ከኮበለለች በኋላ በቪኦኤ ቀርባ በሰጠችው ኢንተርቪውም ኢየሱሴን ይዤ ብዙ አሳልፍያለሁ። ኢየሱስ ጌታ ይህን ያን አድርጎልኛል ስትልም ሰምቻታለሁ። ጠይባ ሀሰን ሙስሊም ካልሆነች ለምን ሂጃብ እንደምታደርግ ስትጠየቅ ሌሎችን ሙስሊም ሴቶች ወደ ጌታ ማምጣት የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው ብላ በማሰቧ እንደሆነ የሚያውቋት ይናገራሉ።
ሌላኛዋ በፎቶው ለብቻዋ የምትታየው በፌስቡክ የታወቀች የጴንጤ ሰባኪ ናት። በቃ ሂጃብ አድርጋ መምጣትና በሂጃቧ ወደ ጌታ መጣራት የምትወደውና የምታዘወትረው ተግባሯ እንደሆነ ትናገራለች። ሰበካዋ በትግርኛ ነው።
በድጋሜ፣ ተመራጮች የሚከተሉትን ሀይማኖት ቢከተሉ በግሌ ግድ አይሰጠኝም። የሆኑትን ቢሆኑ ለህዝብ ለአገር ምን ለመስራት አቅደዋል፣ ምን አጀንዳ ይዘው ወደ ጠረጴዛ መጥተዋል የሚለውን ቅድሚያ እሰጣለሁ። በመሆኑም የሴቶችን ተሳትፎ ምን ይሁኑ ምን አበረታታለሁ። ግን ሂጃብ በመጠምጠማቸው ሙስሊም ናቸው የሚለውን እንደ መጀመሪያ መስፈርት በመውሰድ ካርዳችሁን ለመስጠት የቋመጣችሁ አክራሪዎች ቆም ብላችሁ ሁለት ሶስቴ እንድታስቡና በአገራዊ ጉዳይ ከግለሰቡ ሀይማኖት በፊት መመዘኛችሁ ባህሪ፣ ብቃት፣ ታሪክ … እንዲሆን ነው። ያለበለዚያ ለሙስሊም ያላችሁት ካርድ መጨረሻው ለጴንጤ ይሆንባችኋል።
Filed in: Amharic