>
5:13 pm - Monday April 20, 0150

በአብይ አህመድ ዙሪያ ጥቂት እስልምናዊ ወጎች...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

በአብይ አህመድ ዙሪያ ጥቂት እስልምናዊ ወጎች…!!!

አሰፋ ሀይሉ

እስልምና እውነትን በቀጥታ ተናገር ይላል፡፡ ምንም እንኳ የእስልምና አማኝ ባልሆንም፣ ጥቂት እሰልምና ተኮር ወጎችን ላወራ ስለሆነ – በእምነቱ አስተምህሮት መሠረት እውነቱን በቀጥታ እየተናገርኩ እቀጥላለሁ፡፡ ከራሴ ልጀምር፡፡ ለምሳሌ በእስልምና እምነት እንደ እኔ ዓይነቱ ሰው እስልምናን ያልተቀበለ ሰው «ካፊር» ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ በደምሳሳ ትርጉሙ ኢ-አማኒ፣ የፈጣሪን ኃይል የካደ፣ የረከሰ፣ የተረገመ ማለት ነው፡፡ ይሄን ሳውቅ አልደነገጥኩም፡፡ ከእምነቱ ውጭ ያሉትን በውግዘት ቃሎች የሚጠራ እስልምና ሐይማኖት ብቻ አይደለምና፡፡
ለምሳሌ በጁዳይክ (በቤተ እስራኤል ብሉይ) እምነት ውስጥ – ከጁዳይክ እምነት ተከታይ ውጭ ያሉትን ሕዝቦች «ጎዪም» ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ በደምሳሳ ትርጉሙ ኢ-አማኒ፣ የፈጣሪን ኃይል የካደ፣ ሊባረክ የማይችል፣ የተረገመ፣ የረከሰ ማለት ነው፡፡ በክርስትና እምነትም ውስጥ እንዲሁ እምነቱን የማይቀበል ሰው የሚጠራበት ስም አለ፡፡ «መናፍቅ» የሚል፡፡ መናፍቅ በደምሳሳ ትርጉሙ ከሃዲ፣ እርኩሰት የተጣባው፣ ያልዳነ፣ የተረገመ፣ ክፉ ነገርን የሚጠራ፣ እንደማለት ነው፡፡
እምነቶቹ ከራሳቸው ውጭ ያለውን የሚኮንኑት አማኞችን ወደ እነርሱ ለማምጣት ነው፡፡ ጥብቅ አንድነት ለመፍጠር ነው፡፡ በሌሎች እምነቶች ከመዋጥና ከመሸርሸር ለመዳን ነው፡፡ ምክንያታቸውን ስናውቅ አጠራራቸው አያስደነግጠንም፡፡
አሁን ወደ ጀመርኩት ወደ እስልምናው ነገር ልመለስ፡፡ በእስልምናው እንደ እኔ ዓይነት ከእስልምና ውጭ ባሉ ሰዎች ተወልዶ በሌላ እምነት የኖረ ሰው «ካፊር» ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ በእርግጥ እንዳንዶች ይበልጥ ሰላማዊ የሆነን የእስልምና እሳቤ ለመስበክ የሚሹ ዘመናውያን እስልምና «ካፊር» ብሎ የሚጠራው እምነት የሌለውን ሰው ነው (በክርስትና «አረመኔ» እንደሚባለው)፣ እንጂ ከእስልምና ውጭ ያለውን ሰው ሁሉ ለመጥሪያነት የሚያገለግል አይደለም ይላሉ፡፡
ከቅዱስ ቁርዓንና ሀዲሳት መጻሕፍት የሚያጣቅሷቸውን ማስረጃዎች ስንመለከት ግን – ያው የአንድዬ አላህን ፈጣሪነት እና የነብዩ መሀመድን (ሰ.አ.ወ.) ነቢይነት አምኖ ያልተቀበለ ሰው ሁሉ -ያው «ካፊር» ነው፡፡ ይህ አያከራክርም፡፡ ይህ ካላከራከረ በእስልምና ዓይን ስታይ እኔ «ካፊር» መሆኔም አያከራክርም፡፡ አላህ ይስጥልኝ፡፡ ይህንንስ ማን አየበት? እስልምና ምንም ዕውቅና ባይሰጠኝስ ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር? ቢያንስ በካፊርነተ አውቆኛል፡፡ ግን ደስ የሚለው እስልምና ዕድሜ ልክህን «ካፊር» አድርጎህ የሚቀር እምነት አይደለም፡፡
እንደ እኔ «ካፊር» የሆነ ሰው፣ በእስልምና መግቢያ በር ተዘጋጅቶለታል፡፡ ማንም በምድር ላይ ያለ ሰው የእስልምናን እምነት ከተቀበለ «ካፊር» መባሉ ይቀርለታል፡፡ በእስልምና እምነተ መሠረት አንድ ሰው በዓለም ላይ ሲኖር እየቆየ የሚረዳው እውነት አለ፡፡ ነገሮችን እንደሆኑት አድርጎ ትክክለኛውን መንገድ ይረዳል፡፡ ሰው ሁሉ ትክክለኛውን መንገድ እንዲረዳ የሚያግዘው የፈጣሪ እርዳታም ይቸረዋል፡፡ «ሂዳያህ» ይባላል፡፡ ፈጣሪ የሚያመላክትህ መንገድ፡፡
በእስልምና አስተምህሮት መሠረት ያን መንገድ አስተውለህ ስታውቅ፣ የፈጣሪን እውነተኛ መንገደ ስትገነዘብ «ሂክማህ» ወይም «ሂክመት» አገኘህ ማለት ነው፡፡ የዚህችን ዓለም ትክክለኛ ገጽታ ተረዳህ ማለት ነው፡፡ ሂክማ ካለህ ዕድሜህን ሙሉ ተከትለህ ከኖርክበት ማንኛውም እምነት ወደ እስልምና መግባት ትችላለህ፡፡ ወደ እስልምና የተቀየረ ሰው «ኢህቲዳ» ይሰኛል፡፡ ስለዚህ እስልምና ደስ የሚለው ነገሩ ራሱን ከርችሞ የሚቀመጥ እምነት ሳይሆን፣ ሌሎችም እንዲቀላቀሉት በሮቹን ክፍት አድርጎ የሚጠባበቅ መሆኑ ነው፡፡ አግላይ አይደለም፡፡ አቃፊ ነው፡፡ ተቀባይ ነው፡፡ እጁን በፍቅር ዘርግቶ የተቀመጠ ሐይማኖት ነው፡፡ ይሄን ሳስብ ስለራሴ «ካፊር» መሆን፣ ብዙ አልጨነቅም፡፡ ምክንያቱም ምናልባት አንድ ቀን አላህ ካለ፣ ካፊርነቴ ቀርቶ፣ ኢህቲዳ ልሆን እችላለሁ፡፡ እርጉም መባሌ ቀርቶ ብሩህ ልባል እችላለሁ፡፡ ኢንሻላህ!
ነገር ግን በእስልምና አንድ እጅግ ውጉዝ የሆነ ነገር አለ፡፡ ከሐራሞች ሁሉ የከፋ ሐራም ነው፡፡ ልክ ሀገሩን እንደ ከዳ ሰው በሞት መቀጣት ሁሉ አለበት ተብሎ በብዙ ቦታ በቅዱስ ቁርዓኑ የተነገረ ኃጢያት ነው ይህ በእስልምና እምነት፡፡ ያ ሐራም ምንድነው? ብለን የጠየቅን እንደሆነ – «ሪዳህ» ነው፡፡ የአባትህን እምነት መካድ፡፡ እስልምናን ከተቀበለ አባት ተወልደህ፣ የአላህን አንድ ፈጣሪነት፣ የነብዩ መሀመድን (ሰ.አ.ወ.) ነቢይነትና፣ የቅዱስ ቁርዓንን እውነትነት አምኖ ከተቀበለ ቤተሰብ፣ አምኖ ከተቀበለ ወላጅ አባት ተወልደህ – እስልምናን ከካድክ፣ ከእስልምና ካፈነገጥክ «ሙርተድ» ነህ፡፡ እምነቱን የካደ፣ እስልምና እምነትን አውቆ በፈቃዱ ረግጦ ወደ ሌላ እምነት የገባ ሰው – በቁርዓኑ የሐራሞች ሁሉ ሐራምን የተሸከመ ሰው ነው! «ሙርተድ» ይባላል እንዲህ ዓይነቱ ከሃዲ፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት በእስልምና አስተምህቶ ስታይ እኔ «ካፊር» ነኝ ብያለሁ፡፡ ልክ የጋብቻ ስቴተስህ ምንድነው? ስትባል «ያገባ» ወይ «ያላገባ» እንደምትለው፣ ይሄም የኔ የማያጠራጥር እስልምናዊ «ስቴተሴ» ነው፡፡ «ካፊር» ነኝ፡፡ ደስ የሚለኝ መሆኔንም አልክድም፡፡ ከእኔ የባሰም ግን አለ፡፡ የሀገሬ ጠቅላይ ሚኒስትር፡፡ አብይ አህመድ አሊ፡፡ አብይ አህመድ ግን «ሙርተድ» ነው፡፡ ከ«ካፊር»ም የከፋ ማለት ነው፡፡
«ካፊር» ከልጅነቱ እስልምናን የሚሰብከው ሰው አጥቶ ሊሆን ይችላል፡፡ «ካፊር» ምናልባት ቤተሰቦቹ በሚያመልኩት ሌላ እምነት አስተምህሮዎች በመዋጡ የተነሳ የእስልምናን እውነት ለማየት የሚችልበት ብርሃን ተጋርዶበት ይሆናል፡፡ ወይ በቤተሰቦቹ ተነግሮት ባደገው አስምህሮት ተሸውዶም ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የአላህን ቃል ቢሰበክ፣ የፈጣሪ ትክክለኛ መንገድ ቢነገረው፣ በፈጣሪ እርዳታ ልቡ ወደ ትክክለኛ መንገድ ሊመለስ ይችላል፡፡ እና «ካፊር» ባለማወቁ የተነሳ ብቻ «ሐራም» አይገባም፡፡ ይልሃል የእስልምና አስተምህሮት፡፡
«ሙርተድ»ስ? «ሙርተድ» ግን እስልምናን የሚክደው እያወቀ ነው፡፡ አባቱ ያወረሰውን የአላህ ቃልኪዳን ረግጦ ነው፡፡ እምነቱን አርክሶ ነው፡፡ የነቢዩ መሀመድን (ሰ.አ.ወ.) አስተምህሮትና ቃል ክዶ ነው፡፡ በህጻንነት ዕድሜው አባቱ ከወተት ጋር እያማገ የሰጠውን የፈጣሪን ቃል ክዶ ነው፡፡ ስለዚህ በእስልምና «ሙርተድ» እያወቀ የሳተ ሰው ነውና ከፍተኛው ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ «ሪዳህ» ማለት ነውር እንደማለት ነው፡፡ እያወቅክ ከእውነት ማፈንገጥ፣ እያወቅክ ፈጣሪን ማርከስ፡፡ «ሙርተድ» እንደዚያ ዓይነት ትርጉም ያለው ቃል ነው፡፡ እንደ «ካፊር» ኢ-አማኒ ብቻ ሳይሆን፣ «ነውረኛ፣ አስፀያፊ» የሚልም ቅላጼ አለው፡፡ የ«ሙርተድ» ዋጋ ሞት ነው፡፡ «ሙርተድ» በሐራሙ የተነሳ በሥጋውም በነፍሱም ይሞታል፡፡ ይሄን ሳስብ አብይ አህመድ ያሳዝነኛል፡፡ ለሙርተድ ማዘን ሐራም ይሆን? አላውቅም፡፡ ባልከተለውም እስልምና የ‹‹እዝነት›› እምነት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ለሙርተድ ማዘን ሐራም አይመስለኝም፡፡
በጣም የሚገርመኝ ነገር እስልምና አማኞቹን እስልምናን የከዱ «ሙርተድ» ቢሆኑበትም፣ እስከመጨረሻው ግን የተረገማችሁ ናችሁ፣ እና ተረግማችሁ ቅሩ ብሎ አለመተዉ ነው፡፡ እስልምና ትልቁን ሐራም ለፈጸመው ለሙርተዱም እስከ መጨረሻው ወደ አባቱ እምነት የመመለስ ዕድሉን ይሰጠዋል፡፡ እና እስልምና እንኳን ቃሉን ሳያውቁ ለካዱት ለእኔ ዓይነቶቹ ካፊሮች ይቅርና፣ ቃሉን አውቀውም የአባታቸውን እምነት ረግጠው ለካዱት ለእንደ እነ አብይ አህመድ ላሉት ሙርተዶችም በሩ ክፍት ነው፡፡ እስልምና ለሙርተድ ፊጥሪዎች በሩ ክፍት ነው፡፡ ለሙርተድ ሚሊዎች በሩ ክፍት ነው፡፡ ደስ የሚለው ነገሩ ይህ ነው፡፡ ይቅርታንንና ምህረትን የሚያውቅ እምነት ነው ማለት ነውና፡፡
በእስልምና አስተምህሮቶች – የመጨረሻው የኃጢያቶች ሁሉ ኃጢያት ግን – የአባቱን እምነት የከዳው «ሙርተድ» ዳግም ዕድል ተሰጥቶት – በኢህቲዳ አንዴ ወደ አባቱ እምነት ወደ እስልምና ዳግመኛ ከተመለሰ በኋላ፣ ድጋሚ እስልምናን መክዳት ነው፡፡ ደጋጋሚ ከሃዲ፣ ደጋጋሚ «ሙርተድ» ሲሆን አንድ ሰው መድኃኒት የለውም፡፡ ማለት ነው፡፡ ይሄ ዓይነቱ ሰው በእስልምና የሚደረግለት ነገር ቢኖር ለአስር ተከታታይ ቀናት ይፀለይለታል፡፡ እና ውጉዝ ተብሎ ይተዋል፡፡ ለሥጋም፣ ለነፍስም ሞት፡፡ አዘንኩለት ለአጅሬው፡፡
የፈጣሪ በረከት በሁላችሁ ዘንድ ይሁን!
በረክ አላህ ፊካ!
አበቃሁ!
_______________________________________
ፎቶው፡- ምላጩ «ሙርተድ» (አብይ አህመድ) በእየሩሳሌም «ራባይ» (የእስራኤል ቄስ) መስሎ ትወናውን በብቃት ሲወጣ፡፡
Filed in: Amharic