>

ከዚህ በላይ ብሔራዊ ውርደት ከወዴት ይመጣ ይሆን??? (ያሬድ ሀይለማርያም)

ከዚህ በላይ ብሔራዊ ውርደት ከወዴት ይመጣ ይሆን???

ያሬድ ሀይለማርያም

“የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የሴቶች ቢሮ እንዳስታወቀዉ በክልሉ ርዕሰ-ከተማ መቀሌ፣ አዲግራትና አካባቢዎቻቸዉ፣ ካለፈዉ ታሕሳስ እስከ የካቲት በነበረዉ ጊዜ ብቻ ከ500 በላይ ሴቶች መደፈራቸዉ ተረጋግጧል።” DW Amharic
የጀርመን ድምጽ አክሎ እንደገለጸው ሴቶቹ የተደፈሩት በኤርትራ ሠራዊት እና አንዳንዶቹም በመከላከያ አባላት እንደሆነ ገልጿል። በዚህ ዘገባውም አንዲት ሴት በ15 የኤርትራ ወታደሮች መደፈሯንም ዘግቧል።

ጥያቄ፤

+ እናንት ለሴቶች መብት መከበር የቆማችሁ ድርጅቶች እና የመብት ተሟጋቾች ከወዴት ናችሁ? ምነው ድምጻችሁ አይሰማ?
+ እናንት አገሪቷ በሴቶች እኩልነት ሰማይ ጥግ ደርሳለች እያላችሁ የመንግስቱን ካቢኔ የሞሉ ሴቶች ፎቶ የምትደረድሩ ተመጻዳቂዎች የት ናችሁ? ምነው ድምጻችሁ አይሰማ?
+ እናንት የእናት፣ የእህት እና የሴት ልጆች ጥቃት ያመናል፣ ያስቆጣናል የምትሉ ምሩናን፣ የኪነጥበብ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች እና የመብት አቀንቃኞች ምን ዋጣችሁ? ምነው ድምጻችሁ አይሰማ?
+ በአውሮፓ እና በአሜሪካ አደባባዮች ላይ በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ሕግ ከማስከበር አላለፈም የሚል መፈክር ያሰማችሁ አገር ወዳድ ወገኖች ይህን ስትሰሙ ምን ይሰማችሁ ይሆን?  ምነው ድምጻችሁ አይሰማ?
+ ትግራይ ላይ ለደረሰው ሰብአዊ ቀውስ ሁሉ ህውሃት ነው የሚል ሙግት የምታነሱ ሰዎች፤ በአዲግራት እና አቅራቢያዋ ከተሞች ብቻ ከ500 በላይ ሴቶች መደፈርም ህውሃት ይሆን ተጠያቂው?
+ የአንዲት ሴትን በባላ መጠቃት ትልቅ አገራዊ አጀንዳ ድርጋችሁ ሚዲያውን በጩኸት ታጨናንቁ የነበራችሁ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የት ገባችሁ? ምነው ድምጻችሁ አይሰማ?
+ ከዚህ በላይ ብሔራዊ ውርደትስ ከየት ይመጣል?
+ እኛው እርስ በርሳችን እየተላተምን መልሰን ሴቶቻችንን የጎረቤት አገር ወታደር መጫወቻ እንዲሁን ካደረግን በኋላ የምዕራባዊያን መግለጫ እንቅልፍ ቢነሳን ምን ዋጋ አለው?
+ ኢትዮጵያን መውደድ በምን ይሆን የሚለካው? ሴት ልጆቿ በዚህ መልኩ ሲጠቁ እያዩ እንዳላየ እና እንዳልሰማ በመምሰል ይቻል ይሆን?
አዎ አሁንም በትግራይ ክልል የተፈጸመው ግፍ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ፣ አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ አለም አቀፍ ማህበረሰቡም ችግሩን በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ እንዲረዳው እና ተጎጂዎቹን እንዲደግፍ መደረግ አለበት።
ነውራችንን ለመሸፈን በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ ማጉረጥረጥም ሆነ መጮኹ ፋይዳ የለውም። ወደ ውስጣችን እንመልከት። በቅርቡ እንዳልኩት ለውጪ ኃይሎች ጫና ያጋለጠን በውስጣችን ያለው በሽታ ነው። የውስጥ ፖለቲካችን ተበላሽቷል። እውነቱን መጋፈጥ ፈርተናል። እደግመዋለሁ እንደ ማህበረሰብ እውነትን የመፍራት ህመም እያሰቃየን ነው። ኢትዮጵያ በጎጥ ፖለቲካ በተለከፉ ልጆቿ ክፉኛ ተሰቅፋ ተይዛ እየማቀቀች ነው። የውስጥ ሽኩቻችን የሳባቸውና ለረዥም ጊዜ መበታተኗን የሚመኙ የውጭ ኃይሎችም ዙሪያችንን ከበውናል።
ኢትዮጵያ ወዴት? የሚለው ጥያቄ መነሳት ካለብት አሁን ነው ጊዜው።
ፍትሕ ለግፏን!!!
Filed in: Amharic